Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የተውሂድ አይነቶቹ



ተውሂድ፡- አላህን በጌትነቱ በብቸኛ ተመላኪነቱ በስሞቹ እና በባህሪያቱ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ተውሂድ በ ሦስት የሚከፈል ሲሆን እነሱም፡
-
1. ተውሂደ አል-ሩቡቢያህ:- አላህን በስራዎቹ አንድ ማድረግ፡፡ ይህም ማለት፤ መፍጠር፣ሲሳይን መስጠት፣ነገሮችን ማስተናበር፣ መግደል እና ህያው ማድረግ በመሳሰሉት ድርጊቶቹ አላህን ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡
• ከአላህ ሌላ ፈጣሪ የለም፡፡ አላህ ይህንን እንዲህ በማለት ይገልፅልናል፡-
(አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው) አል-ዙመር 62
• ከአላህ ሌላ ሲሳይን የሚሰጥ የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-
(በምድርም ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለም ሲሳዩ አላህ ዘንድ ያለ ቢሆን እንጂ) ሁድ 6
• ከአላህ ሌላ ነገሮችን የሚያስተናብር የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-

(ነገርን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያስተናብራል) አል-ሰጅዳህ 5
• ከአላህ ሌላ ህያው ሊያደርግ እንዲሁም ሊገድል የሚችል የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-

(እርሱ ህያው ያደርጋል ይገላልም ወደርሱም ትመለሳላችሁ) ዩኑስ 56

ይህን ዓይነቱን የተውሂድ ክፍል በረሱል ዘመን የነበሩ ከሀዲያን አጋሪዎች ያልካዱት ቢሆንም ከባዕድ አምልኮ ባለመላቀቃችዉ ወደ ኢስላም ሊያስገባቸው አልቻለም፡፡ አላህም ይህን የተውሂድ ክፍል ማረጋገጣቸውን በማስመልከት እንዲህ ይላል፡-
(ሰማያትና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ) ሉቅማን 25

2- ተውሂድ አል-ኡሉሂያህ፡- አላህን በአምልኮ አንድ ማድረግ፡፡ በዱዓእ (ልመና)፣በፍራቻ፣በመመካት፣እርዳታን እና ጥበቃን በመጠየቅ እንዲሁም እርሱ ባሮቹን ባዘዘባቸው ሌሎች አምልኮቶች ሁሉ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ የአምልኮ ዓይነቶችን ሁሉ ያለምንም አጋር ለርሱ ብቻ ማድረግን ግዴታ ያደርጋል፡፡
• ከአላህ ሌላ ማንንም አንለምንም፡፡ አላህ እርሱን ብቻ መለመን እንዳለብን ሲነግረን እንዲህ ይላል፡-
(ጌታችሁም አለ! ለምኑኝ እቀበላችሁአለሁና) አል-ጋፊር 60
• ከአላህ ሌላ አምልኮታዊ የሆነ ፍራቻን ማንንም ቢሆን አንፈራም፡፡ አላህ እንዲህ ይለናል፡-
(አትፍሯቸውም አማኞች የሆናችሁ እንደሆነ {እኔን ብቻ} ፍሩኝ) አል-ኢምራን175
• ከአላህ ሌላ በማንም አንመካም፡፡ አላህ አማኞች በእርሱ ላይ ብቻ ሊመኩ እንደሚገባ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡
(አማኞች እንደሆናችሁ በአላህ ላይ ብቻ ተመኩ) አል-ማዒዳህ 23
• ከአላህ ሌላ ፍጡራን በማይችሉት ጉዳይ ላይ እርዳታን ከአላህ ዉጪ ከማንም አንጠይቅም፡፡ ይህን በማስመልከት አላህ በሱረቱል ፋቲሀ ላይ ደጋግመን ምናነባቸዉን አንቀፆች አዉርዷል፡፡
(አንተን ብቻ እናመልካለን፤ ከአንተም ብቻ እርዳታ እንጠይቃለን) አል-ፋቲሀ 5
• ከአላህ ሌላ ከማንም ጥበቃን አንጠይቅም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
(የሰዎች ጌታ በሆነው እጠበቃለሁ በል) አል-ናስ 1

ይህ የተውሂድ ክፍል የአላህ መልዕክተኞች ለሰው ልጆች ለማስተላለፍ ከአላህ ይዘው የመጡት ዋነኛው መልዕክት ነው፡፡ ሁሉም ነብያቶቸ የዳዕዋቸዉ ዋና ተልዕኮ አምልኮን ባጠቃላይ ለአላህ ብቻ ማድረግ (ተውሂደል ኡሉሂያህ) ነው፡፡ ይህንን አላህ (ሱ.ወ) በቀጣዩ አንቀፅ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡
(በየህዝቡም ሁሉ ዉስጥ አላህን አምልኩ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኞችን በእርግጥ ልከናል) አል ነህል 36
ይህንኑ የተውሂድ ክፍል እና የነብያቶች መልዕክት ነዉ የፊተኞቹ ሆኑ በዘመናችን የሚገኙ አጋሪዎች ያስተባበሉት፡፡ የመካ ሙሽሪኮች መልዕክተኛው አንድን አምላክ ብቻ አምልኩ ባሏቸው ጊዜ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ አላህ እንዲህ ይላል፡-
(አማልክቶቹን አንድ አምላክ አደረጋቸዉን? ይህ አስደናቂ ነገር ነው‹አሉ›) ሷድ 5

አላህ (ሱ.ወ) በየዘመናቱ ከላካቸው ነብያት (ኑህ፣ሁድ፣ሳልህ እና ሹዓይብ) ጥሪ ይህን ይመስል እንደነበር በተለያዩ አንቀፆች ገልፆልናል (ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ ከእርሱ በቀር ምንም አምላክ የላችሁም...) አል-አእራፍ 59/65/73/85

3- ተውሂድ አል አስማዕ ወስሲፋት

በቁርዓን እና ትክክለኛ በሆኑ የመልዕክተኛው ሀዲሶች ውስጥ የመጡትን የአላህ ስሞች እና ባህሪያት ከማንም ስሞችና ባህሪያት ጋር ሳያመሳስሉ፣ ቃሉን ሳያዛቡ፣ ትርጉማቸዉን ሳይለውጡ ወይም ሳያስተባብሉ ለአላህ እንደሚገቡ በማመን ማፅደቅ ማለት ነው፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) ስሞች ብዙ ናቸዉ፡፡ ከነርሱም መሀከል ለምሳሌ አል-ራህማን፣ አል-ሰሚዕ፣ አል-በሲር፣ አል-አዚዝ እና አል ሀኪም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አላህ በአጠቃላይ በስሞቹ እና በባህሪዎቹ እሱን የሚመስል እንደሌለ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-
(እንደርሱ ያለ ምንም ነገር የለም፤ እርሱ ሰሚዉና ተመልካቹ ነው) አል-ሹራ 11

አላህን በመስማትም ይሁን በመመልከት ባህሪያቱ ፍፁም የሚመስለዉ የለም፡፡ ይህ አንቀፅ የአላህን ባህሪያት ዉድቅ ለሚያደርጉትም ይሁን በባህሪያቱ ከፍጡራን ጋር ለሚያመሳስሉት ሰዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ልንከተል የሚገባንን መርህ በሚገባ ቀርጿል፡፡አላህ እራሱን በገለፀባቸዉ ባህሪያቱ ስንገልፀዉ ከአምሳያ እናጠራዋለን!!


Sultan Khedir