Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ፡- “አንዲት ሙስሊም ሴት ከሌላ ሙስሊማ ወይም ኪታቢያህ (የመፅሀፉ ተከታይ ከሆነች) ሴት ዘንድ ግልፅ ልታደርገው የሚፈቀድላት ከጌጧ እና ከአካሏ የቱ ነው?” ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ ረሒመሁላህ

Ibnu Munewor's photo.
ጥያቄ፡- “አንዲት ሙስሊም ሴት ከሌላ ሙስሊማ ወይም ኪታቢያህ (የመፅሀፉ ተከታይ ከሆነች) ሴት ዘንድ ግልፅ ልታደርገው የሚፈቀድላት ከጌጧ እና ከአካሏ የቱ ነው?”
መልስ፡- ይሄ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዳለ የሙስሊም ሴቶች ልጆች፣ እናቶችና ሚስቶቻቸው ከዚህ
እውነታ ከባድና አደገኛ የሆነ መዘናጋት ውስጥ ናቸውና፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰበቡ አንዳንድ የፊቅህ ሰዎች የወደቁበት የግንዛቤ ፈር መልቀቅ ነው፡፡ ይሄ ፈር መልቀቅ (በኪታቦች ላይ) ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ወደዚህ መዝሀብ የሚጠጉ ሰዎችም በይሁንታ ተቀብለውታል፡፡ በተለይ ደግሞ ይሄ መዝሀብ በአንድ ሀገር ላይ ወይም በነዋሪዎቹ ላይ የሞራል የበላይነት (ተቆጣጣሪነት) ሲኖረው (ችግሩ ይሰፋል፡፡) በብዙ የፊቅህ ኪታቦች ላይ “የሴት ሀፍረተ-ገላ ከሴት አንፃር ልክ የወንዱ ሀፍረተ-ገላ ከወንድ አንፃር እንዳለው ነው፣ ማለትም ከእንብርት እስከ ጉልበት” የሚል ይገኛል፡፡ ይሄ በርግጠኝነት ውድቅ ነው፡፡
ይሄ በመጀመሪያ ማስረጃ የሌለው አቋም ነው፣ በኪታብም በሱናም፡፡ በትክክለኛ ሱናም፣ በደካማ ሱናም፣ ኧረ እንዳውም መሰረተ-ቢስ በሆኑ ሱናም የሌለ ነው፡፡ እንዲሁ ባዶ እሳቤ (ረእይ) ብቻ ነው፡፡ ይሄ እሳቤ ደግሞ ውድቅ ነው፡፡ ለምን? የተከበረውን ቁርኣን ይፃረራልና፡፡ ሁላችንም እናነባለን፡፡ ግና በሚያሳዝን ሁኔታ አሸናፊና የላቀ በሆነው አላህ ማስገንዘቢያ መገንዘባችን፤ (ቁርኣንን አያስተነትኑምን? ወይስ ልቦቻቸው ቁልፎቿ አሉባትን?) በሚለው ትእዛዙ መታዘዛችን የቀለለ ነው፡፡
ለምሳሌ እኛ (ጌጣቸውንም ከርሷ ግልፅ ከሆነው በስተቀር አይግለጡ) የሚለውን የላቀውን እና ከፍ ያለውን (ጌታ) ንግግር እናነባለን፡፡ ይሄ ማመሳከሪያችን አይደለም፡፡ ማመሳከሪያችን (ጌጣቸውንም ለባሎቻቸው፤ ወይም ለአባቶቻቸው፤ አለያም ለባሎቻቸው አባቶች፤ አለያም ለወንዶች ልጆቻቸው፤ አለያም ለባሎቻቸው ወንዶች ልጆች፤ አለያም ለወንድሞቻቸው፤ አለያም ለወንድሞቻቸው ወንዶች ልጆች፤ አለያም ለእህቶቻቸው ወንዶች ልጆች፤ አለያም ለሴቶቻቸው … ካልሆነ በስተቀር አይግለጡ) የሚለው ነው፡፡ የዚችን አንቀፅ መልእክት ለመረዳት ማለትም አንዲት ሴት ከሌላ ሴት ዘንድ የሚኖራትን ሀፍረተ ገላ እንደምትገድብልን (ለማወቅ) የሆነን ሸሪዐዊ እውነታ ልናስታውስ የግድ ይለናል፡፡ እሱም (ሴት ሀፍረተ-ገላ ነች) የሚለው የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር ነው፡፡ የዚህ (አባባል) መልእክቱ ልቅ ነው፡፡ ሴት ሁለ ነገሯ ሀፍረተ ገላ ነው፡፡ ይህን ልቅ መርህ ከጌታችን መፅሀፍ ወይም ከነብያችን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሱናህ ካልሆነ በስተቀር ከራሳችን የመነጨ ገደብ ልናስገባበት አይገባም፡፡ “የአንዲት ሴት ሀፍረተ-ገላ ከሌላ ሴት ዘንድ ከእንብርት እስከ ጉልበት ነው” የሚል ግልፅ ማስረጃ አለን? መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም (ሴት ሀፍረተ ገላ ነች) ያሉ ከሆነ ከላይ ያሳለፍናት (ጌጣቸውንም ለባሎቻቸው ወይም ለአባቶቻቸው … ካልሆነ በስተቀር አይግለጡ) የምትለዋ አንቀፅ ይህን ግልፅ ታደርጋለች፡፡
ስለዚህ አንዲት ሴት ልጅ ከአባቷ ዘንድ ስትሆን ሀፍረተ-ገላዋ የቱ ነው? ከእንብርት እስከ ጉልበት ነውን? መልሱ፡ “ለዚህ መሰረት የለውም” የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን አንቀፁዋ ሀፍረተ ገላዋ ከዚህ በሰፋ እንደሆነ ታጠነክራለች፡፡ ይሄ ደግሞ (ጌጣቸውንም አይግለጡ) የሚለውን ስንረዳ ግልፅ ይሆናል፡፡ ጌጣቸው ሲባል የተፈለገው ምንድን ነው? የጌጥ ቦታዎች ማለት እንጂ እራሳቸው ጌጦቹ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ጌጦቹ የሚደረጉበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ዘንድ ጆሮ ላይ የሚደረገው ጉትቻ (የጆሮ ጌጥ)…፡፡ ስለዚህ የጌጥ ቦታዎች የቶቹ ናቸው? ከእንብርት በላይ ያለው (አካል) የጌጥ ቦታ የሆነበት ጊዜ አለ? እንዳው በጃሂሊያህ ዘመን እንኳን? መልሱ፡ የለም የሚል ነው፡፡
የብብት ስር የጌጥ ቦታ ነውን? ሽንጦች የጌጥ ቦታዎች ናቸውን? በጭራሽ!! እነዚህ (ሴት ሀፍረተ-ገላ ነች) በሚለው ሐዲሥ ግልፅ መልእክት መሰረት ከሀፍረተ-ገላ ናቸው፡፡
ስለዚህ “ለአንዲት ሙስሊማ ሴት የጌጥ ቦታዎች የሆኑትን እንጂ ግልፅ ልታደርግ አይፈቀድላትም” ትላለች ማለት ነው፣ አንቀፁዋ፡፡ የጌጥ ቦታዎች የሚባሉት ደግሞ እራስና ያካበበው፣ ጉትቻዎች የሚደረጉበት፣ የሀብል ቦታ የሆነው አንገት፣ የአንባር ቦታ የሆነው የእጅ አንጓ፣ የ“ዱምሉጅ” ቦታ የሆነው የእጅ ጡንቻ፣ የአልቦ ቦታ የሆኑት እግሮች ናቸው፡፡ ማለትም የውዱእ ቦታዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ የውዱእ ቦታዎች፡ አንዲት ሙስሊማ ሴት ከሙስሊማ እህቷ ፊት ግልፅ ልታደርግ የሚፈቀዱላት የጌጥ ቦታዎች ናቸው፡፡”
ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ ረሒመሁላህ፡፡ ዐረብኛውን በዚህ ሊንክ ገብተው ማገኘት ይችላሉ፡፡ http://www.alwaraqat.net/showthread.php…
ሼር ማድረገዎን አይርሱ፡፡