Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በሩ ከመዘጋቱ በፊት በጊዜ ይቶብቱ

አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በሩ ከመዘጋቱ በፊት በጊዜ ይቶብቱ
የሰው ልጅ ስህተተ-ብዙ ነው፡፡ አላህ ደግሞ ምህረተ-ሰፊ ነው፡፡ ሰው ሺህ ጊዜ ቢያጠፋ ከእያንዳንዱ ጥፋቱ በኋላ እውነተኛ ተውበት ከጠየቀ አላህ ይቅር ይለዋል፡፡ አላህ እንደ ሰው አይደለምና “ይህን ሁሉ ጊዜ ስታጠፋ አታፍርም? አሁንስ አበዛሃው!” አይልም፡፡ ከአላህስ መልካም ስሞች አንዱ “አተዋብ” አይደለምን? ተውበትን በእጅጉ የሚቀበል፡፡ ስለዚህ የተውበት በር እስካልተዘጋ ድረስ ይቅርታ የማግኘት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ሰፊ የተውበት እድል ሁሌ ክፍት ሆኖ ማንንም ያለ ገደብ የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ ቀይ የሚበራበት፣ ደወል የሚደወልበት ጊዜ አለና አውቆ መዘጋጀቱ ብልህነት ነው፡፡ የተውበት በር መቼ ነው የሚዘጋው?
1. በጣእረ-ሞት ጊዜ፡- አንድ ሰው ከወንጀል ባህር ውስጥ ሲዋኝ ቆይቶ ድንገት ከሞት አፋፍ ላይ ሲደርስ የጥፋቱ ግዝፈት፣ የመልካም ስራው ቅለት፣ የዚያኛው ዓለም ህይወት ከፊቱ ድቅን ሲልበት ባሳለፈው ይፀፀታል፡፡ ሌላ እድል ቢሰጠው ያስባል፡፡ አላህ ተውበቱን ቢቀበለው ይመኛል፡፡ ከንቱ ምኞት!!! እርግጥ ነው የአላህ እዝነት አላለቀም፣ አያልቅምና፡፡ ለዚህ ባሪያው የሰጠው የተውበት ጊዜ ግን አለቀ፡፡ ያ ረቢ ከእንዲህ አይነት ፀፀቱ ዘላለም ከማይጠፋ አስፈሪ ፍፃሜ አንተ ጠብቀን፡፡ ወንድም እህቶች! ሞት አማክሮ አይመጣም፡፡ ዘመኑ ሞት የበዛበት ዘመን ነው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ ዘወትር ካልፈተሽን ዘላለማዊ ፀፀት ላይ ላለመውደቃችን ምንም ዋስትና የለም፡፡
2. ሌላው የተውበት በር የሚዘጋበት ጊዜ ፀሀይ በመውጫዋ (በምእራብ) ስትወጣ ነው፡፡ የዚህን ጊዜ የአልማጮች ማልመጥ፣ የአሽሟጣጮች ማሽሟጠጥ፣ የሙናፊቆች መዋለል፣የከሃዲዎች መንቀባረር ከንቱነቱ ግልፅ የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ግን እስቲ አስቡት! ሰው አገር አማን ብሎ ከእንቅልፉ ሲነቃ ፍፁም እንግዳ ነገር ሲያገኝ፣ ከለመደው በተለየ ፀሀይን በምእራብ ስትወጣ ሲያይ ምን ይሰማዋል? በተለይም ክስተቱ ሌላ እጅግ አስፈሪ ክስተት (ቂያማ) እንደተቃረበ አመላካች መሆኑ የበለጠ አስደንጋጭ አያደርገውም? ላሐውለ ወላቁወተ ኢላ ቢላህ!!!
አንዳንድ “የተማሩ” መሀይሞች ግን “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል;” ይላሉ፡፡ ምነውሳ? ከተወለዱ ጀምሮ ፀሀይን በምስራቅ እንጂ በምእራብ ስትወጣ ስላላዩ፡፡ በተጨማሪም “ፀሀይ በምእራብ ወጥታ ታውቃለች” የሚል ታሪክ ካባት ካያቶቻቸው ስላልሰሙ፡፡ በቃ!!!
ስለሆነም ፀሀይን ያክል ግዙፍ ፍጡር የተለመደ “ተፍጥሮዋን” ለቃ በምእራብ ትወጣለች ማለት የማይመስል ወሬ ነው - እነኝህ “ምሁራኖች” ዘንድ፡፡ ይሄ ወሬ የመጣው ከፈረንጅ ቢሆን ኖሮ አይናቸውን ሳያሹ ይቀበሉ ነበር፡፡ በእንግሊዝኛም ያስተምሩን ነበር፡፡ ግን ወሬው የመጣው ከማን ነው? ከሙሐመዱልአሚን!! በስሜታቸው ከማይናገሩት ነብይ! ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም!!
ግን እኮ “ፀሀይን በምእራብ እንድትወጣ ያደርጋታል” የተባለው አላህ እንጂ ኦባማ ወይም ቡሽ አይደለም!!! ለአላህ የሚያቅተው ነገር አለ እንዴ? የፈለገውን ከማድረግ በሚያቅተው “አምላክ” የሚያምን ሰው የሚያምነው ጭንቅላቱ ውስጥ በጠረበው አቅመ-ቢስ ጣኦት እንጂ ሁሉን ቻይ በሆነው አሸናፊ ጌታ አይደለም!!! ያለበለዚያ አላህን በቅጡ አላወቀም፡፡ ቢያውቅማ እንዲህ ባላመነ ነበር፡፡ በደለኞች ከሚሉት፣ ከሚያምኑት፣ ከሚያስቡትም ሁሉ አላህ ጥራት ይገባው! ሲጀመር ፀሀይን እኛ በለመድነው መልኩ በምስራቅ እንድትወጣ ያደረጋት ማነው? ፀሀይን ካለመኖር ወደመኖር ያሸጋገራትስ ማነው? ባጠቃላይ ዓለምን ካልነበር ያስገኘው ማነውና?!!! አላህ እንዲህ ይላል፡- (… ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ እራሳቸው ፈጣሪዎች ናቸው? ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? ይልቅ እርግጠኞች ሆነው አያምኑም) አጡር፡ 35-36
ወደ ነገራችን እንመለስ፡፡ ተውበት! ተውበት! ተውበት!!!
አስፈሪው ጊዜ፤ ጣእምን ቆራጭ፣ አይቀሬው ሞት ከመምጣቱ በፊት ተውበትን እናብዛ፡፡ ከምናውቀውም ከማናውቀውም፣ ከትልቁም ከትንሹም፣ ከድብቁም ከስውሩም፣ ካለፈውም ከሚመጣውም ተውበት እናድርግ፡፡ (በላቸው፡- እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፤ አላህ ኃጢአቶችን በመላ ይምራልና፡እርሱ መሀሪውና አዛኙ ነውና)) አዙመር፡53