Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከስክሪን በስተጀርባ ካሰፈሰፉ ሰይጣናት ሁሉ "በአላህ እጠበቃለሁ"¹!


ከስክሪን በስተጀርባ ካሰፈሰፉ ሰይጣናት ሁሉ
"በአላህ እጠበቃለሁ"¹!
እህቴ ሆይ!
በቅድሚያ፤ ያለሽው በፈተናዎች ዘመን ስለሆነ የተጋረጠብሽን ለመወጣት ካንቺ ጥንቁቅነት፣ ቆራጥነትና በአላህ መመካት የመሳሰሉ ባህርያትን መላበስ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ልብ በይ።
ባለንበት ዘመን አንቺን ወደ መጥፎ ነገሮች የሚጎተጉቱ ወስዋሶች በርካታ ናቸው።
☞ በተለይም ነፍሲያ፣ የሰው ሰይጣናትና የጂን ሰይጣናት ተጠቃሾች ናቸው።
ነፍሲያ ማለት የየራሳችን ግላዊ ስሜት ሲሆን፤
የሰው ሰይጣናት ስንል ደግሞ እንደ እኛው ሰዎች የሆኑ፤ ግና በሩቅም በቅርብም ሆነው ወደ ክፉ ነገር የሚያነሳሱን፣ ወደ ስህተት የሚገፋፉንና ለወንጀል የሚያመቻቹን የጥፋት ጓዶች ናቸው።
ባህሪያቸው የሰይጣንን ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ የሰው ሰይጣናት ይባላሉ።
የጂን ሰይጣናት ደግሞ በተፈጥሮአቸው ከማይታዩት ከጂኖች/አጋንንቶች የሚመደቡ ሲሆን፤ በቁንጮአቸው ኢብሊስና ዝርዮቹ የሚመሩ ናቸው። እነኝህ ሰዎችን በስውር የሚጎተጉቱና ለወንጀል የሚዳርጉ ክፉ ፍጡሮች ናቸው።
☞ የሰው ሰይጣናዊነት አንዱ ባንዱ ላይ በሚያደርገው ክፉ እምነትና ተግባር የሚገለፅ በመሆኑ በብዙ ነገሮች ውስጥ ይገባል።
ለምሳሌ ያክል በዘመኑ የመገናኛ አውታር በኢንተርኔት በሰው ሰይጣኖች ገፋፊነት ብዙ ፈሳዶች ሲተገበሩ ይታያል ይሰማልም።
ሙስሊሟን ሴት ለማጥቃት እና ወደ ብልግና ለመሳብ ከስክሪን ጀርባ እንዳሰፈሰፉ መሽቶ የሚነጋባቸው ወስላቶች እዚህ ጋር ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያዩ ዘዴዎች ካንቺ ጋር ይፃፃፋሉ፣ ያወጋሉ። አንቺም ሂጃብሽ፣ ድብቅነትሽና ጥንቃቄሽ ትርጉም እንዲያጣ በሚያደርግ መልኩ በሱስ ትጠመጂና ወሬ ለጀመረ ሁሉ በርሽን ክፍት ታደርጊያለሽ።
የዚያኔ ቀድመው የተዘጋጁት መሰሪዎች የባጡን የቆጡን እየፈለፈሉልሽና እያስለፈለፉሽ ወደ ተንኮል መረባቸው ይከቱሻል። የትዳርም ይሁን ሌላ ወሬ ይዘው በምርቃና ያከንፉሻል፤ ላሰቡት ፀያፍ ምግባር ግብአት እስክትሆኚም በነገር ያዋኙሻል፤
ይህ ጉዳይ አንተን ወንድሜንም ይመለከተሃል ።
በእንደዚህ አይነቶቹ የሰው ሰይጣናት ተሸንግለህ እውነተኛ ማንነቷን በውል ከማታውቃት ሴት ጋር የቻት የወሬ ትጀምራለህ፤ ቀስ በቀስም ውሃ ውስጥ እንደገባ ጨው ትሟሟለህ።
ሀራምን የመራቅ ብቃትህ፣ ሃይልህና ትእግስትህ ሁሉ ይመናመናል።
እናስታውስ...
