Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዓቂዳ ምንድ ነው ?

ዓቂዳ ምንድነው 
ዓቂዳ በዐረብኛ ቋንቋ “አሰረ ፣ አጠበቀ ፣ ቋጠረ…” ከሚሉ ጥሬ ቃላት የተገኘ ነው፡፡ የስርወ ቃል ትርጉሙም በኃይል አጥብቆ መቋጠርን ያመለክታል፡፡ የአብዛኛዎቹ ኡለማዎች (ኢስጢላሀዊ) የስስምነት ፍቺ በአማኙ ዘንድ ፍፁም ጥርጣሬ የሌለበት ቁርጥ ያለ እምነት (ኢማን) ማለት ነው፡፡
      ኢስላማዊ አቂዳ አላህ (ሱ.ወ) በጌትነቱ፣ በአምለክነት፣ በስሞቹና በባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አቂዳ የሆነው ኢማን በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻህፍቱ፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀደር (ክፉም ሆነ ደጉ በአላህ ቅድመ ውሳኔ መሆኑን) ማመን ነው፡፡
      ከዚህም በተጨማሪ በተረጋገጠ መልኩ በተላለፉት የዲን መሰረቶችና መርሆዎች፣ ከህዋሳት ንግዛቤ በራቁ (የገይብ) ጉዳዮች ማመንን ይጨምራል፡፡ እንዲሁም በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወርቃማ የእስልምና ክፍለ ዘመናት በሕይወት ኖረው ያለፉ የቀናው ጐዳና የሃይማኖት መሪዎች የደረሱበትን ስምምነት (ኢጅማዕ) መቀበል ነው፡፡ በአጠቃላይ ለአላህ (ሱ.ወ) ትዕዛዛት፣ ፍርድና መልዕክተኛውን በመከተል ረገድ ያለአንዳች ማመንታት እጅ መስጠትና በቁርጠኛነት ማመን ማለት ነው፡፡
      ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት ኢስላማዊ አቂዳ አላህ (ሱ.ወ) ለባሪዎቹ ለመረጠው፣ የወደደውና የሰጠው ብቸኛ እምነት መሆኑን ማወቅና በፍፁም ልብ መቀበል ይገባል፡፡ ይህም ሲባል በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወርቃማ የእስልምና ክፍለ ዘመናት የኖሩት ሰሀባዎች እና ታዕቢዮች የተጓዙበትን ቅን የእምነት ጐዳና የተከተሉ የሐቀኛ ምህመናን የአሕሉ ሱና ወልጀመዓ እምነት ነው፡፡
      ከዚህ በተጨማሪም ኢስላማዊ አቂዳ ሌሎች እሱን የሚያመለክቱና የሚተኩት ተላዋጭ መጠሪያዎች አሉት፡፡ እነርሱም አተውሂድ፣ አሱንና፣
ኡስሉዲን፣ አልፊቁሀል አክበር፣ አሸሪዓ እና አል ኢማን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
ዓቂዳ የሰዎች ሁሉ መሰረት  
     የሰው ልጆች ሁሉ ሲፈጠሩና ወደዚህች ዓለም ሲመጡ አላህ (ሱ.ወ) ለባሪያዎቹ የመረጠውና የወደደውን የኢስላማዊ አቂዳ እምነት ይዘው ነው፡፡ ነገር ግን ሸይጧን ከእነ ሰራዊቱ ከዚህ የቀና የእምነት ጐዳና በማስወጣት በአስከፊ የባዕድ አምልኮና ሽርክ ውሰጥ እንዲዘፈቁ አድርጓቸዋል፡፡
      የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን በተመለከ በአስተላለፉት ሀዲስ፡- “ማንኛውም ሰው የሚወለደው በኢስላም (በትክክለኛው እምነት) ላይ ነው፤ ከዚያ በኃላ ወላጆቹ አይሁድ ወይም ክርስቲያን ወይም እሳት አምላኪ ያደርጉታል፡፡” ብለዋል የሀዲሱ አስላላፊ አቡ ሁረይራ
በዚህ ዘገባ መጨረሻ ላይ፡- “ከፈለጎችሁ የሚከተለውን የቁርአን አንቀፅ አንብቡ፤ … የአላህን ፍጥረት ያቺን አላህ ሰዎችን በአርስዎ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት) የአላህን ፍጥረት እና (ሃይማኖት) መለወጥ የለም፣ ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡” አል ሩም 3ዐ (ቡኻሪ እንደዘገቡት)
