Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መሪየም ቢንት ኢምራንን ታውቃያትለሽን?

መሪየም ቢንት ኢምራንን ታውቃያትለሽን?
---------//--------

ውዲቷ እህቴ!
ስለ መርየም ቁርዓን ምን እንደሚል አንብበሽዋል?
ጌታችን በተከበረ ቃሉ ምን ያህል የተከበረችና ንፁህ ሴት እንደነበረች ሲያሞግሳት እንደነበር አላነበብሽምን?

ምን ነካሽ እህቴ?
አንቺ እኮ አንድ ነሽ! ልትሆኚውም የምትችይው ለአንድ ሰው ነው። ለምን አደባባይ ፎቶ ለጠፍሽ? ለምንስ በካፊርም በሙስሊምም ወንዶች ሆድ ቁርጠት የሚያስነሱ ቃላት ትሸመገያለሽ?

ቆንጆ ነሽ! ጌታሽ የሰው ልጅ ባማረ መልኩ ፈጥረነዋል ብሎሻል! ታዲያ ያማረሽ መሆንሽ ከጌታሽ የመጣልሽን ቃል ስለምን ጀርባ ሰጠሽው?! ከአላህ ፍቃድ ውጭ ተሰብስቦ ሊጎዳሽም ሊጠቅምሽ የማይችል ፍጡር ቃል በለጠብሽን?

እህቴ ሆይ! ስትጎጂ ማየት አልሻም! እኔ ካንቺ በልጬ አይደለም ይህን የምነግርሽ ግና አድምጪኝ... አዎን! "በስጋ ከተዛመደ ይልቅ በእምነት የተዛመደ ይበልጣልና" አድምጪኝ!

ወደ እሳት ስትጎተቺ በፍፁም ማየት አልፈልግም! አንቺ የአንድ ሆነሽ ሳለ አደባባይ ላይ ፎቶሽ ለጥፈሽ ስንቱን ወንድ ፈተንሽ? አስበሺው ታውቃለሽ? ስንቱን ወንጀል ሸምተሽ ፌስ ቡክሽን እንደምትዘጊ አስተውሰሽዋልን?
በአንቺ ፎቶ የመጣ በኮሜንት ሲያበረታታሽ የነበረውም ሰው ወንጀል ሳይቀነስ ላንቺም እንደሚሆን ዘነጋሺው? ስንቱ መላኢካ እየረገመሽ ሊሆን እንደሚችል ታውቂዋለሽ?

ለምን ግን ማሰብ ተሳነን እህቴ? መግቢያዬ ላይ መርየምን ታውቃታለሽ ብዬ ለምን እንደጠየኩሽ ልገርሽ አድምጪኝ፤

መርየም ማለት በተቀደሰ በአላህ ቃል(ቁርዓን) ላይ ስሟ ለ24 ጊዜ የተጠቀሰች ምርጥ የአላህ ባለሟል ነበረች! እርሷ እንዳቺና እንደኔ ሴት ነች ነገር ግን ከጌታዋ ጋር ባላት ግንኙነት እጅጉን ትበልጠናለች! የቁርዓን ምዕራፍም በስምዋ የተሰየመላት ብቸኛ ሴት ነች። እሱም ምእራፍ (19) ሱረቱ መርየም የሚል ምእራፍ አላት። ይህም ምእራፍ ስለ ህወት ታሪክዋ የሚያወራ ሲሆን መርየም በቁርዓን ላይ በስማቸዉ ምእራፍ ከተሰየመላቸዉ ስምንት ሰዎች ዉስጥ አንዷ ነች መርየም በተለይ ከቁርዓን ላይ የተጠቀሰችው ከአስያ ጎን ለጎን ነዉ። ቁርዓን (66:11) ማንበበብ ትችያለሽ! እራሷን ከፈተና ጠብቃ በጨዋነት እንደኖረች ቁርአን መስክሮላታል።

መርየም በእስልምና በጣም ግዴታ የሆነ ህግን ነበር ያከበረችው! እኔና አንቺስ? በሚዲያ ፊትና እንሁን እህቴ? በጭራሽ ይህ መሆን የለበትም።

