Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አብሺሩ-- በአላህ ቃል አትጠራጠሩ !

 



አብሺሩ-- በአላህ ቃል አትጠራጠሩ !

በአላህ ፈቃድ የታሰሩ ይፈታሉ። የቆሰሉም ይሽራሉ።
የፈሰሱ ደሞችም ይታፈሳሉ።
የተሰበሩ ልቦችም ይጠገናሉ።
የወደሙ የባይታወሩ ኡማ ንብረቶችም ይካሳሉ-ይተካሉ።
በዳይም "አ ን ድ ቀን" የስራውን ያገኛል።
በበደልና ድንጋጤ ብዛት የታመሙ ልቦችም ይፈወሳሉ፤ ንዴታቸውም ይበርዳል፤ በደስታና እርካታም ይቀየራል።
ሌሊት ምንም ቢረዝምና ጭለማም ቢበረታ መንጋቱ አይቀርም።
ያኔ ስንዴው ከእንክርዳዱ፣ ፈረሱም ከአህያው ይለያል።
በማን አለብኝነት እንደሻው ሲሆንና ሲያደርግ የቆየ በሙሉም የግፉን ዋጋ ይቀምሳል።
ይህን ሁሉ የምንጠብቀው ከሃያሉ አላህ ብቻና ብቻ ነው።
ከሰው ግፍን ማባባስና በሰው ቁስል መደሰትን እንጂ ሌላ ምንም አላየንም።
ድሮም ኢስላም የተጠበቀው በአላህ እንጂ በሰዎች አይደለምና።
ሰው ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን ጠንቅቆ የማያውቅና ከበደል የማይላቀቅ ፍጡር ነው።
ጥቂቶች ለማስተካከል ቢጥሩም ጥረታቸው ክልክ ባለፈው ግፍ ተሸፍኗል።
ማንም ግን ከአላህ ፍርድ ሊያመልጥ አይችልም! ሰማይ ምድሩ የሱ ነውና!።
በጥበቡ በዳይን ለተወሰነ ጊዜ አውቆ ይተወዋል፤ የያዘው ቀን ግን ለሌሎች መማሪያ ያደርገዋል።
ፊርዓውን፣ አቡ ጀህል፣ ሻሮንና የሀገራችን ኢስላም ጠል መሪዎች ፍጻሜያቸው ምን እንደነበረ ታሪክ ይናገራል።
ግፈኞች ላይ በየተራ ያ ታሪክ እስኪደጋገም ድረስ የአላህ ባሮች ሊሰቃዩ ይችላሉ፤
ግን ሙእሚን መቼም ተስፋ አይቆርጥም፤ እጅም አይሰጥም።
የሚገጥመው ነገር በሙሉ ለበጎ እንደሆነ ያውቃል።
አላህ ዲኑንና ባሪያዎቹን ለመርዳት ቃል እንደገባ ያምናል፤ ቃሉንም በትዕግስት ይጠብቃል።
"ከታገሳችሁ፣ አላህንም ከፈራችሁ ተንኮላቸው ምንም አይጎዳችሁም፤ አላህ ስለሚያደርጉት ነገር በሙሉ በዕውቀቱ ከባቢ ነው -ሴራቸውን ያከሽፋል-" (ኣል ዒምራን 120) በሚለው የቁርኣን ቃል የሚያምን ሰው የካፊር ሴር ምንም ቢበዛ አይበግረውም።
"አትድከሙ -ተስፋ አትቁረጡ- አትዘኑም ሙእሚኖች እስከሆናችሁ ድረስ እናንተ ናችሁ የበላዮች" ኣል ዒምራን 139።
የሚለው የአላህ ቃል ለእያንዳንዱ አማኝ ትልቅ ብርታትና መቼም የማይጨልም ተስፋ ነው።
የከሃዲያን በደል መቆሚያና መቀመጫ ያሳጣቸው ሰሓባዎቻቸው ለነቢዩ
صلى الله عليه وسلم.
"ዱዓ አያደርጉልንም እንዴ? አላህን ድል አይጠይቁትም እንዴ.." ባሏቸው ጊዜ በአላህ ያመነ ሰው መፈተኑ የማይቀርና ከጥንት ጀምሮ ያለ መሆኑን ከነገሯቸው በኋላ (ወላሂ ይህን ጉዳይ -ኢስላምን- አላህ የተሟላና ከዳር እስከ ዳር የሚደርስ ያደርገዋል። አንድ ሰው ከሰንዓ እስከ ሐድረመውት -ከአንድ ሀገር ወደሌላ ሩቅ ሀገር- አላህን እና ለበጎቹ ተኩላን ካልሆነ በስተቀር ምንም ሳይፈራ ለብቻው በሰላም ይጓዛል። ነገር ግን እናንተ ትቸኩላላችሁ!።) ብለው መልሰውላቸዋል። አል-ቡኻሪይ 3612።
ይህን ያሉት የመካ አምባገነኖች እነ ኸባብንና ሌሎችንም አቅመ ደካማ፣ ወገን አልባ ሙስሊሞችን በእሳት ሁሉ እያቃጠሉ በሚያሰቃዩበት ጊዜ ነበር።
መካ ላይ በሰላም ወጥተው መግባት ያልቻሉ ሰዎችን ከአላህ ውጪ ምንንም ሳትፈሩ ከሀገር ወደ ሀገር በሰላምና በነጻነት የምትጓዙበት ጊዜ ይመጣል "ግን ትቸኩላላችሁ" ብለዋቸዋል!
የኢስላምን ድል በተስፋና በትዕግስት እንጠብቅ።
ትልቁ የድል መሰረት ሰብር-"ትዕግስት" መሆኑን ዘውትር እናስታውስ።
የድል ማፍጠኛ ኢማን፣ መልካም ስራና ዱዓ መሆኑንም አውቀን እንተግብር።
አብሺሩ- የድልን ጎህ ተጠባበቁ።
የስብራት ዜና ብቻ አትቀባበሉ- ለጠላት ብርታትና ወኔ ይሆናልና!።
ከውስጥም ከውጭም እየተረባረቡ ሊያደፈርሱት የሚፈልጉትን ተውሒድ፣ ሊያጠፉት የሚፈልጉትን የነቢዩን
صلى الله عليه وسلم.
ሱንናህ አውቀን በሁሉም ቦታና ሁኔታ ላይ እንተግብረው።
እኛ የሳቸውን ሱንናህ እና ሸሪዓውን ስንተገብር አላህ ዲኑን በመርዳታችን ይረዳናል፤
ሸሪዓን ስንጥስና ስሜታችንን ስንከተል ግን የጠላት መጫወቻ እንሆናለን።
"ሸሪዓን ማክበር የአላህን ክብር ማግኛ መንገድ ነው። ሸሪዓን መናቅና መጣስ ደግሞ እራስን ማናቅና ማዋረድ ነው።
አሕመድ ኣደም/ዛዱል-መዓድ

Post a Comment

0 Comments