Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በትዳር ላይ ጣልቃ ገብነት ያለው ክፋት



በትዳር ላይ ጣልቃ ገብነት ያለው ክፋት

ትዳር:~
በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ የጋራ ስምምነትና መቻቻል ላይ የተመሰረተ ውልና ሂደት ነው ።
በውስጡ በርካታ ሚስጢሮችንም ያቀፈ ህይወት ነው።
~ በዚህም ሂደት ለየት ያለ የህይወት መስመር ይዘረጋል።
~ ወንዱም ሆነ ሴቷ በየትኛውም ፕሮጀክት ሊያስገኙት የማይችሉትን ጥቅሞች ያተርፉበታል።
በትዳር:~
ሰዋዊ ወይም ስጋዊ ስሜታቸውን በሃላል ያረኩበታል። ገላ ሰውነታቸውን እንዲሁም አዕምሯቸውን ያነቃቁበታል ያሳርፉበታል።
ይህንን ታላቅ ልገሳም
አላህ አዝዘ ወጀልለ በሚቀጥለው መልኩ ይገልፅልናል
« هُوَ الَّذِي خَلَقَكُمْ مِنْ نَفْسٍ وَاحِدَةٍ وَجَعَلَ مِنْهَا زَوْجَهَا لِيَسْكُنَ إِلَيْهَا…… »
الأعراف: 189
« እርሱ ያ ከአንዲት ነፍስ (ከኣደም) የፈጠራችሁ ከእርሷም መቀናጆዋን ወደርሷ ይረካ ዘንድ ያደረገ ነው።»
አል-አዕራፍ : 189
ይላል
በሌላ በኩል ከትዳር:~
የሚወዱትን፣ የሚናፍቁትን የአይን ማረፍያ፣ የልብ መርጊያ ፍቅረኛ ወዳጅ በፍቁድ መንገድ ያገኙበታል።
ብሎም በትዳር:~
ዝርያ ይቀጥሉበታል፣ አይናቸውን በአይናቸው በማየት የአብራካቸውን ክፋይ፣ ተተኪያቸውን በትክክለኛው የማፍሪያ መስመር ያፈሩበታል።
እንዲሁም በትዳር:~
ልክ ወላጆቻቸው ዘንድና ጓዶቻቸው ዘንድ አይተው ሲመኙት የነበረውን በቁጥርም በይዘትም መልካም የሆነን ቤተሰብ ያቋቁሙበታል። ዘመድ አዝማድም ያስፋፉበታል።
ለትዳር ከታደሉ:~
የራስ ቤት የራስ ጎጆ በመፍጠር አዲስ ጎረቤት፣ አዳዲስ ወዳጆችን ይመሰርቱበታል።
በተለይ በትዳር:~
የኔ የሚሉትን ደጋፊና ተቆርቋሪ ታማኝ ወዳጅ ከጎን ያገኙበታል። እሱ ለሷ አሷም ለሱ ከማንም በላይ ጓጊና አዛኝ ይሆናሉና።
አላሁ ሱብሃነሁ ወተዓላ ይህንኑ እንድናስተውል ያመላክተናል ።
« وَمِنْ آَيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُمْ مِنْ أَنْفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِتَسْكُنُوا إِلَيْهَاوَجَعَلَ بَيْنَكُمْ مَوَدَّةً وَرَحْمَةً إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآَيَاتٍ لِقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ »
الروم: 21.
« ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደ እነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ ፤ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህም ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ተዓምራቶች ኣልሉ። »
አል ሩም: 21
ይለናል
ሌላኛው ጥቅም በትዳር:~
ከተለያዩ የዘመኑ ፈተናዎችም ሆነ ከግልፁ ዝሙት ይጠበቁበታል። ብሎም የላጤነትን ቁጥር በማሳነስ ብልሹና ርካሽ ምግባርን ለመቀነስ ድርሻቸውን ይወጡበታል። የህብረተሰቡም ክብርና ዝርያ ይፀዳበታል።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳስጠነቀቁን
« إذا جاءكم من ترضون دينه وخلقه فأنكحوه إلا تفعلوا تكن فتنة في الأرض وفساد كبير …… »
« ዲኑንና ስነምግባሩን የምትወዱለት ሰው ለጋብቻ ፍለጋ ሲመጣችሁ አጋቡት። ይህ ካልሆነ ግን በምድር ላይ ከባድ የሆነ ፈተናንና ብልሽትን ታሰፍናላችሁ ። »
በዚህ ሀዲስ መልእክተኛው ዲኑን በመተግበር የሚታወቅ ብሎም መልካም ባህሪ ያለው ሰው እናንተ ዘንድ ያለችን ሴት ሊያገባት ሲጠይቃችሁ እምቢ አትበሉትና አጋቡት። የማታጋቡትና ምትመልሱት ከሆነ ትርፉ ሴቷን መበደልና ወንጀልን ማስፋፋት እንጂ ጠቃሚ ነገር የለውም እያሉን ነው።
በተጨማሪም ለመልካም ትዳር የታደሉ:~ ክቡር መንደር፣ ሃገርና ማህበረሰብ ይገነቡበታል ።
እንዲሁም እሱ በሷ እሷ በሱ ብሎም በሚያፈሩት ልጆችም ሰበብ የዱንያ ላይ ሪዝቃቸውን ያሰፉበታል።
ከጋብቻ በፊት የነበረው ጥበትና ድህነትም ከትዳር በኋላ እየቀለለና የጎደለው እየሞላ እየተመቸ ይሄዳል።
በመልካምነታቸው ልክም የዱንያንና የኣኺራን ስኬት ይጎናፀፉበታል።
ሱረቱል ኑር ላይ ያለውን አንቀፅ
32 ትን ልብ ይበሉ
« وَأَنْكِحُوا الْأَيَامَى مِنْكُمْ وَالصَّالِحِينَ مِنْ عِبَادِكُمْ وَإِمَائِكُمْ إِنْ يَكُونُوا فُقَرَاءيُغْنِهِمُ اللَّهُ مِنْ فَضْلِهِ وَاللَّهُ وَاسِعٌ عَلِيمٌ »
{النور:32}
« ከእናንተም ትዳር የሌላቸውን አጋቡ። ከወንዶች ባሮቻችሁና ከሴቶች ባሮቻችሁም ለጋብቻ ብቁ የሆኑትን አጋቡ ። ድሆች ቢሆኑ አላህ ከችሮታው ያከብራቸዋል። አላህም ስጦታው ሰፊ አዋቂ ነውና»
******
እርግጥ ነው እነዙህ ሁሉ ጥቅሞችና ስኬቶች በሁሉም ትዳሮች ላይ ላይኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በመቻቻል እና በመተላለፍ ታግሰን ለስኬት እንድንበቃ ታዘናል።
عن أبي هريرة. قال: قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: "لا يفرك مؤمن مؤمنة. إن كره منها خلقا رضي منها آخر" أو قال "غيره". [رواه مسلم: 1469].
ከአቡ ሁረይራ በተላለፈ ሀዲስ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፤ « አማኝ ወንድ አማኝ ሚስቱን አይጥላት፤ አንዱን ባህሪዋን ቢጠላባት ሌላኛውን ይወዳልና!» ሙስሊም ዘግበውታል
ይህንን ታላቅ የሆነ የህይወት ማዕከል በቀላሉ ማፍረስና መበተን ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ሁሉም የየራሱን መልካም አስተዋፅዖ ማድረግ ይገባዋል።
