Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አንተን የሚመለከት አሳሳቢ ጉዳይ፤ እወቅበት‬ ግጥም


አንተን የሚመለከት አሳሳቢ ጉዳይ፤
በቸልተኝነትም ይሁን በደለኝነት አንዳንድ ወንዶች በቀድሞ ሚስቶች ወይም እጮኛዎች ላይ በሚከፍቱት የማጥላላት ዘመች የብዙ እህቶች ስም ጠልሽቶ ልባቸው በሀዘን ተሰብሮ ይኖራሉ። ወንድሜ ሆይ!!
ዙልምና በደል በአኼራ ጨለማን ያወርሳልና አሁኑኑ
መካሪ ግጥም በእህት ኪያ ኡሙ ሙዓዉያ
ደካማ ሴት ሆኜ ያውም የዚህ ዘመን
ነውሬ የበዛ የተሞላሁ እንከን
እንዳይታይብኝ ሸሽጌ ያኖርኩት
ሰው እንዳያገኘው ሽፍንፍን ያረግሁት
በልቤ ሙዳይ ዉስጥ አለ ብዙ ነገር
ፍጡር የማያውቀው ከፈጣሪ በቀር
ታዲያ መተንፈሱ ባማረኝ ግዜና
ከሴት ወንድ ይሻላል ሲሉ ሰማሁና
ከወንድም የወንድ ወንድ ከጎኔ አግኝቼ
ለውጪው ሽፋኑ አትኩሮት ሰጥቼ
"ጥሩ ያላህ ባሪያ" ነው ብዬ ገምቼ
የቅርቤ ሰው ሆኖ የዘውትር መካሪ
በርቺ በሸሪዓው ሱናም ላይ ጠንክሪ
እያለ ጧት ማታ ቢመክረኝ አመንኩት
የእህትነቴን አመኔታ ቸርኩት
አማክረው ጀመር ስለ ሁሉም ጉዳይ
አንስቼም ሰጠሁት የሚስጥሬን ሙዳይ
ደግሜ ደግሜ እያልኩት "አደራ"
ነገሬን ሊደብቅ ለሰው ላያወራ
አለኝ "ኧረ ኡኽቲ አትጠራጠሪ"
ሰው ይሰማል ብለሽ በፍፁም አትፍሪ
የሱና ወንድምሽ እመኚኝ አብሽሪ
እኔማ አመንኩህ
መቼ ጠረጠርኩህ
ውስጤን አሳየሁህ
ጥሩ ወንድሜ ነህ አላህ ይጠብቅህ
እያልኩ መረቅሁህ
ከዚያም
በጥቂት ቆይታ ባጭር ቀናት እድሜ
ትንሽ ተቀያይመን እኔና ወንድሜ
ጥፋቱ ከሱ ነው ወይስ ከኔ ነበር?
ብቻ ተኳረፍን በማይረባ ነገር
ሗላ ያቺን ሙዳይ አደራ ያልኩትን
የሆዴን የልቤን የሸሸግሁበትን
እሜዳ አውጥቶ አረገው ብትንትን
ለብዙ ዘመናት የያዝኩት ሚስጥሬ
ከየሰው ጓዳ ገብቷል አሉኝ ዛሬ
ህም
የሱና ወንድምሽ ~ ነኝ አትፍሪ ብሎ
የተቀበለኝን በአላህ ስም ምሎ
ቁርዓንም ኪታብም የሚያውቅ ይሄ ሰው
በጣም ባጭር ግዜ ቃሉን ያፈረሰው
ስሜን በየቦታው በክፉ ሚያነሳው
ሚስጠሬን በመንገድ የሚነሰንሰው
ለአንድ አላህ እንጂ ለማነው ምከሰው?
ካፍ ከወጣ አፋፍ እንዳለው ተረቱ
በማን እፈርዳለሁ የኔው ነው ጥፋቱ።
ካወቀ ቡሃላ ታሪኬን በሙሉ
ዛሬ ግን ዞረና የምላሱ ምርኮ አድርጎኛል አሉ።
ይገርምሃል
ደካማዋ ነፍሴ ብዙ መከረችኝ
"ድንቄም መነሀጅ እቴ" በይ ተይዉ አለችኝ
"ያፈር የሱና ሰው፣ ምናል ቢቀሩብሽ?" ብላ ገሰፀችኝ።
ምነው ኧረ ምነው!
ሱናን መያዜኮ ለራሴ ብዬ ነው
በአንድ ተራ ሰው ዛሬ ተናድጄ
እኮ በምን ሂሳብ ልውጣ ከመንሐጄ?
ነፍሴም አትሞኚ በቃ ይሄን ያህል
እሱ እራሱን እንጂ ማንንም አይወክል።
እና ወንድሜ ሆይ
እኔስ ተፀፅቼ ብዙ አንብቻለሁ
ይበለኝ ግድ የለም የጄን አግኝቻለሁ
ያለፈው አለፈ እኔም ልማርበት
የማንቂያ ደወል ነው የምባንንበት
ይልቅ ስለ ነገው በደምብ አስብበት
ለብዙ ሺ ዘምን የምንቆምበት
ፀሀይ ወደ አናት የምትቀርብበት
ምላስ ተለጉሞ የተቀረው አካል የሚናገርበት
ያ ጉደኛ መዝገብ የሚገለጥበት
የተረሳ ሁሉ የሚታወስበት
ፍትሃዊው ጌታችን በባሮቹ መሀል
ፍርድ የሚሰጥበት
አዎ ለዚያች ቀንህ አንተው እወቅበት!!!
ኪያ ኡሙ ሙዓዉያ