ወደ ተውሒድ፣ ሱና እና መንሀጀ ሰለፍ የሚጣሩ ሰዎች ለአላህ ሲሉ መታገስ ግድ ይላቸዋል፡፡
የአላህ ባርያዎች ሆይ! ዳእዋ ማድረግ ማለት አርቲስትነት አይደለም፡፡ ሂሳብ ከፋዩ አላህ ነው፡፡ ሃቅ ከምንም በፊት ሊቀደም ይገባዋል፡፡ ሰዎች ደስ የሚላቸውን አርስት ብታነሳ ሁሉም ደስ ይለዋል፡፡ ግን ዳእዋ አላህ እና መልክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ባዘዙት ደረጃ፣ እርከን፣ ተቀዳሚ እና ተከታታይ መሰረት በጥበብ የሚፈጸም አምለኮ እንጂ የሰዎችን መደሰት እና አለመደሰት የምናዳምጥበት አይደለም፡፡
አብዛኛው ሰው ለምሳሌ
- ሴቶች ባሎቻቸው ሲመከሩ በጣም ደስ ይላቸዋል፡፡ ግን ሂጃብሽን አስተካክይ፣ ፊልም አትይ፣ ሜክ አፕ አትቀቢ፣ ዙረት አታብዢ ከተባለች “ጨፈጨፈን እኮ ይሄ ሰውዬ” ይላሉ፣
- ወንዱም በበኩሉ ስለማግባት ስለመሳሰለው አርስት ሲወራ በተለይ መሀር ሊወደድ አይገባም ሴቶች በቀላሉ ትዳር ውስጥ ሊገቡ ይገባል ሲባል ወንዶች ጮቤ ይረግጣሉ፡፡ አይ ኡስታዝ በጣም ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እኮ ናቸው ይላሉ፡፡ ግን አገራችን ላይ ያለውን ሽርክ (በአላህ ላይ ማጋራት) ጫን ብለው ከተናገሩ “አጥባቂ፣ ሰው አባራሪ፣ ጥበብ የሌላቸው” እና የመሳሰለውን ይባለሉ፡፡
- አባትም የራሱ መብት ሲነገረው ጮቤ ይረግጣል፡፡ እንዴት አይነት አንደበተ ርቱእ ዳኢ መሰላችሁ ይላል፡፡ ወድያው በአላህ ላይ አታጋሩ ሸህ እገሌ ድረሱልኝ አትበሉ አላህን ብቻ ለምኑ ተብሎ ምክር ሲሰጥ “ወሃብዬች፣ ወልዬችን የማይወዱ፣ ቀብር አትዘይሩ የሚሉ” እና ብዙም እያሉ የውሸት ክስ ይከሳሉ
- አህባሽን በማስረጃ ስታንኮታኩትለት በጣም ጮቤ የሚረግጠው ሰው አንድ ልቡ የታመመ ኡስታዝ ብሎ የሚከተለው ሰው “1000 ገጽ ኪታብ ከመጻፍ 1 ሰኣት ፊልም ፓወር አለው” ያለው አባባሉ ሸሪኣን ይጋጫል፡፡ ይሄ ኡማውን ከዲን አርቆ ወደ ፊልን መጣራት ነው ስትለው “ኡማውን በታተናችሁት” ይልሃል፡፡
- ሃብታሞች ዘካ ክፈሉ ሲባሉ አብዛኛው ሰው ሀብታሞች ላይ የሚታዘዘው ትእዛዝ ደስ ይለዋል፡፡ ከዛም አልፎ “ሀብታሞች እኮ ዘካቸውን አስተካክለው ቢከፍሉ አለም ላይ አንድም ድሀ ባልኖረ” ይላሉ፡፡ ሀብታሞች እንዲህ አላደረጉም “ዘካቸውን በአግባብ አልከፈሉም” ብሎ አፉን ሞልቶ የሚተቸው ሰው በተገላቢጦሹ “እገሌ እኮ ሰሃባ ይሳደባል ተጠንቀቁት” ሲባል እንዴት የሰው ስም ታነሳላችሁ? ሲል ገንዘብን አስመልክቶ ሃብታሞችን በመተቸት አስተያየት የሰጠው ሰው ሰሃባ አይሰደብ ሲባል ግን ሚዛኑን ገልብጦት “እንዴት ሰው ታማላችሁ፣ እንዴት ሰው ትተቻላችሁ” እያለ የዚህን ኡማ ምርጦች ለሚሳደብ ሰው ጥብቅና ይቆማል፡፡ አላሁል ሙስተኣን
