Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እህቶች ሒጃብ ላለመልበስ የሚያነሷቸው ማማኸኛዎች. .


እህቶች ሒጃብ ላለመልበስ የሚያነሷቸው ማማኸኛዎች. .
1) «አላህ ወደራሱ ሲመራኝ እለብሳለሁ!»
የምርሽን ነው እህቴ? አላህ ቁርኣንን አውርዶ፤ ነቢያችንን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ልኮ ወደራሱ አልመራሽምን? ከሰዎች መርጦ ሙስሊም አድርጎ ወደ ኢስላም አልመራሽምን?
2) «ገና ልጅ ነኝ! ትልቅ ስሆን እለብሳለሁ. .»
እንዴትስ ሆኖ ነው ነገን እኖራለሁ ብለሽ በነፍስሽ ላይ ዋስትና የወሰድሽው? በየትኛውም አጋጣሚ የሞት መላእክት ሊጎበኝሽ ሊመጣ ይችላልኮ! በመጣ ግዜ "ትልቅ እስክሆን ጠብቀኝ?" ብለሽ ማስተዛዘኛ ልትሰጭው አይቻልሽም. .
فَإِذَا جَاءَ أَجَلُهُمْ لَا يَسْتَأْخِرُونَ سَاعَةً ۖ وَلَا يَسْتَقْدِمُونَ
{{ ግዜውም (የሞት መላእክት) በመጣ ግዜ አንዲትንም ሰዓት አያቆዩም። አያስቀድሙምም ።}} [አልአዕራፍ 34]
የሞት መላእክት ሲመጣ ልጅ ሆንሽ ትልቅ አይለይሽም!
ሁላችንም ለአላህ ጥሪ መልስ ለመስጠት መሽቀዳደም ይገባናል. .
سَابِقُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا كَعَرْضِ السَّمَاءِ وَالْأَرْضِ أُعِدَّتْ لِلَّذِينَ آمَنُوا بِاللَّـهِ وَرُسُلِهِ ۚ ذَٰلِكَ فَضْلُ اللَّـهِ يُؤْتِيهِ مَن يَشَاءُ ۚ وَاللَّـهُ ذُو الْفَضْلِ الْعَظِيمِ ﴿٢١﴾
{{ከጌታችሁም ወደሆነችዋ ምህረት፤ ስፋቷ እንደ ሰማይና ምድር ስፋት ወደሆነችዋ ጀነት ተሽቀዳደሙ። ለእነዚያ በአላህና በመልእክተኛው ላመኑ ሰዎች ተዘጋጅታለች። ይህ አላህ ለሚሻው ሰው የሚሰጠው ችሮታው ነው። አላህ የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው }} [አልሐዲድ 21]
3) «ሒጃብ መልበስ በጣም ይሞቃል!»
ውድ እህቴ ሆይ! እስኪ ልጠይቅሽ. . የዱኒያዋ ፀሃይ ወይንስ የጀሃነም እሳት? የትኛው የበለጠ አቃጣይ ነው?
አላህ ስለ ጀሃነም እሳት ሲነግረን እንዲህ ይላል. .
قُلْ نَارُ جَهَنَّمَ أَشَدُّ حَرًّا ۚ
{{የጀሃነም እሳት አቃጣይነቱ እጅግ የከፋ ነው}} [አትተውባ 81]
4) «እኔ ሒጃብ ከለበስኩ ልክ አንዳንዶች እንዳወለቁት ወደፊት ላወልቀው ስለምችል እፈራለሁ»
ይህንን ማማኸኛ ሁሉም ሙስሊም ቢጠቅመው ኖሮ ዓለም ላይ ኢስላምን የሚያራምድ አንድም ግለሰብ ባልቀረ ነበር። ሶላትን ሁሉም በተወ ነበር ምክንያቱም ኋላ ላይ ማቆምን ተፈርቶ፤ ረመዳንን መጾም በተተወ ነበር ምክንያቱም ኋላ ላይ መተውን ተፈርቶ፤ ሌላም ሌላም. . ! እህቴ ሆይ መመራት ያላው በአላህ እጅ ነው። ነገን ላወልቀው እችላለው ብለሽ ሒጃብን መተውሽ ቀድሞውኑ መልበስሽ ላይ ጥርጣሬ እንደታከለበት ያሳብቃል። የነገውን ለአላህ ተይው! አንቺ ዛሬ መንገዱ ላይ ብቻ መሆንሽን አረጋግጪ. .
አላህ እንዲህ ይላል. .
وَاعْبُدْ رَبَّكَ حَتَّى يَأْتِيَكَ الْيَقِينُ
{{እርግጠኛይቱ (ሞት) እስከምትመጣ ድረስ ጌታህን ተገዛ}} [አልሐጀር 99]
እህቴ ሆይ! አንቺ ስለነገው አታውቂም። በመሆኑም ሞትሽ እስኪመጣ ድረስ ሒጃብሽን አውልቀሽ ጌታሽ ጋር አትጣዪ!
5) «ሒጃብ ከለበስኩ ትዳር አላገኝም. .»
እህቴ የምታነሳው ይህ ማማኸኛ የመነጨው አንድን ትልቅ ጉዳይ ባለማወቅና ባለመረዳት ነው ብለን መደምደም እንችላለን። እርሱም ትዳር ማለት ከአላህ የሚመጣ ሲሳይ መሆኑ! በርግጥም ትዳር ሲሳይ ነው። የእያንዳንዳችን ሲሳይ ደግሞ እልፍ ዓመታት ቀድሞ በለህወል መሕፉዝ ላይ ተከትቧል። ቀለሙም ደርቋል። እኛ ዛሬ ላይ ሪዝቅ ፍለጋ ውር ውር የምንለው ሰበቡን ለማድረስ እንጂ ከተከተበልን ሲሳይ ቅንጣት ልንጨምር አይደለም። ሆኖም አላህን የሚፈራ ካላሰበው፥ ካልጠበቀው ምንጭ አላህ ሲሳይን ይለግሰዋል።
አላህ እንዲህ ይላል . .
‏‏وَمَن يَتَّقِ اللَّهَ يَجْعَل لَّهُ مَخْرَجًا وَيَرْزُقْهُ مِنْ حَيْثُ لَا يَحْتَسِبُ وَمَن يَتَوَكَّلْ عَلَى اللَّهِ فَهُوَ حَسْبُهُ إِنَّ اللَّهَ بَالِغُ أَمْرِهِ قَدْ جَعَلَ اللَّهُ لِكُلِّ شَيْءٍ قَدْرًا‏}
{{አላህን የሚፈራ መውጫን ያደርግለታል። ከማያስበውም በኩል ሲሳይን ይለግሰዋል። በአላህ ላይ የተመካ አላህ በቂው ነው። አላህ ጉዳዩን አድራሽ ነው። አላህ ለነገሩ ሁሉ የተወሰነን ግዜ አድርጓል።}} [አጥጦላቅ 2-3]
ስለዚህ እህቴ ሆይ! አላህ ትዳርን ወይንም ሲሳይን እንዲለግስሽ ከፈለግሽ እርሱን ፍሪው እንጂ ሒጃብሽን እያወለቅሽ አታምጽፂው። አላህን በማመጽ ትዳር አይገኝም። አላህን ፍሪው ባላሰብሽው በኩል ምርጡን ትዳር ይለግስሻል።
አላህ ሆይ! ለሙስሊሟ እህቴ ሒጃብን አግራላት። በርሱም ላይ ጽናትን ለግሳት።

Abu Aisha