Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“አዋጅ! በሴቶች ላይ መልካምን ዋሉ አደራ!”


“አዋጅ! በሴቶች ላይ መልካምን ዋሉ አደራ!”
እርግጥ ነው ትዳር በራሱ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ትዳር ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ባልና ሚስት እንደ አቡሽ እና እንደ ሚሚ የሚነፋረቁበት ወይም የሚቦርቁበት መዋእለ ህፃናት አይደለም፡፡ አዎ በአንድ ጎጆ ውስጥ የሚኖር ሰው ቀርቶ በሆነ አጋጣሚ የተገናኘም ሰው ሊገፋፋና ሊጋጭ ይችላል፡፡ ይሄ በዱንያ ውስጥ ከምንፈተንባቸው ነገሮች አንዱ እንደመሆኑ በጥንቃቄ ልንጓዝ ይገባናል፡፡ ጌታችን እንዲህ ይላል፡- “ከፊላችሁንም ለከፊላችሁ ፈተና አድርገናል፡፡ ትታገሳላችሁን?” [አልፉርቃን፡ 20]
በትዳር ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ እጅግ የበዙ ግፎችን ስመለከት እና ስሰማ የራሴ ሁኔታ ያስፈራኛል፡፡ ብዙ ሰው የትዳር ሰሞን “አበድኩልሽ ከነፍኩልሽ” እንዳላለ በእጁ ማስገባቱን ባረጋገጠ ማግስት ነገሮች መቀየር ይጀምራሉ፡፡ እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች “አይንሽን ላፈር” የሚለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አንዳንዱ ለአስቤዛ መቶ ሰጥቶ የሁለት መቶ መስተንግዶ የሚጠብቅ አለ፡፡ ሌላው ለውጭ ሰው ተጨዋች፣ ተግባቢ፣ ሳቂታ፣ ገራገር ነው፡፡ ከቤቱ ሲገባ ግን ልጆቹ “መጣ መጣ” እያሉ በፍርሃት የሚያንሾካሹኩበት፣ ሚስት ካሁን አሁን “ምን ይል ይሆን?” እያለች በስጋት የምትዋጥበት አራስ ነብር ይሆናል፣ ግስላ፡፡ “የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ” ይሏል እንዲህ ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን “ከአማኞች ኢማኑ የተሟላው ስነ ምግባሩ ያማረው ነው፡፡ ከናንተ በላጫቻችሁ ለሴቶቻቸው በላጭ የሆኑት ናቸው” ብለው ነበር፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 284] ሌላው ሚስቱን፣ የልጆቹን እናት ከጭቃ የጠፈጠፋት ይመስል እንዳሰኘው ያደርጋታል፡፡ ከልጆቿ ፊት ያዋርዳታል፡፡ በዚህም ወይ እናት በልጆቿ እንድትናቅ በር ይከፍታል፤ አለያ ደግሞ ከተበዳይ እናታቸው ወግነው አባታቸውን እንደ ጠላት እንዲያዩ ያስገድዳል፡፡
መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በሴቶች ጉዳይ አደራችሁን” ብለው ነበር፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እጅግ ብዙ ወንድ ግን “ሴትና ጫማ ከአልጋ ስር” ነው ፖሊሲው፡፡ ሁሌ እሷን ካልከሰተ፣ ሁሌ እሷን ካላዋረደ ወንድ የሆነ አይመስለውም፡፡ ወንድሜ ከሚስትህ የሆነ የማትወደው ባህሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ሰው ነችና ይሄ የሚጠበቅ ነው፡፡ ግን ስላንተስ ማን ያውራ? አንተስ የሚጠላ ጎን አይኖርህምን? ምነውሳ ታዲያ የራስህንም ብታይ? ምነው በጎ ጎኖቿንም ብትመለከት? ምንም ጥሩ ነገር ሳታይባት ነው ለትዳር የመረጥካት? ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “አንድ ሙእሚን ወንድ አንዷን ሙእሚናህ ሴት (ሚስቱን) አይጥላ፡፡ ከሷ የሆነን ባህሪ ቢጠላ ሌላ የሚወደው አለውና፡፡” [ሙስሊም]
አንተ ያማረህን ከውጭ እየሰለቀጥክ ቤትህን የምትዘነጋ ከሆንክ ማሰቢያ የቀለለህ ገልቱ ነህ!! አንተ “እኔ ነኝ ያለ” እያማረጥክ እየለበስክ ሚስትህን የምትረሳ ከሆንክ ቀላል ነህ፣ ኪሎህ ቢከብድም ዋጋህ የወረደ!! ለመሆኑ ሚስትህን አንተ ካልፈቀድካት ማን ይፍቀዳት? ቤተሰቦቿማ አንተን ሰው ብለው፣ አንተን ባል ብለው አደራ ሰጥተውሃል!! ታዲያ ምነው አደራ በላ ትሆናለህ? አንተ በሚስትህ ላይ የምትሰራውን በእናትህ፣ በእህትህ፣ በሴት ልጅህ ላይ ሲፈፀም ብታየው ያስደስትሃልን? ይሄው ውዱ ነብይ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ከምትበሉት አብሏቸው፡፡ ከምትለብሱትም አልብሷቸው፡፡ አትምቷቸውም፡፡ አላህ አስቀያሚ ያድርግሽ እያላችሁም አትርገሟቸው” ይላሉ፡፡ [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 1861] እስኪ ይህን ሐዲሥ እንደ መነሻ ይዘን እራሳችንን እንፈትሽ፡፡
አንዳንዱ አቅሙ ሳይኖረው ሁለተኛ ያገባና ቤቱን የጦርነት አውድማ ያደርገዋል፡፡ እራሱም ቤተሰቡም የሰቀቀን ህይወት እንዲገፉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላው ሁለተኛ ባገባ ማግስት የመጀመሪያዋን ከነመኖሯም ይረሳታል፡፡ ጌታችን (አለማስተካከልንም ከፈራችሁ አንዲትን ብቻ ያዙ…) ሲል ነበር ያዘዘው፡፡ [አንኒሳእ፡ 3] እሱ ግን “ትዳር አላት” እንዳይባል እርግፍ አድርጎ ትቷታል፡፡ “ትዳር የላትም” እንዳይባል ኒካሑ እንዳለ ነው፡፡ ((በአየር ላይ) እንደተጠለጠለችም አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ (ወደ ወደዳችኋት) መዘንበልን ሁሉ አትዘንበሉ) ብሎ ነበር ጠቢቡ ጌታ፡፡ [አንኒሳእ፡ 129] ልብ በል! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሁለት ሚስት ኖሮት ወደ አንዷ ያጋደለ ሰው ነገ በቂያማ ቀን አንድ ጎኑ የወደቀ ሆኖ ይመጣል” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑ መዋሪዱዝዞምኣን፡ 1089] ታዲያ መጨረሻህ ይህ እንዲሆን ነው የምትፈልገው? ወንድሜ የበደልካት ሚስትህን ሞት ሳይቀድምህ በፊት በጊዜ “ዐፍው” አስብላት፡፡ ያለበለዚያ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት “ግፍ ነገ የቂያማ ቀን የጨለማ ንብርብር ነው፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] በየጓዳው በበዳይ ባሎቻቸው ግፍ ሳቢያ ደም እንባ የሚያነቡትን ሴቶች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ወላሂ ወንድነትህን ተጠቅመህ በደካማዋ ሴት ላይ የምትፈፅመው ግፍ እሷ ላይ ከደረሰው የከፋ ያስከፍልሃል፡፡ “የተበዳይን እርግማን ተጠንቀቅ፡፡ በሷና በአላህ መካከል መጋረጃ የለምና!!” ይላሉ ከልብ ወለድ የማይናገሩት ነብይ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] የስሙን መጠሪያ የዐይን ማረፊያ ልጆቹን ከሷ አግኝቶ፣ ስሜቱን በሷ ላይ አርክቶ፣ ህይወቱን በሷ ላይ መስርቶ፣ የቤት ጣጣውን ሁሉ ከሷ ላይ ጥሎ፣ ሁለ-ነገሯን እንደ ሸንኮራ መጥጦ… ከዚያም አለጠም ጣፈጠ ያለፈውን ሁሉ በመዘንጋት ምንም ዋጋ እንደ ሌላት ልክ እንደ ቆሻሻ፣ እንደ ቆረቆንዳ መወርወር ምን የሚሉት ኢ-ሰብኣዊነት ነው?! ምን የሚሉትስ ገልቱነት ነው?! በእናትህ፣ በልጅህ፣ በእህትህ ላይ እንዲህ ቢፈፀም ደስ ይልሃልን? አትጠራጠር! የእጅህን ታፍሳለህ! የዘራሃውን ታጭዳለህ! “አልጀዛኡ ሚን ጂንሲል ዐመል” ይላሉ አበው፡፡ “ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው” እንደማለት፡፡
አትዘንጋ!! ልክ አንተ በሚስትህ ላይ ሐቅ እንዳለህ ሁሉ ሚስትህም ባንተ ላይ ሐቅ አላት፡፡ ሃይማኖታችን እንዲህ ነው የሚያዘው፡-