      ከአባታችን አደም (ዐ.ሰ) ዘመን አንስቶ እስከ ነብዩላሂ ኑህ (ዐ.ሰ) ዘመን ድረስ የነበሩት ሕዝቦች በዚህ የአቂዳ እምነት ጐዳና በቀጥተኛነት ይጓዙ እንደነበር በቁርአንና በሐዲስ ውስጥ በበርካታ አንቀጾች ተገልጿል፡፡ የተለያዩ ሰሃባዎች ንግግሮችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡
      ከእነዚህ የቁርአን ማስረጃዎችም በአል-በቀራህ ቁጥር 213 ላይ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሰዎቹ ሁሉ አንድ ሕዝብ ነበሩ፤ (ተለያዩ)፡፡ አላህም ነቢያትን አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርጎ ላከ፡፡›› (አል በቀራህ 213)  

በዓቂዳ መለያየት እንዴት ተከሰተ 
ከሰሃባዎች ዘመን አንስቶ ያሉ የቁርአን  ትንታኔ (ተፍሲር) ሊቃውንት በነብዩላህ አደም (ዐ.ሰ) እና በኑህ (ዐ.ሰ) አፈጣጠርና ትውልድ መካከል የአስር ክፍለ ዘመናት ልዩነቶች እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ክፍለ ዘመናት ውሰጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አላህ (ሱ.ወ) ሰዎችን በፈጠረበት፣ ለባሪያዎቹ በመረጠውና በወደደው በትክክለኛው የኢስላማዋ አቂዳ የእምነት መንገድ ይጓዙ እንደነበረም ይገልፃሉ፡፡
      በክፍለ ዘመናቱ መጨረሻም ላይ ግን ሸይጧን ከክፍለ ሰራዊቱ ጋር ተባብሮ በከፈተው በልብ የሚስብ ዘመቻ የሰው ልጅ የአቂዳን የእምነት ፈለግ በመሳት እጅግ አስከፊ ወደሆነው የባዕድ አምልኰና የሽርክ አዘቅት ውስጥ መውደቅ ችሏል፡፡  
      ኢማሙል ቡኻሪ በቅዱስ ቁርአን ሱረቱ-ነህ ውስጥ ስለተጠቀሱት የወድ፣ሱዋዕ፣የጉስ፣ የዑቅ እና ነስር የተባሉት ሰዎች ከአብድላህ ኢብኑ አባስ ንግግሮች የሚከተለውን ዘግበዋል፡፡ “…እነዚህ ከኑህ መላክ በፊት የነበሩ ደጎግ የአላህ ባሪያዎች ሰዎች ስሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ደጋግ ባሪያዎች በሞቱ ጊዜ ሕዝቡ ክፉኛ ማዘኑን በመመልከት  ሸይጧን ወደ ሕዝቡ በመምጣት እነዚህን ደጋግ የአላህ ባሪያዎች ለማስታወስ ይረዳችሁ ዘንድ በየመቀመጫ ስፍራቸው (የመታሰቢያ) ምስላቸውንና ሀውልታቸውን አኑሩ፣ በየስማቸውም ሰይሟቸው በማለት መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ሰዎቹም የተባሉትን ተገበሩ ነገር ግን በዚያን ወቅት እነዚህ ምስሎች አልተመለኩም ነበር፡፡ ይህኛው ትውልድ አልፎ ትውልድ በትውልድ በተተካ ጊዜ (አላህን በብቸኛነት የማምለክ የተውሂድ) እውቀት በተረሳ ጊዜ እነዚያ ምስሎች ተመለኩ፡፡” ይላል ዘገባቸው
      በዚህም ምክንያት የሰው ልጆች ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ነብያትን በተከታታይ ላከ መሰረታዊ መልዕክታቸውንም ይህንኑ ጥመት ማሳወቅ ነበር፡፡
በአላህ መደንገጉ 
“አላህ ዘንድ (ተቀባይነት) ያለው ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነው፡፡” (አል ዒምራን 19)
 “ለእናንተ ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ” (አል ማኢዳህ 3)
“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖት የሚፈልግ ሰው ፈፅሞ ከእርሱ ተቀባይነት የለውም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡” (አል ዒምራን 85)
“አላህን ተገዙ፣ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡” (አል ኒሳእ 36)“በላቸው፡- አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኃልና …” (አል ዒምራን 31)“ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ በማጥራትና ወደ ትክክለኛው መንገድ በመዘንበል አላህን እንዲገዙ እንጂ አልታዘዙም” (አል በይና 5)“በአላህ ላይ ብቻ ምዕመናን ይመኩ” (አል ዒምራን 16ዐ)“ለአላህም አምሳያዎችን አታድርጉ፤ አላህ ያውቃል እናንተ ግን አታውቁም “ (አል ነህል 74)‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡›› (አል ሹራ 11)“ከሰማይና ከምድርም ሲሳይን የሚሰጣችሁ የሆነ ከአላህ ሌላ ፈጣሪ አለን ከእርሱ በቀር አምላክ የለም” (አል ፋጢር 3)“ለአንተም በእርሱ እውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፣ መስሚየም ማያም፣ ልብም እነዙህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከነሱ ተጠያቁ ነውና” (አል ኢስራእ 36)
ነብያት ሁሉ ያስተማሩት (ሁሉም ነብያት አስተምረውታል)    
   አላህ (ሱ.ወ)  በተለየዩ ዘመናት በርካታ ነቢያትን ልኳል፡፡ እነዚህ ነብያት ለተላኩላቸው ሕዝቦች ያስተምሩ የነበረው የአላህን ብቸኛ አምላክነት የሚገልፀውን (ተውሂድ አል ኡሉሂያ) የተውሂድ ክፍል እንደነበረ ቅዱስ ቁርአን ይነግረናል፡፡
‹‹በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፡፡›› (አል ነህል 36) በሱረቱል አንቢያ ውስጥም አላህ (ሱ.ወ)  ወደየህዝቦቻቸው ስለላካቸው መልዕክተኞች ለነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ሲገልፅላቸው እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡›› (አል አንቢያ 25)
      በየዘመናቱ ወደ ሕዝቦቻቸው የተላኩ ነቢያት በአቂዳ ዙሪያ ጠንከር ያለ የፀና አቋምና እምነት እንዲኖራቸው ነበር፡፡ ሕዝባቸውን ያስተምሩና ይመክሩ፣ ያስጠነቅቁና ይዘክሩ የነበረው፡፡ ህዝቡ ግን ጌታቸው ለእርሱ የዋለውን ውለታና የጣቸውን ሲገባቸው አስተባበሉ፡፡ በአመፀኛነታቸውም ገፉበት፡፡
      በአቂዳ ዙሪያ ባሉ የዲን ጉዳዮች ማወላወል ፈፅሞ የለም፡፡ የሐቀኛ ምዕመናን የአህሉ ሱና ወልጀመዓ የሕይወት መመሪያ የሆነውን ቁርአንንና የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ሙሉ በሙሉ መከተል ብቻ ነው፡፡ በየዘመናቱ የላኩት ነቢያትም ያስተማሩት ይህንኑ ነው፡፡
ነቡዩላሂ ኑህ 
የጠመመውን ትውልድ ለማቅናት አላህ (ሱ.ወ) ነብዩላሂ ኑህን ሌሎች ነቢያቱን በላከበት መንገድ ነበር የላካቸው፡፡ ኑህም ሕዝባቸውን እንዲህ በማለት ሌት ከቀን ተጣሩ፡ -
“ህዝቦቼ ሆይ እኔ ለእናንተ ገላጭ የሆንኩ አስጠንቃቂ ነኝ፡፡ አላህን ተገዙት፣ ፍሩትም፣ ታዘዙትም፡፡” (ኑህ 2-3)ነብዩላሂ ኑህ የተላኩለት ህዝብ ግን ሊሰማቸውና ከሚከተለው የጥመት መንገድ ሊመለስ አልቻለም፡፡ እርስ በእርሳቸውም በባዕድ አምልኳቸው ዙሪያ አደራ መባባሉን ቀጠሉት
