Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መውሊድ ውስጥ እነዚህ አደጋዎች አሉ!

 


መውሊድ ውስጥ እነዚህ አደጋዎች አሉ!
~~ ~ ~~~~ ~ ~ ~ ~ ~ ~ ~ ~~~
1. መውሊድን ማክበር የነብዩን ﷺ እና የምርጥ ትውልዶቻቸውን ፈለግ መጣስ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-



(وَمَن يُشَاقِقِ ٱلرَّسُولَ مِنۢ بَعۡدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُ ٱلۡهُدَىٰ وَيَتَّبِعۡ غَيۡرَ سَبِيلِ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ نُوَلِّهِۦ مَا تَوَلَّىٰ وَنُصۡلِهِۦ جَهَنَّمَۖ وَسَآءَتۡ مَصِيرًا)  
 
{ቅኑም መንገድ ከተገለፀለት በኋላ መልእክተኛውን የሚጨቃጨቅና ከአማኞቹም መንገድ ሌላ የሆነን የሚከተል ሰው በተሾመበት ላይ እንሾመዋለን። ጀሀነምንም እንከተዋለን። መጨረሻይቱም ከፋች።} [አኒሳእ፡ 115]
2. መውሊድ “ዒባዳ ነው” ብሎ የሚያስብ ሰው “ዲኑ ሙሉእ ነው” የሚለውን ጌታ እያስተባበለ፣ ነብዩ ﷺ አደራቸውን አልተወጡም እያለ እየሞገተ ነው። ኢማሙ ማሊክ እንዲህ ይላሉ፡- “በኢስላም ውስጥ መልካም ናት ብሎ የሚያስባትን ቢድዐ የፈጠረ ሰው ሙሐመድ ﷺ ተልእኳቸው ላይ ሸፍጥ ሰርተዋል ብሎ እየሞገተ ነው። ምክንያቱም አላህ {ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ} ብሏልና።”
ነብዩ ﷺ በመሰናበቻው ሐጅ ላይ “አጥብቃችሁ ከያዛችሁት ከሱ በኋላ የማትጠሙበትን ነገር በርግጥም ትቼላችኋለሁ፣ የአላህን ኪታብ። እናንተ ስለኔ ትጠየቃላችሁና ምንድን ነው የምትሉት?” ሲሉ ሶሐቦችም “አንተ በርግጥም እንዳደረስክ፣ አደራህን እንደተወጣህና እንደመከርክ ነው የምንመሰክረው” አሉ። ይህኔ አመልካች ጣታቸውን ወደ ሰማይ እያነሱ ከዚያም ወደ ሰዎቹ እየጠቆሙ “ጌታዬ ሆይ! መስክር” አሉ ሶስት ጊዜ በመደጋገም። [ሙስሊም፡ 3009]
3. የመውሊድ ቢድዐን የሚፈፅም ሰው የማይመነዳበትን ከንቱ ልፋት እየለፋ ያለው። ነብዩ ﷺ “የእኛ ትእዛዝ የሌለበትን ስራ የሰራ እሱ (ስራው) ተመላሽ (ውድቅ) ነው” ብለዋል። [ቡኻሪ፡ 3/69፣ ሙስሊም፡ 4590] እባኮትን በከንቱ አይልፉ!!
