Shame አሳፋሪ፤ ነውር ነው፡፡
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በመልክተኞች መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በሰሃባዎቻቸው እና ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡
ያሳዝናል፤ ይከፋል፤ ሙስሊሞች መመሪያ እንደሌላቸው የበላይነት ምንጭ የሆነ ዲን እንደ መመሪያ እንደሌላቸው፤ አላህ የጠላላቸውን እራስ መጉዳት እራስን መግደል ሸይጧን በተዘዋዋሪ አሳምሮ አቀረበላቸው፡፡
ጫት ስንቱን አደነዘዝ፤ አፈዘዘ፡፡ በሃይማኖትም ጉዳይ ይሁን በማህበረሰባዊ ጉዳይ ስንቱን አሽመደመደ፡፡ ባል እና ሚስትን አናናቀ፤ ወላጅ እና ልጅን አራራቀ፤ ታላቁን የሰው ልጆች ለጌታቸው እንዲፈፅሙት የተገደዱትን ሰላት በጀመዓ እንዳይፈፅሙ አደነዘዛቸው፤ ሰላት ላይም ችላ እንዲሉ አደረጋቸው፡፡
ባል ሚስቱን በስሜት ማርካት እንዳይችል አደረገ፤ ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርግ ነው የሚጠበቀው፡፡
ምርቃናውን ‹‹መስበሪያ›› እየተባል አላህ የከለከለውን ‹‹መጠጥ›› የሚጠጣም ሞልቷል፡፡ ሺሻ፤ ሲጋራ ከዛም ቅሞ ቅሞ ጀዝቦ ማበድ እና መንገድ ላይ የጫት እንጨት መለቃቀም፡፡
ኢስላም አንድን ሙስሊም ክብሩን እንዲጠብቅ ያዘዋል፡፡ ጫት አንድ ሰው ለራሱ ደንታ እንዳይኖረው በማድረግ፤ እራሱን እንዲጥል፤ የቆሸሸ ልብስ እንዲለብስ ከሚያደርገው አደንዛዥ ቅጠል ውስጥ ነው፡፡ አላህ ኡማውን ከዚህ መጥፎ ቅጠል ይጠብቀው፡፡
ወደ ዋናው አርስት ስንመለስ፡፡ ግን ጫቱ በማን ብር ነው የሚቃመው???
1) በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ግማሹ ‹‹የሰው ኪስ አውልቆ (ሰርቆ)›› ጫት ይቅማል፡፡
2) ግማሹ ሴት ልጁን ወይንም ሴት እህቱን አረብ አገር ልኮ፤ እሷ እዛ ሰው ቤት ግርድና ተቀጥራ ማንም ጮሆባት፤ እንቅልፍ አጥታ፤ በረሃ አሳብዷት በላከችው ገንዘብ እሱ እዚህ ቁጭ ብሎ ይቅማል፡፡
ይህን የምታደርገው ወንድም አላህን ትንሽ አትፈራውም??? ያ የፈጠረህን ጌታ፡፡ አላህ ወንድን ልጅ እንጂ ግዴታ ያደረገበት ሚስቱን እና ሴት ልጁን እንዲንከባከብ እና እንዲቀልብ፤ አንተ አታፍርም ሚስትህን አረብ አገር ልከህ ወይንም ያችን ውድ ሴት ልጅህን ልከህ በሷ ብር ስትቅም??? እንደው መርዝ አይሆንብህም???
3) አንተ እናትህን ገንዘብ ካልሰጠሸኝ ይህን አደርጋለሁ፤ አገር ጥዬ እጠፋለሁ፤ እታነቃለሁ፤ እገልሻለሁ እያልክ እናትህን የምታስፈራራ ወጣት ነገ አላህ ፊት ችሎ የሚቆም ሀፍረት አለህ??? እናትህን እንዲህ አዛ እያደርግክ በሷ ብር የምትቅም፡፡
ልብ በሉ ‹‹እናቱን አገላለው›› ያለው ወጣት ወሬ ለማጣፈጫ ሳይሆን እውነተኛ አዲስ አበባ ላይ የተደረገ ነው፡፡ ካፊር ነው እንዳትሉ ሙስሊም ነው፡፡
4) ሚስትህን ስራ ልከህ ይሄ በሰፊው ክፍለ ሃገር ላይ አለ፤ እሷ ሰርታ ባመጣችው ጫት ልቃም የምትል ትንሽ እንደው ሃፍረት አይሰማህም??? አዲስ አበባም ላይ እየተለመደ ያለ አሳዛኝ ክስተት አለ፡፡ አንዳንድ ወንዶች ትዳር ሲፈልጉ ‹‹ምን አላት›› ይላል፡፡ ከዛ እሱ ጫት ቤት ቁጭ ብሎ ቅሞ ይመጣል፡፡ አረ ወንድ ሁን፤ ሰርተህ ልታበላት እንጂ ያገባሃት፤ እሷ በሰራችው ጫት እንድትቅም አይደለም፡፡
ማጠቃለያ፡- ሰውንም ዘርፎ ይቃም፤ ሴት ልጁን ወይንም ሚስቱን አረብ አገር ልኮ፤ እናቱንም አስፈራርቶ ይሁን አባቱን ተቆጥቶ ተቀብሎ የሚቅም ሁላ፤ አላህ የሰጠውን ጤነኛ ጨጓራ፤ ጥርስ፤ ሳንባ እና ሌሎችም አካላቱን ለምን እንደጎዳ ሊጠየቅ ስለሚችል ይጠንቀቅ፡፡ እራስህን አንቀህም ግደል፤ በሃሺሽም ግደል፤ ጫት ቅመህም ጨጋራህን፤ ሳንባህንም ሌላ ሌላ አካላትህን ተራ በተራ አጥፍተህ እራስህን ብትገል ልትጠየቅ ትችላለህ ተጠንቀቅ፡፡
አላህ ሆይ! ሀቁን በሃቅነት አሳየን የምንቀበለውም አድርገን፤ ባጢልን በባጢልነት አሳየን የምንርቀውም አድርገን፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በመልክተኞች መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በሰሃባዎቻቸው እና ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡
