Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የላኢላሀ ኢለላህ ማብራርያ

የላኢላሀ ኢለላህ ማብራርያ 

ቢስሚላህ አላ በረከቲላህ ጁማዱ ታኒ 14 / 1433 ዓመተ ሒጅራህ ተመሰረተ

የመጀመርያው ትምህርት

فما معنى لا إله إلا اللّهላኢላሃ ኢለላህ ፍችው ምን ማለት ነው?بِسْمِ اللّهِ الرَّحْمَنِ الرَّحِيمበአላህ ሥም ፍፁም አዛኝ ፍፁም ርኀሩሁ በሆነው ።

በዓለማችን ላይ ከሙስሊሞች ቁጥር ጋር ከሚጠቃለሉ የሕብረተሰብ ክፍል ውስጥ፤ ስለ ላኢላሃ ኢለላህ ትርጉም በቂ እውቀት የሌላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይስተዋላል። በዚህም የተነሳ የላኢላሃ ኢለላህን አላማ በቃልና በተግባር፤ የሚሽር፤ የሚቃወም፤ ወይንም የሚያበላሽ ተግባር ሲፈፅሙ ይታያሉ።ጥያቄ ፡ - የላኢላሃ ኢለላህ ፍቺው፤ አላማውና መስፈርቶቹ (ሹሩጥ) ምንድን ነው?መልስ ፡ - ይህ ከአላህ በስተቀር በሃቅ ሊመለክ የሚገባው አምላክ የለም፤ (ላኢላሃ ኢለላህ) የሚለው ቃል ያለአንዳች ጥርጥር የኢስላም ሃይማኖት ዋንኛው ምሰሶ ነው። ከዚህ ላኢላሃ ኢለላህ ከሚለው ቃል ጋር መሐመዱን ረሱሉላህ የሚለው ቃል ሲቆራኝ ከኢስላም መሰረቶች ውስጥ የመጀመርያው ይሆናል።ሰሂህ ሃዲስ ላይ እንደተዘገበው ረሱል (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) {እስልምና በአምስት መሰረቶች ላይ ነው የተገነባው አሉ። እነሱም ላኢላሃ ኢለላህ መሐመዱን ረሱሉላህ ብሎ መመስከር፤ ሰላት መስገድ፤ ዘካት መስጠት፤ የረመዳንን ወር መፆም፤ ወደ አላህ ቤት ሐጅ ማድረግ ናቸው} ብለዋል።ሰሒሔን ሃዲስ ላይ ኢብኑ አባስ (ረዲየሏሁ ዓንሁ) እንዳወሩት፦ ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሙዓዝን (ረዲየሏሁ ዓንሁ) ወደ የመን ሲልኩት እንዲህ አሉት፦ { በእርግጥ በሄድክበት የአህለል ኪታብ ሕዝቦች ይገጥሙሃል ያኔም ላኢላሃ ኢለላህ ብለው እኔም መልእክተኛ እንደሆንኩኝ እንዲመሰክሩ ጥሪ አድርግላቸው፤ጥሪህን ከተቀበሉት፤ አላህ በቀንና በማታ አምስት ሰላቶችን ግዴታ እንዳደረገባቸው አስተምራቸው፤ይህንንም ከተቀበሉህ፤ከሃብታሞቻቸው እየተወሰደ ወደ ድሃዎቻቸው የሚመለስ ምፅዋት (ዘካት) ግዴታ እንደተደረገባቸው አስተምራቸው} አሉት። በዚህ ነጥብ ዙርያ ብዙ ሃዲሶች ተወርተዋል፤ላኢላሃ ኢለላህ ማለት፦ ከአላህ በስተቀር በሃቅ የሚያመልኩት አምላክ የለም ማለት ሲሆን፤ ይህም ሲብራራ ከአላህ ሌላ ያሉትን ተመላኪዎች ሁሉ ውድቅ አድርጎ፤ በሃቅ ሊመለክ የሚገባው ጥራት የተገባው አላህ ብቻ መሆኑን ማፅደቅ ነው።የተከበረው አላህ በቁርአኑ እንደገለፀው፦