- (ለእነሱም (ለሴቶቹ) የዚያ በነርሱ ላይ ያለባቸው (ሃላፊነት) አምሳያ (ሐቅ በባሎቻቸው ላይ) አላቸው፡፡” [አልበቀራህ፡ 228]
- (በመልካም ተኗኗረዋቸው፡፡) [አንኒሳእ፡ 19]
- “አዋጅ! ለናንተ በሴቶቻችሁ ላይ ሐቅ አላችሁ፡፡ ለሴቶቻችሁም በናንተ ላይ ሐቅ አላቸው፡፡” [ሶሒሑልጃሚዕ፡ 7880]
- “ለቤተሰብህም ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡ እያንዳንዱን ባለ ሐቅ ሐቁን ስጥ!” [ቡኻሪ]
- “ለሚስትህ ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ይልቅ ቂል አትሁን፡፡ ለሚስትህ፣ ለልጆችህ ደግ፣ ምቹ ሁንና ቤትህን ምድራዊ ጀነት አድርገው፡፡ ብቻ አንተ ቻልበት፡፡ ከጅምሩ ሷሊሐዋን ምረጥ፡፡ ወይም ሷሊሐ እንድትሆን ጣር፡፡ ያኔ ገና ስታያት ትረካለህ፡፡ በልጆችህ አስተዳደግ ትረካለህ፡፡ ላንተ ባላት መቆርቆር ትረካለህ፡፡ በጨዋነቷ፣ በቁጥብነቷ ትረካለህ፡፡ ዱንያ ላይ ከዚህ በላይ ምን ድሎት አለ?! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ዱንያ መጣቀሚያ ነች፡፡ ከመጣቀሚያዎቿ ሁሉ በላጩ ደግ (ሷሊሐህ) የሆነች ሴት ናት” ይላሉ፡፡ [ሙስሊም]
ልብ አድርግልኝ!! እያወራሁ ያለሁት ሃላፊነት የማይሰማው ደዩስ ባል እንደሚያደርገው እንድትሆን አይደለም፡፡ ምን ለበሰች? አይገደውም፡፡ ማን ጋ ዋለች? አይደንቀውም፡፡ የት አመሸች? አይሞቀውም፡፡ ይሄ ደዩስ ነው! ከርፋፋ ነገር፡፡ ደይዩስነት ከእንስሳትም አሳማዎች ጋር ነው በስፋት የሚንፀባረቀው፡፡ የወንድ አልጫ ማለት ይሄ ነው፡፡ እራሱ ኃላፊነቱን ጥሎ ጠፍቶ የሚያጠፋ እንከፍ፡፡ እንጂ ወንድ ማለት “ወጥ ቀጠነ” ብሎ አቧራ የሚያስነሳ፣ ምግብ ላይ የሆነ ጉድፍ አገኘሁ ብሎ አገር የሚበጠብጥ አይደለም፡፡ ቢገባህ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የቀረበላቸው ምግብ ከተመቻቸው ይበሉታል፡፡ ካልሆነ ግን አቃቂር እያወጡ ነገር አይሰነጥቁም፣ በነገር አይሸነቁጡም፡፡ ታዲያ አርአያህ ማን እንዲሆን ነው የምትፈልገው? ጌታችን (ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልእክተኛ ላይ መልካም ምሳሌ አለላችሁ!!) ይላል፡፡ [አሕዛብ፡ 21]
ወንድሜ የሚስትህን ነውር ለማንም አታውራ፡፡ ማንም ቢሆን የሚስትህን ያክል ቅርብ አይደለም፡፡ አንተን ባል ብላ ለእናት ለአባቷ የማትገልጠውን ገላዋን ላንተ ነፃ አድርጋለች፡፡ ልብስ እንደሆንክላት ልብስህ ሆናልሃለች፡፡ አዎ ሚስትህ ከየትኛውም አልባሳት የበለጠች ምቾትን የምትሰጥህ፣ ነውርህን የምትሸፍንልህ ቆንጆ ልብስህ ናት፡፡ ልብስህን እየገሸለጥክ የራስህን ነውር ባደባባይ አታስጣ፡፡ ሌላው ቀርቶ ብትፈታት እንኳን ነውሯን አትዝራ፡፡ ከሰለፎች አንዱ ከሚስቱ ጋር የሆነ ክፍተት ይኖርበታል፡፡ “ምንድነው ችግሩ?” ቢሉት “እንዴ! እንዴት ብየ የሚስቴን ነውር አወጣለሁ?” አላቸው፡፡ ከሚስቱ ጋር ሲለያይ ጊዜ “እሺ አሁንስ ምን ነበር ችግሯ? ንገረን” አሉት፡፡ “እንዴ! እኔ ምን አግብቶኝ ነው የሌላ ሰው ነውር የማወጣው?” አላቸው፡፡ እኛ ግን አብረንም ሆነን ከሰው ሁሉ ለአካላችን ቅርብ የሆነች ሚስታችንን ነውር የሷን ያክል ለማይቀርበን ምናልባትም ይሄ ነው የሚባል ቅርበት ለሌለን ሰው እንዘከዝካለን፡፡ ከተለያየንማ ጭራሽ የሌለውንም ጭምር እንቀደዳለን፡፡ አንዳንዱማ የራሱን ነውር ለመሸፈን በሌለችበት የሚወነጅል አለ!! አላሁልሙስተዓን!! ያለባትን ብናወራ ያገጠጠ ሃሜት ነው፣ በህይወት አጋራችን ላይ የሚፈፀም ክህደት!! የሌለባትን ብናወራ አይን ያወጣ ቅጥፈት ነው፣ ድንገት ያስተዋሉ እለት ህሊናን የሚጠዘጥዝ ውርደት!!
