Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሰው ምረጥ



           ምርጥ መነበብ ያለበት ፅሁፍ በወንድም Abu Abdellah Ibn Abdellah


በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩህሩህ በሆነው፡፡

የአላህ ሰላት እና ሰላም በነቢያችን፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረባዎቻቸውና የነሱን ቅን ፈለግ በተከተሉት ላይ ሁሉ ይረጋገጥ፡፡

ከሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪ ውስጥ አብሮ መኖር፣ መጋባት፣ መጎዳኘት፣ መጎራበት እና ወዘተ የሆኑ ማህበራዊ ግንኙነቶች የማይቀሩ እውነታዎች ናቸው፡፡ በነዚህ የህይወት እንቅስቃሶዎቻችን ውስጥ በየዘርፉ ሙሉ የሆነው ሀይማኖታችን ኢስላም ደግሞ እንዴት መኗኗር እንዳለብን በግልፅ አስቀምጦልናል፡፡ ወሊላሂል ሀምድ፡፡

ሆኖም ግን ብዙዎቻችን ይህን ሙሉ የሆነው እምነታችን ያስቀመጣቸውን ዘይቤዎች ባለማወቅም ይሁን ችላ በማለት ምእራብ አመጣሽ እስታዬሎችን እየተከተልን የራሳችን የሆኑ ብርቅዬ ሱናዎችን ስንተዋቸው ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ና እንደዋና ምክኒያት የሚታየው የሰዎች ሰው መረጣ እና ዲንን ጠንቅቆ የአለማወቅ ውጤቶች ናቸው፡፡

የአላህ መልእክተኛ (ሰዐወ) ለሰሃባዎቻቸው ‹‹ ከናንተ በስተፊት የነበሩ ሰዎችን ሱና (አካሄድ ) ስንዝር በስንዝር ትከተላላችሁ፣ የፍልፈል ጉድጓድ ውስጥ እንኳን ቢገቡ ተከትላችሁ ትገባላችሁ ፡፡ አሏቸው፣ ሰሃባዎችም አንቱ ያላህ መልዕክተኛ ሆይ! አይሁድንና ነሳራን ነውን? ብለው ጠየቁ፡፡ ረሱልም፡- እና እነሱን ካልሆነ ማንን ሊሆን ነው፡፡›› አሉ ፡፡ እስኪ አስቡት ዛሬ ላይ የምናየው የኛም ሁናቴ ከዚሁ በምንም የሚለይ አይመስለኝም፡፡ አነጋገራችን፣ አበላላችን፣ አጠጣጣችን፣አለባበሳችን፣ አካሄዳችን፣ ኧረ እንደውም አኗኗራችን ባጠቃላይ ምን እንደሚመስል ያደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል!! ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ላይ ከቀጠልን መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል እጅግ በጣም ነው ሚያስፈራው፡፡ በዚህ ሰዓት ወለድ መብላት እንደቀላል ወንጀል ነው ሚታየው፤ ዚና መስራት እነደ ዝና ነው የሚወራው፤ሰውን ማማት እንደ መልካም ተግባር ነው የሚቆጠረው፤ ሰራተኛ ቀጥሮ (ሌባ ናት/ ነው) እያሉ ደመ ወዝ መከልከል ቀላል ነገር ሆኗል ፤ ወጣቱ ኒካህን ትቶ ገርል ፍሬንድና ቦይ ፍሬንድን እንደሃላል ሲረማመድበት፤ ኧረ ስንቱ ተጠቅሶ ስንቱ ይተዋል!!

በነዚህ ተግባሮቻችን ላይ ሆነን አጀላችን ቢደርስና ሞት መጥቶ ቢወስደን ፍፃሜንያችን ምን ሊሆን እንደሚችል ለሁላችንም የሚጠፋን አይመስለኝም ፡፡ ግና ይህንን ያስታወስን አይመስልም፡፡

ይህ ሁሉ ሆኗል ብለህ/ሽ ግን ተስፋ አትቁረጥ/ጪ!!፡፡ አዛኙ አምላካችን እንዲህ ይላል፡፡

قُلْ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ أَسْرَفُوا عَلَى أَنْفُسِهِمْ لَا تَقْنَطُوا مِنْ رَحْمَةِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يَغْفِرُ الذُّنُوبَ جَمِيعًا إِنَّهُ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ (53)

‹‹እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ!! ከአላህ ራህመት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ በላቸው፡፡ አላህ ወንጀልን ሁሉ ይምራል፡፡ እሱም አዛኝ እና መሃሪ የሆነ አምላክ ነው፡፡›› (ዙመር 53)

አሁንም አልረፈደም የአላህ እዝነቱ ሰፊ ነው፡፡ ወደርሱ የተመለሰን ሁሉ ይቅር ይላል፡፡ እነዚህን ነገራቶች ለማስተካከል ግን መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር ከላይ በርእሱ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አብረናቸው የምንውላቸውን ሰዎች እጅግ አጣርተን ማወቅና በጥንቃቄ መምረጥ አለብን፡፡ ለዚህም ነው የአላህ መልእክተኛ (ሰዐወ) ‹‹ሰውዬው በወዳጁ እምነት ላይ ነው፡፡ አንዳችሁ (ከመወዳጀቱ በፊት) ማንን እነደሚወዳጅ ያጣራ (ይመልከት)፡፡›› አቡ ዳውድና ቲርሚዚ ዘግበውታል ፡፡ አልባኒ (ረሁ) በሰሂህ አቡዳውድ 4046 ላይ ሰሂህ ብለውታል፡፡

እስኪ አሁን ወደራሳችን ዞር ብለን ጓደኞቻችንን እና ወዳጆቻችንን እንመልከት፡፡ ጓደኞቻችንን ሁል ግዜ ስናገኛቸው ኢማናችን ይጨምራል ወይስ ይቀንሳል?ምናልባትም ይህን እንዴት ልንፈትሸው እንችላለን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ የዚህ መልስ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ጓደኛህ እሱ ጋር ስትሄድ ሁሌ ሚያወራህ ስለ ሴት፤ ስለዱንያ፤ ስለ ሰው ስህተት፤ ….ወዘተ የሚያወራ ከሆነ፣ እነዲሁም ሁል ጊዜ ዲንን እንድትማር የማይገፋፋህ፤ ወደ መስጂድ በሚኬድበት ሰዓት ቸልተኛ ከሆነ፤ ሁሌ መዝናናትንና መሳሳቅን ከሆነ የሚያዘወትረው፣ ይህ ሰው አይጠቅምህም፡፡ ራቀው! ወላሂ አይጠቅምህም ራቀው፡፡ ምናልባትም ከሱ ጋር በመኖርህ የሱን ባህሪ ተላምደህ ምኑም ላይታይህ ይችላል፡፡ እስኪ እራስህን በሌላኛው ሚዛን መዝነው፡፡ እንዲህም ብለህ ራስህን ጠይቅ፡- ከዚህ ሰው ጋር ከተጎዳኘው ምን ያህል ጊዜ ሆነኝ? እስኪ በራሴ ላይ ምን አይነት ለውጥ አምጥቻለው? የኔ እኩያዎች (ጓደኞቼ ) በእውቀት ከኔ በምን በልጠውኛል? ከዚህኛው ወዳጄ ጋር በኖርኩባቸው ጊዜያቶች ምን ያክል ኪታቦችን ቀርቻለሁ? ምን ያክል ጊዜ ቁርዓንን አኽትሜያለሁ? እና ወዘት ጥያቄዎችን ራስህን ጠይቅ፡፡ ከዚያም በአላህ ፈቃድ ማንነትህን ታገኘዋለህ፡፡

አንዳዶቻችን ጋር ደግሞ የሚስተዋል ስህተት አለ፡፡ እሱም እኔ እራሴን የማውቅ ሰው ነኝ፡፡ እኔን ማንም አይመራኝም ሲሉ ይስተዋላል፡፡ ረሱል (ሰዐወ) ግን እንዲህ ይሉናል፡፡ ‹‹ከመጥፎ ሰው ጋር ስለመቀማመጥና ከመልካም ሰዎች ጋር ስለመጎዳኘት ሲናገሩ ‹‹ ከመልካም ሰው ጋር መጎዳኘት ልክ እንደ ሽቶ ተሸካሚ (ሻጭ) ነው፡፡ እሱ ሽቶ ይቀባሃል፡፡ አሊያም ተሻሽተሀው ጥሩ ሽታን ትወስዳለህ፡፡ ወይም ደግሞ ከሱ ጥሩ መዓዛን ታገኛለህ፡፡ ከመጥፎ ሰው ጋር የመዋል ምሳሌው ልክ እንደወናፍ ነፊ ነው፡፡ ወናፍ የሚነፋ ሰው አብረኸው ከዋልክ ወይ በእሳት ልብስህን ያቃጥለዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከሱ መጥፎን ሽታ ታገኛለህ፡፡›› ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡

ከሰለፎች (ከቀደምት ደጋጎች ንግግር ስንመለከት) አብደላህ ቢን ሸውዘብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ አሉ፡- ‹‹አላህ በወጣቶች ላይ ከዋለው ታላቅ ፀጋ ይቆጠራል፡- በሱና ጠንከር ካሉና ወደ ሱና ከሚያነሳሱ ሰዎች ጋር መጎዳኘት፡፡›› ሸርሁ ኢሱሉል ኢእቲቃድ አህለ ሱና/ ላለካኢ/ (1/60) ገፅ 31

