Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ውዷ እህቴ አላህ ይዘንልሽና የተከበርሽው እህቴ አስታውሽ!



بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ
💎ውዷ እህቴ💎💐

አላህ ይዘንልሽና የተከበርሽው እህቴ አስታውሽ!

አላህ ከጃሂሊያ አውጥቶ ለኢስላም እንዳበቃን፤ ከዚያ ፈጣሪ ተዘንግቶ ጣኦታት ከሚመለኩበት፣ ሰብዐዊነት ጠፍቶ ጭካኔ ከሰፈነበት፣ ሴት ልጅ መወለዷ ከሚጠላበት፣ ከነህይወቷ ከምትቀበርበት፣ ሚስት እንደንብረት ከምትወረስበት የጨለማዎች ዘመን አላህ በቃችሁ ሲለን ወደ ብርሃን አወጣን። ታላቁን ነቢይ(صلى الله عليه وسلم) ወደ ቀጥተኛው መንገድ ተጣሪ አድርጎ ላከልን።

ከሀይማኖትም ኢስላምን መረጦ በርሱም ላይ እንድንሞት አዘዘን። አልሀምዱሊላህ!
“እርሱ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ሊያወጣችሁ ያ ግልፅ የኾኑን አንቀጾች በባሪያው ላይ የሚያወርድ ነው፡ አላህም ለእናንተ በእርግጥ ርኅሩህ አዛኝ ነው” አል-ሀዲድ 9

ሙስሊም እህቴ እስቲ ያለሽበትን ሁኔታ አስተውይ። ላፍታ ቆም በይና ያንቺንና የሙስሊሞችን ሁኔታ ተመልከች፤ ነቢዩ(صلى الله عليه وسلم) እና ሶሀቦች( ) ከነበሩበት ዘመን ጋር አስተያዪው። እውን ነቢዩ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) በተውን ጎዳና ላይ ፀንተናል ወይስ የራሳችንን መንገድ ቀይሰናል? ካስተዋልሽ ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሁኖ ታገኚዋለሽ። ብዙዎቻችን ላይ ክልክ ያለፈ አላዋቂነት ተንሰራፍቶ የተፈጠርንበትን አላማ ዘንግተናል፤ አኸይራን ሩቅ አስቀምጠናት በዱኒያ ተወጥረናል …
ከነቢዩ( صلى الله عليه وسلم) ፈለግ ይልቅ ግለሰቦችን በጭፍን መከተልን ተያይዘዋል፤ ሱናን ትተው ቢድዐ ውስጥ ተዘፍቀዋል። በመሰረተቢስ እምነቶች ተተብትበው ዳግም ወደ ሽርክ ነጉደዋል። ባዕድ አምልኮ በከፊል አንጃዎች ውስጥ ነፍስ ዘርቷል ብሎም ተንሰራፍቷል። ይሄኔ የሙስሊሞች አንድነት ተንዶ የጠላት መሳለቂያ ሁነዋል። በጉልበትም በባህልም ተወረዋል፤ ማንነታቸውን ዘንግተው ለዲናቸው ባይተዋር ሁነዋል። ወደ ሱና የተጠጋ፣ተውሂድ ላይ የቆመም እንደ እንግዳ ታይቷል። ዋ… እኛ! ምን ያክል ከድን ርቀናል?

ነቢዩ(صلى الله عليه وسلم ) እንዲህ ብለው ነበር- “ኢስላም እንግዳ ሆኖ ነው የጀመረው ወደፊትም እንግዳ ሁኖ ይመለሳል፤ እንደ እንግዳ ለሚታዩት ጡባ(ጀነት) አለችላቸው” አልባኒ ሰሂህ ነው ብለውታል"

📝መሸፈን ነውር ሆኖ መገላለጥ ወደናል፤ ሰሀቢያት ለሂጃብ እንደሮጡት እኛ ለመራቆት ተንደርድረናል፡፡ ገደል ቢገቡ ላንተዋቸው ካፊሮችን የሙጢኝ ብለናል፡፡ አላህን መታዘዝ ኋላ ቀርነት መስሎን በማመጽ ስልጣኔ ተኮፍሰን፣ በማይምነት ኋሊዮሽ ተጉዘናል። የጀነት ትኬት እንደደረሰው ዒባዳን ትተን፣ ገሩን ዲን አክብደን ከባዱን ወንጀል አቅለናል። ታዲያ እንዴት አላህ ይረዳናል?