ዋናው ከዚህ አርስት ጋር የፈለኩት የሚከተለውን አጠር ያለ ምክር ነው፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው አንስቶ እስከሩቅ ድረስ ጠላት አድርጎ ያዛቸው፡፡ ባልዋሉበት ስማቸውን አጠፋ፡፡ ከሳቸው አስጠነቀቀ፡፡ በታታኝ፣ ደጋሚ፣ እብድ እና ሌላም ሲሉ በመጥፎ ስማቸውን አጠፉት፡፡ ነገር ግን ጌታ አላህ የሳቸውን ማንነት ስለሚያውቅ መሰከረላቸው እንዲህም ሲል
نٓ ۚ وَٱلْقَلَمِ وَمَا يَسْطُرُونَ
(ኑን)፤ በብርእ እምላለሁ በዚያም (መልአኮች) በሚጽፉት፡፡
مَآ أَنتَ بِنِعْمَةِ رَبِّكَ بِمَجْنُونٍ
አንተ በጌታህ ጸጋ የተጎናጸፍክ ስትኾን ዕብድ አይደለህም፡፡
وَإِنَّ لَكَ لَأَجْرًا غَيْرَ مَمْنُونٍ
ላንተም (ከጌታህ) የማይቋረጥ ዋጋ በእርግጥ አልለህ፡፡
وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ
አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡
ታድያ አንተ/አንቺ የአላህ ባርያ ሆይ! ሰዎች ያሉትን ቢሉ አላህ መልክተኛውን ባዘዘበት በመካከለኝነት ባህሪ ላይ ድንበር ሳይታለፍ፣ ዝቅጠት ውስጥ ሳይገባ ለመሆን መጣር እንጂ ከዛ ውጭ ከአላህ ውጭ ሂሳብ ከፋይ ስለሌለ ሰዎች ያሉትን ቢሉ ወደፊት መገስገስ ነው፡፡
ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም)ን አላህ በሱረቱ ሙደሲር ላይ ለእርሱ ሲሉ እንዲታገሱ መክሯል
يَٰٓأَيُّهَا ٱلْمُدَّثِّرُ
አንተ (ልብስህን) ደራቢው ሆይ!
قُمْ فَأَنذِرْ
ተነሳ አስጠንቅቅም፡፡
وَرَبَّكَ فَكَبِّرْ
ጌታህንም አክብር፡፡
وَثِيَابَكَ فَطَهِّرْ
ልብስህንም አጥራ፡፡
وَٱلرُّجْزَ فَٱهْجُرْ
ጣዖትንም ራቅ፡፡
وَلَا تَمْنُن تَسْتَكْثِرُ
ማብዛትንም የምትፈልግ ኾነህ፤ (በረከትን) አትለግስ
وَلِرَبِّكَ فَٱصْبِرْ
ለጌታህም (ትዕዛዝ) ታገሥ፡፡
የአላህ ባርያ ሆይ! ሃቅ ላይ ሁን አንጂ የማንም ተህዚር (ሰዎች ካንተ ማስጠንቀቃቸው) አይጎዳህም፡፡ አላህ ከባጢል ይጠብቀን፡፡ ባጢል ላይ ከሆንክ የማንም ተዝኪያ አይጠቅምህም፡፡ በዳእዋ ስራ ላይ ትግስት ከባዱን ቦታ ይይዛል፡፡
አላህ ልጅ አለው እያሉት ታግሶ ከሃዲያንን ያበላል ያጠጣል፡፡ ከአላህ በላይ ታጋሽ የለም፡፡ ሰዎች ያሉትን ቢሉ ሂሳብ ከፋዩን አላህ አስቦ የሚሰራ ሰው እነዚህን ሁሉ ከዛም ከዚህም የሚሰነዘሩ ትችቶች እውነት ከሆኑ ተቀብሎ ማስተካከል፣ ካልሆኑ ንቆ ትቶ ወደፊት በመገስገስ አገራችን ላይ ያለውን የተንሰራፋ ሽርክ፣ ቢድአ ፍልስፍና በማስረጃ ይፋ በማድረግ ህዝቡን ማስጠንቀቅ፡፡ አምሳያ እና ምትክ ወደ ሌለው ብቸኛው ሃቅ ተውሒድ እና ሱና ወደ ሰለፎች ጎዳና ተግቶ መማር እና ማስተማር፡፡
አላህ በዚህ ዳእዋ ላይ ሃቅን ተረድተው ሃቅን ከሚያስተላልፉት ታጋሾ ያድርገን፡፡
