Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በ ሱብሂ ሰላት ውስጥ «ቁኑት» አለን?


Abubeker Delil
በ ሱብሂ ሰላት ውስጥ «ቁኑት» አለን?

(ሙሉውን ላያነቡት አይጀምሩት! ጉዳዩ ብዙዎችን ያነጋገረ እና ብዙ ኡለማኦች ግራ የተጋቡበት ርእስ ነውና አንብበው ይጠቀሙበት የቁኑት ትርጉምንም በአጭሩ ከታች ተጠቅሷል)
《《《★በዚህ ጉዳይ ላይ የኡለማኦች አቋም አራት አይነት ሲሆን በአጭሩ ይሄን ይመስላል።
① ቁኑት በ ሱብሂ ሰላት ጠንካራ ሱና ነው! በእርሱ ላይ መዘውተር ተወዳጅ ነው!
ይህ አቋም ማሊክ አና ሻፊኢይ የመረጡት ሲሆን ለዚህ አመለካከታቸው መረጃችን ነው ያሉትን እንዲህ ጠቅሰውታል።
1 «...ነብያችን በሱብሂ ሰላት «ቁኑት» ያደርጉ ነበር...»
(ሙስሊም 678 ቲርሚዚ 401 አቡዳውድ 1441 ነሳኢ 2/202)
2 «...አነስ (ረዲየላሁ አንሁ) በሱብሂ ሰላት ነብያችን «ቁኑት» ያደርጉ ነበር? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ "አዎን" (ያደርጉ ነበር) ብለዋል።
(ቡኻሪ 1001 ሙስሊም 677)
3«...የአላህ መልእከተኛ ዱንያን እስኪለያዩ ድረስ በሱብሂ ሰላት «ቁኑት» ከማድረግ አልተወገዱም...»
(አህመድ 3/164 ዳረቁጥኒይ 2/39 በይሀቂይ 2/201 ኢብኑ አል―ጀውዚ በ «ኢለል –አል–ሙተናሂያህ» 1/441 ላይ ዘግበውታል ሀዲሱ ግን ተቀባይነት የለውም ሰሂህ ፊቅሁ ሱና 1/365 ይመልከቱ)
በመጨረሻም እነዚህና መሰል መረጃዎችን በመጥቀስ አቋማቸውን ገልፀዋል።
② ይህ አቋም ደግሞ በሱብሂም ይሁን በሌሎች ፍርድ ሰላት ላይ «ቁኑት» ማድረግ የተሻረ «መንሱኽ» እና ቢድኣህ (ፈጠራ) ነው! ብለዋል። አቡ ሀኒፋ ይህን መርጠዋል።
ለዚህ አቋማቸውም መረጃ ነው ያሉትን ሲጠቅሱ ደግሞ 1 አቢ ማሊክ አል አሸጃኢይ ለአባቱ: – አባቴ ሆይ! ከነብያችን ፣ ከ አቡበከር ፣ ከ ኡመር ፣ ከኡስማን እንዲሁም እዚህ ኩፋ ውስጥ ከአሊይ ጀርባ ለ ሃምሳ (50) አመት ሰግደሀል። ቁኑት ያደርጉ ነበር ወይ? አለ። አባቱም: – ለጄ ሆይ! (ይሄማ) ፈጠራ ነው አሉት።
(ቲርሚዚ 402 ኢብኑ ማጃ 1241 አህመድ ደግሞ በሙስነዳቸው 3/472 ላይ ዘግበውታል። የሰነድ ቅብብሎሹ ትክክል (ሰሂህ) ነው ሰሂህ ፊቅሁ ሱና 1/365 ይመልከቱ)
2 አሙ ሰለማ እንዲህ ብላለች«... በሱብሂ ቁኑት ከማድረግ የአላህ መልእከተኛ ከልክለዋል...»
(ዳረ ቁጥኒ 2/38 ዘግበውታል የሰነድ ቅብብሎሹ ግን «ታሊፍ» ነው ተብሏል የቀደመውን ምንጭ 1/365 ይመልከቱ)
3 ኢብኑ ኡመር ስለ ቁኑት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል «...ማንም ሲሰራው ተመልክቼው አላቅም...»
