Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኸዋሪጆች እና ሐዳዲዮች ያላቸው ተመሳስሎሽ!

 

ኸዋሪጆች እና ሐዳዲዮች ያላቸው ተመሳስሎሽ!
1) ሁለቱም በአፍላ እና በአስተሳሰብ ለጋ በሆኑ ወጣቶች የተሞሉ ስብስቦች ናቸው!
- ዛሬ ላይ ኸዋሪጆች የእኔ የሚሉት ረባኒ (ጥልቅ እውቀት ያለው) ዐሊም አንድም የለም። ሁለት ወይንም ሦስት ሳይሆን አንድም የላቸውም።
ነገር ግን በሞራልና በትኩስ ስሜት የተሞላ አፍላ ወጣት ግን ሞልቷቸዋል። የሸይኽነት ዶጎማ ተሰጥቶት፤ በሙፍቲነት ካባ ተለብሶ መርጂእ /መመለሻ/ የሆናቸው ሩወይቢዷ ግን እልፍ አላቸው።
የአላህ መልእከተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለነርሱ ሲናገሩ. .
(حُدَثَاءُ الْأَسْنَانِ)
« በእድሜ አፍላ ናቸው! »
በሌላም ሐዲሥ እንዲህ አሉ . .
سُفَهَاءُ الْأَحْلَامِ
«የአስተሳሰብ ለጋዎች ናቸው!»
ሆኖም ግን ምን ያደርጋል. . ዑለማዎች ግን ጀርባ ሰጥተዋቸዋል፤ ከነርሱም ያስጠነቅቃሉ።
ስለዚህ. .
ኸዋሪጆች ዑለማዎችን ይጠሏቸዋል። ሒሳቡ ቀላል ነው።
- ሐዳዲዮች የመሪያቸውን የሕያ አልሐጁሪ ተከታዮች ብንመለከት በጨቅላ ሕጻናት የተሞሉ፤ በአስተሳሰብ ያልበሰሉ፤ የቁርኣንና የሐዲሥ ጠለቅ ያለ እውቀት የሌላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። ተመልከቱ እውጭ ሃገርም ይሁን እዚሁ ሃገር ውስጥ እነርሱን ደግፎ፤ ለእነርሱ የሚከላከል አንድ እንኳን በእድሜ ጠና ያለ ሰው ጥቀሱልኝ ብላችሁ ማንን ትጠቅሱልኝ ይሁን? በአላህ ይሁንብኝ! ሐዳዲዮች ጋር በእድሜ የገፋ፤ በአስተሳሰብ የበሰለ፤ በተሞክሮ የተካነ አንድም ሰው አይተን አናውቅም። ከመሪያቸው የሕያ አልሐጁሪ ጀምሮ በጉርምስና ላይ ያሉ የአፍላ ወጣቶች ጥርቅም ናቸው።
2. ኸዋሪጆች መሪዎችን ፤ ሐዳዲዮች ዑለማዎችን አይወዱም!
- በየትኛውም ዘመን በየትኛውም ቦታ ያሉ ኸዋሪጆች ከሙስሊም መሪ ጎን አይቆሙም። እንዲያውም በሙስሊም መሪ ላይ አመጽን ያነሳሳሉ። መሪዎችን በጸያፍ ቃላት እየገለጹ ሙስሊሞች በመሪዎቻቸው ላይ ያላቸውን እምነት ይሸረሽራሉ። በስተመጨረሻም መሪውን በኩፍር ወንጅለው በርሱ ላይ ጂሃድን ያውጃሉ። ጠቅለል ባለ ቃል መሪያቸው ዐብዱ’ላህ ኢብን ሰባእ ለተመሪዎቹ መልእክቱን ሲያስተላልፍ እንዲህ ይላል. .
