Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

‹‹የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለም›› ለወንድም ‹‹ሃምሳ ሃምሳ›› የተሰጠ ምላሽ


‹‹የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለም››

ለወንድም ‹‹ሃምሳ ሃምሳ›› የተሰጠ ምላሽ
የተፈጠርንለት ዓላማ የሆነው ‹‹ ተውሒድ ይቅደም ›› መባሉ ምነው ቅር አሰኘህ?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
መግቢያ
=====
ወደዋናው ሃሳብ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት አንድ አስፈላጊ አሳሳቢና በየትኛውም አጋጣሚና ሁነት የሕይወታችን መርሕ የሆነውን ነገር ማወቅ ይገባናል ። ይህም አላህ ወደዚች ምድር ሲያመጣን ለሌላ ለምንም (እደግመዋለው ለምንም ) ጉዳይ ሳይሆን እሱን በብቸኝነት (በተውሒድ) እንድንገዛው ነው (ቁርአን 51:56)። ይህንንም ወሳኝ መልዕክት ለሰዎች ያደርሱ ዘንድ ነቢያትንም ልኳል (ቁርአን 16:36) ። ነቢያትም አላህ ባዘዛቸው መልኩ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተው ይህን ተውሒድ ለሕዝቦቻቸው አስተምረዋል ። ለዚህም የሰው ልጆች አለቃ የሆኑት አሽረፈል ኸልቅ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ህዝቦቻቸውን ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተው አስተምረዋል ። እኛም የርሳቸውን ፈለግ እንከተል ዘንድ አብክረው ነግረውናል ።

ጁንዱብ ኢብኑ ጁንዳ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላል ፡-

‹‹ ገና ወጣቶች በነበርንበት ጊዜ ከረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጋር ሆነን ከቁርዓን በፊት እምነትን (ተውሒድን) እንማር ነበር ። ከዚያም ቁርዓንን እንማራለን እሱም ኢማናችንን ይጨምርልን ነበር››

(ኢብኑ ማጃሕ ዘግበውታል አልባኒ ሰሒሕ ብለውታል) ዛሬ ላይ ግን ይህን መርሆ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚጣረሱ ሰዎች ከኩፋሮችም ከሙስሊሞችም ይገኛሉ ። ይሄ አዲስ ክስተት አይደለም ። በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጊዜም ቢሆን በታሪክ አላህ በብቸኝነት ተመላኪ ይሆን ዘንድ የሚታገሉ ሰዎች ብሎም ለዚህ ሰማይና ምድር ለቆሙበት ዓላማ ቅድሚያ ይሰጥ የሚሉ ወገኖች ስም ይሰጣቸዋል ፣ ይዋሽባቸዋል ፣ ሕዝብ ዘንድ ይሄው የሩሱሎችን ዳዕዋ እንዳያደርሱ ጥሪያቸውን ጥላሸት ይቀቡባቸዋል ።

የቶውፊቅ አሳኢግን ከሳውዲ መባረር አስታከህ እንዲህ ስትል ፅፈሃል ‹‹በእኛም ሀገር ቅድሚያ ለተውሂድ የሚለው አባባል ለተውሂድ በመቆርቆር ሳይሆን የዚሁ የሳውዲ ባለስልጣናት ኤክስፖርት ያደረጉትን ፌክ አስልምናን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የማራገብ ሂደት ነው።››

• እንደው አላህን አትፈራም፤ አታፍረውምም፡፡ ቅድሚያ ለተውሂድ ምን ያድርግህ ወንድም?
በአገራችን የነጃሺ፣ የአሊ ጎንደር፣ የቡሬው ሸህ ቀብር ይመለካል፤ የቦረናውም እንዲሁ፡፡ እንዲያውም ‹‹የቦረናው ደግዬ እርዱኝ አባብዬ›› ይሉታል፤ አዲስ አበባ ላይ ሸይህ ሀሰን በቱል ቀብሩ ይመለካል፤ የኑር ሁሴን ቀብር ይጠወፋል፤ የቀብር አፈሩ ይበላል ተበጥብጦ ይጠጣል፤ ጎጃም ላይ ለውሻ ይታረዳል በአመት በአመት፤ አብሬት ላይ ስንት ሽርክ አለ፤ ቃጥባሬ ላይ ለቀብር ይሰገዳል፤ ስንት ድግምተኛ እና ጠንቋይ በየመንደሩ ተቀምጧል፤ መውሊድ እየተባለ ስንት የሽርክ ስንኞች ሰዎች ሲሉ ይውላሉ፤ እና ሌሎችም፡፡
ሱብሃነላህ! ታድያ አንተ ይህ ሁሉ ሽርክ እና ቢድዓ የሞላበት አገር ላይ ሆነህ ሽርኩን የሚያስፋፉትን፤ የሽርክ መንዙማ ባዮችን የሚያስተዋውቁት ሚድያዎችን፤ ቢድዓውን የሚያሰራጩትን፣ ድራማ፣ ፊልም፣ ቀልድ እያሉ የኡማውን ልብ የሚያደርቁትን ትተህ ‹‹ቅድሚያ ለተውሂድ›› ይሰጥ የሚሉ ወንድም እና እህቶችን መተቸት ቀናህ? ለምን?? ምንን በምን መሸፈን ነው የፈለግከው?

