Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የዘመኑ ፌስቡክ እውነታ

የዘመኑ ፌስቡክ እውነታ

ማርክ ዙከርበርጝ (የፌስቡክ መስራች) ‹ ፌስ-ቡክ › በሚል ስም ይህን ድሕረ ገፅ ሲሰይም በትንሹም ቢሆን ልክ ነበር። ፌስ = ፊትቡክ = መፅሃፍ ። ሰዎች ትክክልኛ ፊታቸውን (ማንነታቸውን) ከሕብረተሰቡ የሚደብቁበት መፅሃፍ ነው ።

አይደለምን ?  እስኪ አላህ ያዘነለት ሲቀር ብዙሐኑ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዴት እንደሆነ እንመልከት..

      አንድ ወንድም እንዴት እንደሚደረግ እራሱ የማያውቀው ወይንም የማይተገብረውን ጙሱል (የዘር ፈሳሽ ከፈሰሰ በኋላ የሚደረግ ትጥበት) ለሌላው ኮፒ ፔስት አድርጎ ግድግዳው ላይ የሚለጥፈው በፌስቡክ ብቻ ነው ።

-       አንድ እሕት ለመጨረሻ ጊዜ መቼ እንደሰገደች የማታስታውሰውን ተሃጁድ (የሌሊት ሰላት) ከነጥቅሞቹ ፖስት የምታደርገው በፌስቡክ ብቻ ነው ።

-       እሕት የፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ.. ‹‹ ባዳ የሆናቹ ወንዶች የፌስቡክ ጓደኝነት ጥያቄ (friend request) እንዳትልኩልኝ! አልቀበላቹም! ›› ብላ ለጥፋ.. ግን ፖስቶቻቸውን የምትወድላቸው ወንዶች ጋር እራሷ የፌስቡክ ጓደኝነት ጥያቄ  ትልካለች።

-       ወንድም ፌስቡክ ግድግዳው ላይ.. ‹‹ በጊዜ ማግባት ያለው ፋይዳ…. ›› ብሎ እየፃፈ እሱ ግን ሃያ አምስት ዓመቱን ያለትዳር እያገባደደ ሚስት ፍልጋ እንኳን እግሩን ለማንሳት ሃሳብ የለውም ።

-       እሕት የፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ.. ‹‹ ሚስቶች ሆይ! የባላችንን ሐቅ እንጠብቅ ›› ብላ እየፃፈች እሷ ግን ባሏ ወደቤት ሲመጣ ከመቀመጫዋ ተነስታ እንኳ በፈገግታ አትቀበለውም ። ምክንያቱም እሷ ስልኳ ላይ በፌስቡክ ቢዚ ናትና ።

-       ወንድም እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዐት ፌስቡክ ላይ ስለ አቂዳ፣ ተውሒድና ሱና እየተከራከረ ያመሽና ሱብሂ ፈጅር ሰላት አዛን ሲል ሌላው  ለሰላት ወደ መስጂድ  ሲሄድ እሱ ግን እያንኮራፋ ነው ።

-       ወንድም ፌስቡክ ላይ ስህተት የሰራችውን ሙስሊም እሕቱን.. ‹‹ እሕቴ ሆይ እዚህ ጋር ተሳስተሻልና አስተካክዪው ››  ሲላት… ‹‹ አንድ ኪታብ እንኳን ሳትቀራ እኔን ልታርም ትሞክራለህን? ›› ትለዋለች ።

-       እሕት ፌስቡክ ላይ ስህተት የሰራውን ሙስሊም ..  ‹‹ ወንድሜ ሆይ እዚህ ጋር ተሳስተሃልና አስተካክለው ››  ስትለው ‹‹ የሰው አይብ ከምትፈልጊ በራስሽ አይብ ቢዚ አትሆኚም ?›› ይላታል ።

-       በፌስቡክ ብቻ አይደለምን… ‹‹ አንድ ኪታብ ቀርተህ ‘‘እዩኝ እዩኝ’’ ትላለህ ? ›› የሚባለው ግለሰብ እራሱ በተራው ‹‹ አንድ ኪታብ ቀርተህ ‘‘እዩኝ እዩኝ’’ ትላለህ? ›› ብሎ ለሌላው መልስ የሚሰጠው ? ታዲያ ማነው እውነትም አንድ ኪታብ ቀርቶ ‘‘እዩኝ እዩኝ’’ የሚለው? ። ላስቃቹ አልፈልግም ግን መለየት አያዳግትምን ?