‹‹አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ወድንም፣ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የዑቅንም ነስርንም አትተው፡፡›› (ኑህ 23)ይህን በመሰለ መልኩ ነብዩላሂ ኑህ ቀጥተኛሉንና ሐቀኛውን የኢስላማዊ አቂዳ እምነት እያስተማሩ በሕዝቦቻቸው ውስጥ፡-
‹‹በውስጣቸውም ሺህ ዓመትን አምሳ ዓመት ሲቀር ተቀመጠ፡፡›› (አል አንከቡት 14)  ኑህ በኖሩባቸው ዘመናት በሙሉ ለሕዝባቸው ተውሂድን አስተማሩ፡፡ በተለይ ከሽርክ ይጠነቀቁ ዘንድ በፅኑ አስገነዘቡ፡፡
ነብዩላሂ ሁድ
ነብዩላሂ ሁድ (ዐ.ሰ) ወደ ግድ ሕዝቦች የተላኩበትን የአቂዳ ዳዕዋ እንዲህ በማለት ነበር የጀመሩት፡-
‹‹ወገኖቼ ሆይ አላህን ተገዙ ፣ ከእርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም፡፡›› (አል አዕራፍ 65 \አል ሁድ 5ዐ)       ነብዩላሂ ኑህ (ዐ.ሰ) በተላኩለተ ሕዝቦቸው እንዳስተማሩትና እንዳስጠነቀቁት ሁሉ ነብዩላሂ ሁድም ለህዝባቸው አቂዳን አስተምረዋል፡፡ ከዚህ ጠንካራ የእምነት መሠረት ፈቀቅ እንዳይሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
      ሁሉም ነቢያት በተለያዩ ዘመናት ለተለያዩ ህዝቦች ይላኩ እንጂ የመልዕክታቸው ስረ መሰረት አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ የዓድ ህዝባች ነብዩላሂ ሁድን (ዐ.ሰ) ሊሰሙ አልፈቀዱም፡፡ ህዝቡ የተላከላቸውን አንድ ነብይ በማስተባበላቸውም ተመሳሳይ መልዕክት ይዘው የተላኩትን ሁሉንም ነቢያት እንዳስተባበሉ ተቆጥሮባቸዋል (ተመስሎባቸዋል)፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓኑ እንዲህ ሲል ገሰፃቸው፡፡
   ‹‹ዓድ መልዕክተኞችን አስተባበለች፡፡›› (አል ሹዓራ 123) 
ነብዩላሂሳሊህናነብዩላሃሹዓይብ 
በአላህ አንድነትና እሱን ብቻ ስለመገዛት የሚገልፀውን ኢስላማዊ የአቂዳ ትምህርት መልዕክት በመያዝ ነበር፡፡ ነብዩላና ሷሊህ ወደ ሰሙድ ህዝቦች የላኩት፡፡ ለመድየን ህዝቦች የተላኩት ነብዩላሂ ሹዓይብም በተመሳሳይ መልኩ ቀደምት ነቢያት ለህዝባቸው የተላኩበትን የአቂዳ መሰረታዊ መልዕክት በመያዝ ነበር ዳዕዋ ያደረጉት፡፡ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ በመግለፅ ነበር ህዝቡን ከጥመት እንዲመለስ ያስተማሩትና ያስጠነቀቁት፡፡
ነብዩላሂ ኢብራሂም     
  በአላህ አንድነትና እሱን ብቻ ስለመገዛት ባለው የተውሂድ አስተምህሮ ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የሕይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል የመጨረሻ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የስጋገ ዘመዶቻቸውና የገዛ ቤተሰባቸውን ጨምሮ ህዝባቸው በጠላተነት ተነስቶባቸዋል፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) መልዕክተኛ ነበሩና በማያልቅበት ቸርነት፣ በአስደናቂው ተአምራቱ፣ በመለኮታዊ የበላይነቱ ጥበቃው አልተለያቸውም፡፡
      ለአላህ (ሱ.ወ) ሲታዘዙ ቅንጣት የማያወላውሉ በመሆናቸውም የአላህን የወዳጅነት ማዕረግ ለመጐናፀፍ በቅተዋል፡፡ ተውሃድን በተመለከተ ታላቁ ሞዴል አርአያ ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ)  ናቸው፡፡ ይህንንም በተመለከተ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ገልፆልናል፡-
