Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጫት/Khat/

ጫት/Khat/

بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَـنِ الرَّحِيمِ

ጫት/Khat/

ጫት ቀይ ባህር አካባቢ ባሉ ሀገሮች የተለመደ የዕፅ አይነት ነው። ጫት በተለያዩ ሀገሮች የተለያየ ስም አለው ለምሳሌ በኢትዮዮጲያ-ጫት፣ በየመን-ጋት፣ በሶማሊያ-ቃት/ጃድ ሲባል ምዕራባውያን ካት(khat) እያሉ ይጠሩታል(Wiki..) ብዙ ሰዎች ጫትን ራሳቸውን ለማነቃቃት፣ ለማንበብና ጊዜያቸውን ለማሳለፍ …እንደመዝናኛም ይጠቀሙበታል። ጫት እንደ glycosides, tannins, more than 40 alkaloids, amino acids, vitamins, minerals & amphetamine, caffeine, Catharine, Cathinone, eduline and ephedrine (Gianniniet al, 1986) ያሉ ንጥረነገሮችን በመያዙ ሰውነታችን በተለይ አእምሮአችን ከሚችለው በላይ የሆነ ስራን እንዲያከናውን ይረዱታል። ሆኖም አዕምሮአችን ለጥቂት ጊዜ ፈጣን ከሆነ በኋላ በጫት ሱስ እየተጠመደ ይሄድና በስተመጨረሻ ያለ ጫት የማይንቀሳቀስ ፉርጎ ይሆናል። ምንም እንኳን ጫት የኢኮኖሚ ዋልታ እየሆነ የመጣ ቢሆንም ማህበረሰቡንና ሀገርን እያቆረቆዘ የሚገኝ መጥፎ መሳሪያም ነው። መጥፎ ስራን መቃወም ከእምነት ጭምር ነውና በጫት ላይ በተሰሩ ምርምሮች በመመርኮዝ የተወሰኑ የጫት ጉዳቶችን በማቅረብ ምን ያህል ጎጂና በኢስላምም የተወገዘ መሆኑን ለማሳየት እንሞክራለን። የጫትን ጉዳቶች ለመረዳት እንዲያመቸን ዱኒያዊና አኸይራዊ በማለት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዱንያዊ
በዚህ ርዕስ ስር ጫት በተጠቃሚውና በአካባቢው ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለማሳየት እንደሚከተለው ከፋፍለነዋል።

1, በገንዘብ ላይ
እንደሚታወቀው ጫትና ለማግኘት ገንዘብ ቁልፍ ነገር ነው። ሆኖም እንደኛ ባሉ ድሀ ሀገሮች ከአስፈላጊ ነገሮች አልፎ ተጨማሪ ለሆነ ፍላጎት የሚያበቃ የገንዘብ መጠን የለም። እናም ሰዎች ከልጆቻቸው አፍ በመንጠቅ ገንዘባቸውን ለጫት ሲያውሉ ይስተዋላል። በጅቡቲ 1/3 የሚሆነው ገንዘብ የሚወጣው ለጫት ነው።(Khan 1984)ይህ ደግሞ አባወራዎች አላህ የጣለባቸውን ቤተሰብን የማሰተዳደር ሀላፊነት ባለመወጣት ለተጠያቂነት ይዳርጋቸዋል።
ነቢዩ እንዲህ ብለዋል «ሁላችሁም እረኞች ናችሁ፤ ከረኝነታችሁም ትጠየቃላችሁ።»
በሌላ በኩል ችግረኞች እያሉ እነሱ ገንዘባቸውን በጫት ላይ ማዋላቸው ለተጠያቂነት ይዳርጋቸዋል። አላህ በቁርዐኑ አባካኞችን ከሸይጧን ጋር አቆራኝቷቸዋልና።
«አታባክን፣ አባካኝ የሸይጧን ጓደኛ ነውና»
2, በጤና ላይ
