Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ከጌታቸው መንገድ ያወጣቸው ምን እንደሆነ ያውቃሉ



بسم الله الرحمن الرحيم
ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ከጌታቸው መንገድ ያወጣቸው ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
"عبادة القبور"
የሰው ልጆች የተፈጠሩለት ዋናው አላማ ጌታቸውን በብቸኝነት ማምለክ ሲሆን ይህ ይሳካ ዘንድም አሏህ መልእክተኞችን ልኳል መፃህፍትንም አውርዷል ጥሩና መጥፎን ለይተው የሚያውቁበትንም አቅል ሰጥቷቸዋል:: ከመፈጠራቸውና ደምና ስጋቸው ከመዋሀዱ በፊትምأَلَسْتُ بِرَبِّكُمْ قَالُوا بَلَى شَهِدْنَا أَنْ تَقُولُوا يَوْمَ الْقِيَامَةِ إِنَّا كُنَّا عَنْ هَذَا غَافِلِينَእያንዳንዷን ነፍስ -የሰው ልጆች ሁሉ አባት ከሆኑት ኣደም ጀርባ በማውጣት- (ጌታችሁ አይደለሁም እንዴ? ብሎ ጠይቆ፥ የሰው ልጆችም እንዴታ! ጌታችን ነህ እንጂ! ብለው በመለሱ ጊዜ፣ ይህን ያደረግኩት የቂያማ ቀን ጌታችንና አምልኮ የሚገባህ አንተ ብቻ መሆንህን አላወቅንም ነበር ወይም ደግሞ መጀመሪያ አባት እናቶቻችን ናቸው ያጋሩት እኛም የነሱ ተተኪዎች በመሆናችን ነው ባንተ ያጋራነውና እንዴት ትቀጣናልህ ብላችሁ እንዳትከራከሩ ነው) በማለት አሳውቋል በዚህ መሰረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችበሙሉ በጌታቸው ማንንም ምንም ሳያጋሩ እሱን ብቻ እያመለኩ ቆይተዋል:: ዐብዱሏህ ኢብኑ ዐባስ ረዲየሏሁ ዐንሁ እንደሚናገሩት ( በሰው ልጆች አባት ኣደምና በነቢዩ ኑሕ መሀል አስር ክፍለ-ዘመናት ነበሩ በነዚህ ዘመናት የነበሩ ሰዎችም ጌታቸውን በብቸኝት የሚገዙ ሰዎች ነበሩ) ዘመናት ሲያልፉና ዕውቀት እየቀነሰ ሲሄድ አላዋቂዎች በዘመኑ የነበሩ ደጋግ ሰዎች- እንደ እነ ወድ፣ ሱዋዕ፣ የዑቅና ነስር- ሲሞቱ ሸይጧን "እነሱን እያስታወሳችሁ ዒባዳ ላይ እንድትበረቱ መቃብራቸው ላይ ቤት (ቁባ) ስሩ አላቸው ተታለውም ገነቡ በጊዜው አላመለኳቸውም ግን በግዜው የነበሩ ሰዎች ሲያልቁና ትክክለኛው እውቀት ሲጠፋ ቀጣዩ ትውልድ ሸይጣን ያጠመደው ወጥመድ ላይ ወደቁ ለመጀመሪያ ግዜ በጌታቸው አጋሩ ምንም የማይጠቅሙና የማይጎዱ ፍጡራንን አመለኩ! በዚህም ምድር ላይ ለመጀመሪያ ግዜ የሰው ልጆች አምልኮ ላይ አድስን ነገር ፈጠሩ አሏህም የሰው ልጆችን ወደ ቀድሞው ቀና መንገድ ይጣሩ ዘንድ ነቢዩ ኑሕን ላከ ለ950 ዓመታትም ሰዎች አሏህን በብቸኝነት እንዲያመልኩ ጥሪ እያደረጉ ቆዩ ሰዎች በእውቀት ሳይሆን በስሜታቸው ነበርና የሚጓዙት ጥቂቶችም እንጂ አልተቀበሏቸውም!