Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሰዎች መብት ይከበር!
የመብት አርበኞች ሆይ! "የሴቶች" "የወንዶች" እያላችሁ ውሃ አታላምጡ። ወንጀል ወንድም ይፈፅመው ሴት ወንጀል ነው። በደል በወንድም ይፈፀም በሴት በደል ነው። ግፍ ፆታ የለውም። ስለዚህ ፍትህም ፆታ አይኑረው።
በዚች ምድር ላይ በወንዶች ከሚበደሉ ሴቶች የማያንሱ በወንዶች የሚበደሉ ወንዶች አሉ። ልክ እንዲሁ በሴቶች የሚበደሉ ሴቶች ፣ በሴቶች የሚበደሉ ወንዶችም ብዙ ናቸው።
ባጭሩ የሰው ልጅ በፆታው ሳይሆን በሰውነቱ ይከበር። ወንጀለኛም በፆታው ሳይሆን በወንጀሉ ልክ፣ ሌሎችን በሚያርም መልኩ ይቀጣ።
ሴቶች ሆይ! የተበደለችው ሴት፣ የበደላት ወንድ ስለሆነ ብቻ አታራግቡ። ይልቁንም ወንጀሉን ከመስፋፋት የሚገታ ተገቢ ቅጣት ስለሌለ ጩሁ። ወንዶች ሆይ! "ዘመናይ" ለመባል ሳይሆን ነግ በኔ ብለህ ሰብአዊነት ተሰምቶህ ጥፋቶችን በመቀነስ ላይ ትጋ።
ምናይነት ልክፍት ነው የነካን? እያንዳንዱን ጉዳይ ቡድናዊ ቀሚስ ካላለበስነው አይደምቅልንምሳ?
ሁለት ሰዎች ቢጣሉ ብሄራቸው ተመዝዞ "የእከሌና የእከሌ ብሄር ተጣሉ" ብለን እናጉነዋለን። ልክ የአንድ ብሄር ሰዎች እንደማይጣሉ። በፆታ ሲለያዩም እንዲሁ ነው። በእርግጥ ፆታዊ ወንጀልን በዚህ መልኩ ከመግለፅ ውጭ ምርጫ ሊጠፋ ይችላል። ነገር ግን ወንጀሉን ስናወግዝ፣ መፍተሄ ስንፈልግ ወዘተ ሰብአዊ ቅርፅ ከመስጠት ይልቅ ፆታዊ ቅርፅ መስጠቱ በሚወጡ ህጎችና ፖሊሲዎች ላይ ተፅእኖ እንዳያጠላባቸው፣ ስሜታዊነት እንዳይጫጫናቸው ያሰጋል። ሌሎች የጎንዮሽ መዘዞችንም ያስከትላል። ከንቃተ ህሊና ዘመቻ እስከ አፈፃፀም ድረስ የወንዱን የተባባሪነት ስሜት በስሱም ቢሆን ይጎዳል።ጉዳዩንም ከሰብአዊ ጉዳይ ይልቅ ዘመን አመጣሽ የምእራብ ወረርሽኝ አድርጎ የመመልከት እድሉ ሰፊ ነው።
ኤድስ ለብዙ ሰዎች መቅሰፍትን እንዳመጣው ሁሉ ለብዙ ሰዎች ደግሞ እንጀራ አምጥቶላቸዋል። ስገምት የሴቶች መብት ጩኸትም በከፊል ተመሳሳይ ቅኝት ያለው ይመስለኛል። ለከት ባጣ የሴቶች መብት ጩኸት መንሰኤ ቤታቸውን ያፈረሱ፣ ትዳራቸውን የናዱ፣ ልጆቻቸውን የበተኑ ብዙ ናቸው። በተያያዥ ጩኸት አዙሪት ለፍርድ ቤት ጣጣና ምልልስ፣ ለጠበቃ፣ ለጉቦ የሚወጣውም በቀላል የሚተመን አይደለም። አንዳንዶቹ ከመብት ትግልም አልፈው በሁለቱ ፆታዎች መካከል ያለውን ልዩነት በመዘንጋት አጉል ለወንድነት እየዳከሩ ነው።
በሌላ በኩል የሴቶች መብት ትግል በሚሉት መሰላል በመንጠላጠል ወፍራም እንጀራ የጋገሩ፣ አመዳም ፊታቸውን ያወዙ፣ ያዘመመች ጎጇቸውን ያቀኑ ብዙ ናቸው።
ላንዱ ፍዳ
ለሌላው ፍሪዳ!


Ibnu Munewor