Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ወደ ጥመት ተጣሪ ኢማሞችን ተጠንቀቋቸው!

ወደ ጥመት ተጣሪ ኢማሞችን ተጠንቀቋቸው!
ደጃልን የማያውቀው አለን? ስለርሱ ምን ታስባላችሁ? ስታስቡስ ምን ይሰማችኋል? ፍራቻ? ስጋት? አንድ አይንማ? ግንባሩ ላይ كافر የሚል ጽሑፍ ያለበትና ግዙፍ አካል ያለው . .? በሰው ልጅ ደረጃ ክፋትን ለመግለጽ ከደጃል በላይ ተምሳሌት አግኙ ብትባሉ ማንን ትጠቅሱ ይሁን?
አዎን! የደጃል ፈተና እጅግ የከፋ ነው! የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የርሱን መምጣት ስትሰሙ ሽሹ! አምልጡ! እጋፈጠዋለሁ ብላችሁ እንዳታስቡት! ምክንያቱም የርሱን ፈተና የሚስተካከል ኢማን ላይኖራችሁ ይችላልና!” ብለውናል! መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሚንበር ላይ ቆመው ስለ ደጃል ሁኔታ ለሶሓቦቻቸው ሲነግሯቸው ሶሓቦች በፍርሃት ይርዱ ነበር!
አይገርምም!? በጣም ነው እንጂ የሚገርመው!
እሺ እሱ እንደዛው እንዳለ መልእከተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከደጃል በላይ ለኡማቸው የሚፈሩት ነገር አለ ብላችሁስ? ምን ታስባላችሁ? መቼስ ይህ ከጭንቅላት በላይ መሆን አለበት ትሉ ይሁን?
በርግጥም ነው! እጅጉን ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት፤ ባልተጠበቀ መልኩ ብዙሃን የሚወድቁበት ሙከራ፤ ከሙስሊሞች ሁሉ መልካም የተባሉት ሁሉ የሚታለሉበት አዳጋች መሰናክል . . ነው!
እናሳ! ታዲያ እርሱ ምንድን ነው?
እናንብባ . .
أَخْبَرَنِي أَبُو ذَرٍّ ، قَالَ : " كُنْتُ أَمْشِي مَعَ رَسُولِ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ، فَقَالَ : ( لَغَيْرُ الدَّجَّالِ أَخْوَفُنِي عَلَى أُمَّتِي ) قَالَهَا ثَلَاثًا . قَالَ : قُلْتُ : يَا رَسُولَ اللهِ ، مَا هَذَا الَّذِي غَيْرُ الدَّجَّالِ أَخْوَفُكَ عَلَى أُمَّتِكَ ؟ قَالَ : ( أَئِمَّةً مُضِلِّينَ )
አቡ ዘር እንዲህ አሉ . . “አንድ ቀን ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጋር በእግር እየተጓዝኩ ነበር። እንዲህም ሲሉ ሰማኋቸው . . « ከደጃል በላይ ለኡመቴ የምፈራው ነገር አለ።» እኔም. . «ምንድን ነው ከደጃል በላይ ለሕዝቦቾት የሚፈሩት ያ ረሱሉላህ?» ብየ ጠየቅኳቸው። እሳቸውም. . «ጠማማ ኢማሞችን!» ብለው መለሱልኝ።”
[ሙስነድ ኢማም አሥመድ ረሒመሁላህ]
“ጠማማ ኢማሞች” እዚህ ጋር መግለጽ የተፈለገው ወደ ጥመት የሚጣሩ ዑለማዎች፥ ብልሹ የሆኑ መሪዎችን፥ ዑለማም ሆነ አዋቂ ሳይሆኑ እንኳን በብዙኃን ዘንድ እውቅናን የተቸሩ ታዋቂ ስብእናዎችን ሊሆንም ይችላል።
ዛሬ ላይ ይህ ከደጃል የበለጠ ለእኛ የተፈራልን ፈተና እፊታችን አጋርጦብናል! እመኑም ካዱም ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ዛሬ ላይ የጥመት ተጣሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። ፈተናቸውን መቋቋም በማንችልበት ሁኔታ በየጓዳችን ገብተዋል። ከአፋቸው የሚወጣው የማር እሾህ ተታለን ወደ ጥመት ሲነዱን “በጀ” ብለናል። በየቲቪ ቻናል እና በየራዲዮው ብሎም በየሕትመት ውጤቱ እኛ ጋር ለመድረስ ሲንጠራሩ “አትልፉ! እኛው ያላችሁበት እንመጣላችኋለን!" ብለን ወደነርሱ ዘምተናል። ዲናችን ምሉእ መሆኑን አስተባብለን እነዚህ ሰዎች ያመጡልንን ጭማሪ ተግተናል። ጭማሪዉን ይዘን መሰረቱን ጥለናል። ይህን ፈተና የተረዱ ቅን ዑለማዎች ሲመክሩን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብለን ሸሽተናል። እነዚህ ከደጃል የበለጠ ለእኛ የተፈሩልን የጥመት ተጣሪ የፈተና ስብእናዎች ሲነኩብን ነደናል። የአላህ መብት ሲነካ ግን ተኝተናል። በነዚሁ ስብእናዎች ባለሙያነት የረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ፈለግ በልካችን ተቆርጦ ተሰፍቶ ሲሰጠን “እንዴታ! ይህ ነው እንጂ ኢስላም” ብለናል።. . ምን ይሻለናል?
ከደጃል በበለጠ ለእኛ የተፈራልን ፈተና እፊታችን ተጋርጧል! ጠማማ የጥመት ተጣሪዎች “ኑ! ወደ እኛ!” ብለው ይጠሩናል። የእኛ መልስ ከ “እሺታ” ይልቅ እግሬ አውጭኝ ሊሆን ይገባል!! አዎን! “ደጃል መጣ!” ሲባል እንደምንሸሸው ልንሸሻቸው ይገባል! አፍዝ አደንግዝ ምላሳቸው እንደ እሬት ሊመረን ይገባል! እርግጥ ነው የፈተናቸው ደረጃ በተጨባጭ ደጃል ላይ ይደርሳል ባንልም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሰጉልን ይህን ትልቅ ፈተና በዱዐ እና በሶብር ከትክክለኛ ዑለማዎች ምክርን በማድመጥ ልናልፈው በእኛ ላይ የተገባ ነው።
አላህ ከጠሞ አጥማሚ የጥመት ተጣሪዎች ይጠብቀን
by Abu Aisha