Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቅድሚያ ለተውሒድ እንላለን ምክነያቱም ተውሒድ የልብ መረጋጋት እና የመንፈስ ጥንካሬ ያጎናጽፋልና



ከአላህ ሌላ የሚያመልክ በርካታ ነገሮችን መጥቀም መጉዳት ይችላሉ ብሎ ስለሚያምን ላይሰጡት ይመኛል፣ ላይጎዱት ይሸበራል፣ ላያገኝ ያወጣል፣ በከንቱ ይለፋል። ለፍጡራን የማጎብደድን አስከፊ ቀንበር ከጫንቃችን ላይ አሽቀንጥረን የምንጥለው በተውሒድ ብቻ ነው። ተውሒድ የሌለው ሰው ሌላው ቀርቶ ልጅና ዝናብ ሳይቀር ከፍጡራን በከንቱ ይቀላውጣል። እድሜ ልኩን ደጅ ቢጠናም የሚጠራቸው ሙታኖች ሊሰጡት ቀርቶ ጥሪውንም ካናካቴው አይሰሙም። ለሌላ ሊተርፉ ቀርቶ እራሳቸውንም አያድኑም። ተውሒድ ከሌለህ የሞቱትን ትፈራለህ፣ ስማቸው ሲነሳ ትብረከረካለህ። ዶሪሓቸውን ስታይ በፍርሃት ትርዳለህ። ተውሒድ ሲኖር ግን ተስፋህም ፍራቻህም ወደ ሰማይ ብቻ ነው። ወደ አንድየውና ሃያሉ ጌታ። ﴾አላህ ለባሪያው በቂው አይደለምን? በነዚያ ከሱ በታች በሆኑት ያስፈራሩሀል﴿ የሚለው ቁረኣናዊ መልእክት የአማኞችን ልብ በሐሴት የሚሞላ ድንቅ አገላለፅ ነው! አዎ! “ተውሒድ ማለት የገባበት ሁሉ የደህንነት ዋስትና የሚያገኝበት ትልቁ የአላህ ምሽግ ነው። ለዚያም ነው ከሰለፎች አንዱ ‘አላህን የፈራ ሁሉም ነገር ይፈራዋል። አላህን ያልፈራ ግን በሁሉ ነገር ያስፈራዋል’ ያሉት።”[በዳኢዑልፈዋኢድ፡ 2/470]
በተውሒድ የታነፀ ስብእና ቢለምን ከጌታው ነው። ቢታገዝ በጌታው ነው።
{አንተ ልጅ ሆይ! አላህን ጠብቅ ይጠብቅሃል። አላህን ጠብቅ ፊት ለፊትህ ታገኘዋለህ። ስትጠይቅ አላህን ጠይቅ። ስትታገዝ በአላህ ታገዝ። እወቅ! ህዝቦች ባጠቃላይ በሆነ ነገር ሊጠቅሙህ ቢሰባሰቡ አላህ ላንተ በፃፈልህ በሆነ ነገር እንጂ አይጠቅሙህም። በሆነ ነገር ሊጎዱህ ቢሰባሰቡም አላህ ባንተ ላይ በፃፈው ነገር እንጂ አይጎዱሁም። ብእሮች ተነስተዋል! መዝገቦቹ ደርቀዋል} የሚለው ድንቅ ሐዲሥ የህይወት መመሪያው ነው። [አልሚሽካት፡ 5302]
ተውሒድ በዳበረ ቁጥር ይበልጥ ልብ ይረጋጋል። ኢብኑ ተይሚያህ ረሒመሁላህ እንደሚሉት “በአንድ ባሪያ ልብ ውስጥ ያለው ተውሒዱ በጠነከረ ቁጥር፣ ኢማኑ፣ መረጋጋቱ፣ መመካቱ፣ እርግጠኝነቱ ይበልጥ ይጠነክራል።”
[አልፈታዋ፡ 28/35]
ከዚህ የበለጠ ምን ፀጋ አለ?! ዱኒያ ውስጥ የተውሒድን አርኪ ጣእም ከማጣጣም፣ ከፍጡራን ጫማ ርቆ ከተውሒድ ሰገነት ላይ ከመኖር የበለጠ ምን ጀነት አለ?! “ዱኒያ ውስጥ ጀነት አለች። እሷን እዚህ በዱኒያ ያልገባት የኣኺራውን ጀነት አይገባትም!!”
