በረመዳን ወር ፆም ላይ እያለ ግንኙነት የፈፀመን ሰው የሚመለከቱ ህግጋት
1. በረመዳን ወር ፆም ላይ እያለ ግንኙነት የፈፀመ ሰው በቁርኣን፣ በሱንና እና በኢጅማዕ ፆሙ ይበላሻል፡፡
2. በተጨማሪ ለፈፀመው ከባድ ጥፋት ማካካሻ ይሆን ዘንድ ከፋራ ግዴታ አለበት፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
3. ሴቷ በጥፋቱ ላይ ተገዳ ከገባች ቀዷም፣ ከፋራም የለባትም፡፡ [ሸርሑል ሙምቲዕ፡ 6/404] በምርጫዋ ከገባች ከፋራ ይመለከታታል ወይስ አይመለከታትም በሚለው ብርቱ ውዝግብ ውስጥ መግባት ስላስፈራኝ ትቼዋለሁ፡፡
4. በእለቱ ፆመኛ ሳይሆን ቀርቶ ግንኙነት ቢፈፅም ከፋራ አይመለከተውም፡፡
5. አንድ ሰው ረስቶ በመብላቱ ወይም በመጠጣቱ ምክንያት ፆሙ የተበላሸ መሰለውና ከዚያ በኋላ ግንኙነት ቢፈፀም ከፋራ የለበትም፡፡ ረስቶ መብላትና መጠጣት ፆም እንደማያፈርስ እያወቀ ከዚያ በኋላ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ከፋራ አለበት፡፡
6. በፆም ግንኙነት መፀም ሐራም መሆኑን የማያውቅ ሰው ጥፋቱን ቢፈፅም በጥፋቱ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ከፋራም የለበትም፡፡ “ክልክልነቱን አውቃለሁ፡፡ ቅጣቱን ነው የማላውቀው” ቢል ከተጠያቂነት አይተርፍም፡፡ ከፋራም ይመለከተዋል፡፡ [አልመጅሙዕ፡ 6/381]
7. ፆመኛ መሆኑን ረስቶት (ምናልባት ካጋጠመ) የፈፀመ ሰው ቀዷም ከፋራም የለበትም፡፡
8. ፈጅር ገና ያልወጣ መስሎት ግንኙነት የፈፀመና ኋላ ላይ ፈጅር ወጥቶ እንደነበር ያረጋገጠ ሰው ቀዷም ከፋራም የለበትም፡፡
9. ግንኙነት እየፈፀመ እያለ ፈጅር የወጣበት ሰው ቀጥታ ማቆም አለበት፡፡ ካቆመ ቀዷም ከፋራም የለበትም፡፡ ከቀጠለ ግን ከፋራ ይመለከተዋል፡፡
10. አንድ ሰው ግንኙነት በመፈፀሙ ምክንያት ከፋራ ግዴታ ከሆነበት በኋላ በእለቱ ህመም ወይም መንገድ ቢያጋጥመው ከፋራው አይቀርለትም፡፡
11. በመብላት ወይም በመጠጣት ፆሙን ካፈረሰ በኋላ ግንኙነት የፈፀመ ሰው አቡ ሐኒፋ፣ ማሊክ፣ አሕመድ፣ ኢብኑ ተይሚያ፣ ኢብኑል ቀይም እና ኢብኑል ዑሠይሚን ከፋራ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በዚህ አይነት ሰው ላይ ከፋራ ግዴታ ባይሆን ግንኙነት ለመፈፀም ያለመ ሁሉ ሆን ብሎ አስቀድሞ ፆሙን በመብላትና በመጠጣት የማፍረስ ብልጠት ሊጠቀም ይችላል የሚል ነው፡፡
12. ግንኙነቱን የፈፀመው ከረመዳን ወር ውጭ ከሆነ ከፋራ የለበትም፡፡ ፆሙ ትርፍ ፆምም ይሁን የረመዳን ቀዷም ይሁን ሌላም ግዴታ ፆም ቢሆን፡፡ ከፋራ የሚመለከተው ግንኙነቱ በወርሃ ረመዳን ከተፈፀመ ብቻ ነው፡፡
13. በረመዳንም ሙሳፊር ወይም መንገደኛ ከሆነ ግንኙነት ቢፈፅምም ቀዷ እንጂ ከፋራ አይመለከተውም፡፡ ምክንያቱም መንገደኛ ፍላጎቱ ከሆነ የማፍጠር ሐቅ አለውና፡፡
14. በአንድ ቀን ደጋግሞ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ያለበት ከፋራ በኢጅማዕ አንድ ብቻ ነው፡፡ ግንኙነቱ በተለያየ ቀን የተፈፀመ ከሆነ በቀኖቹ ብዛት ልክ ከፋራ አለበት፡፡