ውድ እህቴ! አንቺስ?!! እስቲ መለስ በይና ራስሽን ገምግሚው። በርግጥ ከዚህ የተለየ ሁኔታ ላይ ነሽ?
ንቂ!!! ካለንበት ፈተና የምንወጣው ወደ ቁርዐንና ሀዲስ ስንመለስ ብቻ ነው። ተውሂድን ስናስቀድም፣ የናቅነውን ሱና መልሰን መለያችን ስናደርግነው፡፡ ዳግም ወደ አላህ ፊታችንን ስናዞር፣ በትዛዙም ስንቆም፣ ተው ያለንን እርግፍ አርገን ስንተው፣ ሂዱ ባለን ስነፈስ፤ ጥቅልል ብለን ስንሰልም ነው ያቺን ተናፋቂ ጀነት የምናገኘው። ያኔ በእምነታችን ቀጥ ስንል…!

“እነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ «አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ» በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ፡፡” 41-20

ወደ ዲናችን መመለስ ለዱኒያም ለአኸይራም ስኬት ቁልፍ ነው። ይህን ቁልፍ ማግኘት ደግሞ በሁላችንም ላይ ግድ ነው፤ አንቺንም ጨምሮ! የዚህ ቁልፍ ማግኛው መንገድ ደግሞ ሌላ አይደለም እውቀት ቢሆን እንጂ! ሸሪዓዊ ዒልም!!! ታዲያ ምን ትጠብቂያለሽ እህት?

📎ኢማሙል ቡኻሪ በሐዲስ ስብስባቸው “እውቀት ከንግግርም ከስራም ይቀድማል” ሲሉ ርዕስ አስቀምጠዋል። ሀፊዝ ኢብኑሀጀር በዚህ አባባል የተፈለገበት ይላሉ፡- “እውቀት ለንግግርና ለስራ ትክክለኝነት መስፈርት መሆኑ ነው።…” ፈትሁል ባሪ

ያ ሙስሊማህ! ከንግርሽም ሆነ ከስራሽ በፊት እውቀት ይቀደማልና ገሩን ዲን ተዋወቂው። እህት ሆይ! አላህ ጀነትን ያዘጋጀው ለሚታዘዙት ባሮቹ ነውና እርሱን ትታዘዢ ዘነድ ትእዛዛቱን ተማሪ። አላህ ምህረቱን ያዘጋጀው ከከለከላቸው ለሚታቀቡት አማኞች ነውና የከለከለሽን በሙሉ ትርቂ ዘንድ ወደ ሸሪዐዊ እውቀት ፍጠኚ። ወደ ቁርዐንና ሐዲስ ተጣደፊ።

ለነገ ምንም ዋስትና የለሽማ! የእውቀት ማዕዶች በዙሪያሽ ተጥደዋልና ተሽቀዳደሚ። አላህ ግዴታ ያደረገብሽን ከሱናው፤ የከለከለሽን ከተፈቀደው ለመለየት ቂርዐት ብቸኛ መንገድ ነውና ተጣደፊ።

"እውቀት ብረሀን ነው ጀህልና ደግሞ ጨለማነው"

🌺ውዷእህቴ🌹 እስኪ ልጠይቅሽ በአላህ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው ?

መልሱን አብረን እንመልከት

በአላህ ማመን ከኢማን መሠረቶች ሁሉ ወሳኙ የላቀ ደረጃ ያለውና የአዕማዶች ዋና ምሰሶ ሲሆን የተቀሩት የኢማን መሰረቶች የእርሱ ቅርንጫፍና በርሱ ውስጥ ተካታቾች ናቸው::

🔹በአላህ ማመን አላህ በጌትነቱ፣ በአምላክነቱ፣ በስሞቹና ባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ማመን ሲሆን እነዚህ ሶስቱ በአላህ ለማመን ዋና ዋና መሰረቶች ናቸው::