“ግባችሁ ላይ ለመድረስ በሞራል ተጓዙ። ቅድሚያ በመልካም ነገር በማዘዝ ከመጥፎም በመከልከል ከዚያም መሪዎችን በማጣጣል ጀምሩ። ይህንኑ እየሰራችሁ ሰዎችን ሳቡ ከዚያም ወደናንተ እንዲያዘንብሉ ገፋፉ።” [ታሪኽ አጥጦበሪ]
ኸዋሪጆች ሰዎችን ወንጀል እንዳይሰሩ ያስጠነቅቃሉ። ሶላት እንዲሰግዱ፤ ዘካ እንዲመጸውቱ፤ ሐጅ እንዲያደርጉ ይመክራሉ። ነገር ግን ሁሉንም ስራቸውን ጥላሸት የሚቀባውን ኃጢዓት ይፈጽማሉ። ሙስሊሞች መሪዎቻቸውን እንዲጠሉና በነርሱ ላይ እንዲያምጹ ያነሳሳሉ።
- ሐዳዲዮች ለዑለማዎች ያላቸው ጥላቻ እንዲህ ነው ተብሎ በመጠን አይገለጽም። ልክ ኸዋሪጆች ሙስሊም መሪዎችን ወደ መጥላት እንደሚጣሩት ሁሉ ሐዳዲዮችም በየዱሩሶቻቸው፥ በየሙሓደራዎቻቸው፤ በየኹጠቦቻቸው የሙስሊሙ ኡማ አይን፥ ጆሮ፥ አንደበት የሆኑትንና የነቢያት ወራሾችን ዑለማዎች እያብጠለጠሉ ህዝቡ ለነርሱ ያለውን እምነትና ፍቅር አውጥቶ በጥላቻ እንዲተካ ነጋ ጠባ ይጥራሉ። ጀማል ያሲን፥ ሱልጣን፥ ከማል፣ ... ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ በእያንዳንዱ ዱሩሶቻቸው ላይ ዑለማዎችን በመተቸት ተማሪዎቻቸው ለዑለማዎቹ ያላቸውን ፍቅር በጥላቻ እንዲቀይሩ ይመክራሉ። በዚህ አካሄዳቸው ቀጥለው ዛሬ ላይ እነርሱ ዘንድ ከየሕያ አልሐጁሪ ውጭ የእኛ የሚሉት አንድም ዓሊም አብሯቸው የለም። የእነርሱን ስሜት ደግፎ፤ ያሉበትን የባጢል መንገድ አጽድቆ፤ የነቀፉትን ነቅፎ፤ ያላቁትን አልቆ. . እነርሱን “በጀ!” ያለ አንድም እደግመዋለሁ አንድም ረባኒ ዓሊም የለም። ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ? እንግዲያው አንድን ሐዳዲ ሄዳችሁ « “ጀምዒይ!” እያለ በሙብተዲዕነት የሚፈርጅ አንድ ዓሊም ጥቀስልኝ እስኪ?» በሉት! ለመልስ መስጫ ግዜም ብዙም ሳታስጨንቁት አንድ ሙሉ ወር አረረ እንዲያውም አንድ ሙሉ ድፍን ዓመት ጀቡት! ብዙም ሳትደክሙ መልሱን እኔ ልንገራችሁ. . አንድም ዓሊም አያመጣም! ሁለት ሦስት አላልኳችሁም! አንድም ዓሊም አያመጣም! ስለዚህ? ስለዚህ ዑለማዎች በዚህ ጽንፍ አካሄዳቸው አማኻኝነት ፊት ነሷቸው! በተከታታይ አካሄዳቸውን ነቀፉባቸው! ስለዚህ ሐዳዲዮች ዑለማዎችን ይጠሏቸዋል። አሁንም ሒሳቡ ቀላል ነው።
3) ሁለቱም “ለሕዝብ ጥቅም ጥብቅና የቆምን ነን!” ብለው ይሞግታሉ!