ስለ መርየም አልጨረስኩም! በቁርዓን ምዕራፍ ዘወትር የተወራላት በአምልኮ ስፈራዎች ዉስጥ በቁርዓን ላይ እንደተጠቀሰው ኢሳ (ዐለይሂ ሰላም) በአለማቱ ጌታ አላህ ፍላጎት በተአምር ከአባት ውጭ ወይንም ያለምን ግንኙነት ነበር በአላህ ተዓምር የተወለደው። መርየም አላህ በምድር ላይ አልቆ የመረጣት ሴት ስትሆን ከአራት ምርጥ ሴቶች ውስጥ አንድዋ ነች።

የተመረጠች መሆኗን ለማረጋገጥ ከፈለግሽ ቁርዓን (3:42) ላይ ገልፀሽ አንብቢ። እዚህ ልፅፍልሽ አልሻም ለምን ብትይኝ የጌታሽ ቃል ቁርዓን ገልፀሽ እንድታነቢ ስለፈለኩ! አራት ለሙስሊም ሴቶች አርአያ ለአማኞች ምሳሌ የሆኑ ሴቶች አሉን፤ እነማን እንደሆኑ ታውቂያለሽን?
እወቂያቸው፤ መርየም ቢንት ኢምራን፣ አስያ ቢንት መህዙም፣ ኽዲጃ ቢንትኹወይሊድ፣ ፋጢማ ቢንት ሙሃመድ(ﷺ)!

ለአላህ ትእዛዛት በሰጡት ክብርና በጨዋነታቸው አላህ መርጧቸዋል። በታሪክ የሚዘከር የክብር ሰሌዳ ላይ ሰፍረዋል። እኔና አንቺስ እህቴ ምንድነው አላማና እቅዳችን?
በምን ይሆን መልካም ታሪክ ተክለን ማለፍ የምንፈልገው?? ሚዲያ ላይ ፎቶ በመለጠፍና የወንዶችን የፊትና ቃላት በመቁጠር?

እንዴትስ አስቻለሽ እህቴ... ሁሉም የኔ እያለ በለጠፍሽው ፎቶ የሚያደንቅሽና ማሻ አላህ እያለ የሚያሞግስሽን ብሎም መፈተኑን ገልፆ የፃፈውን ሁሉ ማየት...
ኧረ አዑዙቢላህ!

እህቴ ለማን ተውበሽ መቅረብ እንዳለብሽ አታውቂምን? አንቺ አንድ ነሽ ልትሆኚም የምትችይው ለአንድ ወንድ ነው።
ከባልሽ እና ከዘመድ አዝማድሽ ውጪ እያቆለማመጠና ለእርሱ ሳትሆኚ የእኔ እያለ የሚጠራሽ ባዕድ ወንድ ያውም በሚዲያ እውነት የሱ ነሽን? አምረሽ ተውበሽ መቀረብ ያለብሽ ለባልሽ እንጂ ለሚዲያ አይደለም! አስተውዪ እራስሽን አትጠብቂ ንፁህ ውብ አትሁኙ እያልኩሽ አይደለም።

እንደውም ነብዩ (ﷺ) ለንፅህና ትኩረት በመስጠት እንዲህ ብለዋል፦ "ንፅህና የእምነት ግማሽ ነው።" (ሙስሊም ዘግበውታል)

ከዛም ከዚህ መጥቶ ያሻውን ይፅፋል ፊቱና ሆዱን አታውቂ ቀይ ይሁን ቢጫ፤ እርሱ ግን እየመራሽ ነው ወደ እሳት መቀጣጫ!

እህቴ ሆይ! ከዚህ ማቅ እናምልጥ እደግምልሻለሁ እኔ ከአንቺ ተሽዬ አይደለም። ግና ለመሻሻል ተፍ ተፍ የምል ሴት ነኝ! ለእኔና ለአንቺ ተምሳሌቶች አሉን እነርሱን ለመከት መሞከሩ የተሻለ ነው። እነርሱ ይበቁናል!

ጨቀጨኩሽ አውፉ በይኝ ቢጨንቀኝ ነው አትፍረጂቢኝ!

እህትሽ ኢልሀም የኢስላም ልጅ ኢሉ

© ተንቢሀት

Post a Comment

0 Comments