Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የእኛን ሰማእት ስንዘክረው. . (ክፍል ሁለት)


የእኛን ሰማእት ስንዘክረው. .
(ክፍል ሁለት)
. . . ይህን ታላቅ ሰማእት ለሸይጧን መስእዋት ለማቅረብ ከግብጽ እና ከኩፋ (ዒራቅ) በመነሳት መዲና ድረስ ተጠራርተው የመጡ አማጽያን ለአርባ ቀናት ያህል ልክ ደም እንደተጠማ አውሬ በቡድን በቡድን ሆነው እበሩ ላይ ሲያጉረመርሙ ከርመዋል። መቀመጫቸውን የዚህ ባለክብር ሰብእና ባለቤት ደጃፍ ላይ ካደረጉ ሰነባብተዋል። እዚህም እዚያም እያሽካኩ ደባና ሸፍጥ ያሴራሉ። ምቹ አጋጣሚን ፈልገው ይህን ሰማእት ሊሰው ዝጅጉ ሆነው በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ይገኛል።
በዚህ አጋጣሚ ላይ ሳሉ የማይደርስ የለምና ዙል ሒጃህ 18 በተከበረችው የጁምዐ ቀን የዚህ ሰማእት እለተ-ህልፈት ሆና ተመረጠች!!!
አዋጅ. . . ! ዛሬ ይህ ታላቅ ሰው በሸይጧን ወታደሮች ተሰውቷል!
አዋጅ. . . ! ዛሬ ይህ ታላቅ ሰው ምድር ላይ ያለውን እድሜ አገባድዶ ወደ ዘላለማዊው ጀነት አርጓል!
አዋጅ. . . ! ዛሬ ይህ ታላቅ ሰው ፈጣሪው ያለበሰውን ኩታ በመናፍቃን ተቀምቶ ጌታው ዘንድ አቤቱታውን ለማሰማት ላይመለስ ሄዷል!
አዋጅ. . . ! ዛሬ ሸይጧን ለዘመናት ሲቋምጥ የነበረውን መስእዋት በላካቸው ወታደሮቹ በኩል ተሳክቶለትት ጮቤ ረግጧል!
አዋጅ. . . ! እኛ ሙስሊሞች ዛሬን ተቆጭተናል! መናፍቃን ግን ተደስተዋል!
ይህን እለት ትውልድ ላይዘነጋው በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ዛሬ. . ስለዚህ ሰማእት እንዘክራለን!
ዛሬ. . ይህን ሰማእት እያወሳን. .
“እንተን የወደደህን እንወዳለን!”
“አንተን የጠላህን እንጠላለን!” ብለን ቃል እንገባለን!
ዛሬ. . የዚህን ሰማእት ገድል እንዳንዘክር የሚሹ ርዝራዥ የሸይጧን ወታደሮችን የሰማእቱን ስም ከ. . .ፍ! አድርገን እያነሳን በቁጭት ይሞቱ ዘንድ እንተዋቸዋለን!
“የእኛን ሰማእት ስንዘክረው” ባለፈው ካቆምንበት እንቀጥላለን . .
ክፍል አንድን ያላነበባችሁ በቀጣዩ አስፈንጣሪ ልታገኙት ትችላላችሁ. .
bit.ly/ሰማእቱን_ክፍል_1
ቆይታችሁ ከእኔ ጋር ይሁን!