- እንደ ኸዋሪጆች ለሕዝብ ሃብት ተቆርቋሪ፤ ለወገን ንብረት አሳቢ ከእኛ በላይ ላሳር ብሎ ሞጋች የለም። ኸሊፋውን ዑሥማን ረዲየላሁ ዐንሁ ለምን እንደገደሉት የሚያውቅ አለን? “ለሙስሊሙ ዑማ የሚውልን ለዘካ፥ ለየቲም፥ ለምስኪን የሚከፋፈል ገንዘብ ለራስህ ጥቅም አውለሃል፤ ከበይተል ማል ዘርፈህ ለቤተሰብህ አድለሃል፤ ዘመድ አዝማድህን ሾመህ ሌላውን ደግሞ ሽረሃል ወዘተ . .” በሚሉ ውንጀላዎች ተነሳሽነት እንጂ በሌላ አልነበረም። ኸዋሪጆች በዑሥማን አገዛዝ ውስጥ የነበሩ የአካባቢ አመራሮች የዘካ፥ የምጽዋት እና የጂዝያ ገንዘብ ለዑሥማን እንዳይከፍሉ ደብዳቤ ጽፈው ይሰዱ ነበር። “ከሙስሊሙ የተሰበሰበው ገንዘብ ወደ ሙስሊሞች የሚታደል አሊያም መሳጂዶች የሚሰሩበት፤ መሳኪኖች እና አይታሞች ጋር የሚከፋፈል ሳይሆን ዑሥማን ረዲየላሁ ዐንሁ ለግል ጥቅሙ የሚያውለው ነው!” ብለው ወሬን ነዝተዋል። (ሙሉ ታሪኩን ሲየር አዕላሙ ኑበላእ እና ታሪኹ ጦበሪ ላይ ያገኙታል)። በዚህም ተነሳስተው ታላቁን ኸሊፋ እስከመግደል ደርስሰዋል። እንዳው ከአነሳሳቸው እንኳን ብንጀምር የአላህ መልእክተኛን ዙል ኹወይሲራ የተባለ ሙናፊቅ ኻሪጂ “አላህን ፍራ! የሙስሊሞችን ገንዘብ በፍትሕ አከፋፍል!” አልነበረም ያላቸው?
- ሐዳዲዮች ለሙስሊሙ ኡማ ከእኛ በላይ የሚያስብ የለም ብለው አቋም ይዘዋል። ለአይታም ተብሎ የተሰበሰበ ገንዘብ ለግል ጥቅም ነው የሚውለው ብለው ከመነሻው መሰብሰቡንም ነቅፈዋል። በተቀናጀ መልኩ ገንዘብ ሰብስቦ መሳጂዶችን መገንባት “የሙተሰቲር ኢኽዋኒ” አካሄድ ነው ብለው ጽንፍ ይዘዋል። ልክ እንደ ኸዋሪጆች ሙስሊሞች ለምጽዋት ሰብሳቢዎች ኸይርን ፈልገው ገንዘብ እንዳይመጸውቱ አዘዋል። የተሰበሰበውም ገንዘብ ለመሳኪኖች፥ ለአይታሞች፥ ለመስኪድ ማሰሪያ የሚውል ሳይሆን “ሰብሳቢዎቹ ኪስ የሚገባ ሳንቲም ነው!” ብለው ሞግተዋል። ከጥላቻ የመነጨው ይሀው አካሄዳቸው ባላዩትና ባልሰሙት ነገር ችኩል ፍርድ እንዲሰጡ ጋብዟቸዋል። እድል ገጥሟቸው በዚህ መሃል እንደሚሞግቱት የተሰበሰበውን ሳንቲም ለኪሱ የሚያስገባ “ሌባ” ያገኙ እለትማ ጮቤ ረግጠዋል። “ተመልከቱ! ጀምዒዮች ማለት በጠቅላላ እነኚሁ ናቸው!” በማለት ያለማቅማማት በጅምላ ፍረጃ ይጠመዳሉ። እዚህ ወጥመዳቸው ስር ለማስገባት ሴራ፥ ደባ፥ ሸፍጥ ከማድረግ ወደኋላም አይሉም።
4) ኸዋሪጆች የነቀፋቸውን በካፊርነት፤ ሐዳዲዮች የነቀፋቸውን በሙብተዲዕነት ከመፈረጅ ምንም አይገዳቸውም! [ብቻቸውን ሐቅ ላይ ናቸው!]
- ኸዋሪጆች ከማክፈር ወደ ኋላ የሚሉ ፍጡሮች አይደሉም። ለእነርሱ ማክፈር ማለት ውሃ የመጠጣት ያህል ቀላል እጅግ በጣም ቀላል ድርጊት ነው። ይህ ድርጊታቸውን ያስተዋለው ታላቁ ሶሓቢ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ አለ. .
«እነርሱ (ኸዋሪጆች) ስለካፊሮች የሚናገሩ የቁርኣን አያዎችን ወሰዱና ለሙስሊሙ ተጠቀሟቸው።» [ቡኻሪ]
አስሰፈራኒ ረሒመሁላህ ዐብዱላህ ኢብን አርዟቅ ስለተባለው የኸዋሪጆች መሪ ሲናገሩ . .