 ‹‹በኢብራሂምና በእነዚያ ከእርሱ ጋር በነበሩት (ምእምናን) መልካም መከተል አለቻችሁ፡፡ ለሕዝቦቻቸው «እኛ ከእናንተ ከአላህ ሌላ ከምትግገዙትም ንጹሖች ነን፡፡ በእናንተ ካድን፡፡ በአላህ አንድ ብቻ ሲኾን እስከምታምኑ ድረስ በእኛና በእናንተ መካከል ጠብና ጥላቻ ዘወትር ተገለጸ፡፡» ባሉ ጊዜ (መልካም መከተል አለቻችሁ)፡፡›› (አል ሙምተሂናህ 4)ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ከህዝቦቻቸው ጋር ከፍተኛ ክርክር ስላደረጉበት ነው ይህ የቁርዓን አንቀፅ የሚያስረዳው፡፡ ይህን ክርክራቸውንና የውይይታቸውን ውጠት አላህ (ሱ.ወ) በሱረቱል አንቢያ 51-57 ባሉ አንቀፆች አብራርቶቃል፡፡ ይህንንም አጠር አድርገን ስንመለከተው፡-
      ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ወገኖቻቸው ከእንጨትና ከድንጋይ ከወርቅና ከመሰል ግዑዞች የተሰሩ ልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፆችን ያመልኩ ነበር፡፡ ነብዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ይህ የወገኖቻቸው ድርጊት አላህን ከመገዛት እውነተኛ ጐዳና ያፈነገጠ መሆኑን በመገንዘባቸውም፡-
‹‹ይህቺ ቅርፃ ቅርፅ ይህቺ እናንተ ለእርሷ (ዘውትር) አምላኪዎች የሆናችሁት ምንድናት?›› (አል አንቢያ 52)በማለት የወገኖቻቸውን ከንቱ የባዕድ አምልኮ በማናናቅ ጠይቀዋቸዋል፡፡ እነሱም ‹‹አባቶቻችን ያመልኩ ነበር፣ እኛም የእነርሱን መንገድ ተከትለን እናመልካለን›› በማለት መልሱላቸው፡፡
ጣዖታትን ማምለክ ስህተት መሆኑን በመግለፅ ሊመለክ የሚገባው አንድ አላህ (ሱ.ወ) ብቻ መሆኑን በድፍረት አስተማሩ፡፡ እኒህ ጣዖታት ከቶም አንዳች ጥቅም እንደሌላቸው፣ ራሳቸውን እንኳ መከላከል እንደማይችሉ፣ በማንም ላይ ጉዳት የማድረስ አቅምና ችሎታ የሌላቸው፣ ጥቃት ቢደርስባቸው እገሌ ነው ብለው መናገር ወይም መጠቆም የማይችሉ አቅመቢስ መሆናቸውን በመግለፅ እይተነተኑ አስተማሩ፡፡
ህዝቡ ከጥመቱ የተነሳ (ሱ.ወ) ቅን ልባናውን የነሳው ነበርና ለተደረገለት የቅን መንገድ ጥሪ ዳዕዋ የሰጠው ምላሽ በእጅጉ የከፋ ነበር፡፡
«ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት፡፡ አማልክቶቻችሁንም እርዱ» አሉ፡፡ (በእሳት ላይ ጣሉትም)፡፡›› (አል አንቢያ 68)እጅግ ከባድ የሆነ እሳት አቀጣጠሉና እዚያ ውስጥ ጣሏቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ኢብራሂም (ዐ.ሰ)  አንዳች ችግር ሳይደርስባቸው በሰላምና በጤና ይወጡ ዘንድ ስለፈቀደ እንዲህ የሚል መልዕክት ለእሳቷ አስተላለፈ፡-
«እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ ሰላምም ሁኚ» አልን፡፡ (አል አንቢያ 69) 
ከመመፃደቅ መራቅ 
ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የአላህ (ሱ.ወ) ትሩፋት አብዝቶ የወረደላቸው ቢሆኑም በእጅጉ ጥንቁቅ ነበሩ፡፡ የታገልኩለትን ተውሂድ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፣ ሽርክን ድባቅ መትቻለሁ፣ ጣኦታትን ሳይቀር በእጆቼ አፈራርሻለሁና ከእንግዲህ ወዲህ እኔና ልጆቼ በዚህ ረገድ በፍፁም አንፈተንባቸውም ብለው የሚኩራሩ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም አላህን፡-
