Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የኢኽዋን ምሽጎችን ማንኮታኮት (ተከታታይ፣ ክፍል-3) ሰይድ ቁጥብ ለማያውቀው


1. ሰይድ ቁጥብ የአላህን ከዐርሹ በላይ መሆን አይቀበልም፡፡ ኢስቲዋእን ልክ አሕባሾች እንደሚያደርጉት በጀህምያ፣ በሙዕተዚላህ እና በአሻዒራህ ተፍሲር ነው የፈሰረው፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 4/2328፣ 5/2807፣ 6/3480] ይመልከቱ፡፡ በዚህ ጉዳይ የአሕባሽን ጥመቶች ለማጋለጥ የምትታትሩ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! የኩፍር ቡላና ዳለቻ የለውም! የሰይድ ቁጥብን ጥመትም እንዲሁ አትርሱ፡፡ እንዳውም ከአሕባሽ በበለጠ ሰይድ ቁጥብ ብዙ ጭፍን ተከታዮችና ጭፍን ተከላካዮች አሉት፡፡
2. ሰይድ ቁጥብ አደገኛውን የ“ወሕደተልውጁድ” በተጨማሪም የጀህምያዎችን፣ የቀደሪያዎችንና የጀብሪያዎችን ዐቂዳ አስፍሯል፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 4/2249፣ 5/2719፣ 6/4002]
3. ሰይድ ቁጥብ በነብያትና በህዝቦቻቸው መካከል የነበረው ፍጭት ምክኒያቱ ምን እንደሆነ አያውቅም!! እንደሚታወቀው በነብያትና በህዝቦቻቸው መካከል ለነበረው ፍጭት ምክኒያቱ ተውሒዱልኡሉሂያህ እንጂ ተውሒዱሩቡቢያህ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ የመካ ሙሽሪኮች የአላህን ፈጣሪነትና ጌትነት በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ ችግራቸው እሱን ብቻ በብቸኝነት ለማምለክ ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው፡፡ ሰይድ ቁጥብ ግን ምን እንደሚል ተመልከቱ፡፡ “የኡሉሂያህ ጉዳይ የውዝግብ አጀንዳ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የሩቡቢያህ ጉዳይ ነው የውዝግብ አጀንዳ የነበረው፡፡ ተልእኮዎች (ሪሳላዎች) ሲጋፈጡት የነበረውም ይህ ነው፡፡ የመጨረሻው ተልእኮም (ሪሳላም) ይጋፈጠው የነበረው ይህ ነው፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 4/1846]
4. ሰይድ ቁጥብ የላኢላሀኢለላህን መልእክት እንኳን በሚገባ አያውቅም፡፡ ላኢላሀኢለላህ ማለት ከአላህ በስተቀር በሐቅ አምልኮት የሚገባው የለም ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ሰይድ ቁጥብ ግን ላኢላሀኢለላህ ማለት “በመፍጠርና በመምረጥ ተጋሪ የለውም” ማለት ነው” ይላል፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 5/2707] የአላህን ፈጣሪነትማ የመካ አጋሪዎችስ መቼ ካዱት? ይሄውና የቁርኣን ዘላለማዊ ምስክርነት!! “ከሰማይና ከምድር ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማነው? መስሚያዎችንና ማያዎችንስ የፈጠረስ ማን ነው? ከሙትም ሕያውን የሚያወጣ ከህያውም ሙትን የሚያወጣስ ማን ነው? ነገሩን ሁሉ የሚያስተናብርስ ማን ነው?” በላቸው፤ በእርግጥም “አላህ ነው” ይሉሃል፡፡ እናም “ታዲያ (እንደሚገባው) አትፈሩትም?” በላቸው፡፡ [ዩኑስ፡ 31]
5. ሰይድ ቁጥብ ኢማንን ወጥና የማይከፋፈል ነው ይላል፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 2/798] ይሄ አደገኛ የሆነ የሙርጂአና የኸዋሪጅ አቋም ነው፡፡
6. ሰይድ ቁጥብ እንደ ራፊዷ/ ሺዓ የነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች በቆሻሻ ቃላት ይወርፋቸዋል!!
