Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዘካህ ሃይማኖታዊ፣ ስነምግባራዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች

ከዘካ ሃይማኖታዊ ጥቅሞች መካከል፦

1/ የአንድ ባሪያ ዱንያዊም ይሁን የመጪው ዓለም ደስታ መዞሪያ የሆኑት የኢስላም ማዕዘናት መካከል አንዱን ተግባራዊ ማድረግ ነው።
2/ እንደሌሎቹ አምልኮዊ ትዕዛዛት ሁሉ ወደ አላህ የሚያቃርብ እና ኢማንን የሚጨምር ተግባር መሆኑ ነው።
3/ ዘካን በመስጠት የሚገኘው ምንዳ ታላቅ መሆኑ ነው። አላህ(ሱብሃነሁ ወተዓላ) እንዲህ ይላል፦

يَمْحَقُ ٱللَّهُ ٱلرِّبَوا۟ وَيُرْبِى ٱلصَّدَقَـتِ وَٱللَّهُ لَا يُحِبُّ كُلَّ كَفَّارٍ أَثِيمٍ ﴿٢٧٦﴾
ትርጉሙም፦ «አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል፤ ምፅዋቶችንም ያፋፋል፤ አላህም ሀጢአተኛ ከሀዲን ሁሉ አይወድም።» (አል-በቀራህ፡ 276)

وَمَآ ءَاتَيْتُم مِّن رِّبًا لِّيَرْبُوَا۟ فِىٓ أَمْوَلِ ٱلنَّاسِ فَلَا يَرْبُوا۟ عِندَ ٱللَّهِ وَمَآ ءَاتَيْتُم مِّن زَكَوةٍ تُرِيدُونَ وَجْهَ ٱللَّهِ فَأُو۟لَـٓئِكَ هُمُ ٱلْمُضْعِفُونَ ﴿٣٩﴾
ትርጉሙም፦ «ከበረከትም በሰዎች ገንዘቦች ውስጥ ይጨመር ዘንድ (ጥቂት ሰጥታችሁ ብዙ ለማግኘት፡፡) የምትሰጡት አላህ ዘንድ አይጨምርም፤ ከምጽዋትም የአላህን ፊት የምትሹ ሆናችሁ የምትሰጡት እነዚያ (ሰጪዎች) አበርካቾች እነሱ ናቸው::» (አር-ሩም፡ 39)
ነብዩም(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦ «ከሐራም የጠራ ከሆነው ገንዘቡ የተምርን ያህል እንኳ ቢሆን ሰደቃ የሰጠ አላህም ከሐራም የጠራ ከሆነው እንጂ አይቀበልም። ልክ አንዳቹህ (ከብዛታቸው) ተራራ እስኪያክሉ ድረስ (የፈረስ እና መሰል እንሰሳት) ግልገሎቹን እንደሚያራባው አላህ በቀኙ ይዞ ያራባለታል።» (ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል)
4/ አላህ ወንጀሎችን የሚሰርዝበት መሆኑ ነው።
ነብዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦ «ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋው ሰደቃም ወንጀልን ያሳብሳል።» እዚህ (ሐዲስ) ላይ "ሰደቃ" በሚለው ቃል የተፈለገው መልእክት ዘካህ እና ከዚያ ውጪ በበጎ ፍቃደኝነት የሚሰጡ ምፅዋቶችን በአጠቃላይ የሚመለከት ነው።