በተለይ ወደ ባለትዳሮቹ መቅረብ የሚችሉ ግለሰቦች ለነርሱ መራራቅና ለአንዳቸው ባንዳቸው ላይ ማመፅ ሰበብ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም በሁለቱ ግለሰቦች ዙርያ የሚገኙ ወዳጆች መልካምን በማሰብም ይሁን በሌላ አስተሳሰብ የወዳጆቻቸውን ትዳር ከሚያናጋ አካሄድ ሊርቁ ይገባል።
ይህ ሲባል ግን እሷ ወይም እሱ ሲበደል በዝምታ ይለፉት ማለትም አይደለም። ይልቁንም ባላቸው ቅርበትና ወዳጅነት ልክ ለማግባባት መጣር አለባቸው።
በባለ ትዳሮች መሃል በመግባት በተለይ ሴቷን የሚቀይሩ፣ ባሏን እንዳትታገስ፣ በእቅሙና በኑሮው ልክ ተቻችላ እንዳትኖር እያናናቁ ገፋገፋ የሚያደርጓት ይኖራሉ።
አንዳንዶችም፤ የራሳቸውን ህይወት የጀነት ኑሮ አስመስለው በእህቶቻቸው ላይ ለመኮፈስ ሲሉ ባላቸውን እና ኑሯቸውን በማሞገስ የሚወረውሯቸው ቃላት ብዙ የዋህ ሚስቶችን ለአመፅ ይገፋፋሉ።
በዚህም ሰበብ ቀላል የነበሩ አለመግባባቶችም ሆኑ ግጭቶች ወደ መካሰስ፣ ወደ መበዳደልና መለያየት ያመራሉ።
ስለሆነም አንዲትን ባለትዳር ሴት በባሏ ላይ እንድታምፅ ያደረጋት ማለትም ስነምግባሯ፣ ፀባይዋ እንዲበላሽ ሰበብ የሆነ ሰውን በተመለከተ ጠንካራ የሆኑ ማስጠንቀቂያዎች ተላልፈዋል።
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት:
”مَنْ خَبَّبَ زَوْجَةَ امْرِئٍ أَوْ مَمْلُوكَهُ فَلَيْسَ مِنَّا “
« ያንድን ሰው ሚስት ወይም አገልጋይ (ሰራተኛ) በሱ ላይ ያሳመፀ ከኛ አይደለም።» ብለዋል።
እንዲሁም፤
"ملعون من خبَّب امرأة على زوجها"
« አንዲትን ሴት በባሏ ላይ ብልሹ እንድትሆን ያደረገ እርጉም ነው!!» ብለዋል
ይህንን በተመለከተም ሸይኽ ሷሊህ ፈውዛን አልፈውዛን ሃፊዘሁላህ ሲያብራሩ :--
“ለመጥፎ ፀባይዋ ሰበብ የሆነ፣ ወደ ክፋት የጎተጎታት ፣ የሳሰባትና በባለቤቷ ላይ እንድታምፅ፣ ስርዓት እንድትጥስ ያደረጋት ሰው የመልካም ሙስሊሞች አባል እንዳልሆነና ኣልፎም ከአላህ ራህመት የራቀ ዕርጉም መሆኑን ያሳያል። ” ብለዋል።
በዚህ መሰረት በተለይ ባሁኑ ወቅት ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ሆኗል። የእያንዳንዱን ቤተሰብ የሚያንኳኳ ዜናም እየሆነ ነው።
ይህ ባህሪ በሚስት ጓደኞች፣ ቤተሰቦች፣ ወላጆች፣ እንዲሁም ጎረቤቶችና ሌሎችም ጣልቃ ገብ ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች የተፈተኑበት ሆኗል።
አዎን! አዛኝ መስለው ለምን እንዲህ አትይውም? ፣ ለምን ልክ አታገቢውም? ፣ ባሎች ሲከበሩ አይወድላቸውም..፣ የድሮ ዘመን ባሎች ባህሪ ነው!! ወዘተ... አይነት
የአመፅ ማነሳሻዎችን በመጠቀም ሚስቶችን በባሎቻቸው ላይ ሲያነሳሱ አላህን አይፈሩም።
ወንዱንም እንዲሁ!!
" አዛኝ ቅቤ አንጓች " እንዲሉ፤
ለትዳሮች መፈረካከስ ሰበብ እየሆኑ "ለሷ ብዬ ነው... ለሱ ብዬ ነው" የሚሉ ወገኖችም ሊመከሩና ይህንን የመሳሰሉ ሃዲሶችን ልብ ሊሉ ይገባቸዋል።
ሸይኽ ሷሊህ ፈውዛን አልፈውዛን አክለው ሲያስረዱ
“በተለይ የሚስት ወገኖች በባሏና በርሷ መካከል ቁርሾን ሊያስወግዱና እርቅ ሊፈጥሩ በዚህም ላይ ሊተጉ ግዴታ ይሆንባቸዋል ።
ዞሮ ዞሮ ይህ ጉዳይ ለራሳቸውም ለሚስቲቱም ጥቅም መሆኑን ሊያስተውሉ ይገባልና። ” ብለዋል።
" المنتقى من فتاوى الشيخ الفوزان "
( 3 / 248 ، 249 ) .
ከዚህ አይነቱ የአጥፊነት ጣልቃ ገብነት መጠንቀቅ አለብን።
አላህ በሰዎች ጉዳይ ገብተን ፊትና ከመፍጠርና ራሳችንንም ከማስረገም ይጠብቀን!!
________
📝 07 ጁማዱሳኒ 1436
27 March 2015