ከዛ ግዜ ጀምሮ እስከ ነቢያት መደምደሚያ ነቢዩ ሙሀመድ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ድረስ ሁሉም ነቢያት በዋነኝነት ይጣሩ የነበረው የሰው ልጆች አምልኮን ለአሏህ ብቻ እንድያደርጉ ነበር ከላይ እንደተገለጸው ለመጀመሪያ ግዜ የሰው ልጆች ከቀናው መንገድ እንዲወጡ ሰበብ የሆነው የቀብር አምልኮ ነው:: ለዚህም ነው ነቢያችን በዚህ ዙሪያ ብዙ የተናገሩት ቡኻሪይና ሙስሊም ከእናታችን ዓኡዒሻ ረዲየሏሁ አንሃ ባስተላለፉት ሀዲስ ( ኡሙ ሰለማ ረዲየሏሁ አንሃ ወደ ሀበሻ በተሰደደች ግዜ ያየቸውን ቤተክርስቲያንና ውስጡ ላይ የነበሩ ምስላምስሎችን ስትነግራቸው ነቢያችን የሚከተለውን መልስ ሰጧት፥ እነሱ እኮ ከመካከላቸው ደግ የሚባል ሰው ሲሞት መቃብሩ ላይ የአምልኮ ስፍራን ይገነባሉ ምስሎችንም ይሰቅላሉ እንዲህ አይነት ሰዎች አሏህ ዘንድ ከሰዎች ሁሉ መጥፎ የሚባሉ ናቸው" ብለዋል በሌላ ኢማም አህመድ አልሙስነድ በተሰኘው መጽሃፋቸው ከዐብዱሏህ ኢብኑ መስዑድ ባስተላለፉት ሀዲስ፥ ነቢያችን "በህይወት እያሉ ቂያማ የምትቆምባቸውና መቃብርን የአምልኮ ስፍራ የሚያደርጉ ሰዎች አሏህ ዘንድ መጥፎ ሰዎች ናቸው" ብለዋል በህይወተ -ዘመናቸው በዚህ መልኩ ከቀብር አምልኮ በማስጠንቀቅም አላበቁም ቡኻሪይና ሙስሊም ከእናታችን ዓኡዒሻ ረዲየሏሁ አንሃ ባስተላለፉት ሀዲስ " ነቢያችን ጣረ ሞት ላይ ሆነው ለብሰውት የነበረውን ኩታ ፊታቸው ላይ እያደረጉ ሲጨንቃቸውና ሲያፍናቸው ደግሞ ዞር እያደረጉት በዚህ - አስቸጋሪና ከባድ - ሁኔታ ላይ እያሉ፥ የአሏህ እርግማን አይሁድና ነሳራ ላይ ይውረድባቸው የነቢያቶችን ቀብር የአምልኮ ስድራ አደረጉ እያሉ ይናገሩ ነበር በዚህም ኡመታቸውን አይሁድና ነሳራ የሰሩትን ስራ ከመስራትና የሳቸውም ቀብር ላይተመሳሳይ ነገር ከመፈጸም እያስጠነቀቁ ነበር" ጣረ ሞት ላይ ከመድረሳቸው በፊት (ሊሞቱ 5 ቀናት ሲቀሯቸው) ደግሞ " ከናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች መቃብርን የአምልኮ ስፍራ ያደርጉ ነበር አዋጅ! መቃብሮችን የአምልኮ ስፍራ አታድርጉ እኔ ከዚህ ተግባር እከለክላችኋለሁ" ብለዋል::ይህን አደገኛ የሸይጣን ወጥመድ ኡመታቸውን በማስጠንቀቅ ብቻ ማብቃት