«ጌታዬ ሆይ! ይህንን አገር (መካን) ጸጥተኛ አድርገው፡፡ እኔንም ልጆቼንም ጣዖታትን ከመገዛት አርቀን፡፡›› (ኢብራሂም 35)በማለት ከመመፃደቅ የፀዳ ልመና ያቀርቡ ነበር፡፡ በመጨረሻም ልጆቻቸው በኢስላማዊ አቂዳ ሕይወታቸውን እንዲመሩ መከሩ፡-
‹‹በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡ ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)፡፡ «ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ» (አላቸው)፡፡›› (አል በቀራህ 132)ነብዩላሂ ሙሳ እና ፊርዓውን
ኢስላማዊ አቂዳ አላህ ዘንድ የተወደደና አላህ (ሱ.ወ) ለባሪያዎቹ የመረጠውና የሰጠው ብቸኛ የእምነት መሰረት የመሆኑን ያህል በየዘመናቱ ፀጥመትና፣ ሽርክና ባዕድ አምልኮ ፈተና ሲያጋጥመው ቆይቋል፡፡ አሁን እስካለንበት ክፍለ ዘመን ድረስም ይኸው ፈተና ይስተዋላል፡፡ ጠባቂው አላህ (ሱ.ወ) ነውና ያጋጠሙተን ፈተናቻች ሁሉ ድል እያደረገ ዘመናትን አቋርጦ ዘለዓለም ይኖራል፡፡
      ነብዩላሂ ሙሳ (ዐ.ሰ) እንደፊተኞቹ ነቢያት በአላህ (ሱ.ወ) የተመረጡ መሆናቸውን አላህ (ሱ.ወ) ሲገልፅ፡-
‹‹ሙሳንም መጽሐፉን ሰጠነው፡፡ ለእስራኤልም ልጆች መሪ አደረግነው፡፡ ከእኔ ሌላ መጠጊያን አትያዙ፤ (አልናቸውም)፡፡›› (አል ኢስራእ 2)በማለት ሙሳ (ዐ.ሰ) የተውሂድ መልዕክተኛ እንደነበሩ ይነግረናል፡፡ በዘመናቸው አላህ የሚገዳደረውን ነውጠኛውን የሀገር መሪ ፊርዓውንን ፈጣሪውን እንዲፈራ፣ አላህን ብቻ እንዲያመልከ፣ በእስራኤል ልጆች ላይ እየፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ ግፍ እንዲያቆም ዳዕዋ አድርገውለታል፡፡
      ህዝባቸውንም ከጥመትና የባዕድ አምልኮ ሽርክ እንዲላቀቅ አስተምረዋል አስጠንቅቀዋል፡፡ ከወንድማቸው ሀሩን (ዐ.ሰ) ጋር ወደ እብሪተኛው ፊርዓውን ሲልካቸውም፡-
 «ወደርሱም ኺዱ፤ በሉትም፡- ‹እኛ የጌታህ መልክተኞች ነን፡፡› የእስራኤልንም ልጆች ከኛ ጋር ልቀቅ፡፡ አታሰቃያቸውም፡፡ ከጌታህ በኾነው ተዓምር በእርግጥ መጥተንሃልና፡፡ ሰላምም ቀጥታን በተከተለ ሰው ላይ ይኹን፡፡ እኛ ቅጣቱ ባስተባበለና እምቢ ባለ ሰው ላይ ነው ማለት  በእርግጥ ተወረደልን፡፡  (ፈርዖንም) «ሙሳ ሆይ! ጌታችሁ ማነው?» አለ፡፡ ጌታችን ያ ለፍጥረቱ ነገርን ሁሉ (የሚያስፈልገውን) የሰጠ ከዚያም የመራው ነው» አለው፡፡ (ጣሃ 47-5ዐ)      ፊርዓውን በዙሪያው ያሉ መሰሎቹ ግን የሙሳን መልዕክተኛነትና አላህ (ሱ.ወ) የሰጣቸውን ተአምራት አስተባበሉ፤ በክህደትና በጥመታቸውም ቀጠሉ፡፡ ከእነርሱ በኃላ ለሚመጣው ትውልድ ማስተማሪያ የሚሆን ቅጣት ተፈፀመባው፡፡
      ነብዩላሂ ሙሳ (ዐ.ሰ) ፊርዓውን ሰራዊቱ በአሻፈረኝ ባይነታቸው የሰጠሙበትን ባህር ተአምራት በድንቅ የአላህ ተአምራት አልፈው ተጓዙ፡፡ 
ተውራትና ጣዖት 
አላህ (ሱ.ወ) በሙሳ መሪነት ሕዝበ እስራኤልን ከፊርኦን ባርነት ነፃ አወጣቸው፡፡ ቃል ወደተገባላቸው የተስፋይቱ ሀገር ተጓዙ፡፡ ህዝበ እስራኤል በአላህ እገዛ ከባርነት ቀንበር ተላቅቀው ነፃ ህዝቦች የሆኑት ህዝበ እስራኤል አላህ (ሱ.ወ) የመረጠላቸውና የወደደላቸውን ጠቅተኛውን የአቂዳ መስመር ተከትለው መጓዝ አቃታቸው፡፡
      በአላህ ድንቅ ተአምራት ባህሩን ተሻግረው እየተጓዙ ሳሉ በጣኦት አምልኮ የጠመዱ ህዝቦችን ባዩ ጊዜ ነብዩላሂ ሙሳን (ዐ.ሰ) እንዲህ በማለት በድፍረት ጠቀቋቸው፡፡