እንዲያውም ከግድፈት የፀዳው የእስልምና ሃይማኖት “ተዉሂድ” የተሰኘበት ምክንያት አላህ በንግስናውና በጌትነቱ አጋር የሌለው ፣ በአካሉ ፣ በስሞቹና ባህሪያቱ አምሳያ የሌለውና እንዲሁም በአምልኮ ቢጤ የሌለው ብቸኛ መሆኑን በማመን የተመሰረተ በመሆኑ ነው::

በዚህ መሰረት የነቢያትና የመልክተኞች ተውሂድ በሶስት እንደሚከፈል ግልፅ ይሆናል::

📎አንደኛው ክፍል “ተውሂዱ ሩቡቢያ”፡- አላህ የሁሉም ነገር ጌታ፣ ንጉስ፣ ፈጣሪና ሲሳይ ለጋሽ መሆኑን ፤ ህይወት ሰጭ፣ ገዳይ፣ ጠቃሚ፣ ጐጂ፣ በጭንቅ ጊዜ ሲጠራ አቤት ባይ፣ የነገሮች ሁሉ ገዥ፣ የመልካም ነገሮች ባለቤት ነገሮችን ሁሉ ወደርሱ መላሽና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አጋር የሌለው መሆኑን ማመን ማለት ነው፡፡

📎ሁለተኛው ክፍል “ተውሂዱል ኡሉሂያ”፡- ራስን ዝቅ ብሎ በመተናነስ፣ በመውደድ፣ በመፍራት፣ በማጐንበስ፣ በግንባር በመደፋት፣ በማረድ፣ ስለትን በማቅረብና በሌሎችም የአምልኮ ዘርፎች አላህን ብቸኛ ማድረግና አጋር እንደሌለው ማመን ማለት ነው፡፡

📎ሶስተኛው ክፍል “ተውሂዱል አስማኢ ወሲፋት”፡- አላህ በቁርአኑና በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሀዲሶች እራሱን በሰየመባቸውና በገለፀባቸው ስሞችና ባህሪያት እርሱን ብቸኛ በማድረግ፣ ከጉድለት፣ ከነውርና የእርሱ መለያ የሆኑትን ባህሪዎች ከፍጡራን ጋር ከማመሳሰል መጠንቀቅ፡፡ እንዲሁም አላህ ሁሉን ነገር አዋቂ፣ በሁሉ ነገር ቻይ፣ ህያው፣ ራሱን ቻይ፣ ማንገላጀትም ሆነ እንቅልፍ የማይዘው፣ ተፈፃሚ የሆነ ፍላጐትና የላቀ ጥበብ ባለቤት፣ ሰሚ፣ ተመልካች፣ አዛኝ እንደሆነ፣ ከዐርሽ በላይ ስልጣኖችን ተቆጣጣሪ፣ ንጉስ፣ ቅዱስ የሆነና ሌሎችም እጅግ በጣም ያማሩ ስሞችና የላቁ ባህሪዎች ያሉት መሆኑን ማመን ማለት ነው፡፡

ለነዚህ ለያንዳንዱ ሶስት ክፍሎች ከቁርአንና ከሀዲስ የሆኑ ብዙ መረጃዎች አሏቸው፡፡

ቁርአን ሙሉ በሙሉ ስለተውሂድ ፣ስለ መብቶቹና ስለ ምንዳዎቹ ፤ እንዲሁም ስለ ሽርክ ፣ ስለ ቤተሰቦቹና ስለ ምንዳቸው የሚያብራራ ነው፡፡

እነዚህ ሶስቱ የተውሂድ ክፍሎች ኡለማዎች የቁርአንና የሀዲስን ጥቅሶች በመከታተልና በማጥናት የደረሱባቸው ሲሆን ይህም የሆነው ከአንድ ባሪያ የሚፈለገውን አላህ በጌትነቱ ፣ በአምልኮው፣ በስሞቹና ባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ማመን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ያላሟላም አማኝ ሊባል አይችልም፡፡

ጥያቄ

1, በአላም ማመን ማለት ምን ማለት ነው?
2, ተዉሂድ በስንት ይከፈላል? ስማቸውስ ምን ምን ይባላል?

ይቀጥላል

Post a Comment

0 Comments