Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የማስታወቂያ ፈገግታዎች!! “እስኪ ፈገግ!” “እኝ” ቀጭ!


የማስታወቂያ ፈገግታዎች!!
“እስኪ ፈገግ!”
“እኝ”
ቀጭ!
ከዚያም ፎቶው “ፈገግታ ሱና ነው!” ወይም ደግሞ “ኢስላምን በወሬ ሳይሆን በተግባር ያስተማረ” ከሚል መሪ ቃል ጋር ይለጠፋል፡፡ አሁን የዚህ ፎቶ ፋይዳ ምንድን ነው? የተሰጠው ርእስ አላማስ?” ከተባለ ገበያ መፍጠር ነው፡፡ አለቀ፡፡ ምን አይነት ገበያ?! ሁለት አይነት ገበያ!!
አንዱ፡- እራስን ይበልጥ ማስተዋወቅ ነው፡፡ “ሳቂታው”፣ “ገራገሩ”፣ “ፈገግታው ይበቃል”፣ “ቁንጅናው”… እንዲያውም አንዳንዱ ሜካፕ ሳይቀር የሚጠቀም አለ፡፡ ከዚያም አንዳንድ እፍረት የቀለላቸው ሴቶች “ውይ ሲያምር” “የኔ ቆንጆ” እያሉ ያዥጎደጉዱለታል፡፡
ሁለተኛው አላማ፡- ማሳጣት ነው፡፡ የዘመኑ የገበያ ስልት “my tyota is fantastic” አይነት ማስታወቂያ ላይ አይቆምም፡፡ “ኒሳን ጥሩ መኪና አይደለም” አይነት ሌሎችንም ከሚያሳጣ ማጀቢያ ጋር እንጂ፡፡ ስለዚህ “በወሬ ሳይሆን በተግባር ያስተማረ” የምትለዋ ሃረግ ዛሬ ዛሬ እየተደጋገመች ያለች “ቅመም” አላማዋ ይሄ ነው፡፡ ከላይ ሲያዩዋት ተግባራዊነትን ማድነቅ ትመስላለች፡፡ አንድምታዋ ግን የሚጠሏቸውን አካላት “ወሬ እንጂ ተግባር የላችሁም፡፡ ስለዚህ ዝም በሉ” መልእክት እንዳላት አዋዋሏ አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ “እናንተ በተግባር ያላየናችሁ በአስተሳሰብ መስመር ከኛ የምትለዩ ወሬኞች ሆይ! መስመራችሁ ከመስመራችን ጋር እስከሚስማማ ድረስ ፀጥ ረጭ በሉ!!” ነው መልእክቷ፡፡ ወይም ደግሞ “እነዚህ ወሬ ብቻ ናቸው እንዳትሰሟቸው” ማለት ነው፡፡
መድረክ ላይ “ተቀናቃኞቻቸውን” በሃሰት ከሚወነጅሉ፣ የሀሰት “ገጠመኝ” እየፈጠሩ በውሸት ከሚደልሉ ቀጣፊ “ዱዓት” ጀምሮ አፉን ከፍቶ እስከሚሰማቸው ታዳሚ ድረስ ይሄ ሌላውን “ወሬ ብቻ” እያደረጉ የመሳል ውንጀላ በሰፊው ይታያል፡፡ ግና እነዚህ ሰዎች ብዙ እውነታዎችን ዘንግተዋል፡-
1. ስለጠሉ ብቻ ያለ እውቀት እየወነጀሉ ነው፡፡ እንጂ የእያንዳንዱን ሰው ውሎ ምን አሳወቃቸው?
2. ጥላቻ ስለጋረዳቸው እንጂ ማስተማርም ስራ ነበር እኮ፡፡
3. ጭፍን ውዴታ ስለጋረዳቸው እንጂ የሚያደንቋቸውም ሰዎች ከሚቿቸው ሰዎች የተለየ የሚታይ ሚና የሌላቸው በሽ ናቸው፡፡
4. ደግሞም “ወሬ ብቻ” እያሉ ከሚወነጅሏቸው ውስጥ ከደዕዋ ስራ ውጭም የሚደንቅና ዘርፈ ብዙ የኸይር ስራ ተሳትፎ ያላቸው ብዙ አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል በማህበራዊ ሚዲያና ምድርም ላይ በሰፊው የሚብጠለጠል አንድ ወንድማችንን ብንወስድ እኔ እንኳን ባረጋገጥኩት ወላሂ ብዙ ኸይር ስራዎችን ይሰራል፡፡ “ችግሩ” ግን ለካሜራና ለገበያ አላቀረበውም፡፡ በሌላ አነጋገር ለነዚህ “ወሬ ብቻ!” እያሉ ለሚኮፈሱ ደረጃ መዳቢዎች የስራውን ሪፖርት አላቀረበም!! እና ምን ማለት ፈልጌ ነው?! ስለማናውቀው ነገር አናውራ! የግድ መተቸት ካሰኘን ከመዋሸት ይልቅ የምናውቀውን ተጨባጭ ጥፋት መዝዘን እናውጣ፡፡
ከነዚሁ የውሸት ጥሩምባ ነፊዎች የሚጠቃለሉት “ቅድሚያ ለተውሒድ የሚለው ከመፈክርነት አልፎ መሬት ላይ ይውረድ” የሚሉ አስመሳዮች ናቸው፡፡ እነሱ እራሳቸው ከሚያብጠለጥሏቸው ሰዎች የተሻለ ቀርቶ የሚቀራረብ ሚናም የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሰው ሲጠላ ያለን ይሸፍናል፡፡ የሌለን ይለጥፋል፡፡ የዘመኑ የራስን ሰው ማድመቂያ አይነተኛ ስልት ሌሎችን በውሸት ጭምር ማብጠልጠል ሆኗል፡፡ እንጂ አሁን በአላህ ሌላው ሁሉ ቢቀር በየቤቱ በገፍ የሚደመጡ የመንዙማ ጉዳጉዶችን እየመዘዘ ለስንቶች ንቃት ሰበብ የሆነው ማነው?! ይሄኮ ብዙዎቻችንን ከተጠያቂነት ያተረፈ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ለእውነት መወገን ቢያቅተን ቢያንስ ለውሸት ባናጨበጭብ ጥሩ ነው፡፡


Ibnu Munewor