«ከርሱ ጋር የተቃረኑትን በጠቅላላ በኩፍር ወንጅሎ ደማቸውንም ሐላል ያደርጋል።» [ለዋሚዐልአንዋር]
- ሐዳዲዮች በሙብተዲዕነት ከመፈረጅ ወደ ኋላ የሚሉ በፍጹም አይደሉም። በዚህ አካሄዳቸው ወደ ቢድዓ የሚጣራ እና ቢድዓ ላይ የወደቀ በነርሱ አይን አንድ ነው። ጭራሽ ከሙብተዲዖች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን የትኛውንም ግለሰብ የነርሱን አቋም ስላልደገፈ ወይንም ሐጁሪን ስለነቀፈ ብቻ ከሱና ገፍትረው አስወጥተው በሙብተዲዕነት ይወስፉታል። ዑለማዎች መካከል ኺላፍ ያለበትን መስአላ እየመዘዙ እያወጡ ከእነርሱ ጋር ያልሄደውን በጠቅላላ “በጀምዒይነት፥ በኢኽዋኒነት፥ በቱራሢይነት . .” ከመወንጀል ወደኋላ አይሉም። በነርሱ አስተሳሰብ ማንም ሰው ከነርሱ ጋር ካልሆነ እነርሱ ላይ ነውና እርሱ ወደደም ጠላም ሙብተዲዕ ነው። ይህ አካሄድ ዋነኛ የሐዳዲዮች ባህሪ ሲሆን በይበልጥ የሚታወቁበትም ጭምር ነው።
5) ኸዋሪጆች ጣዖት አምላኪያንን ትተው ሙስሊሞችን ይዋጋሉ፤ ሐዳዲዮች የቢድዓ ባለቤቶችን ትተው የሱንናህ ባለቤቶችን ይተቻሉ!
- በኸዋሪጆች እጅ የሞተው የሙስሊም ነፍስ ቁጥር ከካፊሩ ነፍስ ቁጥር እጅጉን የበዛ እንዳውም ከሀዲያንን ትተው አማኞች ላይ ዘምተዋል ብለን አፋችንን ሞልተን እስከምናወራ ይደርሳል። ይህ ባህሪያቸው በታላቁ ነቢይ አንደበት እንዲህ ተገልጿል. .
(يَقْتُلُونَ أَهْلَ الإِسْلاَمِ وَيَدَعُونَ أَهْلَ الأَوْثَانِ)
“የኢስላም ባልተቤቶችን ይገድላሉ። የጣዖት ባልተቤቶችን ይተዋሉ።” [ቡኻሪ]
- ሐዳዲዮች ዘንድ የሙብተዲዕ ስም ተነስቶ ስሙ አይብጠለጠልም። ቢነሳም በትንሹ ነካ ተደርጎ ይታለፋል። ነገር ግን ዋነኛ ዒላማቸው ሰለፊዩ ማህበረሰብ ነው። ዋነኛ ግባቸው አህሉልሱንናዎችን ማጥቃት ነው። በተገኘው አጋጣሚ ወደ ተውሒድና ሱንናህ የሚጣሩ ዑለማዎችን፥ ዱዐቶችን፥ ኡስታዞችን ስም እያነሱ ስም በማጠልሸትና በቅጥያ በመጥራት ይዘምታሉ። ሙብተዲዖች ከነርሱ ነጃ ወጥተዋል። ሰለፊዮች ግን (በነርሱ አባባል ጀምዒዮች ግን) ጥርሳቸው ውስጥ ገብተዋል። ስሜታቸውን እየተከተሉ ለውድቀት ተዳርገዋል።
-------
በርግጥም ኸዋሪጆችን እና ሐዳዲዮችን አንድ የሚያደርጋቸውን በርካታ ባህሪያት መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም ግን ለአስተዋይ ይህ በቂው ነውና እዚህ ጋር እናብቃው። ኸዋሪጆችና ሐዳዲዮች ተመሳሳይ ባህሪን ይጋራሉ ማለት ግን <<አንድ ናቸው>> የሚለውን እንደማያስይዝ ለማንም ሊሰወርበት አይገባም።
አላህ እኛንም እነርሱንም ይምራን

Abu Aisha