Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የረመዷን ፆም ከአጥቢና ነፍሰ–ጡር አኳያ

 የረመዷን ፆም ከአጥቢና ነፍሰ–ጡር አኳያ 


አጥቢ እናትና ነፍሰ-ጡር ሴት በመፆማቸው ልጆቻቸው እንዳይጎዱ የሚሰጉ ወይም መፆም የሚከብዳቸው ከሆነ ማፍጠር ይችላሉ፡፡ “ካፈጠሩ ምን አለባቸው?” በሚለው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ለማሳጠር ያክል በዚህ ጉዳይ በዑለማዎች ከተሰነዘሩ ሃሳቦች ሚዛን የሚደፋ እንደሆነ ያመንኩበትን ብቻ ላስፍር፡- 

አጥቢ እናት እና ነፍሰ-ጡር ሴት ካፈጠሩ ያለባቸው ግዴታ በሚችሉ ጊዜ ቀዷእ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ ይሄ አቋም የሐሰኑል በስሪይ፣ የዐጧእ፣ የዶሓክ፣ የኢብራሂም አነኸኢይ፣ የአውዛዒይ፣ የዙህሪይ፣ የረቢዐህ፣ የአቡ ዑበይድ፣ የአቡ ሠውር፣ የኢብኑል ሙንዚርና የሌሎችም ምርጫ ነው፡፡ ዐብደላህ ብኑ ዐባስም ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ማለታቸው ተረጋግጧል፡- 

«تُفْطِرُ الْحَامِلُ وَالْمُرْضِعُ فِي رَمَضَانَ، وَتَقْضِيَانِ صِيَامًا، وَلَا تُطْعِمَانِ» 

“ነፍሰ-ጡር እና አጥቢ በረመዷን ያፈጥሩና ፆምን ቀዷእ ያወጣሉ፡፡ እንጂ አያበሉም፡፡” [ሙሶነፍ ዐብዲረዛቅ አሶንዓኒይ፡ ቁጥር፡ 7564] 

ከኢብኑ ዐባስና ከኢብኑ ዑመር ከዚህ የተለየ ቢዘገብም ቀጥሎ ለሚመጣው ሐዲሥ የሚገጥመው ግን ይሄኛው ንግግራቸው ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡  

ይህንን አቋም የመረጡ ዑለማዎች ማስረጃቸው ቀጣዩ ሐዲሥ ነው፡፡ 

إِنَّ اللَّهَ تَعَالَى وَضَعَ عَنِ الْمُسَافِرِ الصَّوْمَ، وَشَطْرَ الصَّلاَةِ، وَعَنِ الحَامِلِ أَوِ الْمُرْضِعِ الصَّوْمَ أَوِ الصِّيَامَ 

“ከፍ ያለው አላህ ከመንገደኛ ፆምንና ከሶላትም ግማሹን አንስቶለታል፡፡ ከነፍሰ-ጡርና ከአጥቢም እንዲሁ ፆምን፡፡” [አቡ ዳውድ፡ 2408] [ቲርሚዚይ፡ 715] [ነሳኢይ፡ 2274፣ 2275፣ 2277] [ኢብኑ ማጀህ፡ 1667] ሸይኹል አልባኒ “ሐሰን” ብለውታል፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 1835]


ከመንገደኛ ሰው ፆም ተነስቶለታል ማለት ማፍጠር ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ግን በጉዞ መልስ ምንም የለበትም ማለት እንዳልሆነ ለማንም የሚታወቅ ነው፡፡ ይልቁንም በጉዞው ላይ ካፈጠረ ኋላ ቀዷእ ያወጣል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- 

فَمن كَانَ مِنْكُم مَرِيضا أَو على سفر فَعدَّة من أَيَّام أخر 

“ከናንተ ውስጥ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የሆነ ሰው ከሌሎች ቀኖች (ተመሳሳይ) ቁጥሮችን መፆም አለበት፡፡” [አልበቀራህ፡ 184] 

ልክ እንዲሁ ነፍሰ-ጡርና አጥቢ እናትም ፆም ተነስቶላቸዋል ማለት በዚህ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ ማፍጠር ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ልክ በጉዞ ሰበብ ያፈጠረ ሰው ቀዷእ እንደሚያወጣው እነሱም ቀዷእ ያወጣሉ፡፡ ልክ በጉዞ ሰበብ ያፈጠረ ሰው ምስኪን ማብላት እንደማይጠበቅበት እነሱም ምስኪን ማብላት አይጠበቅባቸውም፡፡ ማፍጠር የተፈቀደው ለዑዝር ነው፡፡ በዑዝር ሰበብ (ለምሳሌ በመንገድ፣ በህመም) ያፈጠረ ሰው የሚጠበቅበት ዑዝሩ ሲነሳ ቀዷእ ማውጣት እንደሆነው ሁሉ ነፍሰ-ጡር እና አጥቢ እናትም (ለራሳቸውም ይሁን ለልጃቸው ሲሉ ያፈጠሩበት) ዑዝራቸው ሲነሳ የሚጠበቅባቸው ያለፈውን ቀዷእ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ 

ይሄ ቀዷ ብቻ ነው ያለባት የሚለው አቋም ከዘመናችን ዑለማዎች ውስጥ የኢብኑ ባዝ፣ የኢብኑ ዑሠይሚን፣ የሙቅቢል አቋም ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ ማብላት ሳይሆን ቀዷእ ብቻ ነው የሚመለከታት የሚለውን “እኔ ዘንድ ሚዛን የሚደፋው አቋም ነው” ብለውታል፡፡ [አሸርሑል ሙምቲዕ፡ 6/347] 

ወላሁ አዕለም

=

(ኢብኑ ሙነወር፣ መጋቢት 12/2012)


Post a Comment

0 Comments