በየትኛውም ጉዳያችን በቁርኣንና በሐዲሥ መመሪያ መሰረት ልንጓዝ እንደሚገባ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች በተለያዩ ተፅእኖዎች ላይ በመውደቃቸው የተነሳ በአንድ ጉዳይ ላይ ያላቸው ግንዛቤ ከቁርኣን ሐዲሥ እየጠቀሱም ላይግባቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የአላህን የትነት ብንወስድ በአሁኑ ሰዓት፡
1. “አላህ፡ አለም ውስጥ፣ ከአለም ውጭም፣ በላይም፣ በታችም…፣ ዐርሽም ላይ፣ የትም የለም” የሚሉ አሉ፡፡ አሕባሾች ለዚህ ምሳሌ መሆን ይችላሉ፡፡
2. ሌሎች ደግሞ “አላህ ሁሉም ቦታ ይገኛል” የሚሉ ሱፍዮች አሉ፡፡ በነዚህ አረዳድ ምድር ላይ ባሉ ቆሻሻና መጥፎ ቦታዎች ሳይቀር አላህ አለ ማለት ነው፡፡ አላህ ይጠብቀን፡፡
3. አህሉ ሱና ደግሞ አላህ ከዐርሹ በላይ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ ሶስት ሐሳቦች የተራራቁ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ውድቅ ቢሆኑም አራማጆቻቸው ግን ቁርኣን ሐዲሥ ይጠቅሳሉ፡፡ ችግራቸው ግን ማስረጃዎቹን ሶሐቦችና ተከታዮቻቸው በተረዱት መልኩ ባለመረዳታቸው የመጣ ነው፡፡ እነዚያ ቁርኣኑ ሲወርድ በጊዜው የነበሩ ሶሐቦች፣ የነሱ መልካም ተማሪዎች የሆኑት ታቢዒዮችና በመልካም የተከተሏቸው አትባዑትታቢዒን የተጓዙበት መንገድና ግንዛቤያቸው በየትኛውም ኢስላማዊ ጉዳይ ላይ ገላጋይ ሚዛን ነው፡፡ እነዚህ ናቸው “መልካም ቀደምቶች” (ሰለፉስሷሊሒን) እየተባሉ የሚጠሩት፡፡ ያለነርሱ ኢስላምን ማወቅ ዘበት ነው፡፡ ቁርኣኑና ሱንናው ሙሉ በሙሉ በነሱ ላይ ነው የተላለፈው፡፡ በርካቶች ውዝግብ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ እውነትን መለየት አቅቷቸው የሚዋልሉት የሰለፎችን ግንዛቤ ምን ያክል ዋጋ እንዳለው ካለማወቃቸው ወይም ተግባር ላይ ካለማዋላቸው የተነሳ ነው፡፡ መቼስ ኢስላምን ከሶሐቦች በላይ “አውቃለሁ” ማለት ዘበት ነው፡፡ እነሱ ቁርኣኑ የት እንደ ወረደ፣ መቼ እንደ ወረደ፣ በምን ምክንያት እንደወረደ እና መልእክቱ ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ኢስላምን ቀጥታ ከነብዩ ﷺ አንደበት የተማሩ የኡማው ቀዳሚ ትውልድ ናቸው፡፡ የነሱ፣ የተማሪዎቻቸው እና የተተኪዎቻቸው ቁርኣናዊና ሐዲሣዊ ግንዛቤ ያለ ጥርጥር ገላጋይ ሚዛን ነው፡፡ ይሄ እያንዳንዱ ሙስሊም በስርኣት ሊረዳው፣ ሊያጤነውና ሊጠቀምበት የሚገባ መርህ ነው፡፡
ስለዚህ በየትኛውም ርእሰ-ጉዳይ የአረዳድ ልዩነት አጋጥሞት ሐቁ ከየትኛው ወገን እንደሆነ ለመለየት የተቸገረ ሰው በጉዳዩ ላይ የሚጠቀሱ ማስረጃዎችን ሶሐቦችና ተከታዮቻቸው በምን መልኩ ነው የተረዷቸው ብሎ ሊያስስ ይገባል፡፡ ቁርኣንና ሱናን ያለ አግባብ እየተነተነ የሚፈትን ቢያጋጥመን “እስኪ የነብዩ ﷺ ተማሪዎች በምን መልኩ ነበር የተረዱት?” ብለን ብናስስ ከጭንቅ ከሀሳብ “እፎይ” ማለት እንችላለን፡፡ ይህን ሀሳብ ከሚያጠናክሩ ማስረጃዎች ጥቂቶቹን እንመልከት
