Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ይነበብ ይነበብ !! መካከለኛው ምስራቅ በይበልጥም ኢራቅ እና ሻም (ሶሪያ)

መካከለኛው ምስራቅ በይበልጥም ኢራቅ እና ሻም (ሶሪያ) ላይ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን አርፎ የነበረውን ፊትና የቀሰቀሱትን እና እራሳቸው በራሳቸው "ኢስላማዊ" ደውላ (ሃገር) አቋቁመናል ብለው የሚለፍፉት ኸዋሪጆች ቅጥ ያጣ ፅንፈኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አይሏል ።

ከወር በፊት ማንነቱ የማይታወቅ (አቡ በክር አል በጝዳዲ) የተባለ አንድ ግለሰብ "የሙስሊሞች አሚር ነኝ!" ብሎ እራሱን የሾመ ሲሆን ኸሊፋነቱን ሁሉም ሙስሊም እንዲቀበለውና እሱን መታዘዝና ማክበር ግዴታ መሆኑን አውጆ ሙስሊም ነኝ የሚል ማንም ሰው ወደዚህ ደውለተል ኢስላሚያ ሂጅራ እንዲያደርግ (እያናደደ የሚያስቅ) ትዕዛዝ በምስል የተደገፈ ኹጥባው ላይ አሳስቧል ።

በዚው ኹጥባው ላይ ሙስሊም ነኝ የሚሉ (በነገራችን ላይ "ሙስሊም ነኝ የሚሉ" ብሎ የሚደጋግመው የሱን "ኸሊፋ"ነት የማይቀበል ማንኛውንም ሰው እንደቀልድ አክፍሮ እስላምናውን አናቱ ላይ እንዳለ ኮፍያ ስለሚቀማው ነው (አዎን ፅንፈኛ ተክፊር!!)) ዶክተሮች ፣ኢንጂነሮች ሌሎች ሙያ ላይ የተሳተፉና ኡለማዎች ወደዚህ "ደውለተል ኢስላሚያ" ሂጅራ እንዲያደርጉ አሳስቧል (ጠይቋል ማለት ደብሮኝ ነው) ።

እዚህ ጋር #ኡለማዎች የሚለውን አስምሩልኝማ ። ኸዋሪጆች ከጥንት ጀምሮ አላህን የሚፈራ አንድም ኡለማ ደግፏቸው አያውቅም ። አሁንም የሚታየው ይሀው ነው ። በኡለማ ድርቅ ተመተዋል ። የነሱን ሸይጧናዊ ፊክራ እንዲደግፉላቸው ኡለማዎችን ይጋብዛሉ ። እዚህ ጋር ምን ያስታውሰናል መሰላቹ ?

በሰሃቦች ጊዜ የዛሬዎቹ ዳኢሾች አይነት ኸዋሪጆች ተነስተው ነበር እናም በዕውቀቱ አቻ የማይገኝለት የረሱል ወዳጅ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በሺዎች የሚቆጠሩ ኸዋሪጆችን ጦረኞች ለማናገርና ለመገሰፅ ወዳሉበት ቀዬ ሄደ ። ሄዶ የተናገረውን ሲተርክ እንዲህ ይላል ። (( አይኖቻቸው እጅጉን ደክመዋል (በእንቅልፍ እጦት) ፊቶቻቸው እጅጉን ገርጥቷል (በሱጁድ ብዛት) አፎቻቸው ዚክርን እንጂ ሌላን አይልም)) ።

አይገርምም ? ረሱል ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ስለነሱ ምን አሉ መሰላቹ ((ኸዋሪጆች) ቁርአንን ይቀሩታል ነገር ግን ከጎሮሮዋቸው አያልፍም ። የነርሱ ኢባዳ ከናንተ ጋር ሲነፃፀር የናንተ ምንም (ባዶ) ነው)) ። (ኸዋሪጆች የጀሃነም ውሾች ናቸው) ፤ ((ካፊሩን ትተው ሙስሊሙን ይገድላሉ) ) )

እናም ወደ ኢብኑ አባስ ስንመለስ ኸዋሪጆችን እየተከራከራቸው ሳለ እንዲህ አላቸው ((ከናንተ መሃከል አንድም የአላህ መልዕክተኛ ባልደረባ አላየሁም)) የዛሬዎቹም ኸዋሪጆች ያው ናቸው አንድም ኡለማ የላቸውም !!

የነሱን መርሕ ልንገርህ ወዳጄ ..

ቅድሚያ ስለጭቆና ስለበደል ይተረትሩልካል ፤ ከዚያም ልብክን ካነሳሱልክ በኋላ ስልጣን ላይ ያለን (የሙሊም ሃገር) ማንኛውም አካል ከሚፈፅመው ጭቆና ጋር ቀላቅለው 'ካፊር ነው!' ይሉካል (አንተም አይንክን ሳታሽ "እና ታዲያ!" ትላለክ) ከዚያም ይሄን ተግባር "ተው" ያሉትን ኡለማዎች ‹‹ የንጉሶች ጠበቃ ፣ የቤተመንግስት ፍርፋሪ ለቃቃሚ..›› ይሏቸዋል አንተም አብረህ ታስተጋባለክ ። ከዚያም ሃገሩ የኩፍር ሃገር ነው ይሉካል (አንተም "እንዴታ!" ትላለክ) ከዚያም ሃገሩ ላይ የሚኖር ሁሉ ሙስሊም አይደለም! ይሉካል ("ወቸው ጉድ! እንዴት ሆኖ?" ስትል አብረው ይነሱብካል ይሄኔ ደንግጠክ "አረረ አዎ ሁሉም ካፊር ነው!" ትላለክ) ከዚያም ቀስ በቀስ "አንተም ካፊር ልትሆን ነው ይሄን ካላደረግክ" ትባላልከ ። "መክፈር አልፈልግም" ካልክ ሂድና እነ እንትና መስጂድ ሄደክ ግደላቸው አንተም "ጀነት"ክን ግባ ይሉካል (አጥፍቶ መጥፋት) ። ምርጫው ያንተ ነው (መክፈር ወይንም "ጀነት"ን መግባት) በነሱ መርሕ መሰረት !!

_____________________

ይሄ አስተሳሰብ ከዬት መጣ እንዴት መጣ ወዴት ይሄዳል (በቀጣይ ፅሁፍ እንዳስ ሰዋለን) ኢንሻ አላህ

___________

አሁን ከዚህ ፅሁፍ ጋር ስላያያዝኩት ምስል አንድ ነገር ልበልክና ፅሁፌን ላጠናቅ

ኸዋሪጁ ስለ ታላቁ የዘመናችን አሊም አል አላማ ሸኽ ሳሊሕ ቢን ፈውዛን ሃፊዘሁላህ

ምስሉ ላይ አንድ የነዚህ ኸዋሪጆች አንድ አክቲቪስት በቲዊተር ገፅ ላይ እንደፃፈው

‹‹ ፔኑሱዌላውን ስንቆጣጠር የሳሊህ ፈውዛንን አንገት እንቆርጠዋለን..››

አዑዙቢላህ!!

መልስ ምት ሲበዛበት ነው መሰል በድጋሚ እንዲህ ብሎ ፃፈ..

‹‹ አዲስ ነገር ምንም የለም ። የፈውዛንን አንገት በመቁረጥ ወደ አላህ እንደሚያቃርበኝ ተስፋ አደጋለው..››

ኢናሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን

፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡

አላህ ኡለማዎቻችንን ይጠብቅልን

አላህ ከእንደዚህ አይነት ፅንፈኝነት ይጠብቀን

አሚን