መውሊድን ማን ጀመረው?
(በመረጃ ለሚያምኑ ብቻ?)
~~~~~~~~~~~~~~~~~
መውሊድን የጀመሩት ከ 357 ሂ. በኋላ የነገሱት እራሳቸውን “የነብዩ ﷺ ልጅ የፋጢማ ዘር ነን” እያሉ የሚሞግቱት ሺዐዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
1. ጀማሉዲን ኢብኑል መእሙን (587 ሂ.)፡-
በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመውሊድ በዓልን የሚመለከት መረጃ ሰፍሮ የሚገኘው በኢብኑል መእሙን ስራ ውስጥ ነበር፡፡ የኢብኑል መእሙን አባት የፋጢያ ንጉስ ከፍተኛ ባለሟል ነበር፡፡ በርግጥ በአሁኑ ሰዓት የኢብኑል መእሙን ስራ ከነጭራሹ አይገኝም፡፡ ይሁን እንጂ በመካከለኛው ዘመን የታሪክ ፀሀፊዎች ብዙ ክፍሎቹ እየተጣቀሱ ተላልፈዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚው ተጠቃሽ ደግሞ ግብፃዊው የታሪክ ፀሐፊ መቅሪዚ (845 ሂ.) ነው፡፡ መቅሪዚ ይህን ሰውየ በማጣቀስ በ 517 ሂ. የተከናወነውን የመውሊድ አፈፃፀም በሰፊው አትቷል፡፡ [አልኺጦጥ፡ 2/332] በዚያን ዘመን የሚከበሩ ሌሎች በዓላት እንደነበሩ እንዲህ ሲል ይገልፃል፡-
“የ‘ፋጢሚያ’ ኸሊፋዎች በዓላትና ለተገዢዎቻቸው ነገሮችን ሰፋ የሚያደርጉባቸው እንዲሁም ችሮታ የሚበዙባቸው ዓውደ-አመታት” ካለ በኋላ እንዲህ ይላል፡- “ለፋጢሚያ ኸሊፋዎች በአመቱ ውስጥ በዓላትና ዓውደ- አመታት አሏቸው፡፡ እነሱም … የዓሹራእ ቀን፣ የነብዩ ﷺ ልደት ቀን፣ የዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ ልደት ቀን፣ የሐሰን የልደት ቀንና የሑሰይን የልደት ቀን (ሰላም በነሱ ላይ ይሁን)፣ የፋጢመቱ ዘህራእ ዐለይሃ ሰ፞ላም ልደት ቀን፣ ስልጣን ላይ ያለው ገዢ የልደት ቀን፣ … የገዲር ዒድ (የሺዐዎች ነው)” እያለ ይዘረዝራል፡፡ ከውስጣቸው የፋርስ፣ የሺዐ እና ከክርስትና ደግሞ እንደ ገና፞ እና ሁዳዴ ያሉ የተካተቱበት ሲሆን ባጠቃላይ 28 በዓላት ናቸው በመቅሪዚ የተዘረዘሩት፡፡ [አልኺጦጥ፡ 1/436]
መውሊድ ከምን አይነት በዓላት ጋር እንደተጀመረ ተመልከቱ፡፡ በሌላ ኪታቡም ላይ “በረቢዐል አወል ላይ (የ‘ፋጢሚዮቹ’ ንጉስ) ሌሊት ላይ በጎዳናዎችና መንገዶች ላይ ጧፎች እንዲበሩ ያስገድድ ነበር” ይላል፡፡ [ኢቲ፞ዓዙል ሑነፋእ፡ 2/48] በተጨማሪም “ረቢዑል አወል ላይ የነብዩን ﷺ ክቡር ልደት መፈፀም ብሄራዊ ባአል ሆኖ ቀጠለ” ይላል፡፡ [ኢቲ፞ዓዙል ሑነፋእ፡ 3/101]
2. ኢብኑ ጡወይር (617 ሂ.)፡-
