ፍችና ተያያዥ ነጥቦች
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
አብሮ መኖር ፈተና ለሆነባቸው ጥንዶች ፍች በራሱ ከትልልቅ የአላህ ፀጋዎች ውስጥ ነው። ኢስላም አንዳንድ እምነቶች ጋር እንደሚታመነው የፍችን በር ከርችሞ አይዘጋም። ከነ ጭራሹ ፍችን መከልከል ለማይስማሙ ባለ ትዳሮች ህይወትን መከራ የሚያደርግ ሲሆን ለብልግናም በር ከፋች ነው። እንዲህ አይነቱ ከባድ ህግ በሚያምኑበት ሰዎች ሳይቀር ተፈፃሚነቱ እጅጉን የመነመነ ነው።
ፍች ድጋፍ የሚኖረው ተጨባጭ ምክንያት ሲኖር ነው። ምክንያት አልባ ሲሆን ግን ትዳርን ያክል ትልቅ ተቋም ማራከስ፣ የትዳር አጋርን ቀልብ መስበር፣ የልጆችህን ህይወት ማመሰቃቀል ነው። ስለሆነም ጊዜ ተወስዶ በጥልቀት ያልታሰበበት፣ እንዲሁ በጊዜያዊ ቅራኔ ብቻ የሚፈፀም ፍች ብዙ ጣጣ ያስከትላል። እራስንም ፀፀት ላይ ይጥላል።
እንደሚታወቀው ኢስላም ለሁሉም ነገር ህግና ስርአት አለው። ስለሆነም ማንም እየተነሳ ሲደብረው እየፈታ ሲያሰኘው የሚመልስበት ገደብ አልባ አካሄድን ፈፅሞ አያስተናግድም። ገደቡ ይሄውና:–
(ٱلطَّلَـٰقُ مَرَّتَانِۖ فَإِمۡسَاكُۢ بِمَعۡرُوفٍ أَوۡ تَسۡرِیحُۢ بِإِحۡسَـٰنࣲَۗ)
"ፍች ሁለት ጊዜ ነው። (ከዚህ በኋላ ያለው) በመልካም መያዝ ወይም በበጎ አኳኋን ማሰናበት ነው፡፡" [አልበቀራህ: 229]
ስለዚህ ለሶስተኛ ጊዜ ሚስቱን የፈታ ሰው አለቀ መመለስ አይፈቅድለትም። መመለስ የሚችለው ለርሱ ለማመቻቸት ታስቦ ሳይሆን እውነተኛ በሆነ ጋብቻ ሌላ ሰው አግብቷት፣ ግንኙነት ተፈፅሞ ከተፈታች ብቻ ነው። እንዲህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገቡ ሰዎች በፍች ጉዳይ ላይ በጥልቀት ሊያስቡበትና ጠንቃቃ ሊሆኑ ይገባል።
ሱና፞ውን የጠበቀ የፍች አፈፃፀም ስርአት
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
አንድ የፍች ሂደት ሱና፞ውን የጠበቀ ነው የሚባለው:–
* በሚፈፀምበት ጊዜ የወር አበባ ላይ ካልሆነች፣
* ግንኙነት ያልተፈፀመበት የጡህር ጊዜ ላይ ከሆነ እና
* አንድ ፍች ብቻ ከሆነ ነው።
– የወር አበባ ላይ እያለች መፍታት በቁርኣንም፣ በሐዲሥም፣ በኢጅማዕም ሐራም ነው።
– ከወር አበባ ጠርታ ነገር ግን ግንኙነት ተፈፅሞ ከሆነም እንዲሁ በዚያ የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍች መፈፀም አይቻልም።
ሱና፞ውን ሳይጠብቅ ማለትም የወር አበባ ላይ እያለች ወይም ግንኙነት በተፈፀመበት ጡህር ላይ እያለች ቢፈታ ወንጀለኛ ይሆናል። ፍቺው ግን ተፈፃሚ ነው።
በአንድ ጊዜ የተፈፀመ ሶስት ፍች
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
* በአንድ ጊዜ ሶስት ፍች መፈፀም ቢድዐ ነው። ሐራም ነው።
* በዚህ መልኩ ከተፈፀመ ግን እንደ ሶስት ሳይሆን እንደ አንድ ፍች ይቆጠራል። ለዚህም ሶሒሕ ሙስሊም ውስጥ ከኢብኑ ዐባስ የተዘገበ ግልፅ የሆነ ማስረጃ አለ።
የንዴት ፍች
~~~~~~~~~~
