Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ረመዳንን አስመልክቶ ሌሎች ዑመቶች ያልተሰጡ ለዚህ ዑመት ብቻ የተሰጡ አምስት ልዩ ነገሮች


ወንድሞቼ! እህቶቸ!  የተከበረው ወር፣ ታላቁ ወር መጣላችሁ!! በውስጡ አጅር የሚደራረብበት፣ የአላህ ስጦታ የሚበረከትበት፣ መልካምን ፈላጊ ሁሉ የበጐ ነገራት በሮች የሚከፈቱበት የኸይር ወር፣ የበረካ ወር፣ የስጣታና ገፀበረከት ወር፡፡ የረመዳን ወር ሰዎች መሪ፣ ከቀን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች ሲኾን ቁርአን የተወረደበት ነው፡፡ እዝነትና ምህረት ያካበበው ወር ነው፡፡እነዚህንና ሌሎችን ጉዳዮች በተመለከተ ብዙና ግልፅ መረጃዎች ከቀደመው ትልውልድ ደርሶናል፡፡ ከአቢ ሁረይራ ረዲየላሁ ዓንሁ፣ ተይዞ እንደተወራው ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል ረመዳን በመጣ ጊዜ የጀነት በሮች ይከፈታሉ፤ የእሳት በሮች ይዘጋሉ፣ ሰይጣናትም ይታሰራሉ፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡ መልካም ስራዎች ስለሚበዙና የሰራውንም ባለቤቶች ለማበረታታት የጀነት በሮች የሚከፈቱ ሲኾን ከሙእሚሞቹ ዘንድ ወንጀል ሰለሚቀንስ የጀሀነም በሮች ይዘጋሉ ሰይጣኖችም ይታሰራሉ፡፡ ኢማሙ አህመድ አቡ ሁረይራን ረዐ ጠቅሰው እንደዘገቡት ነብዩ ሰዐወ እንዲህ ብለዋል
የእኔ ኡመቶች ረመዳንን አስመልክቶ ከነሱ በፊት ማንም ያልተሰጠውን አምስት ልዩ ነገሮች ተሰጥተዋል፡፡ የአላህ ዘንድ የፆመኛ አፍ ሽታ ልክ እንደሚስክ ሽታ ነው፣ እስከሚያፈጥሩ ድረስ መላኢካዎች ምህረትን ይጠይቁላቸዋል፣ አላህ በየቀኑ ጀነትን እያሰማመረ መልካም ባሮቼ የሚያስቸግራቸውንና የሚያስከፋቸውን ነገር በመተው ስራ እንደሚሰርቁት አሁን አይሰርቁም በመጨረሻው ሌሊት ምህረት ይደረግላቸዋል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ይህች ሌሊት ለይለቱል ቀደር ናትን? ብለው ሰሃቦች ጠየቋቸው፡፡ አይደለችም ግና ሰራተኛ ስራውን እንደጨረሰ ነው ምንዳው የሚከፈለው አሏቸው፡፡እነዚህ አምስት ነገሮች ለሙስሊሞች ነው የተዘጋጁት አላህ በሙስሊሞች ላይ ፀጋዎቹን ሊያሟላ ከሌላው ህዝብ በተለየ መልኩ ለሙስሊሞች አደረገ፡፡ እናንተ በላጭ ህዝቦች  ናችሁ፤ በመልካም ታዛላችሁ፤ ከመጥፎ ትከለክላላችሁ በአላህም    ታምናላችሁ፡፡ ዘርዘር አርገን አንድ በአንድ ስናያቸው