‹‹በሳውዲ እና በኤሜሬትስ ውስጥ የስልጣናቸውን እድሜ የሚያራዝምና ባለስልጣናቱ ያዘጋጁትን ፎርጅድ እስልምናን የሚያራግብ ካልሆነ በስተቀር እንዲሁም በባለስልጣናቱ ፍላጎት ላይ ብቻ በመመስረት ፈትዋ የሚሰጥ ዓሊም እስካልሆነ ድረስ ቦታ የለውም›› ብለሃል፡
• አንተ እና መሰሎችህ ለምን ስለነዚህ ባለስልጣናት ቀን ከሌት ታወራላችሁ? ስልጣኑን ትፈልጉታላችሁ?
ኢስላም የሙስሊም መሪዎችን አስመልክቶ ምን ነበር ያለን? አስምርበት “ሙስሊም መሪ” ነው ያልኩህ፡፡ ‹‹አረመኔ፤ ጨቃኝ›› እና የመሳሰለውን ስምም ብትሰጣቸው አያከፍራቸውም፡፡ እስካልከፈሩ ድረስ መሬዎች ምን መብት እንዳላቸው ነው ኢስላም ያስተማረው?
‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህ ታዘዙ መልክተኛውን ታዘዙ፤ ከናንተ ውስጥ መሪ ተደርጎ የተሾመባችሁንም›› ያለው አላህ አይደለምነን?
ምናልባት ‹‹እነዚህ መሬዎች እኮ ጨቋኝ፤ መብተት የሚነጥቁ .... ናቸው ›› ትል ይሆናል፡፡ ታድያ እንዲህ አይነት መሪዎችን አስመልክተው ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ምን አሉ?

1) ሰሃባዎች ‹‹ሃቃቸውን የሚጠይቁን ሃቃችንን ግን የሚከለክሉን መሪዎች ካገኙን ምን እናድርግ›› ብለው ነብዩን ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጠየቁ፡፡ እሳቸውም ‹‹ስሙ ታዘዙ!! በነሱ ላይ የተጣለባቸው ሀላፍትና አለ፡፡ በናንተም ላይ የተጣለባችሁ አለ›› አሉ፡፡ ሙስሊም ዘግበውታል
2) ‹‹አዋጅ! በሱ ላይ መሪ የተሾመበት ሰው፤ መሪው በአላህ ላይ ሲያምፅ ካየው ያየውን ነገር ይጥላ፡፡ ለአሚሩ ያለውን ታዛዥነት ግን እንዳያነሳ›› ሙስሊም ዘግበውታል
3) ‹‹ሙስሊም የሆነ ሰው መሪውን ቢወደውም ቢጠላውም መታዘዝ አለበት፡፡ በወንጀል እስካላዘዘው ድረስ፡፡›› ቡኻሪ እና ሙስሊም
4) እንጋደላቸው ወይ ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ሰላትን እስካቋቋሙ ድረስ›› ብለው ነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የመለሱበት አለ፡፡

ተውፊቅ አሳኢግ መሪዎችን ኹጥባ ላይ ሆነ በህዝብ ፊት መቃወሙ መንገድን የሳተ አካሄድ ነው፡፡ ኢስላም ሙስሊም መሪ ጥፋት ሲያጠፋ በአደባባይ ማጋለጥ እና መቃወምን ነው ያስተማረው? በፍፁም! ‹‹መሪ ሲያጠፋ ለብቻው ነው የሚመከረው››፡፡

