Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አንድ ባል የወር አበባ ደም ላይ ካለች ሚስቱ ጋር ግንኙነት መፈፀም እንደማይችል የምናውቀው ስንቶቻችን እንሆን? ጥፋቱስ ከተፈፀመ ማካካሻው ምንድን ነው?


አንድ ባል የወር አበባ ደም ላይ ካለች ሚስቱ ጋር ግንኙነት መፈፀም እንደማይችል የምናውቀው ስንቶቻችን እንሆን? ጥፋቱስ ከተፈፀመ ማካካሻው ምንድን ነው?
1. ብይኑ
በወር አበባ ወቅት የግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀም በጥብቅ የተከለከለ አደገኛ ወንጀል ነው፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡-
وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّى يَطْهُرْنَ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ (222)
“ስለ የወር አበባ ደም ይጠይቁሃል፡፡ ‘እርሱ አስፀያፊ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ሴቶችን በወር አበባ ጊዜ (ከመገናኘት) ራቋቸው፡፡ ንፁህ እስከሚሆኑም ድረስ አትቅረቧቸው፡፡ ንፁህ በሆኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኟቸው፡፡ አላህ ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል’ በላቸው፡፡” [አልበቀራህ፡ 222]
ነብዩም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡- “የወር አበባ ደም ላይ ያለችን ሴት የተገናኘ ወይም ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ ወይም ከጠንቋይ ዘንድ የሄደ ሰው በሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል” ይላሉ፡፡ ሐዲሡን አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል፡፡ [ሶሒሑትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 2433]
2. በወር አበባ ጊዜ ግንኙነት ከተፈፀመ የጥፋቱ ማካካሻው ምንድን ነው?
በዚህ ግንኙነት በማይፈቀድበት ወቅት ላይ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ከባድ ጥፋት ፈፅሟል፡፡ ለጥፋቱ ማበሻ ይሆነውም ዘንድ አንድ ዲናር ወይም ግማሽ ዲናር ሊመፀውት እንደሚገባ ነብያችን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ደንግገዋል፡፡ [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 257] አንድ ዲናር ማለት 4.25 ግራም ወርቅ ሲሆን ግማሹ ደግሞ 2.125 ግራም ነው፡፡ እናም በዚህ ጊዜ ግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ይህን ያክል ይሰድቃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዘመኑ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ ለምሳሌ 800 ብር ቢሆን 4.25 x 800= 3,400 ብር ወይም ደግሞ የዚህን ግማሽ 2.125 x 800=1,700 ብር ሊሰድቅ ይገባል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ አንድ ሰው አንዴ ለፈፀመው ህገ-ወጥ ግንኙነት ቅጣት ይሆን ዘንድ ይህን ያክል ገንዘብ አንዴ ባግባቡ ቢያወጣ ዳግም ወደዚህ ጥፋት የመመለስ እድሉ በጅጉ ይጠብ ነበር፡፡ ነገር ግን ህጉን ባለማወቃችን ወይም ደግሞ የጥፋቱን ክብደትና ማካካሻውን ጠንቅቀን ባለመረዳታችን ምክንያት ስንቶቻችን ነን በወንጀል የምንጨማለቀው?! አላህ ድንጋጌዎቹን የምንረዳ ለህጉ የምናድር ያድርገን፡፡
ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡ “ነፍሱ አሸንፋው የወር አበባ ላይ ያለችን ሴት ከደሟ ከመጥራቷ በፊት የተገናኘ ሰው በሱ ላይ አቅራብ በሆነ ስሌት ግማሽ የእንግሊዝ ፓውንድ ወርቅ ወይም እሩቡን የመመፅወት ግዴታ አለበት፡፡ ይህም ዐብዱላህ ኢብኒ ዐባስ ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ያስተላለፈውን የወር አበባ ላይ ሳለች ሚስቱን ስለሚገናኝ ሰው “በአንድ ዲናር ወይም በግማሽ ዲናር ይሰድቅ” ሲሉ የተናገሩትን ሐዲሥ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ … ምናልባትም በአንድ ዲናር ወይም በግማሹ ተብሎ አማራጭ መሰጠቱ ወደ መፅዋቹ የአቅም ሁኔታ የሚመለስ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን ሰነዳቸው ደካማ ቢሆንም የሐዲሡ አንዳንድ ዘገባዎች ይህን ያመላክታሉ፣ ወላሁ አዕለም፡፡” [አዳቡዝዚፋፍ፡ 50]
3. ግን ለምን በወር አበባ ጊዜ ግነኙነት ተከለከለ?