-       በፌስቡክ ብቻ አይደለምን ባል.. ‹‹ ብዙ ፊትና ስላለ ሚስቴ ፌስቡክ መጠቀም የለባትም! ››  እያለ እራሱ ግን ከሌሎች ሴቶች ጋር የሚሟዘዘው ?

-       ሚስት… ‹‹ የቤት ውስጥ ሃላፊነቶች አሉብኝ ›› ብላ ለጥፋ  ፌስቡክ ላይ ግን እስከ እኩለ ሌሊት ከወንዶች ጋር ስትሟዘዝ ታመሻለች ።  ባሏ ግን ቀድሟት እንቅልፍ ከወሰደው ቆይቷል ።  ( ‘‘አስተኝታው….’’  ነው የሚባለው ? )

-       ወንድም የፌስቡክ ፎቶ አልበምሽ ውስጥ ገብቶ እስኪጠግብ ፎቶዎችሽን ካየና ካስፈልገውም ዳውንሎድ አድርጎ ካበቃ  በኋላ..  ‹‹ ፎቶሽን ፌስቡክ ላይ መለጠፍ ሃራም ነው!››   ብሎ የሚልክልሽ እዚሁ ፌስቡክ ላይ ብቻ ነው ። (እሱማ ልክ ነበር ፎቶሽን መለጠፍሽ ሃራም ነው! ግን እሱ…….   ወይ እሱ! )

-       እሕት ፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ.. ‹‹ በጣም እወደዋለው! እስኪ ማነው ገምቱ? ››  ብላ ለጥፋ ጓደኞቿ የባጥ የቆጡን ኮሜንት ላይ ‘‘እገሌን’’ .. ‘‘እገሌን’’ ብለው ጽፈው… ጽፈው እሷ ሶፋዋ ላይ ቁጭ ብላ እየሳቀች ካሾፈች በኋላ መጨረሻ ላይ.. ‹‹ አላህን ነው!››  ብላ የምትፅፈው በፌስቡክ ብቻ ነው ። እባክሽ እሕትዋ የሚጠቅም ነገር ለጓደኞችሽ ማስነበብ ባትችይ እንኳን ጊዜያቸውን አትግደይባቸው ! ።

-       ወንድም ፌስቡክ ላይ… ‹‹ ለዲኔ ስል አንገቴን ለመቆረጥ እሰጣለው! ›› ብሎ ይፅፋል ግን የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ተከትሎ ሱሪውን መቁረጥ አቅቶታል ። ( ግን አንገቱን ይሰጣል….. ግን ሱሪው አቅቶታል… ወይ ጉድ! )


-       እሕት ፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ.. ‹‹ ''ወሃቢዮች'' ቢድዐ ሐሰናን (ጥሩ ቢድዐን) አያውቁትም! ›› ብላ የምትለጥፈው እዚሁ ፌስቡክ ላይ ነው ።
እፈራለው….. ! ወደፊት ደግሞ ‹ ሽርክ ሐሰና› (ጥሩ ማጋራት)፤  ‹ዚና ሐሰና› (ጥሩ ዝሙት)  የሚል ያሰማን ይሁን?  ወዒያዙቢላህ

-       እሕት ፌስቡክ ግድግዳዋ ላይ ሱረቱል ሉቅማን አንቀፅ 6 ላይክ፣ ሼርና ኮሜንት ለማግኘት ፖስት ታደርጋለች እሷ ግን ስልኳን የሞላው የምታዳምጣቸው ሙዚቃዎችና ነሺዳዎች መንዙማዎች  ናቸው።

-       ወንድም ፌስቡክ ላይ ለጠየቀው ሁላ ፈትዋ ይሰጣል ልክ (ደሊል) ማስረጃ ሲጠየቅ ዌብሳይት (ድሕረ-ገፅ) ይልካል ። (አኺ! ፈታዋ ስትሰጥ ማስራጃህ ዌብሳይት ሊሆን አይችልም ። እርግጥ ነው ዌብሳይቱ ላይ ያሉት ነገሮች ማስረጃ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ግን አንተ ምን አስቸኮለህ?  ኢማሙ ማሊክ ረሒመሁላህ ፡- ‘‘መዲና ውስጥ ብቻ የሚገኙ ሰባ የሚደርሱ ዑለማዎች ተዝኪያ (ውዳሴን) ሳይሰጡኝ በፊት አንድም ፈትዋ ሰጥቼ አላውቅም ’’ ይላሉ ። )

