ምስጢርን የሚመለከቱ ጥቂት ጥቆማዎች
የሙስሊሞችን ምስጢር ማባከን ብዙዎቻችን የተዘፈቅንበት አደጋ ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ
ይላሉ፡- “አንድ ሰው ወሬን እያወራ (ግራ ቀኝ) ከተዟዟረ አማና ነው ማለት ነው፡፡” [አልባኒ ሐሰን ብለውታል፡፡]
አማናን መብላት ደግሞ ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከሙናፊቅ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ሲታመን
መክዳት ነው፡፡ “አላህም አማናዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል” ይላል፡፡ [አንኒሳእ፡ 58]
እናቶቻችን ዓኢሻና ሐፍሷ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የነገሯቸውን ምስጢር በማውጣታቸው ምክንያት ሃያሉ ጌታ
እንደወቀሳቸው ይታወስ፡፡ [አትተሕሪም፡ 4]
ልብ በሉ! አላማዬ እራሴን ነፃ አድርጌ ሌሎችን መውቀስ
አይደለም፡፡ ይልቁንም ብዙዎቻችን እራሴም ጭምር ከተዘፈቅንበት አደገኛ ጥፋት ምላሳችንን እንድንሰበስብ ማስታወስ
ነው፡፡ ጉዳዩ እጅግ አስፈሪ ቢሆንም የሚተርፈው ግን ቀላል ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለው
ነበር፡- “ሙስሊም ለሙስሊም ወንድሙ ነው፡፡ አይበድለውም፡፡ አሳልፎም አይስጠውም፡፡ … የሙስሊምን ነውር የሸፈነ
አላህ በቂያማ ቀን ይሸፍነዋል፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] ሐሰኑል በስሪ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “የወንድምህን
ምስጢር ማባከንህን ከሸፍጠኝነት ነው፡፡” [አስሶምት ሊብኒ አቢ አድዱንያ፡ 214] አንተ የሰው ምስጢር የምትረጨው
ደካማ ሆይ! “ምስጢርን መርጨት ከትእግስት መቅለል፣ ከደረት ጥበት ነው፡፡ በዚህ የሚታወቁት ደካማ የሆኑ ወንዶች፣
ህፃናትና ሴቶች ናቸው” ይላሉ አርራጊቡል አስፈሃኒ ረሒመሁላህ፡፡ [አዝዘሪዐህ ኢላ መካሪሚ አሽሸሪዐህ፡ 213]
ምስጢርን የመደበቅ ፋይዳዎች
1. ምስጢርን መደበቅ የግርማ ሞገስ፣ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡
2. በጠላት ላይ ድልን ለመቀዳጀት ሁነኛ የሆነ ሰበብ ነው፡፡
3. የምቀኛንና የሴረኛን ተንኮል ለመከላከል ይጠቅማል፡፡
4. ወንድማማችነት እንዳይፈርስ ያግዛል፡፡
5. በትዳር አጋር መካከል መተማመን እንዲኖር ያደርጋል፡፡
6. በጥቅሉ ምስጢርን መጠበቅ ከስኬት መሰላሎች አንዱ መሰላል ነው፡፡
ለባለ ምስጢሩ፡-
- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “ጉዳያችሁን ለማሳካት ምስጢራችሁን በመደበቅ ታገዙ፡፡ እያንዳንዱ ባለ ፀጋ ምቀኛ አለው፡፡” [አስሶሒሐህ]
- “ምስጢርህ ምርኮኛህ ነው፡፡ ተናግረህ ካወጣሀው ምርኮኛው አንተ ትሆናለህ፡፡” ዐልይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ [አደቡ አድዱንያ ወድዲን ሊልማውሪዲ፡ 306]
- “ምስጢሩን የደበቀ ምርጫው በእጁ ነው፡፡ ምስጢሩን ያወጣ ግን ምርጫው በሱ ላይ ነው፡፡” ዑትባህ [አልኢሕያእ]
- “አትንገር ብየ ብነግረው አትንገር ብሎ ነገረው፡፡” ሃገርኛ ብሂል
- “ማንንም ምስጥሬን ከሰጠሁት በኋላ ስለረጨው አልወቀስኩም፡፡ እኔ ለመያዝ ከተጣበብኩ እንዴት እወቅሰዋለሁ?!” ዐምር ኢብኑል ዓስ ረዲየላሁ ዐንሁ [ሶሒሑል አደቢል ሙፍረድ፤ 685]
- “አብዛሀኛዎቹ ሰዎች ምስጢራቸውን መቆጣጠር አይችሉም፡፡ ግልፅ ሲወጣ ጊዜ ግን የነገሩትን ይወቅሳሉ፡፡ አቤት
ሲደንቅ! እንዴት እራሳቸው መቆጣጠር አቅቷቸው ሌሎችን ይወቅሳሉ?!” ኢብኑል ጀውዚ [ሶይዱል ኻጢር፡ 273]
ከዚያ እንቁ ዘመን አንድ ድንቅ ምሳሌ!
