Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኹፍ ላይ ስለማበስ


ኹፍ ላይ ስለማበስ
ያለንበት ወቅት ብርዱ የበረታበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በኹፍ ላይ ወይም በካልሲ ላይ ስለማበስ ግንዛቤ ብንይዝ ለራሳችንም እንጠቀማለን፤ ሌሎችንም እንጠቅማለን፡፡
① ኹፍ ማለት ከስስ ቆዳ የሚዘጋጅ ከስር ጀምሮ እስክቁርጭምጭሚት ድረስ ወይም ከዚያም በላይ የሚሸፍን በእግር ልክ የሚዘጋጅ የእግር ልብስ ነው:: ስለዚህ ቁርጭምጭሚት የማይደርሱ አጫጭር ካልሲዎች ከኹፍ ውስጥ አይካተቱም ማለት ነው።
② በኹፍ ላይ ማበስ ማለት አንድ ሰው የተለመደውን የሶላት ውዱእ እያደረገ መጥቶ እራሱንና ጆሮውን ካበሰ በኋላ እግሮቹን ግን በማጠብ ፋንታ በእርጥብ እጅ አበስ ማድረግ ማለት ነው፡፡
③ የሚታበሰው ላይኛው እንጂ ታችኛው ማለትም ምድር የሚረግጠው ክፍል (ፋናችን) አይደለም፡፡ ዐልይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡- “ዲን ባስተያየት ቢሆን ኖሮ ኹፍ ከላይኛው ክፍሉ ይልቅ የታችኛው ነበር የሚታበሰው፡፡ ነገር ግን የአላህ መልእክተኛን ﷺ የኹፋቸውን ላይኛውን ክፍል ሲያብሱ አይቻለሁ፡፡” [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 153] ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ታች እግራቸውን ማበሳቸው ከከፊል ምሁራን የተገኘ ቢሆንም መረጃ የሚደግፈው አይደለም ማለት ነው፡፡ በርግጥ ደካማ ስለሆነ እንጂ ነብዩ ﷺ “ከታችም ከላይም አብሰዋል” የሚል ሐዲስ አለ፡፡ [ዶዒፍ ሱነን አትቲርሚዚ፡ 77]
④ አለባበሱን በተመለከተ ከኺላፍ ለመውጣት ያክል ሁለት እግሮቹን አጥቦ ከጨረሰ በኋላ መልበሱ የሚሻል ቢሆንም በየተራ ቀኙን እንዳጠበ የቀኝ ኹፉን፣ ግራውን አጥቦ ሲጨርስ ደግሞ የግራ ኹፉን መልበስም ይችላል፡፡
⑤ በኹፍ ላይ ማበስ የሚቻለው በጦሀራ (ውዱእ) ላይ እያለ ኹፉ ከተለበሰ ነው፡፡ [አልኢስቲዘካር፡ 2/256] [አልሙግኒ፡ 1/361]
⑥ የሚታበስበት የጊዜ ርዝማኔ ለነዋሪና ለመንገደኛ የተለያየ ነው፡፡ ለመንገደኛ (ሙሳፊር) 3 ቀን እና 3 ሌሎቶች ሲሆን ሙቂም ማለትም በሃገሩ ላይ ተቀማጭ የሆነ ግን ለአንድ ቀንና ሌሊት ነው፡፡ (24 ሰዓት፡፡) [ሙስሊም፡ 276] ታዲያ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ኹፉ ከተለበሰበት ወቅት ጀምሮ ሳይሆን ማበስ ከተጀመረበት አንስቶ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ በሃገሩ ኗሪ (ሙቂም) የሆነ ሰው ዐስር ላይ ውዱእ አድርጎ ኹፉን ቢለብስና በዚሁ ውዱእ ዐስርን፣ መግሪብንና ዒሻን ቢሰግድ ከዚያም ኹፉን ሳያወልቅ ተኝቶ ማለዳ ላይ ውዱእ አድርጎ እግሩን ቢያብስ መቁጠር የሚጀምረው ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡
⑦ አስተባበሱ ቀኝ እግርን በቀኝ እጅ፣ ግራ እግርን በግራ እጅ #በአንዴ ማበሱ በላጭ እንደሆነ ዑለማዎች ይገልፃሉ። በየተራ ቢሆንም ችግር የለውም።
⑧ ኹፍን ማውለቅ ውዱእ አያበላሽም፡፡ የጊዜ ገደቡ ሳያልቅም ይሁን ከተጠናቀቀ በኋላ ኹፋችንን ብናወልቅ ሌሎች ውዱእን የሚያጠፉ ነገሮች እስካልገጠሙን ድረስ ውዱኣችን እንዳለ ነው፡፡
⑨ የማበሻ ጊዜውን ሳይጨርስ በፊት ኹፍን ያወለቀ ሰው እንደገና ቢያስገባም የማበስ ብይኑ ተቋርጧል:: ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ ሰው ውዱእ ቢያጠፋ እንደ ማንኛውም ውዱእ እግሩንም ጭምር ማጠብ እንጂ ካወለቀ በኋላ ባስገባው ኹፍ ላይ ማበስ አይችልም፡፡
(10) ኹፉ ቀዳዳ ቢኖርበትም በላዩ ላይ እያበሱ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቀዳዳ ካለው በላዩ ላይ ማበስ አይቻልም ያሉ ቢኖሩም መረጃ የሚደግፈው ግን አይደለም፡፡ ታላቁ ሰለፍ ሱፍያን አሥሠውሪ ረሒመሁላህ ኹፍን አስመልክተው “እግርህ ላይ እስካለ ድረስ አብስበት፡፡ የሙሃጂሮችና የአንሳሮች ኹፎች የተበሳሱ፣ የተቀዳደዱና የተጣጣፉ እንጂ ሌላ ነበሩ ወይ?!” ይላሉ:: [ሙሶነፍ ዐብዶርረዛቅ፡ 753]
ኹፍ የሚመለከተው ወዱእን ብቻ ነው:: ስለዚህ በጀናባም ይሁን በሌላ ምክንያት ትጥበት ግዴታ በሚሆንበት ጊዜ ኹፍን አውጥቶ ሙሉ አካልን ውሃ ማስነካት ግዴታ ስለሆነ በዚህ ጊዜ በኹፍ ላይ ማበስ አይቻልም፡፡ [ኢርዋኡል ገሊል፡ 104] ኢብኑ ሐጀር እንዲህ ላሉ፡- “በኹፍ ላይ ማበስ ውዱእን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ እንጂ ከሙሉ የሰውነት ትጥበት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ በዚህ ላይ ኢጅማዕ አለ” ይላሉ፡፡ [አልፈትሕ፡ 206]
(11) እስካሁ በኹፍ ላይ ስለ ማበስ ያሳለፍናቸው በካለሲ ላይ ማበስንም የሚመለከቱ ናቸው::
(ኢብኑ ሙነወር፣ ታህሳስ 28/2009)