★★★★★ ~ ተማፅኖ ~ ★★★★★
* ጌታዬ! *
አንተን አልኩኝ’ንጂ ሁሉን እማዋየው
ሰውማ ፍጡር ነው
የውስጤን፣
የሆዴን
ብሶቴን ማን አየው?!
* ረቢ!! *
ሰላሙ፣ ከሪሙ፣ ሁሉን ቻዩ ጌታ
አግዘኝ፤ ፍቀደኝ
ኢማኔ እንዲፀና ውስጤ እንዲበረታ።
* አንድየ! *
ረሕማኑ ረሒሙ፣ ለጢፉ፣ ኸቢሩ፣
ሸክሜ ከብዶብኛል፣
ሰውነቴ ዝሏል፣ የወንጀል ክምሩ
እባክህ ገላግለኝ፣
እጠበኝ፣
ፈውሰኝ፣
አዛኙ፣ ገፉሩ።
* ኢላሂ! *
ሙእሚኑ፣ መቲኑ፣ ዐሊሙ፣ ሐኪሙ
ወዱዱ፣ ሶመዱ፣ ሐሊሙ፣ ቀዩሙ
እባክህ ራራልኝ
መሸሻ፣ መጠጊያ፣
ተስፋ፣ መከታዬ ያላንተ ማን አለኝ?!
* ጎፍታኮ! *
ፋጢሩ፣ ሻኪሩ፣ ጀባሩ፣ ቃዲሩ
ነሲሩ፣ በሲሩ፣ ከቢሩ፣ ቃሂሩ
ጉልበተኛው በዛ፣ አቅማችን ኮሰሰ
ጉልበቱን ተማምኖ፣ ወገኔን ጨረሰ
አደርገው ቢጨንቀኝ እንባየ ፈሰሰ።
* አምላኬ! *
አንድ አርገን በተውሒድ፣ ሰብስበን በሱንና
አድለን ሰኪና፣ አርቀህ ፈተና
"መታ ነስሩላሂ?" የሚል በዝቷልና።
(ኢብኑ ሙነወር፣ መጋቢት 7/2010)
0 Comments