ሌላኛው መውሊድን ከ“ፋጢሚዮች” ጋር በማያያዝ የጠቀሰው ጥንታዊ የታሪክ ፀሐፊ ኢብኑ ጡወይር ነው፡፡ ኢብኑ ጡወይር ለነዚህ የ“ፋጢሚያ” መንግስት ፀሐፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በሶላሑዲን አልአዩቢ ሲደመሰሱም በአይኑ ተመልክቷል፡፡ በዚህኛው ስርኣትም ውስጥ ዳግም አገልግሏል፡፡ በ "ፋጢሚያዎች" መንግስት ስለሚዘጋጀው መውሊድና ስለተትረፈረፈ ምግቡ “ኑዝሀቱል ሙቅለተይን ፊ አኽባሪ ደ፞ውለተይን” በተባለ ኪታቡ ላይ በዝርዝር አትቷል፡፡ “ማን ያውራ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” ይላል ያገራችን ሰው፡፡ እንዲህ አይነት የአይን ምስክር ባለበት እውነታውን መሸምጠጥ እራስን መሸወድ ነው፡፡ ለናሙና ያክል ንግግሩን ቀንጨብ ላድርግ፡-
ذكر جلوس الخليفة في الموالد الستة في تواريخ مختلفة، وما يطلق فيها، وهي مولد النبيّ صلّى الله عليه وسلّم، ومولد أمير المؤمنين عليّ بن أبي طالب، ومولد فاطمة عليها السلام، ومولد الحسن، ومولد الحسين عليهما السلام، ومولد الخليفة الحاضر…
“ኸሊፋው በተለያዩ ጊዜያት በስድስቱ መውሊዶች ላይ የሚያደርጋቸውን መሰየምና ምን ተብለው እንደሚታወቁ ማውሳት፡- እነሱም የነብዩ ﷺ መውሊድ፣ የአሚረል ሙእሚኒን ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ መውሊድ፣ የፋጢማ ዐለይሃስሰላም መውሊድ፣ የሐሰን መውሊድ፣ የሑሰይን ዐለይሂመስሰላም መውሊድ እና የዘመኑ ኸሊፋ መውሊድ ናቸው፡፡ …” [ኑዝሀቱል ሙቅለተይን፡ 217-219]
3. አልቀልቀሸንዲ (821 ሂ.)፡-
ስለ “ፋጢሚያ” መሪዎች ሸንጎ ሲያወራ “ሶስተኛው መሰባሰብ በረቢዐል አወል ወር 12 ላይ በነብዩ ﷺ መውሊድ ላይ የሚኖረው መቀመጥ ነው” ካለ በኋላ ዝርዝር አፈፃፀሙን ይተርካል፡፡ [ሱብሑል አዕሻ፡ 3/576]
4. አሱ፞ንዱቢ (1,097 ሂ.):-
“የተከበረውን ነብያዊ መውሊድ በመዘከር የማክበሩን ሀሳብ የፈጠሩት ፋጢሚዮች እንደሆኑ በርግጥም ያደረግኩት ምርምር፣ ፍተሻ፣ ጥናትና ክትትል አመላክቶኛል” ይላል፡፡ [ታሪኹል ኢሕቲፋል ቢልመውሊዲ አንነበዊ፡ 62]
5. ሙሐመድ ቡኽየት አልሙጢዒይ፣ የቀድሞው የግብፅ ሙፍቲ (1,354 ሂ.):-