(فَإِنْ آمَنُوا بِمِثْلِ مَا آمَنْتُمْ بِهِ فَقَدِ اهْتَدَوْا ۖ وَإِنْ تَوَلَّوْا فَإِنَّمَا هُمْ فِي شِقَاقٍ ۖ فَسَيَكْفِيكَهُمُ اللَّهُ ۚ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ)
"እናም እናንተ ባመናችሁበት አምሳያ ቢያምኑ በርግጥም ተመሩ፡፡ ከዞሩግን እነሱ በጭቅጭቅ ውስጥ ናቸው፡፡" [አልበቀራህ፡ 137]
ስለዚህ መትረፍ የፈለገ ሰው እነሱ ባመኑበት መልኩ ሊያምን ይገባል፡፡ እናም ሶሐቦች ባመኑበት አምሳያ ያመነ በርግጥም ከፈተና ነጃ ወጣ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለን የመረጠ ግን ያለጥርጥር ከመንገድ ወጣ፡፡
(وَمَنْ يُشَاقِقِ الرَّسُولَ مِنْ بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُ الْهُدَىٰ وَيَتَّبِعْ غَيْرَ سَبِيلِ الْمُؤْمِنِينَ نُوَلِّهِ مَا تَوَلَّىٰ وَنُصْلِهِ جَهَنَّمَ ۖ وَسَاءَتْ مَصِيرًا)
"ቅኑ መንገድ ከተገለፀለት በኋላ መልእክተኛውን የሚፃረርና የአማኞቹ ያልሆነን መንገድም የሚከተል፣ በተሾመበት (ጥመት) ላይ እንሾመዋለን፤ ጀሀነምንም እንከተዋለን፡፡ መመለሻይቱም ከፋች!" [አንኒሳእ፡ 115]
ያስተውሉ! ቁርኣኑ በወረደበት ዘመን የነበሩት አማኞች አይነታችን የበዛው እኛ ሳንሆን በተውሒድና በሱናህ የተሳሰሩት ሶሐቦቹ ብቻ ነበሩ፡፡ በአንቀፁ ምስክርነት የሶሐቦች ያልሆነን መንገድ፣ ሶሐቦች የማያውቁትን እምነት የሚከተል አስፈሪ አደጋ ውስጥ ነው ያለው፡፡
ነብዩም ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “ከናንተ የሚቆይ ሰው ብዙ ውዝግቦችን ያያል፡፡ ያኔ ባወቃችሁት ሱንናዬ እና ከኔ በኋላ ያሉ ቀጥተኛና የተቀኑ የሆኑ ምትኮቼንም ሱንናህ አደራችሁን፡፡” [አስሶሒሐህ፡ 937]
ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ እንደሚሉት፡- “ከናንተ ምሳሌን መያዝ የፈለገ የሞቱትን ይያዝ፡፡ ምክንያቱም በህይወት ያለ ፈተናው አይታመንምና፡፡ እነዚያ የሙሐመድ ﷺ ሶሐቦች ከዚህ ህዝብ ሁሉ ልባቸው የመጠቀ፣ እውቀታቸው የጠለቀ፣ ከማይመለከታቸው መግባታቸው የቀለለ ናቸው፡፡ አላህ ለራሱ ነብይ አጋርነት እና ሃይማኖቱን ለማፅናት የመረጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሐቃቸውን እወቁ፡፡ በመንገዳቸው ተጓዙ፡፡ ምክንያቱም እነሱ ቀጥ ባለው መንገድ ላይ ነበሩና!!” [ዘምሙል ከላም፡ 88]