. . ሰይፉ ከአፎቱ ተመዟል . .! በምሉእ ፍጹም እውነተኝነት እዛፉ ስር ሆነው ቃል ኪዳናቸውን ያደሱት ከአንድ ሺህ አራት መቶ በላይ ጀግና ወታደሮች ለቂም በቀል ታጥቀው ተነስተዋል። ሁሉም ሞት ሞት ሸቶታል። ሞትን ግን እንደ ክብር እንጂ በፍርሃት ያየው አንድም አልነበረም። ዛሬ ጦርነት ታውጇል። ሁሉም ጠላት ሜዳ ላይ ገብቶ ሸሂድነትን ለመቀዳጀት ቋምጧል። ሁሉም በያዘው ሰይፍ ጠላትን አርበድብዶ ወደገሃነም ለማውረድ “ሂድ” የሚለውን ቀጭን ትእዛዝ ብቻ ይጠባበቃል።
ይህ ሁሉ ደም ደም የሚሸት ቅድመ ዝግጅት የሚያደረገው እነዚህ ሙስሊም ወታደሮች መሬታቸው በወራሪ ኃይል ተወሮ፤ በሺዎች የሞቅጠሩ ሴቶች፥ አረጋውያን፥ እና ልጆቻቸው ተገድለውባቸውም አይደለም።
በጭራሽ አይደለም! ዛሬ እነዚህ ሙስሊም ወታደሮች ለአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ቃልኪዳናቸውን አድሰው በቆራጥነት ለበቀል የተነሱት አንድ ታላቅ፥ ባለ ክብር፥ ባለ ልቅና ግለሰብ ጠላት ሜዳ መልእክት ለማድረስ በሄድበት የውሃ ሽታ ሆኖ ስለቀረ ነው። በርግጥም ለዚህ ታላቅ ሰው በቀል መልእክተኛውን (ﷺ) ጨምሮ ሙስሊሞች በጠቅላላ “ሞት እንጂ የሚያቆመን ሌላ ምንም አይበግረንም! ለርሱ ስንል ህይወታችን ይሰዋ!" ብለው ምለውና ተገዝተው መነሳታቸው ይህ ሰው በኢስላም ውስጥ ምን ያህል ግዙፍ ደረጃ እንዳለው እንደሚያሳይ ለማንም አይሰወርበትም!
የአላህ ፍቃድ ሆነና እነዚህ ወታደሮች ወጦርነት አውድማ ገብተው ጠላትን ከማርበድበዳቸው በፊት ዑሥማን እንደተወራው ሳይሆን አንዳችም ነገር ሳይነካ ወደ ሙስሊሞች ስፍራ ተመለሰ። መልእክተኛው (ﷺ) ጨምሮ ሙስሊሞች የርሱን በህይወት መኖር ሲያዩ በርግጥም ልባቸው ረጋ። ደስም አላቸው። ጦርነቱም ቀረ። በቦታው ከጠላት ጋር በኢስላም ታሪክ ውስጥ ታላቅ የስምምነት ውል ተካሄደ። የውሉም ስያሜ «ሱልሕ አልሑደይቢይያህ» በመባል ይታወቃል።
በሌላ ግዜ በሌላ ርእስ ስለውሉ አንስተን እንነጋገራለን። ለዛሬ ግን የዚህን ታላቅ ሰው በኢስላም ውስጥ ያለውን ታላቅ ደረጃና ክብር ምን ያህል እንደሆነ እናውራ. .
ዑሥማንና ክብሩ. .
ሁሉም የመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ባልደረባዎች ክብርን የተጎናጸፉ፤ በመልካም እንጂ የማይወሱ አላህ (ﷻ) መልእክተኛውን (ﷺ) እንዲጎዳኙ የመረጣቸው ታላላቅ ስብእናዎች ናቸው።
በርግጥም አላህ ከምርጦችም ምርጡን ይመርጣል! ከታላላቆችም ትልቁን ያተልቃል! ከባለክብሮችም ይበልጥ የተከበረውን ያስከብራል!