ጤና በአብዘኞቻችን እጅ ያለ ያላወቅነው ትልቁ ሀብታችንና ነው። ለዚህም ነው ነቢዩ በተለያዩ ሀዲሶቻቸው የጤናን ደረጃ የገለፁት። ጫት በቅድሚያ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትለው በጥርስ ላይ ነው። ጥርስ ራሱን መተካት የማይችል በመሆኑ በቀላሉ ከተጎዳ ዳግም ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ መጠገኑ የማይቻል ነው። ነቢዩም ጥርሳቸውን ከመንከባከብ አልፈው ተከታዮቻቸውንም ያዙ ነበር።«ባላጠብቅባችሁ ኖሮ በየውዱዑ በመፋቂያ አዛችሁ ነበር» ነቢዩ
በሌላ በኩል ጫት ውስጣዊ አካላት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከመጀመሪያው የከፋ ነው። ጉበት፣ ኩላሊትና የሽንት ፊኛ በጫት ኬሞካሎች  የሚጎዱ ሲሆን ከረጅም አመታት በኋላ እንደ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የስነልቦና ችግርና ሽንተ ማጥ ላሉ ከፍተኛና ብሎም ለሞት ለሚያደርሱ በሽታዎች ያጋልጣል።
በጫት ዙሪያ በተደረጉ ጥናቶች መሰረት ጫት በመተንፈሻ አካለት ፣ በደም ዝውውር አካላት፣ Gastrointestinal sys.፣ Hepatobiliary sys.፣ Genitourinary sys.፣ Obstetric effects፣ Metabolic and endocrine effects፣ በነርቭ አካላት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን ያስከትላል።
ይህ ብቻ አይደለም ጫት አእምሮን ክፉኛ የሚያደነዝዝ፣ በሱስ ከተያዙ በቀላሉ እንዳይላቀቁ የሚያደርግና ድብርትን የሚያመጣ ነው።(Kalix & Braenden,1985) ይህ ደግሞ ጤነኛ የነበረውን የሰዎች አስተሳሰብ አዛብቶ ለተበላሸ ማህበራዊ ህይወትና ለተቃወሰ ጤና ይዳርጋል። እንዲሁም በጫት ሱስ ተጠምደው ብዙ ጊዜያትን ያሳለፉ ወንዶች ስሜታቸው ይቀንሳል ብሎም ያጡታል።
3, በጊዜ ላይ
አረቦች ጊዜ ከወርቅ በላይ ነው ይላሉ። እውነት ነው፣ ጊዜ እጅግ ውድ ሀብታችን ነው። ብዙ ነገሮች በጊዜ ይወጠናሉ በጊዜ ይፈፀማሉ። ጊዜን በትክክል ካልተጠቀምንበት ግን በወቅቱ ማግኘት የሚገባንን ነገር እነድናጣና ብሎም ለኪሳራ እንድንዳረግ ያደርግናል። አንዱ ተጠቃሽ ጫት ነው። ሰዎች ጧት ተፍ ተፍ ሲሉ ቆይተው ስራው ሳያልቅ ከሰዐት ግን ለጫት ሲቀመጡ ይስተዋላል። ሌሎች ደግሞ ጧቱኑ ሲጠምዱት ይታያሉ። ይህ ስራቸውን በጊዜ ፈፅመው ኖሮአቸውን እንዳያሻሽሉ የሚያደርግ የድህነት ማነቆ ነው። ይሀ ችግር እስካለ ድረስ ደግሞ ምርታማነት ያሽቆለቁላል።(Giannini et al)
በሌላ በኩል ጫት፣ ሰው በጊዜው ለአኸይራ ቤቱ የሚሆን ስንቅ እንዳይሰንቅ ያደርገዋል። ይኸኛው ከቀደሙት የባሰ መጥፎ የጫት ገፅታ ነው። ጊዜያችንን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ አላህ ዘንድ ከሚጠብቁን አራቱ ጥያቄዎች ሁለቱን መመለስ አልቻልንም ማለት ነው። አንዱ ሀብትህን በምን አዋልከው? የሚልና በጊዜህ ምን ሰራህበት? በጫት…..
