Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ተቂያ” እና “ኢምቲሃን” በሐዳዲያህ ሰፈር

 
“ተቂያ” እና “ኢምቲሃን” በሐዳዲያህ ሰፈር
(ብታነቡት ትጠቀማላችሁ ኢንሻ አላህ)
1. “ተቂያ” ማለት ምን ማለት ነው?
ተቂያ ማለት ቋንቋዊ ፍቺው «ፍራቻ» ማለት ሲሆን ዲናዊ እና ቴክኒካዊ ፍቺው ደግሞ «አንድን አደጋ ፈርቶ ወይንም ሰግቶ እምነቱን መደበቅ ወይንም ልቡ ካመነበት ነገር ውጭ መፈጸም አሊያም መናገር» ማለት ነው።
ይህ ትርጓሜ የተወሰደው እንዲህ ከሚለው የአላህ ቃል ነው . .
لَّا يَتَّخِذِ الْمُؤْمِنُونَ الْكَافِرِينَ أَوْلِيَاءَ مِن دُونِ الْمُؤْمِنِينَ ۖ وَمَن يَفْعَلْ ذَٰلِكَ فَلَيْسَ مِنَ اللَّـهِ فِي شَيْءٍ إِلَّا أَن تَتَّقُوا مِنْهُمْ تُقَاةً ۗ وَيُحَذِّرُكُمُ اللَّـهُ نَفْسَهُ ۗ وَإِلَى اللَّـهِ الْمَصِيرُ ﴿٢٨﴾
ምእመናን ከምእመናን ውጭ ከሃዲያንን ወዳጆች አድርገው እንዳይዙ። ይህንንም የሚፈጽም ሰው በአንዳችም ነገር ቢሆን ከአላህ አይደለም። ከነርሱ የሚደርስባችሁን ሰግታችሁ ቢሆን እንጅ።
ከዚህ የቁርኣን አያህ እና ከመሰል መልእክት ከሚያስተላልፉ ሐዲሦች ተነስተን “ተቂያ” በኢስላም የሚቻልበት ቦታ እንዳለ መረዳት የምንችል ሲሆን ሆኖም ግን “ይቻላል!” ብለን በጥቅሉ የምንጠቀመው ሸሪዓዊ ብያኔ ሳይሆን ቦታና ግዜ፤ ሁኔታ እና የተጠቃሚው ደረጃን ተንተርሶ ብይኑ እንደሚለያይ ዑለማዎች ተናግረዋል።
1.1 ተቂያ መቼ ይቻላል?
ላለማርዘም ያህል የአንድ ሙፈሲርን ትንታኔ አይተን ወደ ጉዳያችን እንግባ. .
قَال الْقُرْطُبِيُّ : وَالتَّقِيَّةُ لاَ تَحِل إِلاَّ مَعَ خَوْفِ الْقَتْل أَوِ الْقَطْعِ أَوِ الإْيذَاءِ الْعَظِيمِ
ታላቁ የቁርኣን ተንታኝ ኢማም አልቁርጡቢ (ረሒመሁላህ) ከላይ የጠቀስነውን አያህ አስመልክቶ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል. .
“ተቂያህ ከግድያ (ሞትን) ፍራቻ መቆረጥን በመስጋት አሊያም በከባድ ስቃይና እንግልት ወቅት ካልሆነ በቀር አይቻልም።. .”
1.2 ተቂያ በማን ላይ ይቻላል?
“ተቂያ” በመሠረቱ የሚቻልበት ቦታ እንዳለ ብናሳልፍም ተፈጻሚ የሚሆነው ማን ላይ ነው? የሚለው ጥያቄ ግን ወሳኝ እና አንገብጋቢ ነው። ይህን አስመልክቶ ታላቅ ሊቅ ምን ይላሉ . .
ታላቁ የቁርኣን ሙፈሲር ኢብኑ ጀሪር (ረሒመሁላህ) ከላይ መግቢያችን ላይ የጠቀስነውን የጌታችንን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ይላሉ . .