ሣቢት ረሒመሁላህ ሶሐባው አነስ ኢብኑ ማሊክን ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ይላሉ፡-
“ከልጆች ጋር እየተጫወትኩ ሳለሁ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እኔ ዘንድ መጡ፡፡ ከዚያም በኛ ላይ
ሰላምታን አቀረቡ፡፡ ከዚያም እኔን ለሆነ ጉዳይ ላኩኝ;፡፡ በዚህም ምክንያት እናቴ ዘንድ ሳልመለስ ዘገየሁኝ፡፡
ስመጣ ጊዜ ‘ምን አገኘህ?’ አለቺኝ እናቴ፡፡ ‘የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለጉዳይ ልከውኝ ነው’
አልኳት፡፡ ‘ምን ነበር ጉዳያቸው?’ ስትለኝ ‘ምስጢር ነው’ አልኳት፡፡ ‘የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ
ወሰለም ምስጢር ለማንም እንዳትናገር’ አለቺኝ፡፡ ወላሂ ለማንም የምናገር ብሆን ኖሮ ላንተም እነግርህ ነበር
ሣቢት፡፡” [ሙስሊም፡ 2482]
ሰዎች ነንና የሆነ ብሶታችንን የሚጋራን፣ ጭንቃችንን የሚካፈለን፣ አቅጣጫ የሚጠቁመን ምስጢረኛ መፈለጋችን አይቀሬ ነው፡፡ ታማኝ ምስጢረኛ ምን አይነት ሰው ነው?
1. አስተዋይ ህሊና ያለው
2. ከማራገብ የሚገታው ዲን ወይም ተቅዋ ያለው
3. ምክር ለጋሽ፣ መፍተሄ አመላካች የሆነ፡፡ ካልሆነማ ምን ሊሰራልህ ትነግረዋለህ?
4. አለኝታነቱን፣ ርህራሄውን የሚለግስ የሆነ
5. በባህሪው ምስጢር ጠባቂና ቁጥብ የሆነ፡፡ ካልሆናማ በወንፊት ውሃ የምትቀዳው ቂል አንተ ነህ፡፡
ተጠንቀቅ!
- ምስጢር የምትዘራን አታግባ/ የሚዘራን አታግቢ
- የምስጢርህ ሳጥን በበዛ ቁጥር ምስጢርህ የመባከኑ እድል በዚያው ልክ ይበዛል፡፡
- ምስጢርን ከመደበቅ ይልቅ ከእሳት ወላፈን መታገስ ይቀላል፡፡
- ምስጢሩን የሚጠብቅ ወይ ያለመውን ያገኛል ወይ ደግሞ ክብሩን ይጠብቃል፡፡
- ልብህ ለምስጢርህ በቂና ሰፊ ቦታ ነው፡፡
የሰው ምስጢር ለመስማት አታኮብኩብ!!
በአንድ ወቅት ኢብኑ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ ከአንድ ሰው ጋር እየተንሾካሾኩ ሳሉ አንድ ሰው በመካከላቸው ገባ፡፡
ኢብኑ ዑመር ደረቱን መቱትና የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሁለት ሰዎች ሲንሾካሾኩ በፈቃዳቸው እንጂ
ሶስተኛ ሰው በመካከላቸው አይግባ ብለዋል” አሉ፡፡ [ጊዛኡል አልባብ]
ግን ለምን ሰዎች ምስጢር ያወጣሉ?!
1. አጉል መኮፈስ፣ ጉራ፣ ጀብዱ ስለሚፈልጉ
2. ሰው በባህሪው የተከለከለውን ነገር የመፈፀም ጉጉት ስላለው
3. የመበቀል፣ ስም የማጥፋት እኩይ አላማ
4. በሆነ መልኩ ከሚረጨው ምስጢር ተጠቃሚ ለመሆን ማለም ሲኖ ር ነው::
ምስጢር የመጠበቅ ችግር ላለብን
ወንድሜ ወይ! እህቴ ሆይ!
1. እያንዳንዷን እንቅስቃሴያችንን አላህ እየተከታተለን እንደሆነ እናስብ፡፡ መላእክት ስራዎቻችንን ሁሉ እየመዘገቡ እንደሆነ ዘወትር እናስታውስ፡፡
2. ለሁሉም ሙስሊም መልካም እንመኝ፡፡ ከምቀኝነት ክፉ ቫይረስ እንራቅ፡፡
3. በምናወጣው ምስጢር ምክንያት ሰዎች ቢጣሉ፣ ትዳር ቢፈርስ፣ መልካም ግንኙነት ቢሻክር በሚደርሰው ሁሉ ተጠያቂ እንደምንሆን እናስብ፡፡
4. ከዚያም ባለፈ ምስጢር በማውጣትህ ስምህ ይጎድፋል፡፡ ወንፊት፣ ቱልቱላ፣ ምቀኛ፣ የሚሉ ቅፅሎች ቢወጡልህ ምን ታተርፋለህ?! በሂደቱም ለቁም-ነገር የማትበጅ ክብረ-ቢስና ቀላል ትሆናለህ፡፡
እኔንም እናንተንም አላህ ከክፋት ይጠብቀን፡፡ የአላህ ሶላትና ሰላም በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ ይሁን፡፡
ከተለያዩ ምንጮች ተሰብስቦ የተከተበ ነው፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ግንቦት 8/2008)