4, በቤተሰብ ላይ
በቤተሰብ መዋቅር ውስጥ የቅድሚያውን ቦታ ሚይዙት ወላጆች ናቸው። ወላጆች ወልደው እንደማሳደጋቸው ሁሉ ምንም እንኳን ሀቃቸውን ባይመልስም እነርሱን ማገልገል መርዳት እና ለነርሱ ዝቅ ማለት በቁርዐን የተጣለብን ግዴታ ነው።      «…ለወላጆቻችሁም መልካም ስሩ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸውንም ይሁን ሁለታቸውን ኡፍ አትበላቸው አትገላምጣቸውም መልካም ቃልም ተናገራቸው» ኢስራዕ 23
ሆኖም ጫት መንከባከብ የሚገባንን ቤተሰቦቻችንን እንድንረሳና ቁርዐንን እንድንጥስ ምክንያት ይሆነናል። ይህን እየተመለከቱ የሚያድጉት ታናናሾቻችንም ከዚህ በከፋ መልኩ ስርዐት አልባና ጋጠወጥ እንዲሆኑ በር ይከፍታል።
ሚስት ሌላዋ ተጠቂ ናት። ባሏ የጫት ሱሰኛ ከሆነ ለልጆቹም ሆነ ለርሷ ማድረግ የሚገባውን እንክብካቤ አይፈፅምም። ከዚህ በተጨማሪም የሚስቱን ሀቅ ሊያጓድልና ግዴታዎቹንም ሊዘነጋ ይችላል። ይህ ደግሞ በቤተሰብና በግለሰቡ ላይ የሚያሳድረው ስንልቦናዊ መቃወስ ይህ ነው ተብሎ የሚገለፅ አይደለም። ልጆችም በለጋነታቸው ሱሰኞች የሚሆኑበት አጋጣሚም ይከሰታል። ሲገፋ ደግሞ ቤተሰብ እስከ መበተንም ይደርሳል። በጅቡቲ ከሁለት ፍቺዎች አንዱ በጫት ምክንያት እንደሚከሰት ያውቃሉ? (Elmi, 1983)
አኸይራዊ
በዚህ ርዕስ ስር ጫት ምን ያህል አኸይራችንን ሊጎዳ እንደሚችል እናያለን። በቅድሚያ በሶላት ዙሪያ የሚያስከትለውን ችግር እንመልከት።
1, ከሶላት ጋር በተያያዘ
በአብዘኛው የጫት ሱሰኛ የሆነ ሰው አንድ ጊዜ ከተቀመጠ በኋላ እስከሚረካ ለምንም ቢሆን ዳግም መነሳቱ ይከብደዋል። ይህ ባህሪ ደግሞ ቀርተዋል(ስለዲን ዕውቀት አላቸው) የሚባሉ ሰዎች ላይ ሳይቀር የሚስተዋል ነው። እንግዲህ ጫትን እያቃመ ያለ ሰው ሶላት ሲደርስ ተነስቶ መስገድ ከከበደው አደጋው እዚህ ጋር ነው። በብዛት ሰዎች ጫትን የሚቅሙት(የሚፈርሹት) ከዝሁር በኋላ ሲሆን በምርቃና ተውጠው የአሱር ሶላት ሲያልፋቸው ይስተዋላል። ትንሽ ጠንካራ የሚባሉት ጀመዐ ቢያመልጣቸውም ተነስተው በሰዐቱ የሚሰግዱ ሲሆን ሌሎቹ ግን ሶላታቸውን አዘግይተው ሲሰግዱ ጥቂቶች ደግሞ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ከመግሪብ ጋር ያዳብሉታል። ይህ ችግር የሰዎችን ዘልዐለማዊ ቤት ክፉኛ የሚጎዳ ነው። አላህ ግን የአሱር ሶላትን እድንጠባበቃት አዞን ነበር።
«በሶላታችሁ ተጠባበቁ በተለይ በመካከለኛይቱ ሶላት፤ ታዛዦች ሆናችሁ ለአላህ ቁሙ» ቁርዐን
2, ከፆም ጋር በተያያዘ
ከፆም ጋር በተያያዘ ጫት ያለው ሁኔታ አስገራሚ ነው። በሀገራችን ሆን ተብሎ ይመስል ከሱና ፆሞች ጋር በተያያዘ ጫት ሲቃም ይስተዋላል። በቅድሚያ የሚታወሰን ሰኞ ነው። ነቢዩ የተወለዱበት ቀን መሆኑን በመግለፅ ፁመውት፣ ሌሎችም እንዲፆሙት አዘው ነበር። ነገር ግን ከነቢዩ በተቃራኒ ሰዎች ሰኞ ቀንን በመብላትና ጫት በመቃም ሲያሳልፉት ምን ይባላል?
ሌላው ሀሙስ ቀን ነው ነቢዩ ይህንንም ቀን እንዲፆም ሲገፋፉ ሰዎች ግን በተለይ ለሊቱን በመቃም ሲያድሩ ይስተዋላል። ነቢዩ የጁሙዐን ምሽት(በኛ ሀሙስ ማታ) ብቻ ነጥሎ በኢባዳ ማሳለፍን ሲከለክሉ ሰዎች ግን ኢባዳውንም ትተው በባሰ ሁኔታ ከጫት ጋር ሲጋተሩ ያድራሉ። ነቢዩ ይህን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን?