¤ የመጀመሪያው ገፀ በረከት የፆመኛ የአፍ ሽታ ልክ እንደሚስክ ነው አንድ ሰው ከምግብ ሲርቅ አፉ መጥፎ ጠረን ያመጣል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጠረን ሰዎች ዘንድ የተጠላ ቢሆንም አላህ ዘንድ ግን ከሚስክ ሽታ የተሻለ ጥሩ ሽታ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አላህን በመታዘዝና በማምለክ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ማንኛውም አላህን በመተዘዝና በማምለክ የመጣ ነገር እሱ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው፡፡ አላህ ለሰራው ባለቤት የተሻለንና በላጭን ነገር ይተካዋል፡፡ ስለዚያ በአላህ መንገድ ላይ የአላህ ቃል የበላይ ትሆን ዘንድ ሲዋጋ ስለተገደለ ሰው ሰምተሃልን? የውመል ቂየማ ቁሱሉ ደም እያፈሰሰ ይመጣል፤ መልኩ ልክ እንደደም ነው ጠረኑ ደግሞ እንደሚስክ ነው፡፡ በሐጅ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ አላህ መላኢኮችን አረፋ ላይ ስለቆሙ ሰዎች እንዲ ይላቸዋልእነኝህን ባሮቼን ተመልከቱ፤ ፀጉራቸው ተንጨባሮና አቧራ ለብሰው ወደ እኔ መጡ፡፡አህመድና ኢብኑ ሒባን ዘግበውታል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የፀጉር መንጨባረር አላህ ዘንድ ተወዷል፡፡ መነሻው አላህን መታዘዝና ኢህራምን ላለመፍታት እንዲሁም አለባበስን ከማሳመር መጠንቀቅ ስላለባት በመሆኑ ነው፡፡
¤ ሁለተኛው ገፀ በረካት መላኢካዎች እስከ ሚያፈጥሩ ድረስ ምህረትን ይጠይቁላቸዋል መላኢካዎች አላህ ዘንደ የተከበሩ ካዘዛቸው ዝንፍ የማይሉ  ከከለከላቸው የማይቀርቡ ብፁአን ፍጡር ናቸው፡፡ ለፆመኞች የሚያደርጉት ዱዓ በአላህ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ተቀባይነቱ ጥርጥር የለውም፡፡ አላህ ለዚህች ኡማህ መላኢካዎች ዱዓ እንዲያደርጉ መፍቀዱ የኡማዋን ትልቅነት፣ የዝናው ከፍ ማለትም የፆማቸውንም ታላቅ ትሩፋት ይገልፃል፡፡ምህረት (ኢስቲግፋር) መፈለግ ማለት አንድ ሰው ወንጀል በዱንያ ሆነ በአኺራ ድብቅ እንዲሆንለት ይህችንም ወንጀል አላህ እንዲያልፈው መጠየቅ ማለት ሲሆን ይህ ደገሞ ከምንፈልጋቸውና ከምንመኛቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ በላጩ ነው፡፡ የአደም ልጆች ምንጊዜም ተሳሳቾችና ድንበር አላፊዎት ናቸው በመሆኑም የአላህን ምህረት መከጀል ይገባቸዋል፡፡