-       አንዳንዱ ዲነኛ (ሃይማኖተኛ) የሚመስልበት አንድ አካውንት አለው አላህን የሚያምፅበት (ሴት የሚጀናጀንበት ፣ ብልግና የሚፅፍበት ፣ ዘፋኞችንና ኩፋሮችን የሚከተልበት ) ሌላ አካውንት አለው ።  (ኒፋቅ)

-       (የተሳሳት ማጠቃለያ ) እሕት ፌስቡኳ ላይ እንደው.. ‹‹ ሱናን እንከተላለን የሚሉ ወንዶች ሲያስጠሉ ..›› ብላ ፅፋ ስራ ቦታ ወይንም ትምሕርት ቤት ለሚያገኟት ካፊሮች ግን ድዷ እስኪታይ ትስቃለች ።

-       ወንድም ፌስቡክ ግድግዳው ላይ.. ‹‹ የዘንድሮ ሴቶች እፍረት የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም እንዴ? ›› ብሎ ይፅፍና እሱ ግን የሴቶችን ፕሮፋይል አንድ በአንድ እየተከታተል ስልክ ቁጥራቸውን ያደምዳል ።

-       ወንድም ወይንም እሕት ፌስቡክ ላይ ከፃፉት ነገር ስሕተት አይታቹ ልታርሟቸው ስትሞክሩ..  ‹‹ እባክህ ለክርክር ሰዐት የለኝም ሂድና ከስራ ፈት ጋር ተከራከር! ›› ብለው መልስ ይሰጧቿል ። ግን ኦንላይን ቁጭ ብለው.. ‘‘ዋው’’ ‘‘ማሻ አላህ’’ እያሉ የሰው ፎቶ ላይ ኮሜንት ሲሰጡ ትመለከቷቸዋላቹ ።

-       እሕት ፌስቡክ ላይ..  ‹‹የቤተሰቦቻችንን ሐቅ እንጠብቅ›› ብላ ወይንም ወንድም.. ‹‹እናቴ እወድሻለው›› ብሎ ይፅፋል ሆኖም ኢንተርኔት እየተጠቀመ በተመስጦ ዋሎ ሳለ ቤተሰቦቹ አንዳች ነገር ቢያዙት ቆሽቴው ያራል ።

-       ፌስቡክ ላይ አብዝታቹ ዳዕዋ ነክ ትምሕርት ስትፅፉ ሰዎች ብፁዕ የሆነ ኢማነኛ አድርገው ያስቧቿል ። ነገር ግን ምን አልባትም የምታውቁት ነገር የለም ይሆናል ። ግን ደግሞ በዛው ልክ .. ‹‹ የያዝከውን ዕውቀት አካፍለን እንጂ! ›› ብለው ይወተውቷቿል ።

-       ፌስቡክ ላይ ጠለቅ ያለ ክርክር ጠለቅ ባለ ርዕስ ላይ የሚደረግበት ገራሚ መድረክ ነው ቢባል አያስዋሽም። ግን የሚከራከሩት ሰው አንዳንዴ በንዴት ብሎክ ያደርጋቿል ። ይሀው ብሎክ ያደረጋቹ ሰው በሌላ ጊዜ በሌላ ቦታ የናንተን ዕርዳታ ሊጠይቃቹ ይችላል ።

አንድ ጓደኛዬ ያጋጠመውን ልንገራቹ ..
ከአንድ የቢድዐ አራማጅ ጋር ሰፋ ያለ ክርክር ያደርጋል ። በመጨረሻም የቢድዐ አራማጁ ለሚከራከሩበት ርዕሰ ጉዳይ ማስረጃ ማምጣት ሲያቅተው በንዴት ብሎክ (BLOCK) ያደርገዋል ። ጓደኛዬ የሰውየውን ማንነት በደንብ ያውቀዋል ምክንያቱም ፎቶውን ፌስቡክ ላይ ለጥፎ ነበርና ። ያ ግለሰብ ግን ጓደኛዬን አያውቀውም ። እናም ከስድስት ወር በኋላ ይሄው ግለሰብ ከሽማግሌዎች ጋር ሆኖ እሕቱን እንዲድሩለት የጓደኛዬ ቤተሰቦች ጋር ይመጣል ። ጓደኛዬም ፌስቡክ ላይ የተከሰተውን ነገር አስታወሰው ። ሰውየው አገጩ ሊወድቅ እስኪደርስ ደነገጠ ። አላበውም ። ጓደኛዬም በሩን እላዩ ላይ ዘጋበት
ፉዶይል ኢብኑ ዒያድ (ረሒመሁላህ) ፦ ‘‘ለቢድዐ አራማጅ ልጁን የዳረ ከሷ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጧል’’

