Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ፦ ሴት ያለ መሕረም¹ ሐጅ ብታደርግ ሐጇ ትክክል ነውን? ራሱን ያላወቀ ታዳጊ ልጅ መህረም ሊሆን ይችላልን? የመሕረም ሸርጦች ምንድን ናቸው? ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አልዑረይሚን ረሒመሁላህ



ጥያቄ፦ ሴት ያለ መሕረም¹ ሐጅ ብታደርግ ሐጇ ትክክል ነውን? ራሱን ያላወቀ ታዳጊ ልጅ መህረም ሊሆን ይችላልን? የመሕረም ሸርጦች ምንድን ናቸው?

መልስ፦ ሐጇ ትክክል ነው። ነገር ግን ድርጊቷ ማለትም ያለመሕረም ጉዞ ማደረጎ ሐራም ነው። የነቢዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ትእዛዝ መጣስ ነው። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) 《ሴት መሕረም ከሆነ ዘመዷ ጋር ካልሆነ በስተቀር ጉዞ ማድረግ አትችልም》 ብለዋል። (ብኻሪና ሙስሊም)

– ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ልጅ መሕረም ሊሆን አይችልም። ራሱም ጥበቃ ያስፈልገዋልና። ለራሱም የሚጠበቅ ሰው ሌላውን መጠበቅ አይችልም። 

– የመሕረም ሸርጦች መስሊም መሆን፣ ወንድ መሆን፣ ለአቅመ አዳም የደረሰ መሆንና ሙሉ የአእምሮ ጤንነት ያለው መሆን ናቸው። ይህን ካላሟላ መህረም ሊሆን አይችልም።

እዚህ ላይ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ አለ። አንዳንድ ሴቶች ያለመሕረም በአውሮፕላን ጉዞ ያደርጋሉ። ነገሩን እንደቀላል በማየት። ብቻዋን ያለመሕረም በአውሮፕላን ትሄዳለች። ለዚህም የምትሰጠው ምክንያት አንዱ መሕረሟ ከምትነሳበት አየር ማረፊያ ሲሸኛት ሌላ መሕረሟ ደግሞ በምትወርድበት አየር ማረፊያ ሆኖ ይቀበላታል፤ በአውሮፕላን ውስጥ ደግሞ የሚነካት ነገር የለም የሚል ነው። ተጨባጩ ሲታይ ግን ይህ ምክንያቷ ደካማ ነው። የሚሸኛት መሕረሟ ወደ አውሮፕላኑ አያስገባትም። ወደ መጠበቂያ አዳራሽ ብቻ ነው የሚያስገባት። ምናልባት አውሮፕላኑ ከማረፊያው ሳይነሳ ይዘገይና ሴትየዋ ብቻዋን ልትቀር ትችላለች። ወይ ደግሞ አውሮፕላኑ በሆነ ምክንያት በሚሄድበት ወቅት ማረፊያ ማረፍ ሳይችል ቀርቶ ሌላ ቦታ ሊያርፍ ይችላል። እናም ይህቺ ሴት ብቻዋን ልትቸገርና ልትጠፋ ትችላለች። ወደፈለገችው አየር ማረፊያ ደርሳም እንኳ ይቀበላታል የተባለው መሕረሟ ሊቀርባት ይችላል። በበሽታ፣ በእንቅልፍ፣ በመኪና አደጋ ወይም በሌላ ምክንያት ሳይመጣላት ሊቀር ይችላል።

ስለዚህ ማንኛውም ሴት አላህን መፍራት አለባት። ከመሕረሟ ጋር እንጂ ጉዞ ማድረግ የለባትም። አላህ በሴቶች ላይ ሃላፊ ያደረጋቸው ወንዶችም አላህን መፍራት አለባቸው። ሴቶቻቸውን ብቻቸውን መልቀቅ የለባቸውም። ቅናትና ዲን ማጣት የለባቸውም። ሰውየው ከቤተሰቡ ተጠያቂ ነው። አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) በአደራነት እሱ ዘንድ አኖሯቸልና። አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) እንዲህ ይላል ፦

يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ قُوٓا۟ أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًۭا وَقُودُهَا ٱلنَّاسُ وَٱلْحِجَارَةُ عَلَيْهَا مَلَٰٓئِكَةٌ غِلَاظٌۭ شِدَادٌۭ لَّا يَعْصُونَ ٱللَّهَ مَآ أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُون
َ
《እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከኾነች እሳት ጠብቁ፡፡ በእርሷ ላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የኾኑ መላእክት አልሉ፡፡ አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጹም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፡፡》
[አል–ተህሪም: 66፥6]

【ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አልዑረይሚን ረሒመሁላህ】