ነቢዩላህ ዩሱፍ (ዓለይሂሰላም) ባሪያ ሆነው ተሽጦ ነበር። እንደፈለገ በሚያዝዘውና በሚያደርገው ንጉስ ስር በቤተመንግስት ነዋሪም ነበር።
በወቅቱ ነቢዩ ዩሱፍ በንጉሱም ሆነ ንግስቲቱ የታዘዘውን ከመፈም ውጭ አማራጭ አልነበረውም።
አንድ ጊዜ በክፍሉ ውስጥ ብቻውን እያለ የንጉሱ ሚስት በጣም ተውባና ተቆነጃጅታ ዘው ብላ ገባች። በሮቹን ሁሉ ቆላለፈች። ለእርሱ ስትል ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀችም አበሰረችው። የምትፈልገውን እንዲያደርጋትም ሹክ አለችው።
ይህንን ታሪክ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ደ
ገለፀልን፦
{ وَرَاوَدَتْهُ الَّتِي هُوَ فِي بَيْتِهَا عَن نَّفْسِهِ وَغَلَّقَتِ الْأَبْوَابَ وَقَالَتْ هَيْتَ لَكَ ۚ قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ ۖ إِنَّهُ رَبِّي أَحْسَنَ مَثْوَايَ ۖ إِنَّهُ لَا يُفْلِحُ الظَّالِمُون َ}
[يوسف : 23]
« ያቺም እርሱ በቤትዋ የነበረባት ሴት፣ ከነፍሱ አባበለችው፤ ደጃፎችንም ዘጋች፤ ላንተ ተዘጋጅቼልሀለሁና ቶሎ ና አለች፤ "በአላህ እጠበቃለሁ" እርሱ (አሳዳሪዬ የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬንም ያሳመረልኝ ነውና (አልከዳውም)፤ እነሆ! በደለኞች አይድኑም፤ አላት።»
ዩሱፍ : 23
ነቢዩላሂ ዩሱፍ (ዓለይሂ ሰላም) ስሜቱን ከጫፍ የሚያደርሱ ነገሮች ቢያጋጥሙትም ራሱን አቅቦ፣ አሳዳሪ ንጉሱን ባለመክዳት፣ ፈጣሪ ጌታው አላህንም በመፍራት ይህን አጭር ምላሽ ሰጣት።
ምንም በንግስቲቷ ጥላ ስር ቢኖር፣ በሩን ቆላልፋበት ብታስገድደው፣ አማራጭ ማምለጫ ባይኖረውም ተስፋ አልቆረጠም፤ የጭንቅ ግዜ ደራሹ ወደሆነው አላህ ጥሪውን አቀረበ።
"قال معاذ الله"
«በአላህ እጠበቃለሁ አላት»
ዩሱፍ : 23
በልቡ ውስጥ ያለና እርግጠኛ እምነቱ ነበርና ጌታውም አላህ ጠበቀው ፤ ከፈተናም አዳነው።
የዚህ አይነቱ ወደ ፀያፍ ተግባር የሚደረግ ጥሪ ዛሬም በኢንተርኔት የቻት መስኮቶች በተደጋጋሚ እየተለፈፈ ነው። ነገር ግን ከወንዱም ከሴቷም የነብዩ ዩሱፍን አይነት አቋምና ምላሽ ማን ይስጥ 
«በአላህ እጠበቃለሁ!» የሚል!
ሁሌም ከአጉል ስሜት፣ ከሰውና ከጂን ሰይጣናት ለመጠበቅ የአላህ ፍራቻና ዱዓእ ሊለየን አይገባም።
ውድ እህቴ በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች ከሚደረጉብሽ ትንኮሳዎችና የተሳሳቱ ግብዣዎች ራስሽን ተከላከይማንነትሽን ጠብቂ! ክብርሽንም አታስደፍሪ! በአቋምሽ ላይም የፀናሽ ቆራጥ ሁኚ!
«በአላህ እጠበቃለሁ!» ማለት የሁልጊዜ ልማድሽ ይሁን!
አላህ ሆይ! እህቶቻችንን ከጥፋት ሁሉ ጠብቅልን! የሙስሊሙ ማህበረሰብ አለኝታና የቤተሰብ መሰረት ናቸውና ከሰውና ከጂን ሰይጣናት ሁሉ ሰውራቸው! ለትእዛዝህ ተገዢም አድርጋቸው!!
አሚን
ውዷ እህታችን፤ ይህ መልእክት ለጓደኞችሽ ይደርስ ዘንድ፤ «በአላህ እጠበቃለው» የሚለውን ድንቅ መርሆ በኮሜንት ላይ አስፍሪው።
_____________
ተንቢሃት፤ አማኝ ሴቶችን የተመለከቱ ህግጋት
www.fb.com/tenbihat
19/06/1436
09/04/2015