ሶሐባው አቡ ሱፍያንን ረዲየላሁ ዐንሁ "የአቡ ሱፍያንን እስልምና “የከንፈርና የምላስ እስልምና እንጂ የልብ ኢማንና እውነቱን የማግኘት አይደለም፡፡ ኢስላም ወደዚህ ሰውየ ልብ አልሰረፀም፣ ከሰለመ በኋላም የሙስሊሞችን ሽንፈት ሲመኝ የነበረ ነው!!” በማለት በኒፋቅ ይወነጅለዋል፡፡ ይስተዋል!! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን የአቡ ሱፍያንን እስልምና ተቀብለውታል፡፡ አቡ ሱፍያን ሙስሊም ሆኖ ጂሃድ ሲዋጋ አንድ አይኑን እንዳጣ እና ነብዩም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ከፈለግክ ዱዐ ላድርግልህና አይን ይመለስልሃል፡፡ ከፈለግክ ደግሞ (ታገስና) ጀነት አለህ” ሲሉት “ጀነት ይሻለኛል” እንዳለ ኢብኑ ሐጀር ጠቅሰዋል፡፡ [አልኢሷባህ፡ 4066]
ሰይድ ቁጥብ የነብዩን ሶሐቦች ሙዓውያን እና ዐምር ኢብኑልዓስን በመዋሸት፣ በማጭበርበር፣ በማታለል፣ በኒፋቅ፣ በሙሰኝነት … ይወነጅላቸዋል፡፡ [ኩቱቡን ወሸኽሲያት፡ 242] ሙዓውያን ረዲየላሁ ዐንሁ ደግሞ ደጋግሞ በሚያስቀይሙ ቃላት ወርፎታል፡፡ አሁን በነዚህ አስቀያሚ ቃላት የተወነጀለው ሰይድ ቁጥብ ቢሆን ኖሮ ኢኽዋኖች ምን ይሉ ነበር? ለመሆኑ ከሶሐቦቹና ከሰይድ ቁጥብ ማነው የሚበልጠው? ዛሬም ተከታዮቹ ሰይድ ቁጥብ ተሳስቷል ከማለት ይልቅ ሶሐቦችን መወንጀል ነው የሚቀናቸው፡፡ ለሶሐቦች የማይሰጡትን ምክኒያት ለጠማማው ቁጥባቸው ይሰጣሉ፡፡ በኢኽዋኖች “አፍዝ አደንግዝ ድግምት” የተሰራብህ ወገኔ ሆይ! ንቃ!! እስከመቼ ለቡድናቸው በጭፍን በሚሟገቱ ሰዎች ትሸወዳለህ? ኢብኑ ሙባረክ፡ ከሙዓውያ እና ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ማን እንደሚበልጥ ቢጠየቁ “ወላሂ ሙዓውያ ከነብዩ ጋር ሆኖ ባፍንጫው የገባው አቧራ ከዑመር ሺህ ጊዜ ይበልጣል” ብለው ነው የመለሱት፡፡ ልብ በል! ከሙዓውያና ሶሐባን ከሚሳደበው ከጠማማው ሰይድ ቁጥብ ማን ይበልጣል አይደለም የተጠየቁት፡፡ ሌላም ጊዜ “ሙዓውያ እኛ ዘንድ ፈተና ነው፡፡ እሱን በመጥፎ ሲመለከት ያየነውን በሶሐቦች ጉዳይ አናምነውም” ብለዋል፡፡ ኢማሙ አሕመድ “ከሙዓውያና ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ማን ይበልጣል?” ሲባሉ፣ “ሙዓውያ ነው የሚበልጠው፡፡ የነብዩን ሶሐቦች ከማንም ጋር አናወዳድርም” ብለዋል፡፡ አንድ ሰው ኢማሙ አሕመድን “አንድ ሙዓውያን የሚያንቋሽሽ አጎት አለኝ” ቢላቸው “ከሱ ጋር አብረህ እንዳትበላ!” ብለውታል፡፡ ኢኽዋኖች ግን የሚፈልጉት በሶሐባ ክብር የሚረማመድ ሙጅሪማቸውን ሸሂድ እንድትልላቸው ነው፡፡
ሰይድ ቁጥብ ከዚህም ተሻግሮ በኑ ኡመያን በጅምላ በኒፋቅ ይወነጅላል፡፡ “በኑ ኡመያ በጥቅሉ ኢማን ከልባቸው አልሰረፀም፡፡ ኢስላም ለነሱ እንደ ጥቅማቸው ሲያሻቸው የሚለብሱት ሲፈልጉ የሚያወልቁት ካፖርት ማለት ነው፣ ስነ ምግባር፣ ዲን፣ ልቦና የማይገታቸው ሰዎች ናቸው…” ይላል፡፡ (አልዐዳላህ ፡172) ህሊና ያላችሁ አስተውሉ! ሰይድ ቁጥብ በዚህ መልኩ የሚገልፀው እናንተን ቢሆን ምን ትሉ ነበር? በነዚህ አስቀያሚ ቃላት የሚገልፀው የነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች ሲሆንስ? ላንድ ሙብተዲዕ ይሄ ሁሉ ሙግት ለምን? የነብዩን ሶሐቦች በማብጠልጠል የተካነው የኢኽዋኖቹ ቁጥብ የተከተለው የቆሻሾቹን የራፊዷዎች/የሺዓዎች መንገድ ነው፡፡ ሶሐባ የሚሳደብን ሰው በተመለከተ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የአላህ፣ የመላእክትና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን” ብለዋል፡፡ ኢማሙ ማሊክ፡- “የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች የሚሳደብ በኢስላም ውስጥ ምንም ድርሻ የለውም” ብለዋል፡፡ ኢማሙ አሕመድ፡“አንድ ሰው የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦችን በክፉ ሲያነሳ ካየህ ሙስሊምነቱን ተጠራጠረው” ብለዋል፡፡ አቡ ዙርዐህ፡-“አንድ ሰው ከአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦች የየትኛውንም ክብር ሲያጎድፍ ካየኸው እወቅ እሱ አፈንጋጭ ነው” ብለዋል፡፡