ትርጉም {{ ይህ (ሙእሚኖች ድል መጎናፀፋቸው) በእርግጥ አላህ በሐቅ ሊገዙት የሚገባው ጌታ በመሆኑ ነው፤ (ከአላህ) ሌላ የሚጠሩት (ጣዖት) ፍፁም ሐሰት ነው። አላህ በእርግጥ (የፍጥረታት ሁሉ) የበላይና ኀያል ነው።}} ሱረቱል አል ሐጅ - 62ጥራት የተገባው አላህ በቁርአኑ ሲገልፅ፦

ትርጉም { ከአላህ ጋር ሌላ (የሐሰት) ጌታ የሚገዛ (ዒባዳው ትክክለኛ ለመሆኑ) ምንም መረጃ የለውም፤ (የመጥፎ ሥራውን) ምንዳ (በመጪው አለም) አላህ ዘንድ ያገኘዋል። በእርግጥ ከሃዲያን (የቂያማ ቀን ከእሳት ቅጣት) አይድኑም።}} ሱረቱል ሙእሚኒን - 117የተከበረው ኀያሉ አላህ በቁርአኑ እንደገለፀው፦

ትርጉም {{(ሰዎች ሆይ) ጌታችሁ (አምሳያ የሌለው) አንድ አምላክ (አላህ) ነው፤ (ከአላህ) በስተቀር ሌላ (አምልኮ የሚገባው) አምላክ የለም፤ (አላህ ከሁሉም በላይ ለአማኞች) አዛኝ ርኀሩህ ነው፡፡}}ሱረቱል በቀራህ - 163 በሌላ የቁርአን አንቀፅ ፦

ትርጉም {{ (አይሁድና ነሳራ በቁርአን) ሃይማኖትን (ለአላህ) ብቻ በማድረግ ወደ እምነት በመጠቃለል፤ ሰላትን በመስገድ፤ ዘካትንም በመስጠት ፍፆም ሆነው (አላህን እንዲገዙት ነው እንጂ (በሌላ ጉዳይ) አልታዘዙም። ይህም (የታዘዙበት መንገድ) ቀጥተኛው ሃይማኖት (ኢስላም) ነው።}} ሱረቱል በይናህ 5 በቁርአን ውስጥ ላኢላሃ ኢለላህ የሚለውን የተከበረ ቃል የሚያብራሩ ብዙ አንቀፆች አሉ። ላኢላሃ ኢለላህ የሚልም ሰው ትርጉሙን አውቆት አምኖበት በሸርጡ መሠረት ካልሰራበት በስተቀር ቃሉ ብቻ ከሽርክ ተርታ ስለማያወጣው ሊጠቅመውም አይችልም።በእርግጥ መናፍቃን ላኢላሃ ኢለላህ ይሉ ነበር፤ ነገር ግን ስለማያምኑበትና ስለማይሰሩበት የጀሃነም አዘቅት ውስጥ ይዶላሉ። አይሁዶችም ቀንደኛ ከሃዲያን በመሆናቸው ላኢላሃ ኢለላህ ቢሉም ስለማያምኑበት አይጠቅማቸውም።ባለንበት ዘመን ሷሊህ ሙታኖችንና ቀብርን አምላኪዎች ላኢላሃ ኢለላህ ስላሉ ብቻ ሙስሊም ሊሆኑ አይችሉም፤ ምክንያቱም በቃላቸው፤ በተግባራቸውና በእምነታቸው ላኢላሃ ኢለላህን የሚቃወም ሥራ ይፈፅማሉና።አንዳንድ የሙስሊም ምሁራኖች እንደጠቀሱት ስምንቱ የላኢላሃ ኢለላህ ቅድመ ሁኔታዎች (ሹሩጥ) በሁለት ስንኝ ተጠቃለዋል ይላሉ።እነሱም ስለላኢላሃ ኢለላህ ፦ እውቀት (ዒልም)፤ እርግጠኛነት (የቂን)፤ ፍፁምነት (ኢኽላስ)፤ ሐቀኛነት (ሲድቅ)፤ ውዴታ (ሙሐባ)፤ መታዘዝ (ኢንቂያድ) ወዶ መቀበል (ቀቡል) እና ስምንተኛው ከአላህ ሌላ ተመላኪ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ መካድ ናቸው።ይህ ማብራሪያ የላኢላሃ ኢለላህን ቅድመ ሁኔታ (ሹሩጥ) በጠቅላላ አሟልቷል ማለት ይቻላል።

