Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዘካ የሚሰጠው ለምን አይነት ሰው ነው?





ዘካ የሚሰጠው ለምን አይነት ሰው ነው?
~~~
የዘካ ባለሐቆች 8 ናቸው። በቁርኣን እንዲህ ተዘርዝረዋል:–

(إِنَّمَا الصَّدَقَاتُ لِلْفُقَرَاءِ وَالْمَسَاكِينِ وَالْعَامِلِينَ عَلَيْهَا وَالْمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمْ وَفِي الرِّقَابِ وَالْغَارِمِينَ وَفِي سَبِيلِ اللَّهِ وَابْنِ السَّبِيلِ  فَرِيضَةً مِنَ اللَّهِ  وَاللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌ)

"ግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድሆች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በእስልምና) ለሚለማመዱ፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነፃ በማውጣት፣ በባለ እዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሰሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፡፡ አላህም አዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡" [አተውባ: 60]

መጠነኛ ማብራሪያ

ድሃ ማለት:– ለመኖር (ልብሱ፣ ጉርሱ፣ ትዳር ለመመስረት፣ ለመማር፣) ምንም ነገር የሌለው ወይም ትንሽ ነገር ያለው ማለት ነው። እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ዘካ ሊሰጠው ይችላል።

② ምስኪን ማለት: – ለመኖር የሚሆን ነገር በተወሰነ መጠን ያለው ሲሆን የሚበቃው ግን አይደለም።

③ ዘካ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች:– ዘካ እንዲሰበስቡ በመሪ የሚላኩ ሰዎች ናቸው። ዘካ ሶስት ነገሮችን ይፈልጋል። መሰብሰብ፣ መጠበቅና ማከፋፈል። በሶስቱም ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ሰራተኞች ሃብታም ቢሆኑ እንኳ ዘካ ይሰጣቸዋል። 
ልብ በሉ! ለዚሁ ስራ በመንግስት የሚሾሙትን እንጂ የግለሰቦች ወኪሎችን አይመለከትም። ደሞዝተኛ ሰራተኛም እዚህ ውስጥ አይገባም።   

④ ልቦቻቸው (በእስልምና) የሚለማመዱ ማለት ሁለት አይነት ናቸው።

አንደኛ፡- ሙስሊም ያልሆነ ሰው ነው። ሙስሊም ባይሆንም ለተሻጋሪ ፋይዳ ሲባል ነው ሊሰጠው የተፈቀደው።
– ቢሰጠው ይሰልማል ወይም ሌላ ፋይዳ ይገኝበታል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት ከሆነ፣
– የሚያደርሰው ጉዳት ኖሮ በዚህ ማስቆም የሚቻል ከሆነ

ሁለተኛ፡- ሰለምቴ ነው።
– በዲኑ እንዲጠነክር ወይም ለሌላ ሰው መስለም/ መጠንከር ሰበብ ይሆናል ተብሎ ከተገመተ
– በሙስሊሞች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሆኖ በዚህ ማስቆም የሚቻል ከሆነ። [መጅሙዑል ፈታዋ፣ ኢብኑ ተይሚያ: 28/290]

⑤  እራሳቸውን ከአሳዳሪዎቻቸው በመግዛት ነፃ ለማውጣት የሚጣጣሩ ባሪያዎች ዘካ ከሚገባቸው ናቸው።

የተጠለፉ/ የተማረኩ ሙስሊሞችን ማስለቀቅም ከዚሁ ውስጥ ይካተታል።

⑥ ባለ እዳ:– የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ አስቦ እዳ የገባ ሰው ሃብታም እንኳን ቢሆን ዘካ ሊሰጠው ይችላል። 
በራሱ ጉዳይ እዳ የተጫነው ከሆነ በኑሮው ባይቸገር እንኳ እዳውን ለመክፈል ሊሰጠው ይችላል።

⑦ በአላህ መንገድ የሚሰራ ማለት:– ለጂሃድ ዘማች ማለት ነው። ለትጥቅ፣ ለስንቅና አጠቃላይ ዝግጅት ዘካ ይሰጣል።

⑧ መንገደኛ:– አገሩ መግቢያ ከዘካ ገንዘብ ይሰጠዋል።
                   
(ኢብኑ ሙነወር፣ መጋቢት 26/2013)
የቴሌግራም ቻናል :-       

Post a Comment

0 Comments