አላስችል ብሏቸውም አዛኙ ነቢያችን ጌታቸውን እንዲህ ሲሉ ለምነውታል((اللهم لا تَجعَل قَبرِي وثَنا يُعبَدُ )) الحديث" አሏህ ሆይ፥ ቀብሬን የሚመለክ ጣዎት አታድርገው" ሀዲሱን ኢማሙ ማሊክ ሙወጠእ የተሰኛው ኪታባቸው ላይ ያሰፈሩት ሲሆን ሀዲሱ በስተመጨረሻም " የነቢያቶቻቸውን ቀብር የአምልኮ ስፍራ ያደረጉ ሰዎች ላይ የአሏህ ቁጣ ይበርታባቸው (የበረታ ነው) ይላል:: ይህም -እናታችን ዓኢሻም እንደተናገሩት- ኡመቱ ካሁን በፊት እንደነበሩ ህዝቦች የሳቸውንም ቀብር ሊያመልክ ይችላል የሚል ስጋት እንደነበራቸውና ከዚህም ለማስጠንቀቅ ብለው እንደሆነ ያስረዳል:: ይህንንም የበለጠ ግልጽ ከሚያደርጉ ሀዲሶች መካከል አንዱ ኢማም አቡ ዳዉድ አስሱነን በተሰኘው ኪታባቸው ከአቡ ሁረይራ ያስተላለፉትን ሀዲስ እናገኛለን፥ " ቤቶቻችሁን መቃብር አታድርጉ (ቁርኣን ቅሩበት ዝክር በሉበት ከፈርድ ውጪ ያሉ ሰላቶችን ስገዱበት) የኔን መቃብርም - ልክ እንደ መስጂድና የዒድ ሰላት መስገጃ ስፍራዎች - መሰብሰቢያና በየግዜው የሚጎበኝ ቦታ አታድርጉት እኔ ላይም ሰላት አውርዱ የምታወርዱት ሰላትም የትም ብትሆኑ ይደርሰኛል" ብለዋል ታድያ የሰው ልጆች ሁሉ ምርጥ የሆኑትን ነቢያችን ሙሀመድ ሰለሏሁዐለይሂ ወሰለምን ቀብር ማምለክም ይሁን እዛ እየሄዱ ዒባዳ ማድረግ ከተከለከለ ከሳቸው በታች ያሉ ሰዎችን መቃብር ማምለክ ወይም የተቀበሩ ሰዎችን ወደ አሏህ አዳርሱኝ ማለት ወይም ቀብራቸው ዘንድ በመሄድ ዱዓ ማድረግ እንዴት ይቻላል ይባላል?! ይህን ነቢያዊ ምክር የተረዱና የተቀበሉ ዉድ ሰሃቦቻቸውም የነቢያቸውን ትእዛዝ በማክበር ከሞቱ በኋላ ማናቸውም የሳቸው ቀብር አጠገብ በመሄድ ጌታቸውን አልተገዙም (ዒባዳ አላደረጉም) አይደለም ቀብሩን እራሱን ማምለክ! ከሰሃቦች በኋላ የነበሩ ታቢዒዮችም ሁኔታ ይሄው ነበር:: ከነሱም አንዱ የሆነው የፋጢመቱዝዘህራእ የልጅ ልጅ የሆነው ዐሊይ ኢብን አልሁሰይን አንድ ግለሰብ ከነቢዩ ቀብር አጠገብ የነበረች ጎርጓዳ ቦታ ላይ ሆኖ ዱዓ ስያደርግ አይቶት ከቦታው ዞር እንዲልና ከድርጊቱም እንዲታቀብ ነግሮታል በመቀጠልም አባቴ ከአያቴ አያቴ ደግሞ ከቀድሞ አያቴ -ከረሱል- ሰምቶ የነገረኝን ሀዲስ ልንገርህን? ኣሉና ከላይ የተጠቀሰውን <የኔን መቃብርም - ልክ እንደ መስጂድና የዒድ ሰላት መስገጃ ስፍራዎች - መሰብሰቢያ ቦታ አታድርጉት > ሀዲስ ተናግረዋል:: ይህም የሁሉም ደጋግ ቀደምቶች አቋምና እምነት ነበር ሱሀይል ኢብኑ አቢሱሀይል የሚባሉት ሰውም እንዲህ ይላሉ፥ አል ሀሰን ኢብኑል ሀሰን የነቢዩ ቀብር ዘንድ አይቶኝ ጠራኝና ምን እያደረግክ ነበር ሲል ጠየቀኝ እኔም ለነቢዩ ሰላምታ እያቀረብኩ ነው ስል መለስኩለት እሱም " መስጂዳቸው ስትገባ ሰላምታ ካቀረብክ ይበቃል (ቀብሩ ጋ መጠጋት የግድ አይደለም ) አለኝና <የኔን መቃብርም - ልክ እንደ መስጂድና የዒድ ሰላት መስገጃ ስፍራዎች - መሰብሰቢያና በየግዜው የሚጎበኝ ቦታ አታድርጉት > የሚለውን ሀዲስ አነበበልኝ ንግግሩንም እንዲህ በማለት አጠናቀቀ ( ነቢዩ ላይ ሰላትና ሰላም ለማውረድ እናንተም እስፔን ሀገር ያሉም ሰዎች እኩል ናችሁ) ኢስማዒል አልቃዲ ፈድሉ አሰላት ዐላ አንነቢይ በሚለው ኪታባቸው ዘግበውታል ነቢዩን ከማንም በላይ ይወዱ የነበሩት ሰሃቦች እንዲሁ ሶስቱ ምርጥ ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ ደጋግ ቀደምቶች ያላደረጉትን ነገር ዛሬ አዳዲስ መጤ ጎዳናዎችን የሚከተሉ የጥመት ጉሩፖች የቀብር አምልኮን ለማስፋፋት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያል ብዙውን ግዜ በዚህ ነገር የሚመረዙት ተሰዉፍ ያለባቸው ሰዎች ሲሆኑ ተራና አላዋቂው ማህበረ ሰብም ያለ ማስረጃ ዝም ብሎ ይከተላቸዋል የሸይጣን አምላኪ የሆኑ የዲናችን ጠላቶችም ኡማውን ከቁርኣንና ሀዲስ እንዲሁም ከደጋግ ቀደምቶች ፈለግ ለማውጣት ብዙ ሞክረው እምብዛም ሳይሳካላቸው ሲቀር የቀብር አምልኮን የማስፋፋቱን ስራ ሁነኛ አማራጭ አድርገውታል:: ሙስሊሞች በረሃብና በተለያዩ ችግሮች ሲሰቃዩ እንኳ ዞር ብለው የመይመለከቷቸው የኩፍር ሀገራት በሀገራችንና ሌሎችም የሙስሊሞች ሀገራት መካነ መቃብሮችን ለመገንባትና በየግዜው እንዲጎበኙ ለማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላርና ዩሮዎችን መለገስ ጀምረዋል!! ሰይዱል ኸልቅ ሙሀመድ صلى الله عليه وسلم " አይሁድና ነሳራን አሏህ ይርገማቸው የነቢያቶቻቸውን መካነ መቃብር የአምልኮ ስፍራ አደረጉ, ሰዎች ሆይ፥ ቀብሬን የአምልኮ ስፍራ አታድርጉ ወዘተ ብለው ሳለ የተረገሙና አሏህ የተቆጣባቸው ሰዎች መሆናቸውን ነቢያችን የነገሩን ሰዎችን ስራ (ቀብርን ማምለክ) ብዙ አላዋቂ ሙስሊሞች ዘንድ በሰፊው ተንሰራፍቶ እናገኘዋለን ለምሳሌም ኢራቅ ላይ የሁሰይን የሚሉትን ቀብር የሚያመልኩ ሲሆን እንደዚሁ ግብፅ ላይም በበኩላቸው ሁሰይን እዚህ ነው የተቀበረው በማለት የማንና የምን እንደሆነ የማይታወቅን ቀብር ያመልካሉ እዚሁ ግብፅም የዘይነብ ቀብር ነው ብለው የሚያመልኩትም አለ ሌሎችም ብዙ የሙስሊም ሀገራት ላይ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እናገኛለን:: ከሁሉም ይበልጥ በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ደግሞ የሰሃባዎችና የመላው ትክክለኛ ሙስሊም ጠላት የሆነችዋ ኢራን ሀገር ውስጥ ታላቁን ሰሃቢይ ዑመር ኢብኑል ኸጣብን የገደለው (አቡ ሉእሉኣ አልመጁሲይ)ን ቀብር ማምለካቸውና መካነ መቃብሩን እጅግ በጣም አሳምረው ገንብተው እላዩ ላይ "ጀግናው አባታችን" ብለው መጻፋቸው ነው!! አጂብ ዑመረል ፋሩቅን ገድሎ ነው ጀግና አባታቸው የሆነው?? ነገሩ እውነታቸውን ነው ዛሬ ከውጭ ስማቸውን ሙስሊም ለማስመሰል ቢሞ ክሩም የተደበቀው ጥላቻ በየግዜ እየተጋለጠ ነው ያወቀ ያውቃል! ድሮ በዑመር ዘመን በሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ መሪነት በቃዲሲያ ዘመቻ ሀገራቸው ፋሪስ የዛሬዋ ኢራን በሙስሊሞች እጅ ከገባችበት ግዜ ጀምሮ ብዙዎች ውስጣቸው ትልቅ ቅም አዝሏል ዑመርንም ያስገደሉት እነሱ ናቸው ዛሬም ሶሪያ፣ ኢራቅና የመን ላይ ሙስሊሙን እየጨፈጨፉና እያስጨፈጨፉም ያሉት እነሱው ናቸው:: ወደ ፊት ለማድረግ የሚያቅዱትም ከዚህ የከፋና ሌላ ነው! አሏህ ከሁሉም በፊት ቀድሞ ያጥፋቸው!ወደ ርእሴ ልመለስና፥ ሀገራችንም ላይ የተለያዩ ቀብሮች ሲመለኩ ይታያል ለምሳሌ ኦሮሚያ ላይ ሼኸ ሁሴን፣ ደቡብ ላይ አብሬትና አልከሶ፣ ትግራይ ላይ ነጃሺ ወዘተ ይገኛሉ ቀብርን ማምለክ ማለት ለቀብሩ መስገድ ማለት ብቻ አይደለም የትኛዉንም አይነት ዒባዳ ቀብር አካባቤ ሄዶ መፈጸምን የሚያካትት ነው:: ሰዎች ጥሩ ነው ብለው የሚገምቱትን ሰው ሁሉ መቃብር እያመለኩ ባለበት ዘመን የውዱን ነቢያችንን መቃብር ተጋልጦ ቢያገኙት ቦታው ላይ ስንት የሽርክ አይነቶች ሊከሰቱ ይችል እንደነበረ መገመት አያዳግትም! ኢብኑል ቀይም እንደሚሉት " አሏህ የነቢዩን ዱዓ ተቀበላቸው ቀብራቸውንም በሶስት ግንብ እንዲታጠርና እንዲጠበቅ አደረገላቸው" ባለንበት ዘመንም የሳቸው ቀብር ያለበት ሀገር ለተውሂድ የማይጨነቅ ሀገር ቢሆን ቀብሩና መስጂዳቸው ላይ የሽርክ አይነቶች ይታዩ ነበር ግን አሏህ ጀዛቸውን ይክፈላቸውና የሳውዲ መንግስትና ዑለሞች አንዳች እንኳ ከተውሂድ ጋር የሚጻረር ነገር እንዳይከሰት ሌት ተቀን ዘብ ይጠብቃሉ ሆኑም ግን አላዋቂና ሸይጧን የተጫወተባቸው ሰዎች ቦታዉ ላይ ወከባና ግርግር ለመፍጠ ብዙ ሙከራዎችን