አላህን ማየት- የፀጋዎች ሁሉ ፀጋ!!
~
በጀነት አይኖች ያላዩት፣ ጆሮዎች ያልሰሙት፣ ልቦናዎች ያልሳሉት እጅግ አስጎምጂ፣ እጅግ አጓጊ፣ እጅግ አርኪ፣ እጅግ ማራኪ መስተንግዶዎች አማኞችን ይጠብቃሉ። ነፍሶች የሚቋምጡለት፣ ቀልቦች የሚሹት ሁሉ ፍፁም ከሆነ እርካታ፣ ፍፁም ከሆነ ደስታ ጋር በጀነት አለ። ዱንያ ላይ ሳለ እጅግ ፈተና የከፋበት የሆነን ሰው አላህ አንዴ ጀነት አስገብቶ ካወጣው በኋላ {የኣደም ልጅ ሆይ! ፈተና የሚባል አይተህ ታውቃለህን? ችግር አልፎብህስ ያውቃልን?} ብሎ ሲጠይቀው የጀነት ፀጋ ሁለ ነገሩን አስረስቶት {በጭራሽ ጌታዬ ሆይ! ጭራ ፈተና የሚባል አላለፈብኝም! ጭራሽ ችግር የሚባል አላየሁም!} ይላል። [ሙስሊም፡ 2807] አዎ የትንኝ ክንፍ ታክል ክብደት የሌላት ዱንያ እንዴትስ ከጀነት ጥዑም ለዛ ጋር አብራ ትታወሳለች?! {ይህችም የቅርቢቱ ህይወት መታለያና ጨዋታ እንጂ ሌላ አይደለችም። የመጨረሻይቱም ሀገር እርሷ በእርግጥ የዘላለም ህይወት ሀገር ናት-የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ!} አይደል እንዴ ያለን?! [ዐንከቡት፡ 64] አዎ {ህይወት ማለት የአኺራ ህይወት ነው።}
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ፀጋ በላይ ይበልጥ አስጎምጂ የሆነ ቁንጮ ፀጋ አለ። ወደ ሃያሉ፣ ወደ አዛኙ፣ ወደ ርህሩሁ፣ ወደቸሩ አምላክ መመልከት!! ጀነትን ጨምሮ ሁሉን ያስገኘውን ፈጣሪ ከመመልከት የበለጠ ምን ፀጋ አለ?! ሱብሓነላህ!! ይህንን ሐቅ የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን እንመልከት፡-
1. አማኞች እሱን በማየት ይታደላሉ!!
وُجُوهٞ يَوۡمَئِذٖ نَّاضِرَةٌ ٢٢ إِلَىٰ رَبِّهَا نَاظِرَةٞ ٢٣
{ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው። ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው።} [ቂያማህ፡ 22-23]
የዚች አንቀፅ መልእክት አማኞች የአላህን ፊት የሚመለከቱ መሆናቸውን የሚገልፅ እንደሆነ ከዐብዱላህ ብኑ ዐባስ፣ ከሐሰኑል በስሪ፣ ከዒክሪማ፣ ከሙጃሂድ፣ ከቀታዳ፣ ከዶሓክ፣ ከማሊክ፣ ከሻፊዒይ ተገልጿል። [ካሺፉል ጉማህ፡ 134]
2. ከሃዲዎቹ ይህን ትልቅ ፀጋ አይታደሉትም!!
كَلَّآ إِنَّهُمۡ عَن رَّبِّهِمۡ يَوۡمَئِذٖ لَّمَحۡجُوبُونَ
{በጭራሽ! እነሱ (ከሃዲዎቹ) በዚያ ቀን ከጌታቸው ይጋረዳሉ።} [አልሙጦፊፉን፡ 15]
ከሃዲዎቹ ይሰሩት በነበረው ጥፋት ሳቢያ እሱን ከመመልከት እንደሚታገዱ መናገሩ አማኞቹ እንደሚያዩት ይጠቁማል። አማኞቹም የማያዩት ቢሆኑ ኖሮ ከሃዲዎቹን ነጥሎ በቅጣት መልክ ከማየት እንደሚታገዱ አይነግረንም ነበር። በዚች አንቀፅ ላይ ተመስርተው አልኢማም ማሊክ፣ ኢብኑል ማጂሹን፣ ሻፊዒይ፣ ወኪዕ እና ሌሎችም መልካም ቀደምቶች አማኞች አላህን እንደሚያዩ ገልፀዋል። [ካሺፉል ጉማህ፡ 134]
3. አላህን ማየት ለመልካም ሰሪዎች የተገባ ቃል ነው!