እናም..
ፌስቡክ ብዙ አስመሳዮችን የያዘ #ፌክቡክ (የውሸት መፅሃፍ) ነው ። እራስህን የምታውቀው አንተው ብቻ ነህ ። ከእስክሪኑ (ከስልኩ፣ ከኮሚፒዩተሩ) ጀርባ ያለውን ሰው ማንነት አታውቅም ። ሁሉም በፌስቡክ ፅሁፉ ብቻ ቢመዘን እያንዳንዱ ኢማነኛ በሆነ ነበር ። ነገር ግን ከፌስቡክ ውጪ የምንሰራቸው ወንጀሎችን ሁላችንም እናውቀዋለን ።
ቅድሚያ ለአቂና ለተውሒድ ነው የሚገባው ።

ፌስቡክ እ.ኤ.አ በ2004 እ.ኤ.አ ፌስቡክ ከመመስረቱ በፊት  ሁላችንም ከፌስቡክ ውጪ ሕይወት ነበረን ።  እንዲሁም ወደ ፊትም ይኖርናል (ኢንሻ አላህ) ።   ሕይወታችን በዚህ ዌብሳይት ጥገኛ የሆነ ይመስል እራሳችንን በፌስቡክ አንገድበው ። ፌስቡክ ላይ ፖስት የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች በኋላ የፍርዱ ቀን (ቂያማ) ላይ የፃፉት ነገር የሚጠቅማቸው እንዳሉ ሁሉ በነሱም ላይ የሚመሰክርባቸው (የሚጎዳቸው አሉ) ። የምታስተምረውን ተግብረው! ። ዛሬ ላይ ላይክና ሼር ኮሜንት፤ የሰው አድናቆትና ዝናን ፈልጎበት ምንንም ነገር የሚለጥፍ የፍርዱ ቀን ጌታው ፊት ተዋራጅ ነው ። የሰው ወቀሳን ትችትን ሳይሆን አላህን ብቻ ፈርቶ፤ የርሱንም ውዴታ ብቻ ከጅሎ፤ ከእዩልኝ ስሙልኝ ርቆ ያወቃትን ነገር ለሰዎች ይጠቅማል ብሎ የሚያስተላልፍ ሰው ያን ቀን እራሱም ይጠቀማል ።

ስሕተታችን ላይ እርማት ሲሰጠን የሚያርመውን ሰው ማንነት ሳይሆን እርማቱን እንመልከት ። ሙስሊም አንዱ ለአንዱ መስታወት ነው።

ፌስቡክ ላይ ጊዜያችንን አንፍጅ  ። ገደብ ይኑረን ። ከፌስቡክ ተጠቃሚዎች በተሻለ ሰፈርህና አካባቢህ ላይ ያለው ሕዝብ ያንተ ዳዕዋ ያስፈልገዋል ። ለቤተሰብህ ጊዜ ስጥ ። ቅድሚያ ሕይወትህን አስተካክል። ታላቁ ዓሊም ኢብኑል ቀዪም ረሒመሁላህ፡- ‘‘ጊዜውን ለአላህ ሰጥቶ ያላሳለፈው ማንኛውም ሰው ለርሱ የሚሻለው ሞት ነው’’ ይላሉ ።

ይህ ከላይ የተፃፈው ፅሁፍ የሚያጠነጥነው ፀሓፊውን ጨምሮ ሁሉንም ለመምከር ነው።  ከላይ የሰፈረው ፅሁፍ ከሞላ ጎደል እኔ ተርጉሜ ያቀረብኩት ነው ። ማንም ሰው ከራሱ ጋር አገናኝቶት እኔን ለማለት ፈልጎ ነው የሚል ጥርጣሬ ሊያድርበት አይገባም ። ጥቅል የሆነን ዕይታ እንጂ ነጠላ ግለሰብን የሚነካ ፅሁፍ አይደለም ። ሰውን ልትወቅሰው ትችላለህ ፤ ልትመክረው ትችላለህ ፤ እንዲቀበል ልታስገድደው ግን አትችልምአንዳንድ ሰዎች ሐቅን መቀበል ለውጥ ስለሚያስፈልገው ብቻ ስሕተት ላይ መኖርን ይመርጣሉ ። ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም! ። ከነርሱ አትሁን/ኚ ።
አላህ ኢኽላስን ይስጠን

አሚን

Post a Comment

0 Comments