“(እነዚህን መውሊዶች) ካይሮ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠሯቸው የ‘ፋጢሚያ’ ገዢዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያቸውም አልሙዒዝ ሊዲኒላህ ነው፡፡ ከመግሪበል ዐረቢ ተነስቶ በ ሸዋል 361 ሂ. ወደ ግብፅ አመራ፡፡ በረመዷን ካይሮ ገባ፡፡ የመውሊዶችን ሱና፞ የፈጠሩት እነሱ ናቸው፡፡ የነብዩ መውሊድ፣ የአሚረል ሙእሚኒን ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ መውሊድ፣ የክብርት ፋጢመቱ ዘ፞ህራእ መውሊድ፣ የሐሰን መውሊድ፣ የሑሰይን መውሊድ እና ስልጣን ላይ ያለው ኸሊፋ መውሊድ ናቸው፡፡ አልአፍዶል ኢብኑ አሚሪል ጁዩሽ እስከሚሰርዛቸው ድረስ እነዚህ መውሊዶች በተነደፈላቸው መስመር ቀጠሉ፡፡ … ከዚያም አልኣሚር ቢአሕካሚላህ የተጠቀሱትን መውሊዶች ሰዎች ሊረሷቸው ከተቃረቡ በኋላ ዳግም መለሳቸው፡፡ በኢርቢል ከተማ በተገለፀው መልኩ የተፈጠረው መውሊድ ከዚህ ዘመነ ኺላፋ ‘ካይሮ ላይ የ‘ፋጢሚያ’ ኸሊፋዎች ናቸው ቀድመው የጀመሩት’ ከሚለው ጋር አይጣረስም፡፡ ምክንያቱም የ‘ፋጢሚያ’ መንግስት ሰኞ ሙሐረም 10/567 ሂ. ላይ አልዓዲድ ቢላህ አቡ ሙሐመድ ዐብዱላህ ኢብኑል ሓፊዝ አልሙስተንሶር ሲሞት አክትሟልና፡፡ ከፋጢሚያዎች በፊት በኢስላማዊ መንግስት ውስጥ መውሊዶች አይታወቁም ነበር፡፡”
ሸይኹ የ “ፋጢሚያዎቹንም” የሙዞፈሩንም መውሊዶች በዝርዝር ካተቱ በኋላ እንዲህ ይላሉ፡- “ፋጢሚያዎችና ሙዞፈሩዲን የነብዩ መውሊድ ላይ ይሰሩት የነበረውን አንተ ካወቅክ ‘የተፈቀደ ነው’ ብሎ ለመወሰን የማይቻል እንደሆነ ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ትደርሳለህ፡፡” [አሕሰኑል ከላም፡ 44፣ 66]
6. ኡስታዝ ዐሊ ፊክሪ (1,372 ሂ.):–
“ለመጀመሪያ ጊዜ (መውሊዶችን) ካይሮ ላይ የጠነሰሷቸው የ‘ፋጢሚያ’ ገዢዎች ናቸው፣ በ4ኛው ክፍለ-ዘመን፡፡ ስድስት መውሊዶችን ነው የፈጠሩት፡፡ የነብዩ መውሊድ፣ የኢማም ዐሊይ መውሊድ፣ የክብርት ፋጢመቱ አዝዘህራህ መውሊድ፣ የሰይዳችን ሑሰይንና ሐሰን ረዲየላሁ ዐንሁም መውሊድ፡፡ አልአፍዶል ኢብኑ አሚሪል ጁዩሽ እነዚህን መውሊዶች ውድቅ አድርጓቸው ቆይተው ከዚያ በዓልሓኪም ቢአምሪላህ ጊዜ በ 524 ሂ. ዳግም ተመለሱ፡፡” [አልሙሓዶራቱል ፊክሪያህ፡ 84]
ስለዚህ መውሊድ ቀድሞ በሺዐዎች እንደተጀመረ የማያወላዳ ማስረጃ እየቀረበ፤ ንጉስ አልሙዞፈር (630 ሂ.) ነው የጀመረው ማለት ማንም ቢያወራው ከመረጃ የተራቆተ ባዶ ወሬ ነው፡፡ ምክንያቱም እሱ ቀድሞ የተጀመረን ነገር ነውና ያስቀጠለው፡፡ ምክንያቱም እሱ “ፋጢሚያዎች” ከወደቁ በኋላ ነውና የተሾመው፡፡