የላኢላሃ ኢለላህ አላማ ለመተግበር መሟላት የሚገባቸው ስምንቱ ቅድመ ሁኔታዎችን (ሹሩጥ) ዝርዝር፤

አንደኛ፦ እውቀት፤ (ዒልም) ማለት የላኢላሃ ኢለላህን ትርጉም ማወቅ ሲሆን ተቃራኒው ያለማወቅ (ጀህል) ነው፤ እውቀት የሚለው ቃል ሲብራራ ከአላህ በስተቀር በሐቅ ሊገዙት የሚገባው ጌታ የለም ብሎ መረዳት ሲሆን፤ ከአላህ ሌላ ለሆነ ነገር የሚደረጉ አምልኮዎች ሁሉ ሐሰት (ባጢል) እንደሆኑ መገንዘብ ነው።

ሁለተኛ፦ እርግጠኛነት (የቂን) ተቃራኒው ጥርጣሬ ማለት ሲሆን ላኢላሃ ኢለላህ ያለ ሰው ሐቀኛ አምልኮ የሚገባው ለአላህ ብቻ መሆኑን ያላንዳች ጥርጣሬ ማመን አለበት።ሦስተኛ፦ ፍፁምነት (ኢኽላስ) ማለት ላኢላሃ ኢለላህ ያለ ሙስሊም ሁሉንም የአምልኮ ዘርፎችን ለተከበረውና ለኀያሉ ጥራት ለተገባው አላህ ብቻ ማድረግ አለበት። የአምልኮ ዘርፍ ማለትም ስግደት፤ ስለት፤ ልመና፤ መንፈሳዊ እርዳታና ክጀላ ሲሆን። ከአላህ ሌላ ለሆነ ለምሳሌ ለነብይ ወይንም ለወልይ፤ ለመላእክት ወይንም ለጂን፤ ለጣዖት ወይንም ለግኡዝም ሆነ ሕይወት ላለው ነገር አሳልፎ መስጠት በአላህ ላይ ማሻረክ ይሆናል። ስለዚህ በአላህ አምልኮ ላይ ማሻረክ ከላኢላሃ ኢለላህ ሸርጦች ፍፁምነት (ኢኽላስ) የተባለችውን ሸርጥ ያለሟሟላት ይሆናል።አራተኛ ፡ - ሐቀኛነት (ሲድቅ) ማለትም በአንደበቱ ላኢላሃ ኢለላህ ያለ ሙስሊም፤ በልቡም ሐቀኛ መሆን አለበት፤ ምላሱና ልቡ፤ ልቡና ምላሱ አንድ አይነት መሆን አለባቸው። በምላሱ ላኢላሃኢለላህ ያለ በልቡ የማያምንበት ከሆነ የምላሱ ሸሃዳ ለብቻው ምንም አይጠቅመውም፤እንደዚህ አይነቱ እንደማንኛውም መናፍቃን ካፊሮች ነው የሚቆጠረው።አምስተኛ ፡ - ውዴታ (ሙሐባ) ማለት ላኢላሃ ኢለላህ የሚል ሙስሊም የተከበረውና ኀያል የሆነውን አላህ መውደድ አለበት፤ ላኢላሃ ኢለላህ ብሎ አላህን የማይወድ ከሆነ ካፊር ስለሚሆን እንደ መናፍቃን ከሙስሊም ጎራ አይመደብም። (አላህንም የመውደድ ምልክቱ ነብዩ መሐመድን መከተል ነው) ለዚሁም መረጃ አላህ በተለያዩ የቁርአን አንቀፆች ሲገልፅ ፡ -

ትርጉም {{ (አንተ ነብይ ሆይ ለአይሁዶች) በእርግጥ አላህን የምትወዱ ከሆነ እኔን ተከተሉ ያኔም አላህ ይወዳችኋል ሃጥያቶቻችሁንም ይምርላችኋል በላቸው። አላህ መሃሪና አዛኝ ነው።}} አል ኢምራን- 31