قال ابن جرير الطبري : "التقية التي ذكرها الله في هذه الآية إنما هي تقية من الكفار لا من غيرهم"
“አላህ በዚህች አያህ የጠቀሳት ተቂያ እርሷ በኩፋሮች ላይ የምትፈጸም ተቂያ ነች። ከኩፋሮች ውጭ ላሉት ግን አይደለም።”
ተቂያ ቦታውና ሁኔታው አስገዳጅ ሲሆን በኩፋሮች ላይ የሚፈጸም ተግባር እንጂ በሙስሊሞች ላይ የሚቃጣ ሲሆን ካለመቻሉ አልፎ ወደ ውድቀት የሚመራ ታላቅ ወንጀል ነው። በዚህ ወንጀል ከሚታወቁትና ተቂያን ሙስሊሞች ላይ በመፈጸም ተግባራቸውን እንደ ጀብድ ከሚቆጥሩት አንጃዎች ውስጥ ዋነኞቹ የሯፊዷ ሺዐ ቡድን ተከታዮች ናቸው።
የሺዐዎች እምነት ዋነኛ መሠረት ተቂያ ነው ልንል በምንችልበት መልኩ ሺዐዎች ይህንን አሳፋሪ ተግባር በመፈጸም የሙስሊሙን ዓለም ሲያወናብዱ ለዘመናት ኖረዋል።
ሱኒይ መስለው ወደ ሱኒዩ ማሕበረሰብ በመግባት በርካታ የሽርክ ተግባራትን ወደ ሙስሊሙ ኡማ ለማስረጽ ጥረት አድርገዋል። አሁንም ተቂያን በመጠቀም ሱኒይ መስለው ወደ ሙስሊሞች ምድር በመምጣት የሶሓቦችን ክብር እያጎደፉ ሱኒው ዓለም በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ባልደረቦች ላይ ያለውን እምነት እንዲሸረሸር ብዙ ጥረዋል። ሺዐዎች ተቂያን ከመካናቸው የተነሳ ድራማ እየሰሩ በሱኒው ዓለም ለበርካታ ዓመታት መኖር እና ዲኑን መቦርቦር ችለዋል።
2. “ኢምቲሃን”
ኢምቲሃን ቋንቋዊ ፍቺው «ፈተና» ማለት ሲሆን ቴክኒካዊ ፍቺውም ቢሆን ተመሳሳይ ትርጓሜን ያወርሰናል።
ይህን ቃል ያቀፈ የጌታችንን ቃል እናንብብ
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِذَا جَاءَكُمُ الْمُؤْمِنَاتُ مُهَاجِرَاتٍ فَامْتَحِنُوهُنَّ
«እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ምእመናት ወደናንተ ሂጅራ በመጧችሁ ግዜ ፈትኗቸው።» [የፈታኚቱ ምእራፍ አያህ ቁጥር 10]
ይህን የቁርኣን የያህ አስመልቶ ታላቁ ሶሓባ ኢብን ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላል. .
قال ابن عباس : امتحانها : أن تستحلف ما خرجت لبغض زوجها ولا عشقا لرجل من المسلمين ولا رغبة عن أرض إلى أرض ولا لحدث أحدثته ولا لالتماس دنيا وما خرجت إلا رغبة في الإسلام وحبا لله ولرسوله
ፈትኗቸው ማለት፡ ኢስላምን ወይንም የአላህን እና የረሱልን ውዴታ ፈልጋ እንጂ ባሏን ጠልታ፤ ወንድ አፍቅራ፤ ከሃገር ሃገር መዞር አምሯት፤ አዲስ ጉዳይን ሽታ፤ ዱኒያን ፈልጋ . . (በሂጅራ ወደናንተ እንዳልመጣች ፈትኗት) ማለት ነው ብሏል።
2.1 ኢምቲሃን መቼ ይቻላል?
ኢምቲሃን የሚቻለው አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ በቁርኣን አያው እንደጠቀሰው የአንድን ሰው ዓቂዳ ወይንም ለሱና አሊያም ለአማና ያለውን ቦታ ለመፈተሽ በሚያስፈልገን ቦታ ብቻ እንደሆነ ዑለማዎች ይናገራሉ።
ለምሳሌ ያህል የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሴት ባሪያዋን “አላህ የት ነው” ብለው እንደጠየቋትና እርሷም “ከሰማይ ላይ” ብላ እንደመለሰችበት ግዜ ተጠቃሽ ነው።
2.2 ኢምቲሃን በማን ላይ ይቻላል?
ሸይኹል ኢስላም ኢብን ተይሚያህ እንደሚጠቅሱት ለአብነት ያህል አንድን ሰው ወዳጅ አድርገህ ልትይዝ ከፈለግክ አሊያም "ንስሃ ገብቷል" የተባልከው የቀድሞ ወዳጅህን ዳግም ለመወዳጀት ከፈለግክ ጥያቄዎችን አንስተህ ልትፈትነው ትችል ይሆናል። በመፈተንህም በአፉ የሚናገረው እና በቀልቡ የቋጠረው እንደማይጣረስ ለመረዳት ይጠቅምሃል ማለት ነው። አክለውም ዑመር ረዲየላሁ አንሁ ኢብን አቢ ሙሳን የፈተኗቸውን ፈተና አንስተው ያወሳሉ።
ሰለፎችም አንዳንድ ሰዎች ለሱና ያላቸውን አቋም ለማወቅና ለመረዳት የአንዳንድ ኢማሞችን ስም እያነሱ ስለነርሱ ያላቸውን አቋም በመጠየቅ ለኢማሞቹ ባላቸው ፍቅር እና ጥላቻ ሰዎችን ይፈትኑ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው። ሆኖም ይህንን ስንል አንዳንድ የምናከብራቸው ታላላቅ ዑለማዎች ኢምቲሃን “አይቻልም እንዲያውም ቢድዐ ነው” የሚል አቋም እንደሚያንጸባርቁ ካለመርሳት ጋር ነው።
----
ልክ እንደ ተቂያው ሁሉ ኢምቲሃን “ይቻላል” የሚል ማለፊያ ስንሰጠው በልቁ ማለታችን እንዳልሆነ መዘንጋት የለበትም። ሰዎችን ዋሽቶ፥ አጭበርብሮ፥ ተመሳስሎና ሰልሎ በሴራ፥ በደባ፥ በሸፍጥ ተንተርሶ መፈተን ጭራሽ ኢስላም የማያውቀው የሙናፊቆችና የአጭበርባሪ ዱርዬዎች ስራ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም።
ዛሬ ዛሬ ላይ ‘ለሱና ቅርበት አለን’ ብለው የሚሞግቱ ብሎም ‘የሰለፎችን መንሃጅ እናራምዳለን’ ብለው በአደባባይ ከሚለፍፉ ሰዎች ላይ ከላይ ያነሳናቸው ተቂያ እና ኢምቲሃን በማይቻል መልኩ ሲተገብሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
በቅረቡ አንድ የድምጽ ፋይል በዚሁ ፌስቡክ ላይ ተለቆ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰነባብቷል። ከዚህ በኋላ ያለው ጽሑፍ የሚመለከተው እነዚህን ኦዲዮ ፋይሎች ላደመጠና ግራ ለተጋባ ስለሆነ ያላደመጠና ግራ ያልተጋባ ነጃ ወጥቷልና ጽሑፉን ማንበብ ባይቀጥል ብየ እመክራለሁ . .
3.. ጉዳዩ . .
በኋላ ገሃድ እንደወጣው ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሐዳዲዮች በአንድ ሰለፊ ወንድማችን አማኻኝነት ስልጤ አካባቢ ገጠር ውስጥ ካሉ አንድ ሸይኽ ጋር የውሸት ጉድኝት (ልብ በሉ! ተቂያ 1 ይህ ነው) ይጀምራሉ። እነዚህ ሸይኽየውን የተዋወቋቸው ሰዎች ከሸይኽየው ጋር ቅርርብ በመፍጠር እምነት እንዲጥሉባቸው ብዙ ሰርተዋል። (ይህ ሒደታቸው ሸይኹን ባስተዋወቃቸው ወንድም ተተርኳል።) ከዚያም እነዚሁ ሐዳዲዮች ሸይኹ እምነት እንደጣሉባቸው ሲረዱ ካሉበት ሃገረ ደቡብ አፍሪቃ አንድ ጨረታ እንዳዘጋጁ ለሸይኹ ያበስሯቸዋል። (ሌላ ተቂያ።) ጨረታውም የሚዘጋጀው መስጂድ ለመገንባት፤ ሸይኽየውንም ሆነ ሌሎችን ኡስታዞች በኢኮኖሚ ለመደጎም ብሎም ለሌሎች ምክንያቶች ነበር። አንድ ቀን የሸይኹ ስልክ ድንገት ይጠራና በደስታ ብዛት “ሰክረናል” ያሉት ሐዳዲዮች ሸይኽየውን በድምጽ እየቀዱ በርካታ ገንዘብ ከጨረታው እንደሰበሰቡ፤ ጨረታውም ቀጣይ እንደሆነ፤ ሸይኽየውን በገንዘብ ደረጃ ሊደጉሙ እንደተዘጋጁ እና የመሳሰሉትን የተቂያ የውሸት ክምር ለሸይኹ ያበስሯቸዋል። ሸይኽየውም በሚሉት በመስማማት እሳቸውም በተከሰተው ነገር ደስተኛ እንደሆኑ ይገልጹላቸዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሸይኽየው “ኢምቲሃን” እንደተደገሰላቸው ሰዎቹም የተቂያ ድራማ እየተጫወቱ እንደሆነ ምንም ፍንጭ የላቸውም። . . የነዚህ ሐዳዲዮች ከሺዐ ሯፊዷ የወሰዱት የተቂያ ድራማ እና በሰቅጣጭ ለጆሮ የሚከብድ ኢምቲሃን (ፈተና) በዚሁ መልኩ ቀጥሎ ከሸይኹ የሚፈልጉትን ማግኘታቸውን ሲያረጋግጡ ስልኩን ይዘጉና በፌስቡክ “ተመልከቱ እኚን ጀምዒይ ሸይኽ . . !” ብለው መለጠፍ ያዙ።
ተቂያ + ኢምቲሃን ቢል ባጢል = ዘመንኛ ሐዳዲያ
አንዲት ሴት አንድን ‘በዲኑ ጠንካራ ነው’ ተብሎ የሚታሰብን ወንድ መፈተን ፈልጋ የሚያውቁትን ሰዎች አፈላልጋ ልጁን እንዲያስተዋውቋት በመጠየቅ ትተዋወቀዋለች። አንድ ቀን ተከናንባ ልጁ ገለል ብሎ ወደሚገኝበት ስፍራ ሄዳ ስታበቃ በወሬ መሃል ክንብንቧን ትገልጠዋለች። ወንድነቱን የሚፈታተን አውራዋን በማሳየት ትፈትነዋለች። ልጅ ምንም እንኳን ዲኑ ላይ ጠንካራ አቋም ቢኖረውም ሸይጧንና ነፍሲያው ተፈታትነውት ልጅቱን ጎንተል ያደርጋታል። ይህንን ሁሉ ከሩቅ ባስቀመጠችው ቪዲዮ የቀዳችው ይህችው ፈታኝ እንስት የምትፈልገውን እንዳገኘች ስታረጋግጥ ከልጁ ተሰናብታ ይህንኑ ቪዲዮ ገሃድ ታወጣዋለች። “ተመልከቱ ዲኑ ላይ ጠንካራ ነው የምትሉት ይሀው ልጅ እኔን ሲጎነታትለኝ በቪዲዮ ማስረጃው . . ” እያለች መለፈፍ ያዘች። ይሄኔ የልጁ ጠላቶችም የምትለውን ማስተጋባት ጀመሩ። ‘ማስረጃውን’ በትነው የልጁን ክብር ለማጉደፍ ተጣጣሩ።
ይህች እንስት ከፈጸመችው ድራማ (ተቂያ) በተጨማሪ በውሸት ላይ ተመርኩዛና ከልጁ የሚመጣውን አጸፋዊ የወንጀል መልስ ሽታ ይህንን ፈተና (ኢምቲሃን) ፈጽማለች።
ወደኛውም ጉዳይ ስንመጣ ተመሳሳይ ነገር እንስተውላለን። እነዚህ ሐዳዲዮች ተቂያ እና ባጢል የሆነ ኢምቲሃን ፈጽመው ሸይኽየውን ፈትነዋል። እሱ ሳይበቃቸው በሰሩት ሴራ እና ሸፍጥ ጮቤ ረግጠው የሸይኽየውን ክብር ለማጉደፍ አደባባይ ብቅ ብለዋል።
የሐዳዲዮች አጨብጫቢ የሆናችሁ ሁሉ በአላህ ይሁንባችሁ እስኪ ከእናንተ ውስጥ ባለ አስተዋይ አእምሮ ማን ነው ይህ ከንቱ የዱርዬ ስራ የሚያነቃው? ማንን ነው የአላህን ፍራቻ ልቡ ውስጥ የሚጥልበት?
