ኢንተርኔት ተከፈተልን ወይስ ተከፈተብን?
********
ባለፉት ወራት ኢንተርኔት በመቋረጡ ምን ተሰምቶት ይሆን?
.
ኢንተርኔት የሚሰጠው ግልጋሎት ተቆጥሮ የሚዘለቅ አይደለም። አጠቃቀሙ በሸሪዓዊ ልጓም ታስሮ ስርአት ካልያዘ ግን ለሁሉም ሰው አደጋ ነው። ኢንተርኔት በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ ለብዙዎች ጥቅም የሌለው ጎጂ ሱስ እየሆነ በመምጣቱ እራሱን የቻለ ቤተሰባዊና ማህበራዊ እክል ሆኗል። ኢንተርኔት የተዘጋበት አጋጣሚ ብዙዎች እራሳቸውን ለመገምገም እድል ፈጥሯል። ሁሉም ነገር ልክ አለውና ለከት ያለፈ ፍላጎታቸውን በችግርነት የታዘቡ አሉ። ከሰሞኑ የመስጂዶችና የኢልም መድረኮች መሟሟቅ የዚህ ጉልህ ማሳያ ነው።
.
በኢንተርኔት ምክኒያት የአላህን የነብስን እና የቤተሰብን ሀቅ ማጓደልንም ብዙዎች አስተውለው እራሳቸውን አርመዋል። ለመሆኑ ህይወት ኦፍላይን እንዲህ ትጣፍጣለች እንዴ? ምናባዊ ሀያት እንኳንም ቀረብን ያሉም አሉ። አጋጣሚዎችን ለመልካም ስብእና መገንቢያ መጠቀም ብልህነት ነውና፤ ከተፅእኖ ነፃ እያለን እራሳችንን ገምግመን ለመንፈሳዊና ለአለማዊ ህይወታችን የሚበጅ ፕሮግራም ካልቀረፅን ጥፋታችን የበዛ ይሆናል።
እያንዳንዱ ፀጋ ያስጠይቃልና አጠቃቀማችንን ልንገመግም ይገባል።
.
ኢብኑ መስኡድ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤
.
لا تزول قدم ابن آدم يوم القيامة من عند ربه حتى يسأل عن خمس : عن عمره فيم أفناه ، وعن شبابه فيم أبلاه ، وماله من أين اكتسبه وفيم أنفقه ، وماذا عمل فيما علم
.
«በትንሳኤ እለት የአደም ልጅ አምስት ነገሮችን ሳይጠየቅ እግሮቹ ከጌታው ዘንድ አይራመዱም።
እድሜውን በምን እንደፈጀው፣ ወጣትነቱን በምን እንዳሳለፈው፣ ገንዘቡን ከየት እንዳመጣውና በምን ላይ እንዳዋለው፣ ባወቀው ምን እንደሰራበት» ቲርሚዚ ዘግበውታል
.
አዎን! በአኼራ ስለ ሁሉም ነገር ከመመርመራችን በፊት ዛሬ የኢንተርኔት አጠቃቀማችንን ማጤን፤ በግልም ይሁን በገሀድ ጣቶቻችን የሚፅፉትን ሁሉ መገምገምና አራስን ማረም ወቅቱ ነው።
.
ኸሊፋው ኡመር ኢብኑልኸጣብ እንዲህ መክረዋል፤
.
(حاسبوا أنفسكم قبل أن تحاسبوا، وزنوها قبل أن توزنوا، فإن أهون عليكم في الحساب غداً أن تحاسبوا أنفسكم اليوم).
.
.«ከመመርመራችሁ በፊት እራሳችሁን ተሳሰቡ። ከመገምገማችሁ በፊትም ስራችሁን ገምግሙ። የዛሬ እራስን መመርመርና መተሳሰብ ከነገው ምርመራ ለናንተ የቀለለ ነው። »
.
ኢንተርኔት ቢለቀቅም ከጊዜም ይሁን ከአጠቃቀም አንፃር ገደብ ባለው ሁኔታ ልንጠቀም እንደሚገባ መዘንጋት የለብንም!!
----
አቡጁነይድ
ህዳር 24/2009