4. ይህን ቢድዐ የሚፈፅም ሰው ጥመት ላይ ነው። ነብዩ ﷺ “መጤ የሆኑ ነገሮችን ተጠንቀቁ። መጤ ፈሊጥ ሁሉ ፈጠራ ነው። ፈጠራ ሁሉ ጥመት ነው። ጥመት ሁሉ ወደ እሳት ነው” ብለዋል። [ኢርዋኡል ገሊል፡ 608]
5. መውሊድ የሚያከብርና እንዲከበር የሚሟገት ሰው ከሸሪዐዊ ነፀብራቆች ውስጥ አንዱ የሆነውን ነብዩን ﷺ የመውደድ ፅንሰ-ሀሳብን እያዛባ ነው። እሳቸውን ስለመውደድ፣ ስለማክበርና ስለመከተል የሚያትቱ ብዙ የቁርኣን አያዎችን፣ ሐዲሦችንና የሰለፎች ንግግሮችን ቀደምቶቻችን ባልተረዱት መልኩ በመተንተን እነሱ ላልፈፀሙት ቢድዐ ማስረጃ በማድረግ ነብዩን ﷺ መውደድ ማለት መውሊድን ማክበር፣ በሶለዋት ስም መጨፈር ተደርጎ እንዲሳል ተደርጓል። ይህ ምን ያክል እሳቸውን የመውደድ ሸሪዐዊ ነፀብራቅ እየተዛባ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
6. መውሊድን ማክበር በአንድምታ ቀደምቶቻችንን በነገር መውጋት አለበት። ሶሐቦችና ተከታዮቻቸው ከኛ በበለጠ ነብዩን ﷺ የሚወዱ ከመሆናቸው ጋር መውሊድን አላከበሩም። ዛሬ መውሊድን የሚያከብረው የነብዩ ﷺ ወዳጅ፣ የሚቃወመው ደግሞ የሳቸው ጠላት ተደርጎ እየተሳለ ነው። በነዚህ ሰዎች አረዳድ መሰረት ቀደምት ሰለፎች ነብዩን ﷺ “አይወዱም ነበር” ማለት ነው። ይሄ አደገኛ ነገር ነው። እነዚያ ለነብዩ ﷺ ሲሉ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ቤታቸውን ያፈረሱ፣ ገንዘባቸውን የለገሱ ሶሐቦች መውሊድን ስላላከበሩ እሳቸውን “አይወዱም” ቢባል ማን ያምናል?!
7. መውሊድ በአብዛኛው ከባባድ የሆኑ ሺርኮች ይፈፀሙበታል። ቀብር ጦዋፍ የሚያደርጉ፣ ለቀብር ሱጁድ የሚወርዱ፣ ለቀብር የሚሳሉ፣ የቀብር አፈር ለበረካና ለፈውስ የሚወስዱ፣ በጥብጠው የሚጠጡ፣ ስለት የሚወስዱ፣... አሉ። መንዙማዎቹ እራሳቸው በሺርክ የታጨቁ ናቸው። {አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም።} [አኒሳእ፡ 48]
8. መውሊድ ከክርስቲያኖች ጋር መመሳሰል አለበት። የነብይን ልደት በዓል አድርጎ መያዝ ክርስቲያናዊ ሱና ነው። ክርስቲያኖች ገናን የሚያከብሩት የዒሳ ልደት ነው በሚል እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ነብዩ ﷺ “ከሆኑ ሰዎች ጋር የተመሳሰለ ከነሱው ነው” ብለዋል። [ኢርዋኡል ገሊል፡ 1269]
9. መውሊድ ውስጥ ብዙ አይነት ድንበር ማለፍ አለ። በነብዩ ﷺ ላይ፣ በሌሎችም ሙታኖች ላይ ድንበር ማለፍ ይፈፀማል። ይሄ በእለቱ በሚነበቡ ግጥሞች፣ መንዙማዎችና ዶሪሖች ላይ በሰፊው የሚንፀባረቅ ነው። ነብዩ ﷺ ግን “ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ ዒሳን ድንበር አልፈው እንዳወደሱት አታወድሱኝ” ይላሉ። [ጋየቱል መራም፡ 123]