 የእስራኤልንምልጆችባሕሩንአሻገርናቸው፡፡ለእነርሱበኾኑጣዖታት (መገዛትላይበሚዘወትሩሕዝቦችላይአለፉም፡፡ «ሙሳሆይ፡ለእነርሱ (ለሰዎቹ)አማልክትእንዷላቸውለእኛምአምላክንአድርግልን» አሉት፡፡(አል አዕራፍ 138)
ሙሳም ይህ የህዝባቸው የአላህን ብቸኛ አምላክነት መዘንጋት በእጅጉ አሳዘናቸው፡፡ በፊርዓውን የባርነት ቀንበር ተጭኖባቸው በሚሰቃዩባቸው ወቅቶች ስለእስልምና የአቂዳ እምነትና ተውሂድ ለማስተማር እየተጉ የደከሙባቸውን ዘመናት በአጭር ጊዜ ፍሬ ከርስኪ ሲያደርጉት በማየታቸው ከልባቸው አዘኑ፡፡ “እናንተ የአላህን ልቅና እንዲሁም አምልኮ ከአላህ ሌላ ለማንም እንደማይገባ የማታውቁ ህዝቦች ናችሁ፡፡”
 «እናንተየምትሳሳቱሕዝቦችናችሁ፤» አላቸው፡፡ (አል አዕራፍ 138)በማለት የሕዝበ እስራኤል አላዋቂነት እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ ህዝቡ እስራኤል ይህን ጥያቄ በድፍረት በማቅረብ ብቻ አልተወሰኑም፡፡
      ነብዩላሂ ሙሳ (ዐ.ሰ) አላህ (ሱ.ወ) በገባላቸው የማይታጠፍ ቃሉ መሰረት ተውራት ሊሰጣቸው ወደ ቀጠራቸው ስፍራ በሄዱላቸው ጊዜ ወርቆቻቸውን ሰብስበው በማቅለጥ የወይንነ ጣዖት ቀርፀው ማምለለክ ጀመሩ፡፡ ሀሩን (ዐ.ሰ) ይህንን የእስራኤል ልጆችን አመፀኛነት ተቃውመዋል፡፡ ነውረኛ ድርጊታቸውንም በፅኑ ኮንነዋል፡፡
ከወንድማቸው ነብዩላሂ ሙሳ (ዐ.ሰ) ጋር በአላህ (ሱ.ወ) በተመረጠው ቅን  የኢባዳ መሰረት በሆነው የአቂዳ ብቸኛ መንገድ መጓዝ እንደሚገባቸው በማስታወስም፡-
 ‹‹ሃሩንም ከዚህ በፊት በእርግጥ አላቸው፡-  «ሕዝቦቼ ሆይ! (ይህ) በእርሱ የተሞከራችሁበት ብቻ ነው፡፡ ጌታችሁም አልረሕማን ነው፡፡ ተከተሉኝም፡፡ ትዕዛዜንም ስሙ፡፡» (ጣሃ 9ዐ)በማለት ገስፀዋቸዋል፡፡ ነብዩላሂ (ዐ.ሰ) አላህ (ሱ.ወ) ያወረደላቸውን ተውራት ይዘው ሲመለሱ በህዝበ እስራኤል የወርቅ ጥጃ ጣዖት ቀርፀው ሲያመልኩ በመድረሳቸው በእጅጉ አዘኑ፡፡ በፊርዓውን ምድር በባርነት ሲሰቃዩ በነበረበት ዘመን እጅግ አዛኝና እጅግ ርህሩህ በሆነው አላህ የተደረገላቸውን ቸርነት መርሳታቸው በእጅጉ አስከፋው፡፡
      በምድረ በዳ መና ከሰማይ እያወረደ የመገባቸውን ማዕድ ሰፊውን አል ራህማንን ማምለክ ትተው በእጆቻቸው የቀረፁትን የወርቅ ጣዖት ማምለካቸው አበሳጫቸው፡፡ አል ራህማን ብቸኛ የአምልኮ ቅን መንገድ እንዲጓዙ በማስተማር ያሳለፉትን የዳዕዋ ዘመን ከንቱ በድረጋቸው ተቆጡ፡፡
      ሊገዙለት፣ሊታዘዙትና ሊያመልኩት የሚገባውን አንድ አላህ ብቻ መሆኑ በአላህ (ሱ.ወ) የአምልኮ ቅናት ልባቸው ተቃጠለ፡፡ ይህ ምንም ጥቅም የማያመጣ፣ ከቶም ጉዳት ሊፈጥር የማይችል፣ የማይናገር፣ ቢጠይቁትም መልስ የማይሰጥ ግዑዝና በድን ጣዖት ሊመለክ እንደማይገባ ደግመው ደጋግመው መከሩ፡፡
 ‹‹ጌታችሁ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ የኾነው አላህ ብቻ ነው፡፡ እውቀቱ ነገርን ሁሉ አዳረሰ፡፡›› (ጣሃ 98) 
ነብዩላሂ ኢሳ 
ነብዩላሂ ኢሳን (ዐ.ሰ) ሰዎች በተአምራታዊ አወላለዳቸው ከልክ በላይ በመደነቃቸው ከነብይነት ደረጃ አስበልጠዋቸዋል፡፡ የመወለድም ሆነ የመውለድ ባህሪያት ፈፅሞ የሌሉት አላህ (ሱ.ወ) እንደወለዳቸው በመተረት የአምላክ ልጅ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዚህም አልፈው አምላክ ናቸው በማለት ድንበር አልፈዋል፡፡