لِّلَّذِينَ أَحۡسَنُواْ ٱلۡحُسۡنَىٰ وَزِيَادَةٞۖ
{ለነዚያ መልካም ለሰሩት መልካሟ እና ጭማሬም አለላቸው።} [ዩኑስ፡ 26]
ዐብዱላህ ብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ ይችን አንቀፅ ሲያብራሩ፡ “‘መልካሟ’ የተባለው ጀነትን ሲሆን፤ ‘ጭማሬ’ የተባለው ደግሞ ወደ አላህ ፊት መመልከትን ነው” ብለዋል። ተመሳሳይ መልእክት ከሰዒድ ብል ሙሰዪብ፣ ከሐሰኑል በስሪ፣ ከዐብዱረሕማን ብኑ አቢ ለይላ፣ ከዓሚር ብኑ ሰዕድ አልበጀሊ፣ ከዒክሪማ፣ ከሙጃሂድ፣ ከቀታዳና ከሌሎችም ተገኝቷል። [ካሺፉል ጉማህ፡ 134] ይሄ ትንተናቸው ደግሞ ሐዲሣዊ መሰረት ያለው ነው።
4. ለአማኞች አላህን ከመመልከት ይበልጥ የተወደደ ፀጋ የለም! ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ፡
"إِذَا دَخَلَ أَهْلُ الْجَنَّةِ الْجَنَّةَ - قَالَ - يَقُولُ اللَّهُ تَبَارَكَ وَتَعَالَى تُرِيدُونَ شَيْئًا أَزِيدُكُمْ فَيَقُولُونَ أَلَمْ تُبَيِّضْ وُجُوهَنَا أَلَمْ تُدْخِلْنَا الْجَنَّةَ وَتُنَجِّنَا مِنَ النَّارِ؟ قَالَ: فَيَكْشِفُ الْحِجَابَ فَمَا أُعْطُوا شَيْئًا أَحَبَّ إِلَيْهِمْ مِنَ النَّظَرِ إِلَى رَبِّهِمْ عَزَّ وَجَلَّ" ثُمَّ تَلاَ هَذِهِ الآيَةَ {لِّلَّذِينَ أَحۡسَنُواْ ٱلۡحُسۡنَىٰ وَزِيَادَةٞۖ }"
{የጀነት ሰዎች ጀነትን በገቡ ጊዜ አላህ ተባረከ ወተዓላ “እንድጨምራችሁ የምትፈልጉት ነገር አለን?” ይላቸዋል። እነሱም ፊታችንን አላበራህልንምን? ጀነትን አላስገባሃንምን? ከእሳትስ አላዳንከንምን?” ይላሉ። ከዚያም መጋረጃውን ይገልጣል። አሸናፊና የላቀ ወደሆነው ጌታቸው እንደመመልከት እነሱ ዘንድ ይበልጥ የተወደደ ነገር አልተሰጡም!} ከዚያም ነብዩ ﷺ ይቺን አንቀፅ አነበቡ፡- {ለነዚያ ላመኑት መልካሟና ጭማሬም አለላቸው።} [ሙስሊም፡ 181]
5. ጀሪር ብኑ ዐብዲላህ አልበጀሊ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡-
كُنَّا جُلُوسًا عِنْدَ رَسُولِ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- إِذْ نَظَرَ إِلَى الْقَمَرِ لَيْلَةَ الْبَدْرِ فَقَالَ: "أَمَا إِنَّكُمْ سَتَرَوْنَ رَبَّكُمْ كَمَا تَرَوْنَ هَذَا الْقَمَرَ لاَ تُضَامُّونَ فِى رُؤْيَتِهِ"
“በአንድ ወቅት ከነብዩ ﷺ ዘንድ ተቀምጠን ሳለ ወደ ጨረቃ ተመለከቱ። ጨረቃዋ ሙሉ የሆነችበት ሌሊት ላይ ነው። ከዚያም {እናንተ ልክ ይህን ጨረቃ እንደምታዩት ጌታችሁን ትመለከታላችሁ። እሱን በማየትም አትቸጋገሩም} አሉ። [ቡኻሪ፡ 554፣ ሙስሊም፡ 633]
6. አቡ ሁረይራህ ረዲየላሁ ዐንሁ ባስተላለፉት ዘገባ ደግሞ
أَنَّ نَاسًا قَالُوا لِرَسُولِ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- يَا رَسُولَ اللَّهِ هَلْ نَرَى رَبَّنَا يَوْمَ الْقِيَامَةِ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم: "هَلْ تُضَارُّونَ فِى رُؤْيَةِ الْقَمَرِ لَيْلَةَ الْبَدْرِ". قَالُوا: "لاَ يَا رَسُولَ اللَّهِ". قَالَ: "هَلْ تُضَارُّونَ فِى الشَّمْسِ لَيْسَ دُونَهَا سَحَابٌ". قَالُوا: "لاَ يَا رَسُولَ اللَّه"ِ. قَالَ: "فَإِنَّكُمْ تَرَوْنَهُ كَذَلِكَ"
የሆኑ ሰዎች “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በቂያማህ እለት ጌታችንን እናያለን?” ሲሉ ጠየቁ። የአላህ መልእክተኛ ﷺ ታዲያ {ሙሉ በምትሆንበት ሌሊት ጨረቃን ለማየት ትቸገራላችሁን?} በማለት ጠየቋቸው። “አንቸገርም” አሉ። {ከስሯ ደመና ሳይኖር ፀሀዩዋን ለማየት ትጎዳዳላችሁን?} ሲሏቸው “በጭራሽ የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” አሉ። {በርግጥም እናንተ ልክ እንዲሁ ታዩታላችሁ} አሉ። [ቡኻሪ፡ 4581] [ሙስሊም፡ 182]
እነዚህንና ተመሳሳይ መልእክት ያላቸው ማስረጃዎችን መሰረት አድርገው “ቀደምት ሙስሊሞችና ኢማሞቻቸው፣ አማኞች አላህን በአኺራ በአይኖቻቸው እንደሚያዩት ወጥ ስምምነት (ኢጅማዕ) ላይ ደርሰዋል።” [አልፈታዋ፡ 6/512]
=
ኢብኑ ሙነወር
0 Comments