ኢያድ ኢብን ጉኑም እንደዘገቡት ረሱል ሰለላሁአለይሂወሰለም እንዲህ ብለዋል:- ‹‹ ማንም ሰው ሙስሊም መሪውን መምከርና መገሰፅ ከፈለገ በአደባባይ ማድረግ የለበትም እንግዲያውስ ቀረብ ብሎ መሪውን እጁን ይዞ (በፅሁፍም ሆኑ በሌላ ማግኛ ዘዴዎች) ምክሩን ይለግሰው። ምክሩን ተቀብሎት እንደሆን አላማውን አሳክትዋል ካልተቀበለውም በመምከሩ ግዴታውን ተወጥትዋል ›› [አሕመድ ዘግበውታል አልባኒ ሰሒሕ ብለውታል]

- የሸይኽ ኡሰይሚን (ረሒመሁላህ) ደረሳ እንደነበር ጠቅሰሃል
ሸኽ ዑሰይሚን ረሒመሁላህ ይህን የቁርዓን አያን (4:59) ሲፈስሩ ምን ነበር ያሉት ?

‹‹ ምንም እንኳን መሪው ይሄንና ይሄን ቢጣረስም ፤ ወንጀሉ በራሱ ላይ ነው ፤ ነገር ግን እናንተ እሱን መስማትና መታዘዝን ታዛቿል ። ምንም እንኳን መጠጥ ቢጠጣም ወይንም ሌላም ። ከአላህ ወሳኝ ሆኖ የመጣ የሆነን ግልፅ የሆነን ኩፍር (ክሕደት) እስካላየንበት ድረስ ። እስከዚያው ግን እሱን መታዘዝ ግዴታ ነው። ምንም እንኳን እኩይ ሰሪ ቢሆንም ምንም እንኳን ባለጌም ጨቋኝም ቢሆን ›› (ካሉ በኋላ ከላይ የተጠቀሱትን አሐዲሶች ጠቀሱ) [ ምንጭ ሸርሑ ሪያዱ ሳሊሂን ሊሸኽ ዑሰይሚን (ረሒመሁላህ) (3/231-233) ]

ምናልባት ‹‹ታላቁ ጀሀድ በአምባገነን መሪ ፊት ሀቅን መናገር ነው›› የሚለውን ሐዲስ ታነሳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሀዲሱ ‹‹በአምባገነን መሪ ፊት›› እንጂ ያለው በየኹጥባው፣ በየሚድያው ፣ በአደባባይ ህዝብን ማነሳሳት ወይም ቂም እንዲይዙ ማድረግ አይልም፡፡

እንዲህም ብለሀል ‹‹በሌሎች ሀገሮች ያሉ ሙስሊም ህዝቦች በእስልምና ተጠናክረው ኢስላማዊ ፓርቲዎችን ከመረጡና ውጤት ካመጡ በእኛም ሀገር ላይ የህዝብ ጥያቄ ያስነሳብናል በሚልና ለስልጣናቸው በመስጋት››

ስሙን ለመጥራት ድፍረቱን አላገኘህም እንጂ የምታወራው ግልፅ እና ግልፅ ነው (ለገባው) ። አዎን ‹‹ኢስላማዊ›› ፓርቲ ብለክ ብትሸፋፍነውም ፓርቲ የምትለው ‹‹ ኢኽዋንን›› ነው ። ወይንም የሱ ቅርንጫፍ ልጆች ይሆኑት ሌሎችን በኢስላም ስም የሚነግዱ ‹‹ፓርቲ›› ተብዬዎች ነው፡፡ እስኪ ለመሆኑ ‹‹ኢስላማዊ ፓርቲ ነኝ›› ብሎ የተነሳውን ‹‹ኢኽዋነል ሙስሊሙን›› አስመልክቶ ኡለማዎች ምን አሉ፤ ኢኽዋኖችስ በተግባር ምን ሰሩ?