      እሳቸው ግን የአላህን (ሱ.ወ) ብቸኛ ፈጣሪነትና አምላክነት፣ ከእርሱ ውጭ ያሉ ማንኛውም ነገሮች ሁሉ ፍጡራንና ባሪያዎች መሆናቸውን የሚያመለክተውን የተውሂድን አስተምህሮ በእናታቸው ጀርባ ሳሉ ጀምረው በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ በዳዕዋ አካሄደውበታል፡፡
      ወገኖቻቸው የሆኑት አይሁዶች የእናታቸው መርየም  መፅነስና ከጋብቻ ውጭ መውለድ ህግጋቶቻቸው እንደተሻረባቸውና የዝርያ ሐረጋቸው እንደተዋረደባቸው ቆጥረውታል፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) ተዓምራት ማስተባበል፣ ነቢያትን ማንጓጠጥና ማዋረድ፣ የቻሉትንም ማሳደድና መግደል ልማዳቸው ነበርና እውነትኛና ንፁህነቱን መርየም አሽሟጥጠዋል ተሳድበዋል ተራግመዋል፡፡
      መርየም ለአይሁዶች በእቅፍ ውስጥ ያለው ሕፃን (ነብዩላሂ ኢሳ) እንደሚሰጣቸው ጠቆመቻቸው አይሁዶች ግን፡-
 ወደርሱም ጠቀሰች፡፡ «በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን!» አሉ፡፡ (ሕፃኑም) አለ «እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፡፡ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል፡፡» (መርየም 3ዐ)የዒሳ የነብይነት ተልዕኮ የመጀመሪያው ንግግር ሁለት የተውሂድ አንኳር ጉዳዮችን የያዘ ነበር፡፡
የመጀመሪያው ዒሳ (ዐ.ሰ) የአላህ ባሪያ መሆናቸውንና የአምላክ ልጅ እና አምላክ ናቸው በማለት ድንበር ያለፉት ስተተኞች መሆናቸውን የገለፁበት ነው፡፡
ሁለተኛው የተውሂድ ክፍልም ከእሳቸው በፊት እንደነበሩት ነቢያት ሁሉ ተውሂድን ለማስተማር የአላህ መልዕክተኛ ሆነው እንደሚላኩና መጽሐፍም እንደሚሰጣቸው የገለፁበት ነው፡፡ የእሳቸውን ክብር ያጐደፉት አይሁዶች ድርጊታቸው ትክክል እንዳልሆነ አሳወቁበት ነው፡፡ 
ማጠቃለያ 
አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ በጥመት መንገድ እንዲጓዝ አይፈቅድም፡፡ የሰው ልጅ ግን ዘውትር በእምቢተኛነቱ በመፅናት በግልፅ የአላህን መልዕክትና ትዕዛዝ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡ የተላኩለትን መልዕክተኞችም ከመስማት ቸል ብሏል፡፡ በመልዕክተኞቹም አፊዟል አንገሏቷቸዋል አሳድዷቸዋል፡፡
      እጅግ አዛኝና እጅግ ርህሩህ በመሆኑም በየዘመናቱ ለመልዕክተኞቹ መፃህፍት እየሰጠ የሰው ልጅ ከጥመት ጐዳና እንዲወጣና ሲፈጠር ጀምሮ የተዘጋጀለተን ኢስላማዊ የአቂዳ እምነት እንዲከተል ቸርነት ሲያደርግለት ቆይቋል፡፡
      የሰው ልጅ ግን በግልፅ ከሚፈፅመው በተጨማሪ እውነተኛውን የኢስላማዊ የአቂዳ እምነት መንገድ የተከተለ ማስመሰል በስውር ጥመትና ሽርክ፣ ስውር ባሀድ አምልኮና ጣዖት ተተብትቦ ይገኛል፡፡

‹‹አላህ ዘንድ (ተቀባይነት ያለው) ሃይማኖት ኢስላመ ብቻ ነው›› (አል ዒምራን 19)በዚህ የቁርአን አንቀጽ እውነተኛ የኢስላማዊ አቂዳ ተከታይ ይረጋጋል፡፡
 ‹‹ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)፡፡›› (አል ሹራ 13)ነብያችንም (ሰ.ዐ.ወ) ይህን አስመልክቶ በርካታ ሐዲሶችን ተነግረዋል፡፡ ሲመክርን፡-
‹‹የእኔን ሱና ያዙ፣ ከእኔ በኃላም የቅን ኸሊፋዎች (አል ኹለፋሁራሺዲን) ሱናም ያዙ፣ ተመሩበትም፣ በጥርሳችሁ ነክሳችሁ በደንብ ያዙት፤ አዳዲስ ፈጠራቻችን ተጠንቀቁ፡፡ አዳዲስ ለፈጠራዎች ሁሉ ቢድዓ ናቸው ቢድዓ ሁሉ ጥመት ነውና፡፡›› አቡዳውድ እንደዘገቡት