ከዚህ በተጨማሪ አመት ጠብቀው የሚመጡ የሱና ፆሞችን ምክንያት በማድረግ ሰዎች ለመቃምና ለመብላት ሲሯሯጡ ይታያሉ። ለምሳሌ ነቢዩ የዐሹራ ቀን እንዲፆም እንጂ እንዲበላበትም ሆነ እንዲከበር አላዘዙም ሶሀቦቻቸውም አላደረጉትም። ነገር ግን አንዳድንድ አካባቢዎች ያለ ምንም ማስረጃ እንደ በዐል ሲያከብሩትና ከነቢዩ በተቃራኒ ሲፈፅሙ ይስተዋላል። ግን ለምን?
አቡ ነጂ አል ኢርባዲ እንዳስተላለፉት ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል «…በሀይማኖት ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችን ተጠንቀቁ። ምክንያቱም አዲስ ነገር ሁሉ ፈጠራ ነው፣ ፈጠራ ሁሉ ደግሞ ጥመት ነው፣ ጥመት ሁሉ ደግሞ ለእሳት ይዳርጋል።» አቡዳውድ ዘግበውታል
ረመዳን ላይ የጫት ታሪክ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። ቀኑን ፆሞ የዋለው ሰው የጫት አምሮቱን የሚወጣው ለሊቱን እየቃመ በማደር ነው። ነቢዩ በረመዳን ለሊቱን በኢባዳ ህያው ያደርጉ ነበር፤ እኛ ደግሞ በጫት እያጨለምነው ነው። በዚህ ቢበቃ ጥሩ ነቢዩ አበክረው እንድንመገብበት የነገሩንን የሱሁር ሰዐት አሳልፈው በባዶው የሚፆሙ ብዙ ናቸው። እንደ ማምሸታቸውም ሱብሂን ከነጋ በኋላ የሚሰግዱም አሉ። ይህ ፆመን ለአኸይራችን መሰነቅ ሲገባን ጫት ግን አቅጣጫችንን ቀይሮ ለቅጣት እየዳረገን እንዳለ ያስገነዝበና:
3, በጫት ሳቢያ የሚከሰቱ ወንጀሎች
በጫት ሳቢያ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የትየለሌ ናቸው። ቢሆንም ራሳችንን ከጫት ለማራቅ ይረዳን ዘንድ የተወሰኑትን ልጥቀስ። በመጀመሪያ ጫት የሚቅም ሰው የሚፈፅመው ከምላስ ጋር በተያያዘ ነው፤ ብዙ ሰዎች በጫት ሰክረው እውነቱንም ውሸቱንም እየቀላቀሉ እያጋነኑ ሲናገሩ ይስተዋላሉ። ይህ ደግሞ ለማይታመኑና አቅል የማይቀበላቸው ታሪኮች መፈጠር ምክንያት ነው። ሌሎች ደግሞ እንዳሻቸው የወንደሞቻቸውን ስም እያነሱ ሲጥሉ ሲያሙና ሲያንቋሽሹ የአላህን ቃል ሲጥሱ ይገኛሉ።
ጫት ለከባባድ ወንጀሎችም ያጋልጣል። በተለይ ወንዶችና ሴቶች እየተቀላቀሉ በሚቅሙባቸው ቤቶች በጫት ገፋፊነት አስከፊ ቅጣትን የሚያስከትሉ የዝሙት ወንጀሎች ይፈፀማሉ።
«ዝሙትን አትቅረቡት፤ እርሱ በእርግጥ መጥፎ ስራ ነውና መንገድነቱም ከፋ» አል-ኢስራዕ፡32
ሌላው ጫት በሚቃምበት ወቅት የሚፈፀሙ አንዳንድ የምርቃና ኢባዳዎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ሲያመዝን ይስተዋላል። ብዙ ጊዜ የሚፈፀሙት ሶለዋት ማውረድ ዱዐ ማድረግና የመሳሰሉት ሲሆኑ መሰረታቸው ጥሩና የሚደገፍ ቢሆንም አተገባበራቸው ችግር እያስከተለና ከነቢዩ ሱና እያፈነገጠ ይገኛል። ለምሳሌ ሶለዋት የሚደረገው ለብቻ ሆኖ ሳለ ሰዎች ተጠባብቀው በአንድነት ሲፈፅሙና ከነቢዩ ትዕዛዝና ከሶሀቦቻቸው ስራ ያፈነገጠ የቢድዐ ተግባር ሲያደርጉ፤ ዱዐ ሲደረግ ደግሞ ለአላህ ተናንሰንና ድምፃችንን አሳንሰን መሆን ሲገባው ጫት ላይ ግን ከፍ ባሉ ድምፆች አላስፈላጊ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም በዱዐ ላይ ድንበር ሲታለፍ ይታያል። ይህ ደግሞ አይቀጡ ቅጣትን የሚያስከትል ወንጀል ነው።