አንዳንዶች በድፍረት የመውሊድ ሌሊት ከለይለተል ቀድር የበለጠ ነው ብለው እስከሚሞግቱ ደርሰዋል። [አልመዋሂቡ ለዱንያህ፡ 1/135] ሱብሓነላህ!! ይህ ሁሉ የሚባለው እንግዲህ የተወለዱበት ቀን አወዛጋቢ ከመሆኑ ጋር ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው የተወለዱት በሌሊት እንደሆነ የሚጠቁም መረጃ በሌለበት ነው። በዚያ ላይ የተወለዱበት ጊዜ ከ 14 ከፍለ-ዘመናት በፊት ያለፈ እንጂ እንደ ለይለተል ቀድር በያመቱ የሚመላለስ አይደለም። ዐልዩል ቃሪ (1014 ዓ. ሂ.) “(የለይለተል ቀድር) በላጭነት ዒባዳ በሷ ውስጥ በላጭ ስለሆነ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። ይህም {መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺህ ወር በላጭ ናት} በሚለው ቁርኣናዊ ምስክርነት ነው። ለመውሊዳቸው ግን ይህቺ ብልጫ ከቁርኣንም፣ ከሱናም፣ ከሙስሊሙ ህዝብ ዑለማዎች ከአንድም አትታወቅም!!” ይላሉ። [አልመውሪዱ ረዊይ፡ 97]
10. መውሊድን ከኢስላማዊ በአላት ውስጥ ማካተት ሁለት አመታዊ በዓል ያደረጉልንን ነብይ ትእዛዝ መጣስ ነው። ነብዩ ﷺ መዲና ሲገቡ ነዋሪዎቿ የሚጫወቱባቸው ሁለት ቀናት ነበሯቸው። “ምንድን ናቸው እነዚህ ሁለት ቀናት?” ሲሉ ጠየቁ። “በጃሂሊያው ጊዜ እንጫወትባቸው ነበርን” አሉ። ይህኔ “የላቀው አላህ ከነሱ በላጭ በሆኑ ሁለት ቀናት ተክቶላችኋል። እነሱም የአድሓ ቀን እና የፊጥር ቀን ናቸው” አሉ። [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 1039]
11. የመውሊድ በዓልን ማክበር ለሌሎች የቢድዐ በዓላት በር መክፈት ነው። የወልዮች ልደት እያሉ በመቃብር ዙሪያ ለሚልከሰከሱ፣ የልጆች አመታዊ ልደት ለሚያከብሩ ሰዎችና ለሌሎችም ምርኩዝ ማቀበል ነው።
12. የመውሊድ ኪታቦችና የመውሊድ ድግሶች በነብዩ ﷺ ስም በሚነገሩ የውሸት ቂሷዎች የታጨቁ ናቸው። “አብዛኛው በመውሊድ ደስኳሪዎች እጅ ያለው ውሸትና ቅጥፈት ነው” ይላሉ መውሊድ ደጋፊ የሆኑት ሰኻዊ። [አልመውሊዱ ረዊይ፡ 32] መልእክተኛው ﷺ ግን “በኔ ላይ ሆን ብሎ የዋሸ ሰው መቀመጫውን ከእሳት ያዘጋጅ” ይላሉ። [ቡኻሪ፡ 1291፣ ሙስሊም፡ 5]
13. በመውሊድ የቢድዐ ድግስ ላይ ነብዩ ﷺ “ከጭፈራው ይታደማሉ” የሚል ሰቅጣጭ እምነት አለ። የቅጥፈታቸው ቅጥፈት የመውሊዱ ሌሊት ላይ “ነብዩ መጡ” እያሉ ከተቀመጡበት መነሳታቸው ነው። በነገራችን ላይ ነብዩ ﷺ ከሞቱ በኋላ ቀርቶ በህይወት እያሉ እንኳን ሲመጡ ሶሐቦች አይነሱላቸውም ነበር። [አሶሒሐ፡ 358] ኢብኑ ሐጀር አልሀይተሚ እንዲህ ይላሉ፡“የዚህ አምሳያው ብዙዎች የነብዩ ﷺ ልደትና እናታቸው እሳቸውን መውለዷ ሲወሳ የሚያደርጉት መቆም ሲሆን ይህም ምንም አይነት መረጃ ያልመጣበት ቢድዐ ነው።” [አልፈታወል ሐዲሢያህ፡ 58]
14. በመውሊድ በዓላት የተከበሩ የአላህ ቤቶች በጭብጨባ፣ በውዝዋዜና በጭፈራ ክብራቸው ይረከሳል። ይሄ ደግሞ አላህ ከሃዲዎችን እንዲህ ሲል ከወቀሰባቸው ነገሮች ውስጥ ነው፡-