15. እስካሁን ያሳለፍነው ቀጥታ ግንኙነት ከተፈፀመ ነው፡፡ እንጂ ግንኙነቱን በሌላ አካሎቿ ለምሳሌ ጭኗ ላይ ቢያደርገው ቀዷ እንጂ ከፋራ የለበትም የሚለው አቋም የብዙሃን ዑለማእ ምርጫ ነው፡፡ ግንኙነቱ የተፈፀመው በፊንጢጣ ከሆነ ድርጊቱ በራሱ ቆሻሻ ወንጀል ከመሆኑም ባለፈ ከፋራ አለበት፡፡
16. ግንኙነቱ በረመዳን ቀን እስከሆነ ድረስ የፈፀመው ከተፈቀደለት ሴት ጋርም ይሁን በሐራምም ይሁን የከፋራው ብይን እንዳለ ነው፡፡ እያወራን ያለነው ስለወንጀሉ እንዳልሆነ ይታወስ፡፡
ከፋራውን በተመለከተ
1. በረመዳን ቀን ግንኙነት በመፈፀም ፆሙን ያፈረሰ ሰው ጥፋቱን ለማካካስ የተቀመጡት ነጥቦች ሶስት ናቸው፡፡ እነሱም ባሪያ ነፃ መውጣት፣ ሁለት ወር በተከታታይ መፆም እና ስልሳ ምስኪኖችን ማብላት፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እነዚህ አይነቶች በቅደም ተከተል /በተራ/ እንጂ በምርጫ አይደለም የሚፈፀሙት፡፡ የመጀመሪያውን የቻለ ወደ 2ኛውና 3ኛው መዝለል አይችልም፡፡ 1ኛውን ያልቻለ ወደኛው እንጂ ወደ 3ኛው መዝለል አይችልም፡፡
2. ነፃ የሚያወጣው ባሪያ የሌለው ሰው ሁለት ወር በተከታታይ መፆም አለበት፡፡ የጨረቃውን ወር አንድ ሲል ተከትሎ ከሆነ የሚፆመው ሁለቱም ወራት 29፣ 29 በድምሩ 58 ቀን ሆነው ቢያልቁም ሁለት ወር ሙሉ እንደፆመ ነው የሚቆጠረው፡፡ የጀመረው ከወሩ መጀመሪያ ካልሆነ ግን ስልሳውን ቀን መድፈን አለበት፡፡ ፆሙን ሆን ብሎ በመሀል ያቋረጠ ሰው እንደገና አንድ ብሎ መጀመር ግዴታው ነው፡፡ በመሀል የተቋረጠው በህመም፣ የወር አበባና መሰል ከአቅም በላይ በሆነ ዑዝር ከሆነ ከቆመበት ይቀጠላል፡፡ መጠንቀቅ የሚችሉት አይነት ዑዝር ከሆነ ግን በዚህ ማቋረጥ አይቻልም፡፡ ያለበለዚያ እንደገና አንድ ማለት ግድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በመሀል ላይ ከከፋራው ውጭ የሆነ ሌላ አይነት ፆም እንኳን ማስገባት አይቻልም፡፡ [አልሙግኒ፡ 7/367]
3. ሁለት ወር በተከታታይ መፆም ያልቻለ ሰው ያለው ምርጫ 60 ምስኪኖችን ማብላት ነው፡፡ እዚህ ላይ ማከታተል ግዴታ አይደለም፡፡ ባይሆን አንድን ምስኪን በመደጋገም ሳይሆን የተለያዩ ምስኪኖችን ሊሆን ይገባል የሚያበላው፡፡ የማስረጃው ቀጥተኛ መልእክት ይህን ስለሆነ የሚጠቁመው ኺላፍ ተከትሎ ዘው ብሎ ወደ ሌላ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ የሚያበላው ቤተሰቡን ከሚመግበው ምግብ መካከለኛ ከሚባለው ዝቅ ማለት የለበትም፡፡
4. ሶስቱንም የከፋራ አይነቶች መፈፀም ያልቻለ ሰው እስከሚችል ድረስ ይጠብቃል እንጂ ከከፋራ ነፃ አይሆንም፡፡ [አልኢስቲዝካር፡ 10/105]
ወላሁ አዕለም፡፡ መጨመር ወይም መስተካከል ያለበት ነጥብ አለ የሚል ካለ ሀሳቡን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 06/2010)
0 Comments