ያደርጋሉ ግና መቼም ሊሳካላቸው አይችልም! ኢን ሻአ አሏህ እዚህ ጋር ብዙ ግዜ የሚነሳ ጥያቄ አለ እሱም፥ ታዲያ ነቢዩ ቀብርን ማምለክ ከከለከሉ ለምን የሳቸው መስጂድ ውስጥ ቀብራቸው ይገኛል?! መልስ፥ በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ዙሪያ የተነገሩንን ግልጽ የሆኑ የነቢዩ ሀዲሶችን ትቶ እንዲህ አይነት ተልካሻ ምክንያቶችን መደርደር ከአንድ ሙእሚን አይጠበቅም ሆኑም መልሶችን ጠቀለል ባለ መልኩ ለማስቀመጥ 1ኛ: ሲጀምር መስጂዱ ቀብር ላይ አልተገነባም ቀብሩም መስጂድ ውስጥ አይደለም የተደረገው 2ኛ: መስጂዱና የነቢያችን ቀብር መያያዝ የጀመረው በሰሃቦች ዘመን ሳይሆን የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ላይ አልወሊድ ኢብኑ ዐብዲል መሊክ የነቢዩን መስጂድ እያሰፋ ሳለ የቀብሩ ተጋማሽ የነበረውን የእናታችን ዓኢሻን ክፍል ወደ መስጂዱ አስገባው በዚህም አሁን የተከሰተው ችግር ይከሰታል ብሎ አላሰበም ነበር ( ዑለሞች እንዳሉት) ከዛ ግዜ ጀምሮ መስጂዱ በሰፋ ቁጥር ቀብሩና መስጂዱ ይጠጋጉ ጀመር ሆኖም ግን ምስጋናና ውዳሴ ለአሏህ ይገባውና ቀብሩ ሙሉ በሙሉ መስጂድ ውስጥአይደለም ያለው የሱናና የተውሂድ ዘበኞች በተቻላቸው ያክል ወደ አንድ ጎን አድርገውታል ዙሪያውንም አጥረዉታል በተውሂድና በመሳሪያ የታጠቁ ወታደሮችን ቦታው ላይ አሰልፈዋል ሚመክሩ መሻይኾችንም ቦታው ላይ መድበዋል 3ኛ: ነቢዩ በሀዲሳቸው እንደተናገሩት "ነቢያት የሚቀበሩት የሞቱበት ቦታ ላይ ነው" 4ኛ: ከጉዳቱ አንጻር ቀብሩ ተነስቶ ሌላ ቦታ ይሂድ እንኳ ቢባል ከባድ ፊትና ይፈጠራል ከፊትና መራቅና ፊትናን ማብረድ ሽርክን ከመዋጋት የማይተናነስ ግዴታ ነው:: ወሏሁ አዕለም በመጨረሻም፦ የሰው ልጆችን ለመጀመሪያ ግዜ ከጌታቸው መንገድ ያወጣውን፣ ነቢዩ ሊሞቱ አምስት ቀናት ሲቀሯቸው በድጋሜ መልእክታቸውን ለማጠንከር "ቀብርን የአምልኮ ስፍራ እንዳታደርጉ" ጣረ ሞት ላይ ሆነው ደግሞ የሚያመልኩ ሰዎችን የረገሙበትን፣ የሰዎች ሁሉ መጥፎ ማለት ቂያማ በህይወት እያሉ የምትቆምባቸውና ቀብርን የሚያመልኩ ሰዎች ናቸው ያሉለትን የቀብር አምልኮ ተግባር ባለንበት ግዜ ከመቼውም በላይ መስፋፋቱና አንዳንድ ለዲን ይጨነቃሉ የሚባሉ ሰዎችም ይህን አደጋ አቅልለው መመልከታቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ሁላችንም አሏህ ከሽርክና ከመንገዶቹ ይጠብቀን
<አሕመድ ኣደም>ጁሙዓ፥ 7/6/1436ሂ