(وَمَا كَانَ صَلَاتُهُمۡ عِندَ ٱلۡبَيۡتِ إِلَّا مُكَآءٗ وَتَصۡدِيَةٗۚ) [الأنفال: 35]

{በቤቱ ዘንድም ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም።} [አልአንፋል፡ 35]
ሃያሉ ጌታ እንዲከበሩና ስሙ እንዲወሳባቸው ባዘዘባቸው መስጂዶች ውስጥ ድቤ መደብደብ፣ ማጨብጨብና መጨፈር በአራቱም መዝሀብ የተወገዘ እጅግ አስነዋሪ ተግባር ነው። ይህን ቆሻሻ ተግባር መቃረቢያ አድርጎ ማሰብ ደግሞ የለየለት ጥመት ነው። ኢብኑል ጀውዚ ረሒመሁላህ “ዳንስን ወደ ላቀው አላህ መቃረቢያ ነው ብሎ የሞገተ ሰው እንደሚከፍር የዑለማዎች ኢጅማዕ ተቋጭቷል” ይላሉ። [ሶይዱል ኻጢር፡ 168] አቡበክር አጦርጡሺ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “የሱፍያ አካሄድ ቦዘኔነት፣ መሀይምነትና ጥመት ነው። ኢስላም ማለት የአላህ ቁርኣንና የመልእክተኛው ሱና እንጂ ሌላ አይደለም። ዳንስና ውዝዋዜ የመጀመሪያ የፈጠሩት የሳሚሪ ባልደረቦች ናቸው (በነብዩ ሙሳ ዘመን)። ያኔ ድምፅ ያለው የወይፈን አካልን አምላክ ሲያደርግላቸው ጊዜ መጥተው ዙሪያውን ይጨፍሩና ይወዛወዙ ነበር። ማለትም ጭፈራ የከሃዲዎችና የወይፈን አምላኪዎች ሃይማኖት ነው። የነብዩ ﷺ እና የሶሐቦቻቸው መጅሊስ ልክ ከራሳቸው ላይ ወፍ ያረፈ እስከሚመስል መረጋጋት ነበራቸው። እነዚህን ሰዎች አሚሩ መስጂድ ውስጥም ይሁን ሌላ ቦታ ከመፈፀም ሊከለክላቸው ይገባል። በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሆነ ሰው ከነሱ ጋር ሊካፈል፣ በጥፋትም ላይ ሊያግዛቸው አይፈቀድለትም። የማሊክም፣ የአቡ ሐኒፋም፣ የሻፊዒይም፣ የአሕመድም፣ የሌሎችም ሙስሊም ምሁራን መዝሀብ ይህን ነው የሚያዘው።” [ተፍሲሩል ቁርጡቢ፡ 11/238]
15. ብዙ የመውሊድ ዝግጅቶች የሴትና የወንድ ቅልቅል በብዛት አለባቸው። የብልግና መናሃሪያ እየሆኑም ነው። በእለቱ እቃ እያዞሩ የሚሸጡ ሰዎች ሲጋራ፣ ኮንዶምና መሰል ነገሮችን እንደሚይዙ ተጨባጭ መረጃ አለ። ሴተኛ አዳሪዎች መውሊድ በሚከበርበት አካባቢ የተለያዩ ነገሮችን ለመሸጥ በሚል ሽፋን ጊዜያዊ ዳስ በመቀለስ ለጥፋት እንደሚሰማሩ ከሰበሰብኳቸው መረጃዎች አረጋግጫለሁ።
አልመቅሪዚም በ790 በዒማዱል አንባኒ በተዘጋጀው መውሊድ ላይ የታዘቡትን እንዲህ ሲሉ ይገልፁታል፡- “ሜዳው በዓሊሞች እስከሚጨናነቅ ህዝብ ጎረፈ። በዚያች ሌሊት ሴቶችና ወጣቶች ከባለጌዎች ጋር በመቀላቀላቸው ምክንያት ብዙ አይነት ብልግናዎች ተፈፀሙ። ማለዳ ላይ ሌሊቱን የተጠጡ ከሃምሳ በላይ የአስካሪ መጠጥ እንስራዎች በዛውያው ዙሪያ በነበሩ እርሻዎች ውስጥ ተጥለው እንደተገኙ፣ በርካታ ደናግላንም ክብረ-ንፅህናቸው እንደተገሰሰ፣ በጣም ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው ሻማዎችም እንደተለኮሱ ሙተዋቲር የሆነ መረጃ ወጥቷል። በማግስቱ ጧት አላህ የንፋስ ጥቃት ላከባቸውና ከቦታው የነበሩ ሰዎችን ፊታቸውን አፈር አለበሳቸው። ድንኳኖቹንም ቆራረጣቸው። አንድም ሰው ባህር መሳፈር አልቻለም። ከዚያን ጊዜ በኋላ መውሊድ አልተዘጋጀም።” [ዱረሩል ዑቁዲል ፈሪዳህ፡ 2/501]