[መዳሪጁ አልሳሊኪን፡ 1/452]።
አስታውስ! የተፈጠርከው ለአንድየው ጌታ ባርነት ብቻ ነው። ከሌላው በሙሉ ነፃ ነህ። ሌላው በሙሉ ልክ እንዳንተ ባሪያ ነው። የተውሒድ ትጥቅ የታጠቀ ለሱ አምሳያ ባሪያዎች አክብሮትን እንጂ አምልኮትን አይሰጥም። {እነዚያ ከአላህ ውጭ የምትጠሯቸው የናንተው አምሳያ ባሪያዎች ናቸው።} [አዕራፍ፡ 194] ለፈጣሪው ባሪያ ከመሆን የሸሸ ሁሉ ለፍጡር ባሪያ ሆኖ ተንበርክኳል። የሙታን ባሪያ ከመሆን፣ የመቃብር፣ የደጋጎች፣ የሸይጧን፣ የነፍስያ፣… ባሪያ ከመሆን በተውሒድ ነፃ ውጣ። ሰላም ትኖራለህ፣ ሰላም ትሞታለህ! ሰላም ትነሳለህ! በአንፃሩ ከተውሒድ ርቆ “ፍጡርን መፍራት፣ መከጀል፣ የሚፈልጉትን ለማጣት፣ ከሚሰጉት ላይ ለመውደቅ አንድ ሰበብ ነው። ምክንያቱም ከአላህ ሌላ ላለ አካል ባለህ ፍርሃት ልክ ስጋት ይደቀንብሃል። ከሱ ሌላ ባለ አካል ላይ በጣልከው ተስፋ ልክ ንፍገት ይከተልሃል።”[አልፈዋኢድ፡ 64] አትጠራጠር! በአላህ ላይ ማጋራት ውስጣዊ ሰላምን ለማጣት ቀዳሚ ምክንያት ነው። ሃያሉ ጌታ ምን እንደሚል ተመልከት! {በነዚያ በካዱት ሰዎች ልቦች ውስጥ አላህ ማስረጃ ያላወረደበትን ነገር በአላህ ላይ በማጋራታቸው ምክንያት ሽብርን እንጥላለን!} [ኣሊ ዒምራን፡ 151]
በተውሒድ የታነፀ ስብእና ግን በምድራዊ ከንቱ ሃይሎች እምነት አይፍረከረክም። ለማይጠቅሙ ለማይጎዱ የውሸት አማልክት አያጎበድድም። ምክንያቱም ተውሒድ የሰላሙ፣ የደህንነቱ ምንጭ ነውና። ኢብራሂም ዐለይሂስሰላም እንዲህ ይላሉ፦
{إِنِّي وَجَّهْتُ وَجْهِيَ لِلَّذِي فَطَرَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ حَنِيفًا ۖ وَمَا أَنَا مِنَ الْمُشْرِكِينَ (79) وَحَاجَّهُ قَوْمُهُ ۚ قَالَ أَتُحَاجُّونِّي فِي اللَّهِ وَقَدْ هَدَانِ ۚ وَلَا أَخَافُ مَا تُشْرِكُونَ بِهِ إِلَّا أَن يَشَاءَ رَبِّي شَيْئًا ۗ وَسِعَ رَبِّي كُلَّ شَيْءٍ عِلْمًا ۗ أَفَلَا تَتَذَكَّرُونَ (80) وَكَيْفَ أَخَافُ مَا أَشْرَكْتُمْ وَلَا تَخَافُونَ أَنَّكُمْ أَشْرَكْتُم بِاللَّهِ مَا لَمْ يُنَزِّلْ بِهِ عَلَيْكُمْ سُلْطَانًا ۚ فَأَيُّ الْفَرِيقَيْنِ أَحَقُّ بِالْأَمْنِ ۖ إِن كُنتُمْ تَعْلَمُونَ (81) الَّذِينَ آمَنُوا وَلَمْ يَلْبِسُوا إِيمَانَهُم بِظُلْمٍ أُولَٰئِكَ لَهُمُ الْأَمْنُ وَهُم مُّهْتَدُونَ (82)}
{“እኔ ለዚያ ሰማያትና ምድርን ለፈጠረው ቀጥተኛ ስሆን ፊቴን አዞርኩ። እናም እኔ ከአጋሪዎች አይደለሁም” (አለ)። ወገኖቹም ተከራከሩት። “በርግጥም የመራኝ ሆኖ ሳለ በአላህ (አንድነት) ላይ ትሟገቱኛላችሁን? በሱ ላይ የምታጋሩትንም አልፈራም። ጌታዬ የሆነን ነገር ቢሻ እንጂ (ምንም አልሆንምና)። ጌታዬም ሁሉን ነገር በእውቀቱ አካቧል። ታዲያ አትገነዘቡንም?” አላቸው። “እንዴትስ እናንተ የምታጋሩትን ነገር እፈራለሁ? በእናንተ ላይ ማስረጃ ያልወረደበትን እያጋራችሁ እናንተ የማትፈሩትን?! የምታውቁስ ብትሆኑ ከሁለቱ ክፍሎች ይበልጥ ደህንነት የሚገባው የትኛውን ነው?” (አለ)። እነዚያ ያመኑትና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉት እነዚያ ለነሱ ደህንነት አላቸው። እነሱም የተመሩ ናቸው።}
[አልአንዓም፡ 79‐82]
ስለዚህ አልኢማም ኢብኑ አቢልዒዝ አልሐነፊ ረሒመሁላህ እንደሚሉት “ለልቦች ህይወትም፣ ድሎትም፣ መረጋጋትም አይኖርም፣ ጌታቸውን፣ አምላካቸውን፣ ፈጣሪያቸውን በስሞቹ፣ በመገለጫዎቹ እና በተግባራቱ በማወቅ ካልሆነ በስተቀር”
[ሸርሑጥጦሓውያህ፡ 177]
[ተውሒድ፡ የሁለት ሃገር የስኬት ቁልፍ ከሚለው የኢብኑ ሙነወር መፅሐፍ ከገፅ 14‐16 የተወሰደ]