ከዘካ ስነ-ምግባራዊ ጥቅሞች መካከል፦


1/ ዘካህ የሚሰጠውን ሰው ከደጋግ፣ ከገራገር እና ከለጋስ (የአላህ ባሮች) መደዳ ማሰለፉ ነው።
2/ ዘካህ ሰጪውን ላጡ ወንድሞቹ እንዲያዝን እና እንዲራራ ያስገድዳል። ለአዛኞች ደግሞ አዛኙ ጌታ አላህ ያዝንላቸዋል።
3/ በገሃዱ ዓለም እንደሚታወቀው በገንዘብ እና በጉልበት የሚጠቅም ነገር ለሙስሊሞች ማበርከት ለአበርካቹ የመንፈስ እርካታን የሚሰጠው ከመሆኑም ባሻገር ለወንድሞቹ በሚያበረክተው መልካም ነገር ልክ ተወዳጅ እና የሚከበር ያደርገዋል።
4/ እንደ ስግብግብነት እና ስስት ካሉ ባህሪያት ዘካህ ሰጪውን የሚያጠራ መሆኑ ነው። ይህን አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) እንዲህ በማለት ይገለፀዋል፦
خُذْ مِنْ أَمْوَلِهِمْ صَدَقَةً تُطَهِّرُهُمْ وَتُزَكِّيهِم بِهَا وَصَلِّ عَلَيْهِمْ إِنَّ صَلَوتَكَ سَكَنٌ لَّهُمْ وَٱللَّهُ سَمِيعٌ عَلِيمٌ ﴿١٠٣﴾
ትርጉሙም፦ «(መልእክተኛችን ሆይ!) ከገንዘቦቻቸው ስትሆን በርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የሆነችን ምፅዋት ያዝ» (አት-ተውባህ፡ 103) 
  

ከዘካ ማህበራዊ ጥቅሞች መካከል፦

1/ ከአለማችን አብዛኞቹ አገሮች አብዛኛውን የህዝብ ቁጥር ለሚሸፍኑት ድሆች ችግሮቻቸውን መቅረፉ ነው።
2/ ዘካህ ሙስሊሞችን የሚያጠናክር እና የበላይነት የሚያቀናጃቸው ተግባር ነው። ለዚህም ነው -በአላህ ፍቃድ- ወደፊት እንደምንጠቅሰው ዘካህ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ክፍሎች መካከል አንዱ በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግል የሆነው።
3/ ዘካህ በድሆች እና ችግርተኞች ልቦና ውስጥ (ሊፈጠር የሚችለውን) የምቀኝነት እና የቅናት ስሜት የሚያስወግድ መሆኑ ነው። ድሆች ሀብታሞች በገንዘባቸው እንደፈለጉ ሲጣቀሙ እና እነሱ ግን ከዚያ ገንዘብ በየትኛውም መልኩ መጠቀም አለመቻላቸውን ሲመለከቱ፤ ባለሀብቶቹም ከነሱ አንፃር የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት (በተሟላ መልኩ) ባለመወጣታቸው እና ችግራቸውንም ባለመቅረፋቸው ሃብታሞቹን የመጥላት እና በእነሱ ላይ የመመቅኘት ስሜት ውስጥ መግባታቸው የሚከሰት ነው። ሆኖም ሀብታሞቹ ከገንዘባቸው ላይ በየአመቱ የተሰነውን የሚሰጧቸው ከሆነ ግን ይህ ሁሉ (ችግር) ይቀረፋል። በምትኩም በመካከላቸው ፍቅር እና መግባባት ይነግሳል።
4/ ዘካህ ገንዘብን ያሳድገዋል (በረከቱንም) ያበዛዋል። ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- «ሰደቃ ከገንዘብ አያጎድልም።» ለማለት የተፈለገው፡- ከቁጥር አንፃር ገንዘቡ (ለጊዜው) ቢቀንስም ነገር ግን በሰደቃ ምክንያት ለወደፊቱ የገንዘቡ በረከት እና እድገት አይቀንስም ይልቁኑ አላህ ለለጋሹ ቢተካለት እንዲሁም በገንዘቡ ላይ በረከትን ቢያደርግለት እንጂ።
5/ ዘካህ የገንዘብን ጥቅም (ተደራሽነት) እንዲሰፋ ያደርጋል። ምክንያቱም ገንዘብ ወጪ በሚደርግበት ጊዜ አገልግሎቱ ለውስን ሰዎች ከመሆን ይልቅ ብዙ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ። በአንፃሩ የገንዘብ ልውውጥ (ዝውውር) የሚከናወነው በሀብታሞች መካከል ብቻ ከሆነ ግን ድሆች ከዚያ አንዳች ነገር አያገኙም።
እነዚህ ሁሉ የዘካ ጥቅሞች ዘካህ ግለሰብን እና ማህበረሰብን በማስተካከል ረገድ ያለው ሚና እጅግ በጣም አንገብጋቢና ወሳኝ መሆኑን ያመለክታሉ። አዋቂ እና ጥበበኛ የሆነው አላህ ጥራት ይገባው!!




ጣሃ አሕመድ

Post a Comment

0 Comments