በዚህ ሰአት ግንኙነት መፈፀሙ አስፀያፊ መሆኑ ህሊናው ላልታወረ ሁሉ አይሰወርም፡፡ ከዚያም ባለፈ የራሱ የሆነ ጉዳት አለው፡፡ ደረጃው ቢለያይም ለወንዱም ለሴቷም የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ ብዙ ሴቶች የወር አበባ ላይ ሲሆኑ ለአእምሮ አለመረጋጋት፣ ብስጭት፣ ድብርት፣ የጀርባ ህመም፣ የሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ፣ ድካም፣ ራስ ምታትና መሰል ህመሞች ያጋጥሟቸዋል፡፡ የእለት ከእለት ስራዎቻቸውን ለማከናወን የሚያቅታቸው ሁሉ አሉ፡፡ እናም የወር አበባ ኡደታዊ ደም ወቅታዊ ቢሆኑም የተለያዩ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫናዎችን ያሳድራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ግንኙነት መፈፀም በተለይም ሴቷ ላይ ይበልጥ ችግር መፍጠር፣ ይበልጥ ስቃይን መጨመር ነው፡፡ በዚያ ላይ ማህፀን አካባቢ እራሱን የቻለ የህመም ስሜት አለ፡፡ በዚህ ሰአት ማህፀንና አካባቢው ከወትሮው በተለየ መልኩ የመኮማተርና የመድከም ባህሪ ስለሚኖረው ባእድና ውጫዊ አካል ካገኘው የመቁሰል፣ በኢንፌክሽን የመጠቃት፣ ለተጨማሪ ህመም የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡
4. በወር አበባ ወቅት ባል ከሚስቱ የሚፈቀድለት ምንድን ነው?
በወር አበባ ወቅት የሩካቤ ስጋ ግንኙነት እንጂ አብሮ መብላት፣ መጠጣት፣ መቀመጥ አልተከለከለም፡፡ ኢስላም በዚህ ረገድ የተለየ ህግ አለው፡፡ በክርስትና በወር አበባ ወቅት ሴቷ እሷ ብቻ ሳትሆን የነካትም ጭምር የረከሰ ነው፡፡ "ሴት ጊዜዉን እየጠበቀ የሚመጣ የደም መፍሰስ ቢኖርባት የወር አበባዋን ርኩሰት እስከ ሰባት ቀን ይቆያል፡፡ ‪#‎በዚህ_ጊዜ‬ ‪#‎ማንም_ሰዉ_ቢነካት‬ እስከ ማታ ድረስ ‪#‎እርኩስ‬ ይሆናል፡፡ በወር አበባዋ ጊዜ ‪#‎የምትተኛበት_ነገር‬ ‪#‎ማንኛዉም_ነገር_እርኩስ_ይሆናል‬፡፡ ‪#‎የተቀመጠችበትን_ማንኛዉም‬ ነገር ‪#‎የነካ_ሰዉ‬ ልብሱን ይጠብ ሰዉነቱንም ይታጠብ ‪#‎እስከ_ማታ_ድረስ_ግን‬ ‪#‎እርኩስ_ይሆናል‬" ይላል መፅሀፋቸው፡፡ [ዘሌዋዉያን 15: 19-22] አይሁዶችም ዘንድ ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡ “የሁዶች ከነሱ አንዲት ሴት የወር አበባ ካየች ከቤት ያስወጧት ነበር፡፡ አብረዋት አይበሉም፣ አብረዋትም አይጠጡም፣ በቤቶቻቸውም ውስጥ አብረዋት አይቀላቀሉም ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለዚህ ሲጠየቁ የጠራው አላህ ‘ስለ የወር አበባ ደም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስፀያፊ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ሴቶችን በወር አበባ ጊዜ (ከመገናኘት) ራቋቸው’ የሚለውን እስከመጨረሻው አወረደ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‘በቤቶቻችሁ ውስጥ ተቀላቀሏቸው፡፡ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት ሲቀር ሁሉንም ነገር ፈፅሙ’ አሉ፡፡ የሁዶች ይህ ነገር ሲደርሳቸው ‘ይሄ ሰውየ ከኛ ጉዳይ ውስጥ የሚፃረር ቢሆን እንጂ አንድም ነገር አልቀረውም!!’ አሉ፡፡...” [ሶሒሕ አቢ ዳውድ]
ስለዚህ ሸሪዐችን በወር አበባ ወቅት ሴቶችን በምግብ፣ በመኝታና መሰል ነገሮች ማግለልን አያስተምርም፡፡ ደሙ በራሱ ቆሻሻ ቢሆንም ከዚያ ባለፈ ሌሎች ዘንድ እንደሚስተዋለው መላ አካሏን የነካትን ነገር ሁሉ የረከሰ ነው አንልም፡፡ ያሳለፍነው ማስረጃ በቂ ቢሆንም ለማጠናከር ያክል ጥቂት እንጨምር