• የዘመናችን ታላቁ ሙሐዲሥ ሸይኽ አልባኒ ረሒመሁላህ ምን እንዳሉ ተመልከት፡፡

‹‹ኢኽዋነል ሙስሊሚንን ከአህሉ ሱና መቁጠር ትክክል አይደለም ምክንያቱም፤ ሱናን ይዋጋሉና› ‹‹ኢኽዋኖች በዳእዋ ላይ ትኩረት አይሰጡም፤ (ተስፊያ) ኢስላምን ከሰርጎ ገብ ነገሮች ማጥራት እና በንፁህ ላይ መኮትኮት ላይም ትኩረት አይሰጡም፡፡ ጭንቀታቸው ፖለቲካ፤ መቀመጫዎች፤ ምርጫ፤ ፓርላማ እና የመሳሰሉት ናቸው››
ሙሃመድ ሙርሲ ኢኽዋኒ እንዲህ ይላል ‹‹በመሰረቱ በግብፃዊያን መካከል የአቂዳ (የእምነት) ልዩነት የለም፡፡ ሁሉም ግብፃዊያን፤ የአቂዳ ልዩነት የለም፡፡ ግብፃዊያን ወይ ሙስሊም ወይ መሲህይን (ነሷራ ክርስትያን) ናቸው፡፡ በኢስላማዊ እና በመሲህይ(በነሷራ) አቂዳ መካከል ልዩነት የለም ሁሉም የፈለገውን ይመን ልዩነት የለም››፡፡ ይህ ነው ኢስላማዊው የኢኽዋን ፓርቲ እና መንግስት?

ሙስሊም የሆነ ህፃን ልጅ ሱረቱ ኢኽላስን ጠንቅቆ ያውቃታል፡፡ ከነሷራዎች ጋር ያለንም ልዩነት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሙስሊሞች አላህ አልወለደም አልተወለደም ሲሉ ነሷራዎች ኢሳ የአላህ ልጅ ነው ይላሉ፡፡ ታድያ ይሄ ብቻ አይበቃም የኢኽዋኖችን ተንኮል ለመረዳት ወይንም አላዋቂነታቸውን ለመረዳት??? ስለ አላህ ጠንቅቀው ሳያውቁ ህዝብን ይመራሉ ተብሎ ይገመታል??? ሰውን በኢስላም ስም ቢያታሉት አላህን ማታለል አልቻሉም አላህም አዋረዳቸው፡፡
قُلْ هُوَ ٱللَّهُ أَحَدٌ በል «እርሱ አላህ አንድ ነው፡፡
ٱللَّهُ ٱلصَّمَدُ «አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው፡፡
لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ «አልወለደም፤ አልተወለደምም፡፡
وَلَمْ يَكُن لَّهُۥ كُفُوًا أَحَدٌۢ «ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፡፡»
ነሳራዎች ካፊር ለመሆናቸውማ የነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ነብይነት ብቻ አለመቀበላቸው ይበቃል፡፡ የሁዳም ነሳራም አላህ አክፍሯቸዋል ነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) አይቀበሉምና፡፡
لَّقَدْ كَفَرَ ٱلَّذِينَ قَالُوٓا۟ إِنَّ ٱللَّهَ ثَالِثُ ثَلَٰثَةٍ ۘ وَمَا مِنْ إِلَٰهٍ إِلَّآ إِلَٰهٌ وَٰحِدٌ ۚ وَإِن لَّمْ يَنتَهُوا۟ عَمَّا يَقُولُونَ لَيَمَسَّنَّ ٱلَّذِينَ كَفَرُوا۟ مِنْهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ
እነዚያ «አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፡፡ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡

ሸይኽ ተውፊቅ አሳኢግ ይህንን የሙርሲ ስራ ተቃውመው ነበርን? ሙርሲ ‹‹የአላህ (ጥራት ይገባው) ልጅ (ኢሳ) የተወለደበት›› ቀን ነው የሚሉበት በዓል ላይ ግብፅ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ተገኝቶ ለቄሱ እጅ ነስቶ ወጥቷል፡፡ ሸይኽ ተውፊቅ ይህንንስ ተቃውመው ነበር? እየመረጡ መቃወም፣ እየመረጡ ማለፍስ ምንድን ነው የሚያሳየው?
አሁንም ሙርሲ ግብፅ ውስጥ ያለ ቄስ ሲሞት ‹‹አላህን እንለምንለታለን… አላህ ይዘንለት ባባን›› ብሎ በሚድያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ አላህ ግን ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምን) እንኳን ለአጎታቸው አቡ ጣሊብ ምህረት እንዳይጠይቁ ከልክሏቸዋል፡፡ ምክንያቱም በኩፍር ላይ ስለሞተ፡፡ ታድያ እነ ሙርሲ ‹‹ኢስላማዊ›› የሚሉት ምኑን ነው? አይ ፖለቲካ በኢስላም ስም መነገድ ሱብሃነላህ፡፡