ሰይድ ቁጥብ ከዚህም አልፎ በጀነት የተመሰከረለትን፣ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን የዳሩለትን፣ “ሶስተኛ ቢኖረኝ እድረው ነበር” ያሉትን፣ ሶስተኛውን ፍትሃዊ ኸሊፋ ዐሥማን ኢብኑ ዐፋንንም ይወነጅላል፡፡ (የኡስማን ረዲየላሁ ዐንሁ የኺላፋ ዘመን በሶስቱ ኸሊፋዎች ዘመን ውስጥ የገባ ክፍተት እንጂ የእውነት የነገሰው እሱ ሳይሆን መርዋን ነው፤ ዑስማን በስልጣኑ ተከልሎ የሙስሊሙን ገንዘብ ያላግባብ የተጠቀመ፣ ለዘመዶቹ እያዳላ የነብዩን ወዳጆች ያራቀ፣ ኸሊፋ ሊሆን በማይገባው እድሜ ስልጣን ይዞ የመርዋን መጫወቻ የሆነ፣ አገዛዙ ከኢስላም ሩህ የራቀ ነበር፣ ከኡስማን ይልቅ የኡስማን ገዳዮች ለኢስላማዊ ሩሕ የቀረቡ ነበሩ፣ ኡስማን ላይ በተነሳው ፊትና የአቡ ዘር እጅ አለበት ይላል፡፡ (አልዐዳለቱልኢጅቲማዒያህ፡ 160-186)
አስተውሉ! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የዑሥማንን ገዳዮች ሙናፊቆች እንደሆኑ ቀድመው ተንብየዋል፡፡ የኢኽዋኖቹ ቁጥብ ሰይድ ግን እነዚህን ሙናፊቆች ከኡስማን በበለጠ ለኢስላማዊ ሩሕ የቀረቡ ነበሩ ይላል፡፡ ይስተዋል!! ሰይድ ቁጥብ የነብዩን ሶሐቦች ደጋግሞ ባስቀያሚ ቃላት መወረፉ ከራፊዷ ሺዓዎች ጋር የሚያመሳስለው ባህሪው ነው፡፡ ለዚህም ነው የራፊዷው የኢራን መንግስት በስሙ ቴምብር ያሰራለት፡፡ በርግጥ ሰውየው ከሺዐዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበረው፡፡
7. ሰይድ ቁጥብ ኡማውን በጅምላ የሚያከፍር ተክፊሪ፣ ኻሪጂ ነው፡፡ ምን እንደሚል አይተው ይፍረዱ፡፡ “እሄ የምንኖርበት ማህበረሰብ እራሱ ሙስሊም ማህበረሰብ አይደልም፡፡ ለዚያም ነው ኢስላማዊ ስርኣት ያልዘረጋው…” “በመጨረሻም ከነዚህ የጃሂሊያ ስብስብ ውሰጥ የሚካተቱት እነዚህ ሙስሊም እንደሆኑ የሚሞግቱት ህዝቦች ናቸው፡፡” (ፊ ዚላሊልቁርኣን፡ 3/1816፣ 4/2009-2010) “ጉዳዩ የማመንና የመክፈር ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች እንደሚሞግቱት ሙስሊሞች አይደሉም፣ የሚኖሩት የጃሂሊያ ህይወት ነው፣ ደዐዋችን የተነሳው እነኚህን ጃሂሊዮች ወደ ኢስላም ለመመለስ ነው-እንደ አዲስ ሙስሊም ለማድረግ” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 173) “የሙስሊሙ ኡማ ህልውና ከብዙ ከፍለ-ዘመናት በፊት ተቋርጧል፣ እንደ አዲስ መመለስ ይኖርብናል” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 6)፣ “ዛሬ ያለነው ኢስላም ሲነሳ ያጋጠመው ዓይነት ጃሂሊያ ውስጥ ነው ወይም ከዚያ የከፋ!” (መዓሊሙን ፊጦሪቅ፡ 21)፡፡ በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሙስሊሞችን እርድ መብላት ይቻላል ወይ” ተብሎ ሲጠየቅ“እንደ አህሉልኪታብ (አይሁድና ክርስቲያን) እርድ ቆጥራችሁ ብሉ” ብሎ ነው የመለሰው፡፡ (አታሪኹሲሪይ ሊጀማዐቲል ኢኽዋነል ሙስሊሚን፡ 80) ይሄ ሁሉ ጉድ ያለበትን ሰው እያንቆለጳጰሱ ነው ኢኽዋኖች ሌሎችን “ተክፊር” እያሉ የሚወነጅሉት፡፡ “የሌባ አይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ!”