ትርጉም ፦ {{ (የአላህን ግዙፍ ሃይልና ተአምራት ካዩ በኋላ) ከሰዎች መካከል ከአላህ ሌላ (ጣዖታትን በአምልኮ ከአላህ ጋራ) እኩዮች አድርገው የሚይዙ አሉ። (ጣዖቶቻቸውን) ልክ እንደ አላህ ውዴታ ይወዷቸዋል፤ እነዚያ ያመኑት (ሙስሊሞች ግን ከሙሽሪኮቹ) የበለጠ ለአላህ ውዴታ አላቸው። እነዚያ (እራሳቸውን) የበደሉ (ከሃዲያን በመጪው አለም የአላህን አቀጣጥ) በሚያዩት (ጊዜ)፤ ሃይል በጠቅላላ የአላህ መሆኑንና፤ አላህም ቅጣቱ ብርቱ መሆኑን ያውቃሉ። }} በቀራህ - 165ስድስተኛ ፡ - መታዘዝ (ኢንቂያድ) ማለት አላህን ብቻ እየተገዙ ለሸሪዓ ሕግ መታዘዝ ማለት ሲሆን፤ የሸሪዓው ሕግም ለሰው ልጆች አማራጭ የሌለው ብቸኛና ሐቀኛ መሆኑን መመስከር፤ ከዚህ ውጪ ላኢላሃ ኢለላህ እያለ አላህን ብቻ ያልተገዛና ለሸሪዓው ሕግም ሳይታዘዝ የሚኮራ ከሆነ እንደ ኢብሊስና መሰሎቹ ስለሚቆጠር ሙስሊም ሊሆን አይችልም።ሰባተኛ ፡ - ወዶ መቀበል (ቀቡል) ይህም ማለትም ከአላህ ሌላ የሚመለኩትን አምልኮዎች ሁሉ በመተው አምልኮን ፍፁም ለአላህ ብቻ በማድረግና የኢባዳ ዘርፎችን ሁሉንም ሳይሰላቹ እድሜ እስካለ ድረስ በመተግበር ወዶ መቀበል (ቀቡል) ይባላል። ስምንተኛ ፡ - ከአላህ ሌላ የሚመለኩትን ጣዖታት ሁሉንም መካድ ፡ - ይህም ማለት ጌታ ወይንም ወልይ ተብለው ከአላህ ሌላ የሚመለኩ አምልኮዎች ሁሉ ፍፁም ሐሰት መሆናቸውን ማመን።

በዚህ ነጥብ ዙርያ አላህ በቁርአኑ እንደገለፀው ፡ -

ትርጉም {{ .. (ከአላህ ሌላ በተመለኩ) ጣዖታት ሁሉ በመካድ በአላህ (ብቸኛ ተመላኪነቱ) ያመነ፤ ልትበጠስ በማትችል አስተማማኟን ቋጠሮ ((ላኢላሃ ኢለላህን)) ጨበጠ ማለት ነው። አላህ (ንግግሮችን ሁሉ) ሰሚ (አስተሳሰቦችን ሁሉ) አዋቂ ነው።}} አልበቀራህ - 256በሐዲስ እንደተረጋገጠው ረሱል (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) {ላኢላሃ ኢለላህ ብሎ ከአላህ ሌላ በሚመለኩ (ጣዖታት ሁሉ) የካደ ደሙም ሆነ ንብረቱ ይከበራል (ስብእናው ይጠበቃል) ምንዳውም አላህ ዘንድ ነው።} ብለዋል። በሌላ ሐዲስ ረሱል (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) {አላህን አንድ ያደረገና ከአላህ ሌላ በሚመለኩ ጣዖታት የካደ ንብረቱም ሆነ ደሙ ይከበራል።} ብለዋል ፤ ሰሒሕ ሙስሊም ላይ እንደተዘገበው፦ ማንኛውም ሙስሊም ከላይ የተዘረዘሩትን የላኢላሃ ኢለላህ ቅድመ ሁኔታዎችን (ሹሩጥ) በማሟላትና ትኩረት በመስጠት የላኢላሃ ኢለላህን አላማ የግዴታ እውን ማድረግ አለበት። የላኢላሃ ኢለላህን ትርጉም በትክክል አውቆ በሥራ ላይ ያዋለው ሐቀኛ ሙስሊም በመሆኑ ደሙም ሆነ ንብረቱ የተከበረ (ስብእናው የተጠበቀ) ይሆናል። ከዚህ ውጪ ለላኢላሃ ኢለላህ ቅድመ ሁኔታዎች (ሹሩጥ) በቂ እውቀት የሌለው ሰው በስህተት ባእድ አምልኮ ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል። ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ባእድ አምልኮዎች በጠቅላላ ጣዖት ይባላሉ። በዚህ ዙሪያ አላህ በቁርአኑ ሲያብራራ ፦