አላህ ምስክሬ ነው! ሸይኽየው እስከምናውቃቸው ድረስ ለተውሒድ እና ለሱና ዘብ የቆሙ ሰው ናቸው። እድሜያቸውን የገፉት ይህንኑ የአላህ ሐቅ በመማር እና በማስተማር ነው! ታዲያ ምንው ሐዳዲዮች ቢያንስ ቢያንስ በእድሜያቸው እንኳን ክብርን ነፈጓቸው? የት ነው ሐያኣችሁ ያለው? እነ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ እንኳንስ ሙስሊም ሽማግሌን ይቅርና ካፊር ወይንም ሙሽሪክ እድሜ ባለጸጋ ሲያዩ ያለቅሱ አልነበረምን? ቢላሂ ዐለይኩም እናንተ ግን ይህንን የሺዐዎች መሰሪ ስራ ስትሰሩ ከማሰቢያ ጭንቅላታችሁ ጋር ናችሁን?
“ሸይኽየው ጥፋት አጥፍተዋል!” እንኳን ብንል በዚህ አይነት መልኩ ክብርን በሚያጎድፍ፤ ለኢስላም የሰሩትን ስራ መና የሚያስቀር ግፍ በርሳቸው ላይ መፈጸም ምን ቢያነሳሳችሁ ነው?
ለማታውቁ. .! አላህ በሐያት ያቆያቸውና ሸይኽየው ስለራሳቸው እና ስለተፈጠረው ሁሉ በሚገባ ያብራራሉ ብለን እንጠብቃለን ሆኖም እኔ ከሸይኽየው ለመከላከል በመፈለግ ሳይሆን ይህንን ልነግራችሁ እወዳለሁ. .
ሸይኽየው ስዑዲ ላይ በታላላቅ ዑለማዎች ዒልምን ተምረው ከመጡ ወዲህ ስልጤ ዞን ገጠር ውስጥ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን ይዘው ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በቆዩበት በርካታ ዓመትም ከበርካታ የቢድዓ ባለቤቶች ጋር ተጋፍጠዋል። እንኳንስ እነርሱ ይቅሩና ተማሪዎቻቸው እንኳን በዱላ እየተመቱ ከሱፊያ መሳጂዶች ተባረዋል። ሸይኽየው መሠረታቸው ሱኒይ የሰለፎችን መንሃጅ የሚከተሉ ሰለፊይ በመሆኑ ጥፋት እንኳን ብናስተውልባቸው ለእርሳቸው ያለን አመለካከት ልክ የቢድዓ አራማጅ ላይ እንዳሉት አጥፊዎች አይሆንም። እነ ኢማም በጘዊ ሙብተዲዖች ላይ ቦምብ የሆነ ትችት የሚጥሉ ትልቅ ቁርኣን ሙፈሲር ነበሩ። ሆኖም ግን ዐቂዳን የሚያህል ነገር ስህተት ኖሮባቸው መሠረታቸው ሱኒይ ሰለፊይ ነውና ዑለማዎች እሳቸውን ለማብጠልጠል ብእራቸውን አላነሱም። ተመሳሳይ ነገርም እነ ኢብን ሐጀር፥ ኢማም አንነወዊይ የመሳሰሉት ላይ የምናስተውለው ነው።
(ሳላስበው ጽሑፉ ረዝሞብኛልና አፉው በሉኝ)
ለማንኛውም. .
ከነዚህ የዱርዬ ስራ ከሚሰሩ ሐዳዲዮች ጋር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሸውዳችሁ ለገባችሁ ሁሉ የምመክረው ነገር ቢኖረኝ እንዲያው ለሰኮንድም ቢሆን ቆም ብላችሁ እንድታስቡ እንድታስተነትኑ ብቻ ነው።
አላህ እኛንም እናንተንም ይምራን

Abu Aisha