¤ ሶስተኛ ገፀ በረከት ሰይጣናት በሰንሰለትና እግረ ሙቅ ይታሰራሉ እስራቱ መልካም የአላህ ባሪያዎችን እንዲያጠሙና ከሐቅ እንዳያዘናጋቸው ያደርጋል፡፡ ይህም የእሳት ባልደረቦች ይሆኑ ዘንድ ጥሪ የሚያደርጉ ጠላቶቻቸውን በማገት አላህ ባሮችን የገዘበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ ወር ላይ የሚታየው ከፍተኛ መልካም ስራን ለመፈፀም የሚደረግ ጉጉትና ከመጥፎ ነገር ለመታቀብ የሚደረገው ጥረት የሰይጣናቱ መታሰር ውጤት ነው፡፡
¤ አራተኛው ገፀ በረከት አላህ በየቀኑ ጀነትን ያስውባታል ባሮቼ የሚያስከፋቸውንና የሚያስጠላቸውን ነገር እርግፍ አድርገው ትተው ወዳንቺ መምጣትን ፈልገዋል፣ ቀርበዋል ይላታል፡፡ አላህ ለመልካም ባሮቹ ለማዘጋጀት ያሰማምራታል በየቀኑ ባሮቹ ለእሷ ያላቸው ጉጉት ይጨምር ዘንድ፡፡ እንዲህም ይላታል ባሮቼ የዱንያ ጣጣን ትተው ሲያንገላታቸውና ሲያደክማቸው ሲያስቸግራቸው የነበረን ነገር ሁሉ በመተው በጐ ነገርን በመስራት ላይ ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ ወደ ሰላሟና የክብረ ሀገሯ ጀነት የሚያደርሳቸው፣ የዱንያም የአኺራም ብቸኛ የደስታ ምንጭም ይህ መሆኑን አውቀዋል፡፡
¤ አምስተኛው ገፀ በረከት አላህ በዚህ በተባረከ ወር ሌሊቶች በተገቢው ሁኔታ ለሚቆሙ እና ለሚፆሙ ለነብዩ ሙሐመድ  ኡመቶች ምህረትን ይለግሳቸዋል፡፡ ይህም ሰዎች ስራቸውን በሚደመድሙበት ጊዜ የሚከፍላቸው ትሩፋት ነው፡፡ ሰራተኞች የስራ ዋጋቸው የሚከፈላቸው ሰራቸውን ሲያጠናቅቁ ነውና፡፡ አላህ ለባሮቹ በሶሰት መልኩ ችሮታውን ይለግሳቸዋል፡፡ አንደኛ ኃጢአትን ለማሰማር ደረጃን ከፍ ለማድረግ የሚያስችልን መልካም ስራ ባሮች እንዲሰሩ መደንገጉ አንደኛው ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ባይኖር ኖሮ አላህን በዚህ መልኩ ማምለክ ባልቻሉ ነበር፡፡ ኢባዳ በራዕዩ መልክ ከአላህ ወደ መልዕክተኛው ሰዐወ የሚተላለፍ ነው፡፡ ለዚያም ነው ከአላህ ውጭ ሸሪዓን ወይም ስርዓተ ህግን የሚደነግጉ ሰዎችን ያወገዘውና የሽርክ ስራ እንደሆነ የገለፀው፡፡ “ከሃይማኖት አላህ በርሱ ያልፈቀደውን ለርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለነርሱ አሏቸውን?” ሁለተኛ ብዙዎች ወደኃላ ያሉበትን መልካም ስራ እንዲሰሩ አላህ ገጠማቸው፡፡ የአላህ እርዳታና መገጠም ባይኖር ኖሮ ለዚህ ባልታደሉ ነበር ችሮታው የአላህ ነውና፡፡  “በመስለማቸው በአንተ ላይ ይመፃደቃሉ፤ በእስልምናችሁ በእኔ ላይ አትመፃደቁ፤ ይልቁንም አላህ ወደእምነት ስለመራችሁ ይመፃደቅባችኃል፤ እውነተኞች ብትሆኑ (መመፃደቅ ለአላህ ነው) በላቸው፡፡” (አል ሑጅራት 17)  ሶስተኛ አላህ ለኸይር ስራዎች ከፍተኛ ምንዳን አዘጋጅቷል፡፡ አንድ ሀሰና በአስር፣ በሰባት መቶ፣ በብዙ እጥፍ ድርብ ተባዝቶ ይሰጠዋል፡፡ ይህ ችሮታ የአላህ ነው፡፡ ምስጋና የተገባው ይሁን፡፡ ወንድሞቼ!  እህቶቼ! የረመዷን መድረስ  ትልቅ ፀጋ ነው ሐቁን መወጣት ለቻለና አላህን ከመወንጀል ትዕዛዛቱን ወደመፈፀም፤ ከዝንጋታ አላህን ወደ ማውሳት፤ ከአላህን መራቅ ወደ እሱ መመለስን ምርጫው ላደረገ ሰው እውነትም ታላቅ ፀጋ ነው፡፡
አንተ በረጅብ ወር ወንጀል ያልበቃህ ከዚያም በሻዕባን የቀጠልክ አሁን የፆም ወር መጥቶልሃል እንደለመድከው የኃጢአት ወር አታድርገው ቁርአንን አንብብበት ተስቢህም አድርግበት ባለፈው የፆም ነበረ ስንትና ስንት ከቤተሰብ ከወንድሞች ከጐረቤት ግና ወሰዳቸው አይቀሬው ሞት ለአንተ ጊዜ ሰጠህ እንድትማርበት ጌታችን ሆይ ጠልቀን ከገባንበት ዝንጋታ አንቃን፣ ከሞታችን በፊት የተቅዋን ስንቅ ሰንቀን፣ ጊዜያችንን በከንቱ ከማባከን ጠብቀን፣ ለእኛም፣ ለወላጆቻችንም በጥቅሉ ለሁሉም ሙስሊሞች ምህረትን ለግሰን አንተ የአዛኞች አዛኝ ነህና፡፡

ምንጭ 

ዝክረ ረመዳን مجالس شهر رمضان

                            ፔጅ  ላይክ እንዲያረጉ ጋብዠወታለሁ 

Post a Comment

0 Comments