ትርጉም {{ .. (ከአላህ ሌላ በተመለኩ) ጣዖታት ሁሉ በመካድ በአላህ (ብቸኛ ተመላኪነቱ) ያመነ፤ ልትበጠስ በማትችል አስተማማኟን ቋጠሮ ((ላኢላሃ ኢለላህን)) ጨበጠ ማለት ነው። አላህ (ንግግሮችን ሁሉ) ሰሚ (አስተሳሰቦችን ሁሉ) አዋቂ ነው።}} አልበቀራህ - 256 በሌላው የቁርአን አንቀፅ አላህ እንዲህ ብሏል፦

ትርጉም ፦ {{ ወደ ሁሉም ሕዝቦች አላህን ብቻ በማምለክ ጣዖታትን እራቁ (በማለት የሚያዝ) መልእክተኛ በእርግጥ ልከናል። }} አነሕል - 36ሌላው ነጥብ ምንም እንኳን ተመላኪዎቹ ባይፈልጉትም ከአላህ ሌላ የሚመለኩትን ለምሳሌ ነብያት፤ሷሊሆች፡፤መላእክት የመሳሰሉትን ማምለክ ጣዖት ማምለክ ማለት ነው። በእርግጥ እነዚህ የተዘረዘሩት በመሠረታቸው ጣዖት አይደሉም ነገርግን ሰይጣን እንዲመለኩ እያሰማመረ ለሰዎች ሲያመላክታል ሰዎችም የሰይጣንን የአምልኮ መንገድ በተከተሉ ቁጥር አላህ ዘንድ በጣዖት አምላኪነት ይፈረጃሉ። ከሁሉም መጥፎ እኛንም ሆነ ሙስሊሞችን አላህ እንዲጠብቀን እንለምነዋለን።ሌላው የላኢላሃ ኢለላህን አላማ የሚቃረኑ ነጥቦች በሁለት ይከፈላሉ፤ አንደኛው ላኢላሃ ኢለላህን በቀጥታ የሚቃወም ተግባር ሲሆን ሁለተኛው የላኢላሃ ኢለላህን አላማ የሚያሟሉ ግዴታዎችን ያለማክበር ነው።አንደኛ፡ - ላኢላሃ ኢለላህን የሚቃረን ተግባርና ንግግር፤በመፈፀም አጉል እምነት የሚከተል ሰው በቀጥታ ወደ ትልቅ ሽርክ ውስጥ ይገባል። ይኸውም ሙታንን፤ መላእክትን፤ ጣዖታትን፤ ዛፎችን ዲንጋዮችንና ክዋክብቶችን የመሳሰሉትን መለማመን፤ እርድ ማቅረብ፤ መሳልና መስገድ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።ከላይ የተብራሩት ባእድ አምልኮዎች ሁሉም አላህን ብቻ የማምለክ አላማ (ተውሂድን) ይቃረናሉ፤ ባእድ አምላኪውንም ላኢላሃ ኢለላህ የሚለው ቃሉን ያበላሹበታል። ሌላው በተጨማሪ አላህ እርም (ሃራም) ያደረጋቸውን በኢስላም የተደነገጉና በሃራምነታቸው ሕዝበ ሙስሊሙ የተስማማባቸው እንደ ዝሙት፤ አስካሪ መጠጥ፤ ወላጅን መበደል፤ አራጣን ማበደር ወይንም መበደር የመሳሰሉትን ክልክሎች በጠቅላላ የተፈቀደ (ሐላል) ማድረግ የላኢላሃ ኢለላህንና የተውሂድን አላማ ይቃረናል። በተጨማሪ በኢስላም የተደነገጉና በግዴታነታቸው ሕዝበ ሙስሊሙ የተስማማባቸው እንደ አምስት ወቅት ሰላት ግዴታነት፤ ዘካት ማውጣት፤ የረመዳን ወርን መፆም፤ ለወላጆች መታዘዝ ላኢላሃ ኢለላህ መሐመደን ረሱሉላህ ብሎ መመስከርን፤ የመሳሰሉትን መቃወም የላኢላሃ ኢለላህንና የተውሂድን አላማ ይቃረናል።ሁለተኛው፡ - የላኢላሃ ኢለላህን አላማ የሚያሟሉ ግዴታዎችን ያለማክበር ሲሆን ይህም ማለት ለምሳሌ በአማኙ ላይ የተውሂድ ፅናቱን የሚያዳክሙ አጉል እምነትና ሥራዎች ባብዛኛው ትንሹ ሽርክ በመባል ይገለፃሉ፤ ከነሱም ውስጥ የይዩልኝ ሥራ፤ ከአላህ ሌላ በሆነ ነገር መማል፤ አንድን ነገር በአላህና በእከሌ ፍላጎት ነው የተፈፀመው ማለት፤ወይንም ይህ ፀጋ ከአላህና ከእከሌ የተገኘ ነው ማለት፤ የመሳሰሉትን የተሳሳቱ ቃላቶችን መናገር የተናጋሪውን የተውሂድ እምነት ፅናቱን ከማናጋትም አልፎ የላኢላሃ ኢለላህን አላማ የሚያሟሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያለማክበር ይሆናል።ስለዚህ ተውሂድንና ኢማንን የሚቃረኑ ወይንም ምንዳውን የሚቀንሱ ተግባራትን መራቅና መጠንቀቅ ግዴታ ይሆናል። በአህለልሱና ዑለማዎች ዘንድ እንደሚታወቀው ኢማን በንግግርና በተግባር ይገነባል፤ ይኸውም ኢማን አላህን በታዘዙ ቁጥር ሲጨምር ወንጀል በተሰራ ቁጥር ይቀንሳል። ለዚሁም መረጃ ብዙ የእውቀት ባለቤቶች በአቂዳ ኪታቦች ላይ በሰፊው ስላብራሩት የሚፈልግ ሰው በቀላሉ ማግኘት ይችላል። ለአላህ ምስጋና ይድረሰው።በዚሁ ነጥብ ዙርያ አላህ በቁርአኑ ሲያብራራ፦