- በአንድ ወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ዓኢሻ ሆይ! እሱን ልብስ አቀብይኝ” ሲሏት “የወር አበባ ላይ ነኝ” አለቻቸው፡፡ ይህኔ እሳቸው “የወር አበባሽ ከእጅሽ ላይ አይደለም” አሏት፡፡ [ሙስሊም] መይሙናም ረዲየላሁ ዐንሃ ባለቤቷ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የወር አበባ ላይ እያለች አብረዋት ይተኙ እንደነበር ገልፃለች፡፡ [ሙስሊም] ኡሙ ሰለማህ ባስተላለፈችው ደግሞ “በአንድ ወቅት ከአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጋር ጋቢ ለብሼ ተኝቼ ሳለሁ የወር አበባየ መጣብኝና ቀስ ብየ ወጣሁኝና የወር አበባ ልብሴን ያዝኩኝ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‘የወር አበባሽ መጣ?’ አሉኝ፡፡ ‘አዎ’ አልኳቸው፡፡ ከዚያም ጠሩኝና በጋቢው ውስጥ አብሬያቸው ተኛሁኝ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
- እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ “የወር አበባ ላይ ሆኜ የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እራሳቸውን አጥብ ነበር”፣ “ፀጉራቸውን አበጥር ነበር” ትላለች፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]፣ [ቡኻሪ]
- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የወር አበባ ላይ ካለች ሚስታቸው ጋር አብረው ይበሉና ይጠጡ ነበር፣ ኧረ እንዳውም ከዚያም በላይ!! ዓኢሻህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዲህ ትላለች “የወር አበባ ላይ እያለሁ እጠጣና ከዚያም ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም (መጠጫውን) አቀብላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም አፋቸውን አፌን ካሳረፍኩበት ቦታ ላይ አድርገው ይጠጡ ነበር፡፡ የወር አበባ ላይ ሆኜ አጥንት እግጥና ከዚያም ለነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አቀብላቸዋለሁ፡፡ እሳቸውም አፋቸውን አፌ ካረፈበት ቦታ ያደርጉ ነበር፡፡” [ሙስሊም]
- እንዳውም የወር አበባ ላይ ካለች ሚስታቸው እቅፍ ስር ሆነው የተከበረውን ቁርኣን ያነቡ ነበር፡፡ እናታችን ዓኢሻህ እንዲህ ትላለች፡- “(ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እኔ የወር አበባ ላይ ሆኜ ከእቅፌ ውስጥ ይደገፉ ነበር፡፡ ከዚያም ቁርኣን ይቀሩ ነበር፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] “ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እኔ የወር አበባ ላይ እያለሁ ከጎናቸው ተኝቼ ይሰግዱ ነበር፡፡ ሱጁድ ሲወርዱ ልብሳቸው ይነካኝ ነበር” ትላለች፡፡ [ቡኻሪ]
- ባጭሩ ከላይ እንዳሳለፍነው ከግብረ-ስጋ ግንኙነት ውጭ ሁሉም ነገር ይፈቀዳል፡፡ እናም ብልት በሚገባ ከተሸፈነ ያሰኘውን ከሚስቱ ጋር መጫወትና መጣቀም ይችላል ማለት ነው፡፡ ኢብኑ ቁዳማህ ረሒመሁላህ “የደሙ ቦታ በክልከላ መለየቱ ከሱ ውጭ ባሉት የተፈቀደ መሆኑን ጠቋሚ ነው” ይላሉ፡፡ [አልሙግኒ፡ 1/415] ይህ ማለት ግን በፊንጢጣ ግንኙነት መፈፀም ይፈቀዳል ማለት አይደለም፣ ነዑዙቢላህ! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ የተረገመ ነው!” ብለዋልና፡፡ [ሱነን አቢ ዳውድ፡ 2162] በተጨማሪም “…ሴትን በፊንጢጣዋ የተገናኘ ወይም ከጠንቋይ ዘንድ የሄደ ሰው በሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል” ብለዋልና፡፡ [ሶሒሑትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 2433]
ማሳሰቢያ፡-
የወር አበባን የሚመለከተው ብይን የወሊድ ደምንም በተመሳሳይ ይመለከታል፡፡ ኢብኑ ቁዳማህ ረሒመሁላህ “የወሊድ ደም ላይ ያሉም ልክ የወር አበባ ላይ እንዳለችዋ ነው የሚታዩት በዚህ ረገድ” ይላሉ፡፡ [አልሙግኒ፡ 1/419] ወላሁ አዕለም፡፡ ሼር ማድረግ አይርሱ፡፡ ሌሎችን ከጥፋት ይታደጉ፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሐሴ 15/2007)

Post a Comment

1 Comments