① አፄ ቴዎድሮስ ሙስሊሞች ላይ የነበረው የከረረ አቋም ሲነሳ ቂምና ጥላቻን እንደመዝራት የሚሰብኩ ሰዎች ተመሳሳይ አመክንዮ ተጠቅመው አሕመድ "ግራኝ"ን ከመኮነን አይመለሱም። እንዲያውም ከጀኔራል ናፒየር በመተባበር አፄ ቴዎድሮስ ላይ ያሴረውን አፄ ዮሐንስን ከመኮነን አያመነቱም።
② በሙስሊሞች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈፀመውን አፄ ዮሐንስን መቃወማችን የሚከነክናቸውና ይህን ማንሳት አግባብ እንዳልሆነ የሚሰብኩ "ሆደ ሰፊዎች" አፄ ምኒልክ በአፄ ዮሀንስ ላይ ወይም በትግራይ ህዝብ ላይ ይህን ፈፅሟል እያሉ ከመዘርዘር አያመነቱም። እዚህ ላይ ስራቸው ህዝብና ህዝብ ያቃቅራል ወይስ አያቃቅርም የሚለው አያሳስባቸውም። ምክንያታቸው ታሪክ ሊደበቅ አይገባውም የሚል ነው። የታሪክ ተቆርቋሪዎች ሆይ! የኛስ ታሪክ ይደበቅ?
③ አፄ ሃይለ ስላሴ በሙስሊሞች ላይ የፈፀማቸው ሸፍጦች ሲነሱ የሚጎረብጣቸው የሃገር ፍቅር ሰባኪዎች በነ በላይ ዘለቀ ላይ የፈፀመውን በደል ለመኮነን ግን አያመነቱም። ይህንን የተዘነበለ የታሪክ እይታ ተመልከቱ።
በኢትዮጵያ አፄዎች በርካታ ሃይማኖታዊ ጭቆናዎች ተፈፅመዋል። የፈጠራዎቹን ወደጎን ብንተውም ቀላል የማይባሉ ተጨባጭ ብሄር ተኮር አፈናዎች እንደነበሩም ብዙ መረጃዎች አሉ። እነዚህ ታሪካዊ ጠባሳዎች ተዳፍነው ይቅሩ የሚሉ ጭንቅላቶች ዛሬም ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም። እኔ የብሄሬ ጉዳይ አያሳስበኝም። የሚያሳስባቸውንም ልክ እስካላላፉ ድረስ ተሳስተዋል ብየ አላምንም። ባይሆን እኔ በእምነታቸው ሳቢያ እልቂትና አፈና የተፈፀመባቸው ወገኖቼን ታሪክ ሊያፍን የሚዳዳው የታሪክ ወንበዴ ከየትኛውም ብሄር ቢመጣ ማየት አልፈልግም። እንደኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈፀሙ ብሄር ተኮር ጭቆናዎች ይልቅ ሃይማኖት ተኮር የሆኑት ይበልጥ የጎሉም የመረሩም እንደሆኑ አምናለሁ።
ሙስሊሙ አማራ ሆኖም ከሌሎች ህዝቦች በባሰ በአማራ ገዢዎች ተበድሏል። የወሎና የጎንደር ሙስሊሞች ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ናቸው። ሙስሊሙ ትግሬ ሆኖም ከሌሎች ህዝቦች በባሰ በትግሬ ገዢዎች ተጨቁኗል። ሙስሊሙ ኦሮሞም ከሌላው ኦሮሞ የባሰ ግፍ አስተናግዷል።... የኢትዮጵያን ታሪክ በስሱ ያገላበጠ ይህን በቀላሉ ያስተውለዋል። (ሙስሊም ያልሆኑትም ተበድለዋል። ግና በሙስሊሞች ላይ የነበረው የተለየ ነበር።) በርካታ ትናንትናውያን ግን ኤለመንታሪ የታሪክ ፋይዳዎን እንኳን በመዘንጋት በሌሎች ታሪክ ላይ ሊረማመዱ ይሻሉ። ስለሙስሊም አባት አያቶቻችን ታሪክ ስንፅፍ ከታሪክ አጻጻፍ ደንብና ስርኣት አንፃር እንጂ ማንም ከብሔር መነሻ እንዲገመግመን ልንፈቅድለት አይገባም። ታሪክን ለቂምና ለእልቂት ፍጆታ መጠቀም የሚሻ አካል ካለ ከይሲ ነው። ታሪክን እየመረጠ ሊፅፍ እየመረጠ ሊያዳፍን የሚሻ ካለም ተረት እና ታሪክ የማይለይ የታሪክ አተላ ነው።