ትርጉም ፦ {{ (የቁርአን) ምእራፎች በሚወርዱበት ጊዜ (ከመናፍቃን) ውስጥ (አላጋጮቹ) የትኛችሁ ናችሁ ይህ (ምእራፍ) እምነታችሁን የጨመረው? እያሉ (ሲሳለቁ)፤ እነዚያ ያመኑት ግን (የቁርአን ምእራፉ በወረደ ቁጥር) እምነታቸውን ይጨምራል፤ ደስተኞችም ይሆናሉ።}} አተውባ - 124

ትርጉም ፦ {{ እነዚያ ሐቀኛ አማኞች አላህ በሚወሳበት ጊዜ ልቦቻቸው ይፈራሉ፤ (የቁርአን) አንቀፅ በሚነበብላቸው ጊዜ እምነታቸውን ይጨምርላቸዋል፤ በጌታቸውም ላይ ይመካሉ። }} አል አንፋል - 2

ትርጉም {{ እነዚያ (ወደ ኢስላም) ለተመሩት አላህ (ወደ መልካም ሥራ) ምሪትን ይጨምርላቸዋል፤(ለመጪው ዓለም) ቀሪ የሆኑት መልካም ሥራዎች አላህ ዘንድ የተሻለ ምንዳ ሲኖራቸው መመለሻቸውም ((በአኺራ)) ያማረ ነው።}}መልካም ሥራ በጨመረ ቁጥር ኢማን እንደሚጨምር የሚያብራሩ ሌሎችም ብዙ የቁርአን አንቀፆች አሉ። በመጨረሻ ስለ ላኢላሃ ኢለላህ ትርጉም የሚያብራራው አጭር መልእክት በዚሁ ይጠቃለላል።وصل الله على نبينا محمد واَله وصحبه .

ቱሕፈቱል አኽዋን ቢአርካነል ኢስላም ከሚለው ኪታብ የተወሰደ፦

ትርጉም ፡ - ሰይፈዲን ሐበሻ ያሲን

Post a Comment

0 Comments