ወንድሜ! ካለልህ ለሚስትህ ደግ ሁን፡፡ ባል እንጂ ደባል አትሁን፡፡ ስትመጣ ተፍለቅልቃ በደስታ የምትቀበልህ እንጂ ገና መምጫህ ሲቃረብ ልቧ የሚጨነቅ የሚጠበብ፣ ድምፅህ ሲሰማ አመዷ የሚቦን አታድርጋት፡፡ ከቻልክ በመልካም ተኗኗር፡፡ ካልሆነልህ በመልካም ተለያይ፡፡ አለቀ፡፡ (በመልካም መያዝ፤ ካልሆነ በበጎ መለያየት) ይላል ቁርኣኑ፡፡ [አልበቀራህ፡ 229] አስተውል! ብትለያዩም ሙስሊማ እህትህ እንጂ ጠላትህ አይደለችም፡፡ በተለይ ደግሞ ልጆች ካሏችሁ የግፍ ሰንሰለትህን እያረዘምክ ከጓዳህ ጠላት አታፍራ፡፡ ምንም አይነት ቂምና በቀል አያስፈልግም፡፡ በጣም የሚገርመው በሰላሙ ጊዜ ስንት ህይወት እንዳላሳለፉ፣ ስንት መከራ አብረው እንዳልገፉ፣… እህል ውሃቸው አልቆ መለያየት ሲመጣ ጊዜ ለመስማት የሚሰቀጥጡ፣ ለማየት የሚያንቀጠቅጡ ግፎች ሲፈፀሙ ይታያል፡፡ አንዳንዱ ጨቅላ ልጇን ከላዩዋ ላይ የሚመነጭቅ አለ፡፡ ሌላው ድሮ ያልሰጣትን መህሯን የሚክድ አለ፡፡ ዐጂብ የሆነ መውረድ!! ሌላው ከሷ አልፎ ቤተሰቧን ጭምር አበሳ የሚያሳይ አለ፡፡ ሌላው “እስኪ ከዚህ በኋላ የሚያገባትን አየዋለሁ” አይነት የሚፎክር አለ፡፡ አንዴ ከተለያየ በኋላ ከሚያገባት ሰው ጋር መቀያየም ግፋ ሲልም መደባደብ ምን የሚሉት እብሪት ነው?! ሱብሓነላህ! እስኪ ይህን በጉልበት የሚታሰብበት የጃሂሊያህ ሱንናህ ተመልከቱ፡፡ እስኪ እንዲህ አይነቱን ቂላቂል የራሱ ጠላት ታዘቡ፡፡ ይሄ ድሮም ሲበድል እንደኖረ፣ ሲለያይም በሰላም እንዳልተለያየ በግልፅ እያመላከተ ነው፡፡
እስኪ አሁን ጨቅላ ህፃንን ከእናት እቅፍ በመመንጨቅ የፈታትን ሚስት መበቀል ምን የሚሉት አረመኔነት ነው? አቤት የሰው ልጅ ገልቱነት! አቤት የሰው ልጅ ጭካኔ!! በርግጠኝነት ይህን የሚያደርገው ለልጁ ተቆርቁሮ አይደለም፡፡ ተምሳሌት የሆነ ልዩ የእናትነት ፍቅሯን፣ በርህራሄ የሚንሰፈሰፍ አንጀቷን አይቶ በልጇ የሚበቀል ወንድ ያለጥርጥር ወንዶች በወንድነታቸው እንዲያፍሩ፣ ሴቶች ወንዶችን ጭራቅ አድርገው እንዲስሉ የሚያደርግ ሲበዛ ርካሽ የሆነ ምግባር ነው!!
አላህ ማስተዋሉን ያድለን፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 26/2008)

Post a Comment

0 Comments