8. ሰይድ ቁጥብ ጁሙዐ አይሰግድም ነበር!! ዐልይ ዐሽማዊ (የሰይድ ቁጥብ ቅርብ ሰው ነው) በአንድ ወቅት ከሰይድ ቁጥብ ጋር ያጋጠመውን እንዲህ ይገልፃል፡- “የጁሙዐ ወቅት ሲደርስ “ተወንማ እንነሳና እንስገድ” አልኩት፡፡ አስደንጋጭ ነበር! ለመጀመሪያ ጊዜ ሰይድ ቁጥብ ጁሙዐ እንደማይሰግድ አወቅኩኝ፡፡ “ኢስላማዊ ኺላፋ ከሌለ ጁሙዐ የለም፡፡ ያለ ኺላፋ ጁሙዐ የለም!” አለ፡፡ (አትተንዚሙ አስሲሪ፡ 112)
9. ሰይድ ቁጥብ ወደ ሶሻሊዝምና ኮሙኒዝም ሲጣራ!! “መንግስት ንብረቶችንና ሀብቶችን በሙሉ በመንጠቅ እንደገና እንደ አዲስ ሊያከፋፍል የግድ ይለዋል፡፡ እነዚህ ንብረቶች ኢስላም እውቅና በሚሰጠው መልኩ የተገኙ፣ በሚያፀድቃቸው መንገዶች የበለፀጉ ቢሆኑም እንኳን፡፡ ምክኒያቱም ከማህበረሰብ ላይ ጉዳትን ማስወገድ እና በዚህ ህብረተሰብ ላይ የሚጠበቁ ጉዳቶችን መከላከል ከግለሰብ መብቶች ይልቅ ተቀዳሚ ናቸውና፡፡” (መዕረከቱልኢስላም ወረእሰማሊያህ፡ 44)
10. ሰይድ ቁጥብ በርካታ የቁርኣን አያዎችን ለክብራቸው በማይገባ መልኩ በሙዚቃዊ አጣጣል ደጋግሞ ይገልፃቸዋል፡፡ ለዚህም በሙዚቃ ባለሙያ በሙዚቀኛ እንደታገዘ ያለምንም ሀፍረት ይገልፃል፡፡ (አተስዊሩልፈኒይ፡ 89)
11. ሰይድ ቁጥብ በዐቂዳ ጉዳይ ቁርኣን ብቻ እንጂ ሶሒሕ እንኳን ቢሆኑ ሙተዋቲር ያልሆኑ ሐዲሦችን አይቀበልም፡፡ [ፊዚላሊልቁርኣን፡ 6/2008] ልብ በሉ! ይሄ የሙዕተዚላ አቋም ነው፡፡
12. ሰይድ ቁጥብ ደግሞ ደጋግሞ ቁርኣንን “ሲሕር” /ድግምት/ ነው እያለ ይገልፃል!! (አተስዊሩልፈኒይ፡ 11፣ 17፣ 25) አዑዙ ቢላህ!!! ድግምት ነው ሲል ግን ማድነቁ ነው በሱ ቤት፡፡ አያችሁ ይህን የቋንቋ መርቀቅ፡፡ ድንቄም!! “ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” ይላል ያገሬ ሰው፡፡
13. ሰይድ ቁጥብ ነብያትን ሳይቀር ለክብራቸው በማይመጥን መልኩ በነገር ይወጋል፡፡ (አተስዊሩልፈኒይ፡ 200፣ …)
ኢኽዋኖች ሆይ! ይህ ነው ሰይዳችሁ! ይሄ ነው ቁጥባችሁ!!!

(ኢንሻአላህ ክፍል 4 ይቀጥላል)

 የኢኽዋን ምሽጎችን ማንኮታኮት (ተከታታይ፣ ክፍል-1)
የኢኽዋን ምሽጎችን ማንኮታኮት (ተከታታይ፣ ክፍል-2)