ኢብኑ በጣህ ባዘጋጁት አል ኢባና በተባለው ኪታብ ላይ (1/205) ገፅ 33 ላይ እንዲህ ይላሉ፡- ሸይኽ ሙልላ እንዲህ አሉ ‹‹ የሆነን ወጣት በመጀመሪያ ስታየው ከ አህለ ሱናዎች ጋር ከሆነ የሚወዳጀው እሱን ውደደው፡፡ ቅረበውም፡፡ ከአህሉል ቢድዓዎች ጋር አብሮ ሲያብር ( ሲተባበር) ካየኸው ራቀው፡፡ ወጣት መጀመሪያ የተጎዳኘውን ሰው ነው የሚመስለው፡፡››

አቡ ቁላብ የተባሉት ታለቅ ኢማምም እንዲህ ይላሉ ፡፡ ‹‹ ስሜቶቻቸውን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር አብራቹ አትቀማመጡ፡፡ አትከራከሯቸውም፡፡እኔ ወደ ጥመታቸው እንዳይከቷችሁ እፈራለሁና፡፡ ወይም ደግሞ የምታውቁትን ሀቅ (ለስሜቶቻቸው የሚመቹ የሆኑ ሱብሃዎችን በማምጣት) ያለባብሱባችኋልና፡፡ ኢባነቱል ኩብራ (2/437) ገፅ369

እንዲሁም ታላቁ ሰሃባ ኢብኑ አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይላሉ ፡፡ ‹‹ ከስሜት ባልተቤቶች ጋር አትቀማመጥ( አትጎዳኝ) ከነሱ ጋር መጎዳኘት የልብ በሽታን ያመጣልና፡፡›› ኢባነቱል ኩብራ (2/437) ገፅ367

እንግዲህ ይህ ነው የሰለፎች አመለካከት፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰዎች ቢድዓን ስታወግዝ ሊበረታታ ሲገባ በተቃራነው የሚያወግዘውን ሰው ያልሆነ ስም እየሰጡት፤ ያልሰራውን ሰርቷል እያሉ ሰዎች እሱን እንዳይቀርቡት ያደርጋሉ፡፡ ሱብሃነላህ!!!! ይህ ደግሞ ያለጥርጥር በአሁን ጊዜ እያየነው ያለነው ተግባር ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስሜታቸውን ተከትለው ለሚሰሩተ ቢድዓ ሰሂህ የሆኑ ሃዲሶችን እንዲሁም የተለያዩ ግልፅ መረጃዎችን በማምጣት ስትነግራቸው ስሜታቸውን ለማስደሰት ሲሉ የተለያዩ ለመረጃነት የማይበቁ ሹብሃዎችን (ማደናገሪያዎችን) እያመጡ እረታሳቸው ጠመው ሰውም እንዲጠም ምክኒያት ይሆናሉ፡፡ እነዚህን (አሁን መጨረሻ ላይ የጠቀስኳቸውን ነገራቶች) በማስረጃ ማስደገፍ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ፡- ኢስላማዊ ፊልም (ድራማ) የሚባል ነገር የለም ብለህ ስታስተምር፡፡ ለአባቶቻችን እና ለእናቶቻችን ታላቅ ትምህር እየሰጠ ያለውን ብቸኛውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ቴሌቪዥን ጣቢያን ሰደበ ይሉሃል፡፡ አጂብ እኮ ነው!! ይህችን በምሳሌነት አመጣሁ እንጂ የተለያዩ መረጃዎችን ማምጣት ይቻላል፡፡ ስለድራማ ና ፊልም የአላህ ፍቃድ ከሆነ ለብቻው ርእስ በመያዝ በሰፊው ለማየት እንሞክራለን፡፡ አሁን ወደ ርእሴ ልመለስና፤ ልንገነዘበው የሚገባው ነገር ቢኖር እንደዚህ አይነት ሰዎች የኛ አርአያ ሊሆኑ አይገባም፡፡

የኛ አርአያዎች ሊሆኑ ና ልንከተላቸውም የሚገባን እነዚያን ምርጥ ትውልዶች፤ ሰሃባዎች፣ ታቢኢዮች፣ አትባአታቢኢዮችንና የነሱን ቅን ፈለግ የተከተሉትን ምርጥ ትውልዶች ነውና፤ ስራችንን፣ እንቅስቃሴዎቻችን እንዲሁም ሙሉ የሂይወት ዘይቤዎቻችንን በነሱ አካሄድ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል፡፡ አላህ የነዚህን ምርጥ ሰለፎች መንገድ ተከትለው ፍፃሜያቸው ከሚያምርላቸው ሰዎች ያድርገን፡፡

አልሀምዱሊላሂ ረቢል አለሚን፡፡ ወሰላሙን አለል ሙርሰሊን፡፡ ነቢዪና ሙሃመድ ወኣላ አሊሂ ወሳህቢሂ ወሰለም፡፡