እንዲሁም ጫት አንዳንዴ መጤ በዐላትን ታኮ ስለሚመጣ በሱስ ምክንያት የነዚህ ቢድዐ ተግባራት ተሳታፊ ሊያደርገን ይችላል።
የምዕመናን እናት ኡሙ ዐብዲላህ(ረ.ዐንሀ) እንዳወሩት ነቢዩ እዲህ ብለዋል «የእኛ ትዕዛዝ የሌለበትን ድርጊት የሰራ እርሱ(ስራው) ውድቅ ነው።» ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
4, ከሽርክ ጋር በተያያዘ
ከጫት ጋር በተያያዘ ከሚነሱት ጉዳቶች ሁሉ አስከፊው የሽርክ ወንጀል ነው። ሽርክ ከኢስላም የሚያስወጣ የዘልአለማዊውን ህይወት የሚያጨልምና ለዝንትአለም እሳት የሚዳርግ አስከፊ ወንጀል ነው። ሸይጧን ግን ሰዎችን ወደ እሳት ለመዶል ካለው ከፍተኛ ፍለጎት የተነሳ ጫትን ታኮ ሰዎችን ወደ ሽርክ እየጨመራቸው ይገኛል። በጫት ላይ በሚነገሩ የሐሰት ታሪኮች በመማረክ ብዙዎች ወደ ሽርክ ገብተዋል እየገቡም ነው። እነዚህ ቂመሐ ላይ የሚነገሩ ታሪኮችና ጀብዱዎች በጫት የተበረዘውን የሰው አእምሮ ታሪኩ ለተወራለት ሰው(ጂን፣ወሊይ፣ ሸህ…) ተገዥ እንዲሆን ብሎም ይረዱኛል በሚል ስሜት እነርሱን እንዲያመልክ ያደርገዋል። በእንደዚህ አይነት ወንጀል ላይ ደግሞ አላህ ምህረት የለውም!!!
«አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውን(ኃጠዐት) ለሚሻው ሰው ይምራል» አል-ኒሳዕ፥48
በአላህ ፈቃድ መጠነ ሰፊ ከሆነው የጫት ጉዳት የተወሰነውን ለማሳየት ሞክረናል። ከላይ እንደቀረበው ጫት በግለሰቦች፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና ብሎም በሀገር ላይ ውድቀትን የሚያመጣ መሆኑን ተረድተናል። ዋናው ጉዳይ ስለጫት ማወቃችን አይደለም ይልቁንም ራሳችንን ከጫት እንዴት ማራቅ እንችላለን የሚለው ላይ ነው። በአላህ ወይም በነቢዩ ቀጥታ ካልተነገረ በስተቀር አንደን ነገር ሀላል ወይም ሀራም ማለት ክልክል ነው።
«በአላህ ላይ ውሸትን ልትቀጣጥፉ ምላሶቻችሁ በሚመጠኑት ውሸት ይህ የተፈቀደ ነው፣ የህ እርም ነው አትበሉ» አል-ህል፥116 ይሁን እንጂ ኢስላም እንደ ጫት ባሉ ነገሮች ራስን መጉዳት አስቀድሞውኑ ከልክሏል፤ ከሚያመጡት ውጤት አንፃር። ለዚህ ደግሞ ከላይ የዘረዘርናቸው የጫት ጉዳቶችና ውጤቶች በቂ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ አላህና መልዕክተኛው ኸምርን ከልክለዋል። ኸምር ሚለው ቃል ኸመረ ከሚለው ስርወ ቃል የመጣ ሲሆን አእምሮን የሚሸፍን ማለት ነው። ቃሉ በመጠጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። አስካሪ እስከሆነና ከአቅል ውጪ እስከሚያደርግ ድረስ የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር በዚህ ውስጥ ይጠቃለላል። እናም ጫት ሰዎችን ከኖርማል አስተሳሰብ አውጥቶ የሚያናውዝ በመሆኑ በዚህ ክልከላ ውስጥ ይካተታል ማለት ነው።
«እናንተ ሰዎች ሆይ! በምድር ካለው ነገር የተፈቀደ ጣፋጭ ሲሆን ብሉ።» አል በቀራህ፥168
ሰዎች ሆይ! ጫትና መሰል ነገሮችን በመጠቀም ህይወታችንን ለዱኒያም ሆነ ለአኸይራ ኪሳራ ከምንዳርጋት አላህ በሰጠን የተፈቀደ ነገር እንብቃቃ!!! መልዕክታችን ነው።

Post a Comment

0 Comments