Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ማነው ቃል የሚገባ? ሸሪዐው ከማይፈቅድልን አካል ጋር መጨባበጥ እናቁም ፡፡

ማነው_ቃል_የሚገባ?

በወንድም Ibnu Munewor
የምንወዳቸውን ነብይ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ትእዛዝ እናክብር፡፡ ሸሪዐው ከማይፈቅድልን አካል ጋር መጨባበጥ እናቁም ፡፡
1. ኡመይማህ ቢንት ረቂቃህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዲህ ትላለች፡- “ከሴቶች ጋር ሆኜ ኢስላምን ልንቀበል የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጋር መጣን፡፡ ከዚያም “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በአላህ ላይ ምንም ላናጋራ፣ ላንሰርቅ፣ ዝሙትን ላንሰራ፣ ልጆቻችንን ላንገድል፣ በእጆቻችንም በእግሮቻችንንም መሀል ባለ ቅጥፈትን ላንፈፅም እንዲሁም በመልካም አዘኸን ላናምፅህ ቃል ኪዳን እንግባ” አልናቸው፡፡
የአላህ መልእክተኛም (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- “በቻላችሁትና አቅማችሁ በፈቀደ”አሉ፡፡
ከዚያም “አላህና መልእክተኛው ከኛ ከራሳችን በላይ ለኛ አዛኞች ናቸው” አልንና “ሀያ ቃል እንግባልህ የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” አልን፡፡ አሕመድ በዘገቡት ደግሞ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አትጨብጠንም?” ስንል ጠየቅናቸው፡፡
የአላህ መልእክተኛ ግን እንዲህ አሉ “እኔ (አጅነቢይ) ሴቶችን አልጨብጥም፡፡ ለመቶ ሴቶች የምናገረው በተናጠል ለአንዲት ሴት እንደተናገርኩ ነው::” አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል፡፡
2. ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ “አንድ ሰው ያልተፈቀደለትን ሴት ከሚነካ አናቱን በብረት መርፌ ቢወጋ ይሻለዋል::” አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል፡፡
3. ዓኢሻህ ረዲያለሁ ዐንሃ እንዲህ ትላለች “ወላሂ የአላህ መልእክተኛ እጅ ጭራሽ የ(አጅነቢ) እጅ ነክተው አያውቅም፡፡ ከሴቶች ጋር ቃል ኪዳን ሲገቡ እንኳን በንግግር እንጂ በመጨባበጥ አልነበረም”
አንዳንዶች አጅነቢይ ላለመጨበጥ ሲሉ “ውዱእ አለኝ” ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ “ውዱእ ከአጅነቢይ ጋር በመነካካት ይፈርሳል” የሚለው ፊቅሃዊ አቋም ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ አንዳንዶች ግን ይህን እውነታ እያወቁ ላለማስከፋት ሲሉ ብቻ “ውዱእ አለኝ” ይላሉ፡፡ በዚህም ሌላ የባሰ ጥፋት ይፈፅማሉ፡፡ ውሸት!!! ውሸት ከሙስሊም የማይጠበቅ የከፋ ወንጀል ነው፡፡ ኮስተር እንበል፡፡ ሸሪዐን ለመተግበር አንፍራ፡፡ ሰው በወንጀል ሳያፍር እንዴት በሐቅ ያፍራል፡፡
ዲኑን የሚተገብሩት ጥቂቶች ከሆኑ ዛሬ እንደምናየው “አጥባቂ”፣ “አክራሪ” የሚል ታፔላ ይለጠፍላቸዋል፡፡ ዲኑን የሚከተል ቢበዛ ግን ሱና ስለሰራ ሰው አይወነጀልም፡፡ ያለቦታው የሚያፍረውም ድፍረት ያገኛል፡፡ አያድርገው እንጂ ሶላትን የሚሰግዱት ከቀለሉ ሰጋጆች እንደ አክራሪ ይቆጠራሉ፡፡ አሁንም ሳይኖር ይቀራል? ስለዚህ ነብያችንን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በተግባር እየተከተልን ለራሳችንም ለዲናችንም ዋጋ እንስጥ፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡- {በርግጥም በአላህ መልእክተኛ ላይ መልካም አርአያ አለላችሁ…} (አልአሕዛብ፡ 21) {መልእክተኛው ያመጣላችሁንም ያዙ መልእክተኛው የከለከላችሁንም ነገርም ተከልከሉ} (አልሐሽር፡ 7) ግን እስኪ ማነው ከአጅነቢይ ጋር ላለመጨባበጥ ቃል የሚገባ?
እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ ቦታው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው፡፡ ሁለት የክፍሌ ተማሪዎች ጋር ተገጣጠምኩ፡፡ ወንዱን ሰላም አልኩኝ፡፡ ሴቷ እጇን ስትዘረጋ “አልችልም” አልኩኝ፡፡ ወዲያው ወንዱ እንዲህ አለኝ “ይሄ ለሴቶች ያላችሁን ንቀት ነው የሚያሳየው፡፡” እኔም እንዲህ አልኩት “ለሙስሊሟ ሴት እጅህን ዘርግተህ ሳትጨብጥህ ስትቀርስ ምን ትላት ይሆን?”
የደካማውን ፍጡር ከንቱ ትችት ፈርተን መለኮታዊ ትእዛዝ ላይ ልንልፈሰፈስ አይገባም፡፡ ፍጡር ምን ያመጣል? ጀነት የለው እሳት የለው! ግፋ ቢል አላፊ ዱንያ ነው የሚኖረው፡፡ አትሸወድ ሰው እንዲወደኝ ብለህ ከጌታህ ጋር እንዳትጣላ፡፡ የኛ ሞራል ካልላሸቀ በቀር ይሄ እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ የሌሎች እይታ በምንም መልኩ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡ አላህን እንጂ ሰውን ማስደሰት አላማህ አታድርግ፡፡ ስለሰው አትኑር፡፡ የምትገባው የራስህ ቀብር ውስጥ ነው- ብቻህን!!! ሰው ቅን ከሆነ ባይገባው ሲገባው ይረዳሃል፡፡ ቅን ካልሆነ እስኪ ንገረኝ ምኑ ይቀርብሃል? ከሌሎች እምነት ጋር የሆነን ጊዜ (ህመማት/ማማት)ጠብቀው አይደለም ከአጅነቢ ጋር ከተመሳሳይ ፆታ ጋር እንደማይጨባበጡ አታውቅም እንዴ? በባዶ እግራቸውስ እንደሚሄዱ አታውቅምን? ግን ላንተ ሲሆን አክራሪ ትባላለህ፡፡ “ግን እኛ ብቻ ለምን?” እያልክ ብሶት አታውራኝ፡፡ ታዲያ ሐቅ ይዘህ በምቾት ልትኖር ያምርሃል? የዋሆች አንሁን እንጂ! ኣኺሩዘማን ዲንን መጨበጥ ፍም እንደመጨበት የሚከብድበት ጊዜ እንደሆነ አልተነገረንም እንዴ?! ታዲያ ለምን አድሮ ጥጃ እንሆናለን? ይልቅ ልንገርህ፡፡ እኔን የሚገርመኝ የሌሎች ትችት አይደለም የኛ መልፈስፈስ እንጂ፡፡
ሹብሃት
አንዳንዶች ግን ከላይ የተጠቀሱትን ሐዲሶች ችላ ብለው በኢስላም ከአጅነቢ ጋር መጨባበጥ እንደሚቻል ይሞግታሉ፡፡ “መረጃ”ም ይጠቅሳሉ፡፡
1. ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ይላሉ፡- “ከእጃቸው ላይ ጨርቅ አድርገው ሴቶችን ይጨብጡ ነበር” አልባኒ “ዶኢፍ” ብለውታል፡፡ (አዶኢፋህ፡ 4/337) ስለዚህ “ሐዲሡ” ደካማ ከሆነ ወሬ ማስረዘም አያስፈልግም፡፡
2. ሌላም መልእክቱ ግልፅ ያልሆነ የኡሙ ዐጢያህ ሐዲስ አለ፡፡
ሸይኹል አልባኒ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “በጥቅሉ ነብዩ ሴት በእጃቸው እንደጨበጡ የሚያመላክት ጭራሽ አንድ እንኳን ትክክለኛ ማስረጃ አልመጣም፡፡ እንዲሁ ሲገናኙ መጨባበጥ ቀርቶ በቃል ኪዳን ጊዜ እንኳን አላደረጉትም፡፡ ነብዩ ከሴት ጋር ከመጨባበጥ የራቁ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ግልፅ መልእክት ያላቸውን ሐዲሶች ትተው መጨባበጡ ያልተገለፀበትን የኡሙ ዐጢያን ሐዲስ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ በእውነት ሙኽሊስ ከሆነ ሙእሚን የሚመነጭ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ያልተፈቀደችለትን በሚጨብጥ ሰው ላይ ከባድ ዛቻ ከመምጣቱ ጋር፡፡” (አሶሒሓህ፡ 2/28)
እይታችንን እንድንገድብ መታዘዛችን ይታወስ፡፡ ለዐይን ከልክሎ ለእጅ ይፈቅዳል ማለት ደግሞ የማይመስል ነገር ነው፡፡
እዚህ ላይ ኢብኑል ቀይም ረሒመሁላህ እንዲህ ይላል፡- “የሰውን ልጅ የሚያገኙት ጥፋቶች ሁሉ መሰረቱ እይታ ነው፡፡ እይታ ብልጭታን ይወልዳል፡፡ ብልጭታ ሀሳብን ይወልዳል፡፡ ሀሳብ ስሜትን ይወልዳል፡፡ ስሜት ፍላጎትን ይወልዳል፡፡ ፍላጎት ወይም መሻት እየጠነከረ ቁርጠኛ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ ከልካይ ካልከለከለ በቀር፣ አይቀርም ተግባር ይፈፀማል፡፡ እዚህ ላይ ነው “እይታን በመገደብ ላይ መታገስ ከዚያ በኋላ በሚመጡ ነገሮች ላይ ከመታገስ የቀለለ ነው” የሚባለው፡፡ (አልጀዋቡል ካፊ፡ 106)

ሼር በማድረግ የአጅሩ ተቋዳሽ ይሁኑ፡፡