ንዴት ሶስት አይነት ነው ይላሉ ኢብኑል ቀዪ፞ም ረሒመሁላ፞ህ።
① ሰውየው የሚለውን እስከማያውቅ፣ እስከማይለይ የሚያደርሰው ከባድ ንዴት። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ያወጣው የፍች ቃል ከፍች አይቆጠርም።
② ንዴቱ ነገሮችን ከማስተዋል፣ ከማገናዘብ የማይዘጋው ከሆነ ፍቺው ተፈፃሚ ነው።
③ ንዴቱ ማስተዋሉን እስከሚነጥቀው አልደረሰም። ነገር ግን እሳቤውን (ኒያ፞ውን) እንዳያጤን በሚያደርገው መጠን ላይ ከፍ ብሏል። ንዴቱ ሲያገልለት በውሳኔው የሚፀፀትበት መጠን ማለት ነው። በዚህኛው አይነት ላይ እያለ የፍች ቃል ያወጣ ሰው "ፍቺው በተጨባጭ ተከስቷል ማለት አይቻልም" ያሉ ብዙ ዑለማዎች ናቸው።
* ለቀልድ ብሎ ግልፅ በሆነ መልኩ ፍችን የተናገረ ሰው ፍቺው ይታሰባል። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም "ሶስት ነገሮች ምራቸው ምር፣ ቀልዳቸውም ምር ነው። ኒካሕ፣ ፍች እና መመለስ ናቸው" ብለዋል። [አልኢርዋእ: 6/228] ይሄ የአብዛኛው ዑለማእ አቋም ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ኢጅማዕ ጠቅሰዋል። ስለዚህ በማይቀለድበት እንዳትቀልድ።
* በስህተት የፍች ቃል ያመለጠው ሰው ቃሉ ከፍች አይቆጠርም። ያለ አግባብ በፍች ላይ የተገደደ ሰውም እንዲሁ ፍቺው ታሳቢ አይሆንም። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል:–
(إنَّ اللهَ وَضَع عن أمَّتي الخَطَأَ، والنِّسيانَ، وما استُكرِهوا عليه)
"አላህ ከህዝቦቼ ላይ ስህተትን፣ መርሳትን እና የተገደዱበትን ነገር አንስቶላቸዋል።"
* ያበደና የሰከረ ሰው ፍቺው እንደ ፍች አይታሰብም።
* ማሳሰቢያ: – ብዙ ሰዎች ነፍሰ ጡር የሆነችን ሴት መፍታት እንደማይቻል ያምናሉ። ሌላ ተጨባጭ ምክንያት ካልኖረ በስተቀር ነፍሰ ጡር መሆን ፍቺን ከመፈፀም አያግድም።
ፍችና ጥርጣሬ
~~~~~~~~~
* ትዳር በጥርጣሬ አይፈርስም። አንድ ሰው መፍታት አለመፍታቱን ከተጠራጠረ ድርጊቱን እንደ ፍች ሊያስበው አይገባም። ለዚህም ኢጅማዕ የጠቀሱ ዓሊሞች አሉ።
* "ይሄ ከሆነ ፈትቻለሁ" አይነት በቅድመ ሁኔታ (ሸርጥ) የተንጠለጠለ ፍች ላይ የሸርጡ መሟላት አለመሟላት ላይ ከተጠራጠረ ፍቺውን ሊያስበው አይገባም። ምክንያቱም በየቂን የፀናው ኒካሕ በጥርጣሬ አይፈርስምና።
* በፍቺው ቁጥር ላይ (ለምሳሌ 2ኛ ነው ወይስ 3ኛ ብሎ) የተጠራጠረ ዝቅ ያለውን (የቂኑን) መውሰድ የብዙሃን ዑለማእ አቋም ነው።
በሸርጥ ላይ የተንጠለጠለ ፍች
~~~~~~~~~~~
"እንዲህ ካደረግሽ ፍች ነሽ" እና መሰል የሆነ ሸርጥ ላይ የተንጠለጠለ ፍችን በተመለከተ:–
* አላማው ሸርጡ ከተፈፀመ በተጨባጭ ሊፈታ ከሆነ በሸርጡ መፈፀም ፍቺው ተፈፃሚ ይሆናል። ኒካሑ ይወድቃል።
* አላማው የሆነ ጉዳይ እንዲፈፀም ወይም እንዳይፈፀም በፅኑ ለማሳሰብ እንጂ ፍችን አስቦበት ካልሆነ ያ ነገር ቢከሰትም ኒካሑ አይፈርስም። ባይሆን የመሀላ ማካካሻ ግዴታ አለበት። ባጭሩ የፍቺውን ተፈፃሚ መሆን አለመሆን የሰውየው እሳቤ (ኒያ፞) ይወስነዋል።