“ፋጢሚዮች” ከኢስማዒሊያ ሺዐ ቅርንጫፎች ውስጥ መሆናቸው ላይ ውዝግብ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የነብዩ ﷺ ልጅ “የፋጢማ ዘር ነን” ማለታቸውን ብዙሃኑ የታሪክ ፀሐፊዎች አያምኑትም፡፡ ብቻ ጥቂትም ቢሆኑ “በጊዜው የነበሩ ተቀናቃኝ መንግስታት የነዙት ፕሮፓጋንዳ ነው” ያሉ ስላሉ ይህን ክፍል ትቼዋለሁ፡፡ “የነብዩ ﷺ ዘር መሆናቸው ምን ይፈይዳቸዋል?” እንዳንል፡፡ ተፅእኖው ቀላል ስላልሆነ ነው እነሱም በየጁሙዐው ኹጥባ ይህንን ያሳውጁ የነበሩት፡፡ ሌሎችም አጀንዳ አድርገው ያነሱት፡፡ ተፅእኖው ቀላል ስላልሆነ ነው ስድስት መውሊዶችን በሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ጀምረው በውስጣቸው ቅስቀሳ ሲያደርጉባቸው የነበረው፡፡ ዑለማዎች ስለነሱ ምን እንዳሉ ከማንሳቴ በፊት ሰዎቹ በኢስላምና በሙስሊም ዑለማዎች ላይ ያደርሱት የነበረውን ግፍ የሚያሳይ አንድ አሳዛኝ ታሪክ ላስፍር፡፡
የታሪኩ ባለቤት አቡ ተሚም አቡበክር አንናቡሉሲ ይባላሉ፡፡ ግብፃዊ ናቸው፡፡ ዒባዳ የሚያበዙ፣ ሷሊሕና ዛሂድ ሰው ነበሩ፡፡ ደፋር እውነትን ተናጋሪ፡፡ በነዚህ ራፊዷዎች ላይ የሰላ ትችት ይሰነዝሩ ነበር፡፡ የሆነ ጊዜ “አስር ቀስት ቢኖረኝ ኖሮ በአንዱ ሮማውያን ክርስቲያኖችን የምወጋበት ሲሆን በዘጠኙ ግን በኑ ዑበይድን (‘ፋጢሚዮችን’) ነበር የምወጋበት” ማለታቸው ተሰማ፡፡ “ፋጢሚዮች” ዑለማዎችን በሚያሳድዱበት ጊዜ ተይዘው ከመሪው አልሙዒዝ ፊት ቀረቡ፡፡ አልሙዒዝ መውሊድን የጀመረው ሰው እንደሆነ ብዙ ዓሊሞች ይጠቅሳሉ፡፡
አልሙዒዝ፡- “አስር ቀስት ያለው ሰው በአንዱ ሮማዎችን ይውጋበት፡፡ በዘጠኙ ደግሞ እኛን ይውጋበት እንዳልክ ደርሶኛል” አላቸው፡፡
አንናቡሉሲ፡- “እንዲህ አይደለም ያልኩት” አሉት፡፡
አልሙዒዝ፡- (ከአቋማቸው የተመለሱ መሰለው፡፡) “እና እንዴት ነበር ያልከው?” አላቸው፡፡
አንናቡሉሲ፡- “አስር ቀስት ያለው ሰው በዘጠኙ እናንተን መውጋት ያለበት ሲሆን በአስረኛውም እናንተኑ ይውጋበት ነው ያልኩት! ምክንያቱም እናንተ ሀይማኖትን ቀይራችኋል፤ ደጋጎችን ገድላችኋል፤ አምላካዊ ብርሃንን አጥፍታችኋል፤ የሌላችሁን (ነብያዊ ዘር) ሞግታችኋል” አሉት፡፡