ዑመር ኢብኑ ዐብዲል ዐዚዝ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰዎቹ (ሶሐቦች) ከቆሙበት ቁም፡፡ እነሱ ከእውቀት ነው የቆሙት፡፡ ከጥልቅ ግንዛቤም ነው የታቀቡት፡፡ በርግጥም እነሱ ከናንተ በበለጠ እሷን (መጤዋን) በመግለጥ ብርቱ ነበሩ፡፡ በሷም ላይ ትሩፋት ቢኖር ይበልጥ የተገቡ ነበሩ፡፡ ‘ከነሱ በኋላ ነው የተፈጠረው’ ካላችሁ መመሪያቸውን የጣሰ፣ ከሱንናቸው የዞረ እንጂ አልፈጠረውም፡፡ ከእውቀት፡ የሚያረካን ግልፅ አድርገዋል፡፡ በቂ የሆነንም ተናግረዋል፡፡ ከነሱ በላይ የሚጥር ከንቱ ደካሚ ነው፡፡ ከነሱ ያሳጠረ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ የሆኑ ሰዎች ከነሱ ቀሩና ራቁ፡፡ ሌሎች ከነሱ አለፉና ወሰን አለፉ፡፡ እነሱ ግን እዚህ መሀል ላይ ቀጥ ካለ ቅናቻ ላይ ናቸው፡፡ ” [ሉምዐቱል ኢዕቲቃድ፡ 8-9]
አልኢማም አልአውዛዒ እንዲህ ይላሉ፡ “እራስህን በሱናህ ላይ አፅና፡፡ ሰዎቹ (ሶሐቦች) ከቆሙበትም ቁም፡፡ እነሱ ያሉትን በል፡፡ እነሱ ከታቀቡት ታቀብ፡፡ የመልካም ቀደምቶችህን መንገድ ተከተል፡፡ ለነሱ የበቃቸው ይበቃሀልና!!!” [ካሺፉልጉማህ፡ 58]
ኢማሙ ማሊክ፡- “የዚች ህዝብ መጨረሻዋ አይስተካከልም፣ የመጀመሪያዋ በተስተካከለችበት ቢሆን እንጂ፡፡ ያኔ ዲን ያልነበረ ነገር ዛሬ ዲን አይሆንም” ይላሉ፡፡ [ሐጀቱ አንነቢይ፡ 103]
ኢማሙ አሕመድ፡- “እኛ ዘንድ የሱንናህ መሰረቶች የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶሐቦች በነበሩበት አጥብቆ መያዝ፣ እነሱን መከተል፣ ቢድዐዎችን መተው ነው፡፡ እያንዳንዷ ቢድዐህ ጥመት ነች” ይላሉ፡፡ [ኡሱሉስሱንናህ አሕመድ: 1]
ይህንን ከያዝን በኋላ “እስልምናን ሶሐቦች በተረዱት መልኩ ብቻ ተረዱ የሚል ትእዛዝ የለም” የሚለውን የአቡበክር አለሙን ብልሹ ንግግር ታዘቡ ከስር እስክሪን ሾት አድርጌ አስፍሬዋለሁ፡፡ ንግግሩ የራሱን ጥሬነት ከማጋለጡም ባለፈ ብዙ ግድፈቶችን ያጨቀ ነው፡፡ ስለ አራቱ መዝሀቦች ምንነትና የልዩነት መንስኤ፣ የሶሐቦች ግንዛቤ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ እነሱ በተረዱት መልኩ መረዳት ማለትስ ምንድን ነው በሚለው ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት በአጭር ቃላት አስፍሮታል፡፡ ይሄ ሰውየ የኢኽዋን ስራዎችን እየተረጎመ ለህዝብ የሚያቀርብ እንደሆነ ይሰመርበት፡፡ የህዝባችንን አስተሳሰብ “ለማነፅ” ተፍ ተፍ የሚሉት እንግዲህ እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ አላህ ልቦና ይስጣቸው፡፡
0 Comments