(አብዱረዛቅ 4949 ላይ ዘግበውታል)
አና እነዚህን መሰል ዘገባዎች በመጥቀስ የተሻረ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል።
③ ይህ ሶስተኛው አቋም እንደሚያስረዳው ችግር እና መቅሰፍት ካልወረደ በስተቀር ቁኑት አይደረግም ይላል። ይህ የኢማም አህመድ እንዲሁም ከፊል ከኋላ የመጡ የሀነፊያ መዝሀብ ተከታዮች አቋም ነው።
መረጃቸውም በአነስ ሐዲስ የአላህ መልእከተኛ ለሰዎች ዱአ ሊያደርግ ወይ በሰዎች ላይ ዱአ ሊያደርግ ካልሆነ በስተቀር «ቁኑት» አያደርጉም ነበር። ብሏል። (ኢብኑ ኹዘይማ 620 ላይ ዘግበውታል ሰነዱ «ለይን» ነው ተብሏል ሰሂህ ፊቅሁ ሱና 1/366 ይመልከቱ) ይህንን በመጥቀስ ያለ ምክንያት ቁኑት እንደማይኖር አስረድተዋል።
④ ቁኑት ማድረጉም ሆነ መተው ይቻላል! ይላል የመጨረሻው እና ሱፊያን አስ–ሰውሪ ፣ አጥ– ጠበሪ ፣ ኢበኑ ሀዝም እና ኢብኑል–ቀይም የመረጡት አቋም። (ታህዚቡል–አሳር 1/337 አል–ሙህላ 3/143 ዛዱል–መአድ 1/274 ይመልከቱ)
ኢብኑል ቀይም ኪታቡ ሰላት ወ ሁኩሙ ታሪኩሀ በሚባለው መፅሀፋቸው ( ገፅ 120) ላይ የሐዲስ ሰዎች በሱብሂ ሰላት ቁኑትን በሚከለክሉት እና በመቀሰፍት መውረድ ብቻ ተግባሩ የተወደደ ነው በሚሉት ሰዎች መሐል ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም ድርጊቱን መፈፀምም ሆነ አለመፈፀም ሱና መሆኑን እንዲሁም በሰራውም ሆነ ባልሰራው ባጥላላውም ሆነ ባስወደደው አካል እንደማያነውሩ ገልፀዋል።
ታድያ ትክክለኛው አቋም የትኛው ነው?
በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ ከብዙ ትግል እና እልህ አስጨራሽ አሰሳ በኋላ ኡለማኦች ተከታዩን አቋም ይዘዋል።
« በሰነድ ቅብብሎሹም ሆነ በንግግር ደረጃ ሰሂህ የሆኑ ሀዲሶች እንደሚጠቁሙት ነብያችን በምክንያት እና በመቅሰፍት ግዜ ብቻ ነው ቁኑትን የተጠቀሙት አንዲሁም እንዳንዴ መስራቱ እና እንዳንዴ መተዉ የተሻለ ነው! አላሁ አእለም!
ማሳረጊያ!
ከዚህ ውጪ እንዳንድ በእውቀት ያልበሰሉ እንጭጭ ወጣቶች የሚሰሩት የተገበረውን ሰው ሙብተዲእ ብሎ የሚፈረጅ ተግባር ከሱና እንዳልሆነ ሳናስታውስ አናልፍም። (ሰሂህ ...1/367)》》》
__________________________
ምንጭ እና የገፅ ቁጥር የምጠቅሰው በጭፍን ከመከተል ለመራቅና ለፈላጊዎች መመለሻ እንዲሆን ነው ሌሎች አስታዋሾችም ቢሆኑ ይህን መንገድ ቢከተሉ የተሻለ ይመስለኛል! ወሰላም!
__________________________________
ቁኑት ማለት ከ ቋንቋዊ ትርጓሜው ከተነሳን በትእዛዝ መዘውተር ፣ ፍራቻ ፣ ዝምታ እና መሰል ፍቺዎች አሉት እዚህ ቦታ ላይ ግን የተፈለገው ከዊትር በኋላ የሚደረገው ዱአ ነው! ይህም ከመጨረሻው ሩኩእ መነሳት በኋላ ተቁሞ የሚደረግ ነው።
_________________________