ከዚህ በኋላ መሪው ለሁለት ቀን ከባድ ግርፋት እንዲገረፉ አደረገ፡፡ በሶስተኛው ቀን ህይወታቸው እያለ ቆዳቸው እንዲገፈፍ አንድ የሁዲ ታዞ ቀረበ፡፡ የሁዲው የታዘዘውን እየፈፀመ ነው፡፡ እሱ ይገፍፋል፤ እሳቸው በፅናት ቁርኣን ይቀራሉ፡፡ የሁዲው ሰብአዊነት ይዞት አዘነና ስቃያቸውን ሊያሳጥርላቸው ፈለገ፡፡ እንዲህም አለ፡ “ልቤ አዘነለት፡፡ እናም ደረቱ ጋር ስደርስ በቢላዋ ወጋሁትና ሞተ፡፡” ከዚያም ገለባ ከነሰነሱባቸው በኋላ ሰቀሏቸው፡፡ ኢንናሊላሂ ወኢንና ኢለይሂ ራጂዑን!! አልኢማም አድዳረቁጥኒ ረሒመሁላህ እኚህን ሰውየ እያወሱ ያለቅሱ ነበር፡፡ እንዲህም ይሉ ነበር፡- “እሱ ቆዳው እየተገፈፈ ሳለ ይህ በመፅሐፉ ውስጥ የተመዘገበ ነው የሚለውን ይቀሩ ነበር፡፡” ይሄ እንግዲህ እነዚህ “ፋጢሚዮች” በዑለማዎች ላይ ከፈፀሟቸው ግፎች ውስጥ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው፡፡ [አልቢዳያህ ወንኒሃያህ፡ 11/284] [ሲየሩ እዕላሚንኑበላእ፡ 16/148-150]
አሁን ደግሞ እነዚህን “ፋጢሚያዎች” አስመልክቶ ዑለማዎች ምን እንዳሉ በስሱ እንመልከት፡-
1. ኢብኑ ተይሚያ (728 ሂ)፡- “እነሱ (‘ፋጢሚያ’) እጅግ አመፀኛና እጅግ ከሃዲ ከሆኑ ሰዎች ውስጥ ናቸው፡፡ … የታወቀውና ምንም ጥርጥር የሌለበት ነገር ቢኖር ለነሱ በኢማን፣ በተቅዋና የፋጢማ ዘር ነን በሚሉት ሙግት የመሰከረላቸው በማያውቀው ነው የመሰከረው፡፡… የሙስሊሙ ህዝብ ምሁራንና መሪዎች ብዙሃኑ እነዚህ ሰዎች ክህደታቸውን ደብቀው ኢስላምን የሚያንፀባርቁ አፈንጋጭ መናፍቃን እንደሆኑ ነው የሚመሰክሩባቸው፡፡” [መጅሙዑል ፈታዋ፡ 35/127-128]
2. ኢማሙ አዝዘሀቢ (748 ሂ.)፡- “ኢስላምን ገልብጠው ራፊዷነትን ግልፅ አወጡ፡፡ የኢስማዒሊያ መዝሀባቸውን ስውር አደረጉ፡፡” [አስሲየር፡ 15/141]
3. ኢብኑ ከሢር (774 ሂ.)፡- “ ‘ፋጢሚዮች’ ከነገስታት ሁሉ ሀብታሞቹ፣ ጨካኞቹ፣ በዳዮቹ፣ ነጃሳዎቹና ቆሻሾቹ ነበሩ፡፡ በንግስናቸው ጊዜ ቢድዐዎችና መጥፎ ነገሮች ተንሰራፍተዋል፡፡ የጥፋት ሰዎች በዝተዋል፡፡ ከዑለማእና ዓቢዶች ደጋጎች ቀለዋል፡፡ በሻም ምድር ላይ ክርስትና፣ ዱሩዚያና ሐሺሺያ በዝቷል፣…” ተነካክቶ የተወሰደ፡፡ [አልቢዳያህ ወንኒሃያህ፡ 12/267]
4. ቃዲ ዒያድ፡- “የበኑ ዑበይድ ሁኔታ የአፈንጋጭና ኢ-አማንያን ሁኔታ እንደሆነ የቀይረዋን ዑለማዎች በአንድ ድምፅ ወስነዋል፡፡ ይህም ሸሪዐን የሚፃረር ነገር በማንፀባረቃቸው ነው፡፡ በኢጅማዕ አይወረሱም፡፡…” [ተርቲቡል መዳሪክ፡ 7/277]
ስለዚህ ማስተዋሉን ያልተነጠቀ፣ በራሱ ጭንቅላት የማሰብ ነፃነቱን ያልተገፈፈ ሰው መውሊድ በነዚህ የኢስላም ጠላቶች የተጠነሰሰ ቢድዐ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡
ከ “መውሊድ፣ ታሪክ፣ ግድፈት፣ እርምት” መፅሐፍ ተነካክቶ የተወሰደ ነው፡፡
0 Comments