16. የመውሊድ ጨፋሪዎች በውዝውዛኔና መሰል ነገሮች ሰውነታቸው ዝሎ ሌሊቱን ገፍተው ስለሚተኙ አብዛኞቹ የፈጅር ሶላትን የተወሰኑት ደግሞ ዙህርንም ጭምር አይሰግዱም። ለነገሩ ክፍለ - ሃገር ላይ አብዛኛው ታዳሚ ከነጭራሹ ሶላት ሰጋጅ አይደለም።
17. መውሊድ ለማክበር አገር አቋርጠው ረጃጅም ርቀቶችን የሚጓዙ ሰዎች ሞልተዋል። ነብዩ ﷺ ግን ለቢድዐ ቀርቶ ለአላህ ታስቦ ለሚፈፀመው አምልኮት እንኳን ከሶስቱ መስጂዶች (መስጂደል ሐራም፣ መዲና የነብዩ መስጂድ እና አቅሷ) ውጭ አገር አቋርጦ መጓዝ እንደማይገባ አሳስበዋል። [ቡኻሪ፡ 1189፣ ሙስሊም፡ 3450] አገር አቋርጠው ያለ መሕረም የሚጓዙ ሴቶችም ቀላል አይደሉም። ነብዩ ﷺ ግን “ማንኛዋም ሴት ከቅርብ ወንድ ቤተሰቧ ጋር እንጂ እንዳትጓዝ” ብለዋል። [ቡኻሪ፡ 1862]
18. መውሊድ የልዩነት መንሰኤ ነው። ለዚህም መውሊድ በተቃረበ ቁጥር የሚነሳውን ውዝግብ መስማቱ ብቻ በቂ ነው። በመውሊድ ላይ ስላልተጋሯቸው ብቻ “ወሃቢ”፣ “የነቢ ጠላት”፣ “ከአይሁድ በከፋ ዲን ያበላሹ” እያሉ ሙስሊሞችን መወንጀል የተለመደ ዘመቻ ነው። ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላህ እንደሚሉት “ቢድዐህ ከልዩነት ጋር የተቆራኘ ነው።” ስለዚህ ቢድዐው እስካለ ድረስ መቆራቆሱ አይቀርም። አልኢማም ሸውካኒ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ደግሞም ይሄ መውሊድ ከተከሰተ በኋላ ውዝግቡ ተጧጡፏል። በዚህም ላይ የሚፃፉት ኪታቦች ከከልካዩም ከፈቃጁም በዝተዋል። … ከነሱ ውስጥ እንደማይፈቀድ ቁርጥ አድርጎ የተናገረ ሲኖር ከነሱ ቢድዐነቱን አምኖ መጥፎ ነገር ካልተቆራኘው በሚል መስፈርት የፈቀደው አለ፣ ምንም ማስረጃ ግን አላመጣም።” [አልፈትሑ ረባኒ፡ 2/1091-1095]
ጥፋቶቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም። ይህን ሁሉ ጉድ አጭቆ የያዘ ቢድዐ ከጥቃቅን ነገሮች ነውን? ህሊና ያለው ይፍረድ። በርግጥ ጥቂቶች ቢሆኑም ከነዚህ ጥፋቶች ውስጥ ከፊሎቹን የሚርቁ አሉ። ግና አንደኛ ጥቂት ናቸው። ሁለትኛ እነዚህ እራሱ ድግሳቸውን በሺርክ የተቀላቀለ መንዙማ ባዮችን ይጋብዙበታል። ከሺርኩ ቢጠራም ድርጊቱ በራሱ መረጃ የለውምና ከቢድዐነት አይዘልም። ሶስተኛ በጥፋት የተወረረውን መውሊድ ሊያወግዙ ቀርቶ የሚያወግዙትን የሚነቅፉ ናቸው። ስለሆነም ጥፋታቸው ከነዚያኞቹ ጥፋት ብዙም የራቀ አይደለም።
===
ኢብኑ ሙነወር

Post a Comment

0 Comments