ዒዳ
~~~
* ዒዳ ማለት አንዲት የተፈታች ወይም ባሏ የሞተባት ሴት ሌላ ሰው ማግባት የምትከለከልበት የጊዜ ገደብ ሲሆን በቁርኣንም፣ በሐዲሥም፣ በኢጅማዕም የፀና ሐቅ ነው።
* የወር አበባ የምታይ ሴት የዒዳዋ ዘመን ሶስት የወር አበባ ጊዜ ነው። ከነጭራሹ ግንኙነት ያልተፈፀመበት ኒካሕ ከሆነ ግን ዒዳ መቁጠር አይጠበቅባትም። መመለስም ከፈለገ ሙሉ ለሙሉ አዲስ ኒካሕ ነው የሚጠበቅበት።
* ነፍሰ ጡር ሴት ዒዳዋ የሚጠናቀቀው ስትወልድ እንደሆነ ቁርኣን ውስጥ ሰፍሯል። [አጦ፞ላቅ: 4]
ቢያስወርዳትስ? ያስወረዳት ፅንሱ 4 ወር ከሞላው በኋላ ከሆነ ዒዳው በዚያው ይጠናቀቃል። ያስወረዳት ፅንሱ ቅርፅ ማውጣት ከጀመረበት ጊዜ በኋላ ከሆነም ዒዳው በዚያው ያልቃል።
* ባሏ የሞተባት ሴት ዒዳዋ 4 ወር ከ10 ቀን ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:–
(وَٱلَّذِینَ یُتَوَفَّوۡنَ مِنكُمۡ وَیَذَرُونَ أَزۡوَ ٰجࣰا یَتَرَبَّصۡنَ بِأَنفُسِهِنَّ أَرۡبَعَةَ أَشۡهُرࣲ وَعَشۡرࣰاۖ )
[سورة البقرة 234]
"እነዚያም ከናንተ ውስጥ የሚሞቱና ሚስቶችን የሚተዉ (ሚስቶቻቸው) በነፍሶቻቸው አራት ወሮች ከዐስር (ቀናት ከጋብቻ) ይታገሱ፡፡ [አልበቀራህ: 234]
* ሚስቱን ለአንዴ ወይም ለሁለተኛ ጊዜ ፈቶ ዒዳ እየቆጠረች ባለችበት ሁኔታ እሱ ቢሞት ዒዳዋን ከሞተበት ጊዜ ጀምራ እንደገና ትቆጥራለች። ንብረት ካለውም ትወርሳለች።
* ፍቺው መመለስ የማይቻልበት የመጨረሻ ፍች ከሆነ ዒዳዋን ሳታጠናቅቅ ቢሞትም የጀመረችውን ብቻ ነው መጨረስ የሚጠበቅባት።
* በአንድ ወይም በሁለተኛ ፍች የተነሳ ዒዳ የምትቆጥር ሴት ዒዳዋ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከቤቷ መውጣት የለባትም። ግልፅ ብልግና ካልታየ በስተቀር ከቤት ማስወጣትም አይፈቀድም። [አጦ፞ላቅ: 1]
* በዚህ ሁኔታ ላይ መመለስ የሚቻልበት ፍች ላይ ያለች ሴት ለባሏ ፊቷን መግለጥ፣ መዋዋብ፣ ከሱ ጋር ማውራት፣ ተገልሎ መቀመጥ ትችላለች። ግንኙነት የሚፈፀመው ግን ከመለሰ በኋላ ወይም በመመለስ ኒያ ሲሆን ነው።
* በአንድ ወይም በሁለተኛ ፍች የተነሳ ዒዳ የምትቆጥር ሴት ዒዳዋ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከልብስም ከጉርስም ለሚስቱ እንደሚያደርገው ሊያሟላ ይገባዋል። ዒዳዋ እስካልተጠናቀቀ ድረስ በቀላሉ መመለስ ይችላል። ዒዳዋ ከተጠናቀቀ በኋላ መመለስ ቢፈልግ ግን አዲስ ኒካሕ ነው መስፈርቱን አሟልቶ የሚያስረው።
* ለሶስተኛ ጊዜ ከፈታ ግን ከዚህ በኋላ መመለስ የሚችለው በትክክለኛ ኒካሕ ሌላ ሰው አግብታ ከተፈታች ብቻ ነው። ለቀድሞ ባሏ ሐላል ለማድረግ ታስቦ የሚፈፀም ጊዜያዊ ጋብቻ እጅጉን የተወገዘ ነው።
አዋቂው አላ፞ህ ነው።
ማሳሰቢያ:– እርምት ያለው ሰው ቢያደርሰኝ ደስ ይለኛል።
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 18/2012)
0 Comments