Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ፋጢማ ቢንቲ ነስር ኢብኑል ዐጥጧር አልበግዳዲያ ረሒመሀላህ

ፋጢማ ቢንቲ ነስር ኢብኑል ዐጥጧር አልበግዳዲያ ረሒመሀላህ ለዱንያ ብልጭልጭ ደንታ የሌላት ዛሂዳ፣ አላህን በብዛት የምትገዛ ዓቢዳ፣ እጅግ ጌታዋን የምትፈራ ታላቅ ሴት ነበረች። ጀናዛዋን ታላላቆች የሸኙት ሲሆን በእለቱ ጎዳናዎችን ያጨናነቀው ህዝብ ብዛት ለዒድ ሶላት ከሚወጣው የበዛ ነበር። ፋጢማ በህይወቷ ከቤቷ የወጣችው ሶስት ጊዜ ብቻ ነው። እሱም ለአስገዳጅ ጉዳይ። [አልቢዳያ ወንኒሃያ: 12/367] ከቤቷ የወጣችው
① ያገባች እለት፣
② ሐጅ ያደረገች እለት እና
③ የሞተች እለት" ብቻ ነው ይባላል። ወላሁ አዕለም።
እቱ: አንቺ በሳምንት ስንት ጊዜ ከቤትሽ ትወጫለሽ? ምክንያቶችሽ ምን ያክል አንገብጋቢ ናቸው? እስኪ ጣጣ ሳያመጣ በፊት "እግሬ ሆይ! እግር አታብዛ" ብለሽ ንገሪው። ነገ ምላስሽ ተለጉሞ ባንቺው ላይ ሊመሰክር የሚቆምበትን ጊዜ ዛሬ አስታውሽው። ጠቢቡ እንዳለው ከፊታችን አንድ ቀን አለ። ያ እንኳን
(يَوْمَ تَشْهَدُ عَلَيْهِمْ أَلْسِنَتُهُمْ وَأَيْدِيهِمْ وَأَرْجُلُهُمْ بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ)
"በእነሱ ላይ ምላሶቻቸው፣ እጆቻቸውና እግሮቻቸው ይፈፅሙት በነበሩት ነገር የሚመሰክሩባቸው ቀን፡፡" [አንኑር: 24]
እና እህቴ! ጌታሽ ካንቺ ስንት እጥፍ ለሚያስከነዱ ንፁህና ቁጥብ ለሆኑት የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሚስቶች እንኳን እንዲህ ብሏል:
(وَقَرْنَ فِي بُيُوتِكُنَّ وَلَا تَبَرَّجْنَ تَبَرُّجَ الْجَاهِلِيَّةِ الْأُولَىٰ ۖ وَأَقِمْنَ الصَّلَاةَ وَآتِينَ الزَّكَاةَ وَأَطِعْنَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ ۚ إِنَّمَا يُرِيدُ اللَّهُ لِيُذْهِبَ عَنْكُمُ الرِّجْسَ أَهْلَ الْبَيْتِ وَيُطَهِّرَكُمْ تَطْهِيرًا)
"በቤቶቻችሁም ውስጥ እርጉ፡፡ እንደ ቀደምቱ የዘመነ መሃይምነት መራቆትም አትራቆቱ፡፡ ሶላትንም በደንቡ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ታዘዙ፡፡ የነቢዩ ቤተሰቦች ሆይ! አላህ የሚሻው ከእናንተ ላይ እርክሰትን ሊያስወግድና ማጥራትንም ሊያጠራችሁ ብቻ ነው፡፡" [አልአሕዛብ: 33]
ስለዚህ:
① አስታውሺ። አላስፈላጊ ዙረት በመቀነስ ከቤትሽ መረጋጋትሽ በራሱ ከጌታሽ አጅር የምታገኝበት ዒባዳ ነው።
② ባይሆን ወላጆችሽን፣ ዘመዶችሽን ለመጠየቅ፣ ሶላት በመስጂድ ለመስገድ (በላጩ በቤት ከመሆኑ ጋር)፣ ዒድ ላይ ለመካፈል፣ ደዕዋ ወይም ደርስ ላይ ለመታደም፣ ወዘተ መውጧትሽ ከዚህ ዒባዳ ጋር የማይጋጭ ሌላ ዒባዳ እንደሆነ ይስተዋል።
③ ሌላም አለ። ታላላቅ ሶሐብያት ከቤታቸውም ወጥተው የቤታቸውን ቀዳዳ ለመድፈን ተፍ ተፍ ይሉ እንደነበር ብዙ መረጃዎች አሉ። ይህም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች መውጣቷ ችግር እንደሌለው ጠቋሚ ነው። ሶሐብያት ሌላው ቀርቶ ከዘማቾች ጋር በመውጣት ስንቅ ያቀርቡ፣ የቆሰሉን ያክሙ ነበር።
ባጭሩ በልክ መሆን ጥሩ ነው። ባንድ በኩል እንደ ዘመኑ ሴቶች በውሃ ቀጠነ ያለ ፈቃድ ዙረት ማብዛት፣ በየካፍቴሪያው ከወንድ ጋር መጋፋት፣ በሚፈለጉ ጊዜ ከቤት መታጣት፣ ወዘተ ... ይሄ ከሙስሊም ሴቶች የማይጠበቅ የሐያእ መቅለል ነው። ነገር ግን በቤቷ መቀመጧ ከቤተሰቦቿ ጋር እስከምትቆራረጥ፣ ይበልጥ ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን እስከ ማሳለፍ ሊያደርሳት አይገባም። "ከነገር ሁሉ በላጩ መካከለኛ የሆነው ነውና።"
[ኢብኑ ሙነወር: ታህሳስ 04/2009]