ስለዚህ የአላህ ባርያ ሆይ! የተብለጨለጨ ሁሉ ወርቅ አይደለም፡፡ በእሳት ተፈትኖ ነው የወርቅ ወርቅነቱ የሚታወቀው፡፡ “ለኢስላም ነው የምንሰራው፤ ሸሪዓን ለመተግበር ነው” ያለ ሁሉ በተግባር ይሰራዋል ማለት አይደለም፡፡ ከኢስላም አፈንግጦ የወጣ አስተምሮታቸውን በኢስላም ስም አራምደው ስንቱን ምስኪን ሲያታሉት ኖረዋል እየኖሩም ነው፡፡ ኢኽዋን በኢስላም ስም የሚንቀሳቀሱ፣ ኢስላምን ሽፋን አድርገው ሙስሊሞችን ከመሪዎቻቸው ለያይተው፤ በመሪዎቻቸው ላይ አሳምፀው አለም ላይ እንደሚታየው ደም አፋሰው፤ አገር አበጣብጠው ሙስሊሞችን የጠላት መጫወቻ እንዲሆኑ ሰበብ የሆኑ ናቸው፡፡ ደግሞም ልብ በሉ! ኢኽዋኖች ኢስላምን ስልጣን ላይ ለመድረስ እንደሽፋን እየተጠቀሙበት እንደሆነ የገለፁት እኔ ሳልሆን ታላላቅ ዑለማዎች ናቸው፡፡ ይህንን በደንብ አስምሩልኝ፡፡

ሙርሲ “ሸሪዓን ትትገብራላችሁን” ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹የኢስላም ሸሪዓ በግብፅ ህግ ውስጥ አለኮ?›› ነው ያለው፡፡ ግን ሸሪዓ ከነበረ ለምን ቀድመው እንደሌለ አስመስለው ህዝቡን ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት መቀስቀስ አስፈለጋቸው? ለምንስ እራሱ ሙርሱ ስልጣን ከመያዙ በፊት ‹‹ሸሪዓ፤ ከዛም ሸሪዓ›› እያለ ሸሪዐን ለመመለስ እንደሚታገሉ ሰበከ? መዋሸቱስ ለምን አስፈለገ?

በጥቅሉ ከሙርሲ እስከ ቀርዳዊ ሌሎችም ብዙ ኢኽዋኖች ለፊልም፣ ሙዚቃ፣ ድራማ፣ … ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገታሉ፡፡ “ኢስላማዊ” እያሉም ከኢስላም ጋር እነዚህን ጥፋቶች ያቆራኟቸዋል፡፡ በነሱ ቤት መልካም እየሰሩ ነው፡፡ ነገር ግን “ጥሩ እየሰራሁ ነው” ያለ ሁሉ ጥሩ እየሰራ ነው ማለት አይደለም፡፡ አታይም እንዴ አላህ ምን እንደሚል
وَإِذَا قِيلَ لَهُمْ لَا تُفْسِدُوا۟ فِى ٱلْأَرْضِ قَالُوٓا۟ إِنَّمَا نَحْنُ مُصْلِحُونَ
ለነርሱም «በምድር ላይ አታበላሹ» በተባሉ ጊዜ «እኛ አሳማሪዎች ብቻ ነን» ይላሉ፡፡
أَلَآ إِنَّهُمْ هُمُ ٱلْمُفْسِدُونَ وَلَٰكِن لَّا يَشْعُرُونَ
ንቁ እነርሱ አጥፊዎቹ እነሱው ናቸው፤ ግን አያውቁም፡፡

የሚገርመው ደግሞ ግብፅ ላይ በሚልየኖች የሚቆጠሩ ሽርክ እና ቢድዓ ላይ ተዘፍቀው እያዩ፤ እነዚህን ሰዎች ቅድሚያ ለተውሂድ እና ሱና ሰጥተው ማስተማር ሲገባቸው ሁሌ ፖለቲካ እየወተወቱ ህዝቡን ያስተኙታል፡፡ እውነት የዲኑ አስተምህሮት እንዲህ ነው? አላህ እንዲህ ይላል

