Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መውሊድ እና ነባሩ እስልምና አይተዋወቁም





       በሺርክ የተወረረውን፣ በኹራፋት ያበደውን፣ በመውሊድ የታጀበውን የሱፍዮች እስልምና “ነባሩ እስልምና” እያሉ የሚያሞካሹ ጩኸቶችን አልፎ አልፎ እንሰማለን። ይህንን የማይቀበለውን “ወሃቢ” በማለት በሙሀመድ ኢብኑ ዐብዲል ወሃብ የተጠነሰሰ መጤ ኢስላም እንደሆነ ሊነግሩን ነው። ይሄ “ነባሩ” የሚሉት ኢስላም ግን ፍፁም እንግዳ የሆኑ መጤ አስተሳሰቦችን አጭቆ የያዘ “ኢስላም” ነው። የዚህ ፎርጅድ “ኢስላም” አብይ መገለጫ የሆነውን መውሊድ እንደ አብነት ብንወስድ ደጋፊዎቹ ሳይቀሩ ከነባሩ ኢስላም ውስጥ የማይታወቅ መጤ እንደሆነ መስክረዋል። ለምሳሌ፦
  1.  አቡ ሻማህ፦ “በዘመናችን ከተፈጠሩ ከዚህ አይነት ነገሮች ያማረ ከሆነው የላቀው አላህ ይጠግናትና በኢርቢል ከተማ በያመቱ ከነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) የልደት ቀን ጋር በሚገጥመው ቀን ይፈፀሙ የነበሩ ሶደቃዎች፣ በጎ ነገሮች፣ ጌጦችንና ደስታን ማንፀባረቅ ነው።” [አልባዒስ ዐላ ኢንካረል ቢድዕ ወልሐዋዲስ: 95] የተሰመረበትን ያስተውሉ።(«በዘመናችን የተፈጠሩ»የሚለውና «ጋር በሚገጥመው ቀን» የሚሉት ሀረጎች ናቸው በመፅሀፉ ላይ የተሰመረባቸው)
  2. ኢብኑ ሐጀር አልዐስቀላኒ፦ “የመውሊድ ድርጊት መሰረቱ ቢድዐ ነው። ከሶስቱም ክፍለ‐ዘመናት መልካም ቀደምቶች አልተላለፈም።” [አልሓዊ ሊልፈታዊ: 1/188]
  3. ሰኻዊ፦ “የተከበረው መውሊድ ተግባር ከተከበሩት ሶስቱ ክፍለ‐ዘመናት ይኖሩ ከነበሩት ደጋግ ቀደምቶች ከአንድም አልተገኘም። ይልቁንም የተከሰተው ከዚያ በኋላ ነው።” [ሱቡሉልሁዳ ወርረሻድ: 1/439]
  4.  አትተዝመንቲ፦ “የመውሊድ ተግባር በመልካም ቀደምቶች የኢስላሚ ቀዳሚ ዘመን አልተከሰተም።”[አስሲረቱ አሸሽኒያህ: 1/441]
  5. አልሓፊዝ አልዒራቂ፦ “ይህንን ነገር ምግብ በማብላት መልኩ እንኳን ከሰለፎች አናውቅም።”[ተሸኒፉል ኣዛን: 136]
  6. ሲዩጢ፦ “የመጀመሪያው ይህን ስራ የፈጠረው የኢርቢሉ ንጉስ ሙዞፈር ነው።”[አልሓዊ: 1/189]
  7. ዘርቃኒ፦ “መውሊድን መፈፀም ቢድአ ነው።”[ሸርሑልመዋሂብ: 1/264]
ይስተዋል። እነዚህ ሁሉም የመውሊድ ደጋፊዎች ከመሆናቸው ጋር ቢድዐህ እንደሆነ ግን በአንድ ድምፅ እየመሰከሩ ነው። {ወሸሂደ ሻሂዱን ሚን አህሊሃ }
ከነሱ ውጪ ያሉ አሊሞች መውሊድን ቢድዐህ ነው እንደሚሉ በግልፅ የሚታወቅ ነው። ለአብነት ያክል፡

8. አሽሸውካኒ፦ “ቢድዐህ በመሆኑ ላይ ከሙስሊሞች አንድም አልተቃወመም” ይላሉ። በተጨማሪም፦ “ቢድዐህ በመሆኑ ላይ የሁሉም ሙስሊሞች ኢጅማዕ እንዳለበት አስረግጠንልሃል” ይላሉ። [ፈትሑርረባኒ: 2/1088፣ 1091]
9.  ሙሐመድ ረሺድ ሪዷ፦ “ይሄ መውሊድ ያለ ንትርክ ቢድዐህ ነው” ይላሉ። [ፈታዋ ረሺድ ሪዷ: 4/1243]
10. ሸይኽ ዐሊ መሕፉዝ፦ “ከቢድዐዎች በመሆኑ ላይ ንትርክ የለም”[አልኢብዳዕ ፊመዷሪል ኢብቲዳዕ: 297]
ስለዚህ አንባቢ አንድ ቁም‐ነገር ሊጨብጥ ይገባል። እሱም መውሊድ በደጋፊም በነቃፊም ኢጅማዕ መጤ ፈሊጥ ቢድዐህ ነው። በየመንደሩ ከዚህ የተለየ እያስተጋቡ ለሚበጠብጡ አካላት ይሄ መብረቅ ነው!! “ነባሩ እስልምና” እያሉ ልባችንን ለሚያደርቁ ሁሉ አንድ መልዕክት ይድረሳቸው። ነባሩ ኢስላም ማለት የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም)፣ የሶሐቦች፣ የታቢዒዮች፣ የአትባዑትታቢዒን ኢስላም ነው። የአራቱ ኢማሞች፣ የነቡኻሪ የነሙስሊም ኢስላም እንጂ የሱፍዮች ኢስላም አይደለም። ይሄ ኢስላም ነባር ካልሆነ የማን ኢስላም ነው ነባር የሚሆነው? እንዳየነው መውሊድ በደጋፊዎችም በነቃፊዎችም ኢጅማዕ ቢድዐህ ነው፣ መጤ ፈሊጥ። መጤ ደግሞ በየትኛውም አረዳድ ነባር ሊሰኝ አይችልም። ስለዚህ መውሊድ ከነባሩ እስልምና ውስጥ የለም ማለት ነው። ስለዚህ መውሊድን የሚቃወመው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ኢስላማዊ አረዳዱ ሐሰን ታጁ እንደሚለው የሀያና የሰላሳ አመት እድሜ ያለው ፈሊጥ ሳይሆን ከሱፍዮቹ ኢስላማዊ አረዳድ በበለጠ ጥንታዊ ነው።

[መውሊድ: ታሪክ፣ ግድፈት፣ እርምት ከሚለው የኢብኑ ሙነውር መፅሀፍ ከገፅ 46 እስከ 48 የተወሰደ]