وَعَدَ ٱللَّهُ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ مِنكُمْ وَعَمِلُوا۟ ٱلصَّٰلِحَٰتِ لَيَسْتَخْلِفَنَّهُمْ فِى ٱلْأَرْضِ كَمَا ٱسْتَخْلَفَ ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِهِمْ وَلَيُمَكِّنَنَّ لَهُمْ دِينَهُمُ ٱلَّذِى ٱرْتَضَىٰ لَهُمْ وَلَيُبَدِّلَنَّهُم مِّنۢ بَعْدِ خَوْفِهِمْ أَمْنًا ۚ يَعْبُدُونَنِى لَا يُشْرِكُونَ بِى شَيْـًٔا ۚ وَمَن كَفَرَ بَعْدَ ذَٰلِكَ فَأُو۟لَٰٓئِكَ هُمُ ٱلْفَٰسِقُونَ

‹‹አላህ እነዚያን ከእናንተ ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን እነዚያን ከእነሱ በፊት የነበሩትን እንደተካ በምድር ለይ በእርግጥ ሊተካቸው፣ ለእነሱም ያንን የወደደላቸውን ሃይማኖታቸውን ሊያደላድልላቸው፣ ከፍርሃታቸውም በኋላ ጸጥታን ሊለውጥላቸው ተስፋን ቃል ሰጥቷቸዋል፡፡ በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ይግገዙኛል፡፡ ከዚያም በኋላ የካደ ሰው እነዚያ እነርሱ አመጸኞች ናቸው፡፡››
መስፈርቱ “በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ይግገዙኛል” ሆኖ ሳለ ኢኽዋኖች ግን በተገላቢጦሹ ፖለቲካን አስቀድመው ህዝብ በሽርክ እና ቢድዐ ሲጨማለቅ ዝም ይሉታል፤ ይህም ለኢስራኢል፤ በአሜሪካ እና በሌሎችም መከራን እና የበታችነትን እንዲያገኝ ታላቅ ሰበብ ሆኗቸዋል፡፡

ከስልጣን ሲወርዱ ሰልፍ በወጡበት ራቢየተል አደውያ ላይ የሚከተሉትን ውሸቶች ለተከታዬቻቸው ዋሽተዋል፡-
- ‹‹ጂብሪል ወርዷል››፣ ‹‹መርየም ወርዳለች››፣ “አላህን አየነው!!”
ሱብሐነላህ!! ታድያ እንዲህ አይነት በውሸት የተጨማለቁ አታላይ ፖለቲከኞችን ነው አላህ የሚረዳው? አላህ ኡማውን ከተንኮላቸው ይጠብቀው፡፡

ወደ አገራችን ስመለስ “ቅድሚያ ለተውሂድ” የሚሉ ወንድሞችን በብዛት ስማቸውን ለማጥፋት፤ እነሱን የሙስሊም ጠላት አድርጎ ለማቅረብ ስትሯሯጡ እናያለን፡፡ በተዘዋዋሪው የደገፏችሁን ክርስትያኖችን ‹‹ክርስትያን ወንድሞቻችን›› እያላችሁ ትጠራላችሁ፡፡ ሱብሃነላህ አላህ እኛንም እናንተንም ይምራን፡፡ እነሱ ወንድሞቻችሁ ሆኑ “ቅድሚያ ለተውሒድ” የሚሉት ደግሞ የዲን ጠላቶች፣ ቅጥረኞች ሆኑ? ያሳዝናል፡፡ እስኪ ይህን የአላህ ቃል አስታውሱ
مُّحَمَّدٌ رَّسُولُ ٱللَّهِ ۚ وَٱلَّذِينَ مَعَهُۥٓ أَشِدَّآءُ عَلَى ٱلْكُفَّارِ رُحَمَآءُ بَيْنَهُمْ
የአላህ መልክተኛ ሙሐመድ እነዚያም ከእርሱ ጋር ያሉት (ወዳጆቹ) በከሓዲዎቹ ላይ ብርቱዎች በመካከላቸው አዛኞች ናቸው፡፡ እናንተ ማን ላይ ነው ብርታታችሁ?
ታድያ ካፊሮችን ‹‹ወንድሞቻችን›› እያላችሁ ለምን ይሆን ‹‹ላኢላሃኢለላህ ሙሃመዱ ረሱሉላህ›› የሚሉ ሙስሊሞችን የናንተን ቢድዓ ስላልተጋሩ በመጥፎ የምታነሷቸው?

በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳግም እመለሳለሁ ኢንሻ አላህ፡፡ ሃቅን በሃቅነቱ እንዲያሳየን የምንቀበለውም እንዲያደርገን፤ ባጢልን በባጢልነቱ እንዲያሳየን የምንርቀውም እንዲያደርገን አላህን አለምነዋለሁ፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረቦቻቸው እና ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡

Post a Comment

0 Comments