ወራቶች ሁሉ የአላህ ናቸው። ሁሉም መልካም ቢሆኑም አላህ ግን የረመዷን ወርን ይበልጥ መልካሙ ወር አድርጎ መረጠው! በሳምንት ውስጥ ያሉ ቀናቶች ሁሉ የአላህ ናቸው። ሆኖም አላህ ከሳምንት ውስጥ ካሉ ቀናቶች ጁምዐን አላቃት። ነቢያቶች ሁሉ የአላህን መልእክት እንዲያደርሱ በአላህ የተመረጡ ታላላቅ ሰዎች ናቸው። አላህ ግን ከሁሉም ምርጥ ነቢያቶች ሙሐመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን ከምርጦችም ምርጥ፥ የሰው ልጆች ሁሉ አለቃ አደረጋቸው።
አላህ የሰው ልጆችን ሁሉ ቀልብ ተመለከተና ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምን እንዲጎዳኙ አስሓቦችን መረጣቸው። ልቅናም ሰጣቸው። ከአስሓቦች ሁሉ ደግሞ ከአላህ ነቢይ ጋር ስደትን የተሰደዱትን ሙሃጂሮች አበለጣቸው። ከሙሃጂሮች ሁሉ ደግሞ ከአቡ በክርና ዑመር ቀጥሎ ታላቁን ኸሊፋ ዑሥማንን አብልጦ መረጣቸው።
۝ ((انظُرْ كَيْفَ فَضَّلْنَا بَعْضَهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ ۚ)) ۝
۩ከፊላቸውን ከከፊላቸው እንዴት እንዳስበለጥን ተመልከት. .۩
ይላቸዋል ታላቁ ጌታችን አላህ ለመልእክተኛው (ﷺ). . [አልኢስራእ 21]
አዎን! አላህ (ﷻ) ከአስሓቦች ሁሉ ከአቡ በክርና ከዑመር ቀጥሎ ዑሥማንን ከፍተኛ ደረጃን ሰጥቷቸዋል።
ኢብን ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ. .
«ረሱል (ﷺ) በመሃከላችን እያሉ እንዲህ እንል ነበር. . “ከረሱል (ﷺ) ቀጥሎ ከሰዎች ሁሉ በላጩ አቡ በክር፥ ዑመር፥ ዑሥማን ናቸው።” እንል ነበር። ረሱልም (ﷺ) ሰምተው አይቃወሙንም ነበር።» [ቡኻሪ]
ዑሥማን የጀነት ነው!
ጀነት የአላህ ስጦታ ናት። ለወደደው እንጂ አሳልፎ የማይሰጣት። ከውድም ውድ የሆነችዋን ጀነት እውስጧ ለመግባት የሰው ዘር በጠቅላላ ይቋምጣል። ብዙዎች እንደተመኟት ሳያገኟት ይቀራሉ። ሙእሚኖች ግን ይታደሏታል። ጥቂቶች ገና በዲኒያ ሳሉ በነርሱና በጀነት መካከል ያለው አጥር “ሞት” እንደሆነ በነቢይ አንደበት ተመስክሮላቸዋል። አንዳንዶች በጥቅል፥ አንዳንዶች በተናጥል ጀነትን እንደሚወርሱ ተበስረዋል። ታላቁ የሙእሚኖች መሪ ዑሥማን ቢን ዐፋን ግን በበርካታ አጋጣሚዎች የጀነት ሰው መሆኑን የአላህ መልእክተኛ አረጋግጠውለታል. .
አቡ ሙሳ ረዲየላሁ ዐንሁ አንድን አጋጣሚ ሲተርክ እንዲህ ይላል ፦
« በመዲና ካሉ የማሳዎች በአንዱ ውስጥ ከረሱል (ﷺ) ጋር ነበርኩኝ። አንድ ሰው መጣና በሩ እንዲከፈትለት ጠየቀ። ረሱል (ﷺ) “በሩን ክፈትለት። በጀነትም አበስረው!” አሉኝ። ከፈትኩለት እርሱም አቡ በክር ነበር። ረሱል (ﷺ) እንዳሉኝም አበሰርኩት አላህን አመሰገነ። ከዚያም አንድ ሰው መጣና በሩ እንዲከፈትለት ጠየቀ። ረሱል (ﷺ) “በሩን ክፈትለት። በጀነትም አበስረው!” አሉኝ። ከፈትኩለት እርሱም ዑመር ነበር። ረሱል (ﷺ) እንዳሉኝም አበሰርኩት አላህን አመሰገነ። በድጋሚ አንድ ሰው መጣና በሩ እንዲከፈትለት ጠየቀ። ረሱል (ﷺ) “በሩን ክፈትለት። ከበርካታ መከራዎች ጋር በጀነት አበስረው!” አሉኝ። ከፈትኩለት እርሱም ዑሥማን ነበር። ረሱል (ﷺ) እንዳሉኝም ነገርኩት አላህን አመሰገነና “እገዛ በአላህ ነው!’’ አለ። [ቡኻሪ]
ዐብዱ’ረሕማን ቢን ዐውፍ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፦
«አቡ በክር የጀነት ነው፤ ዑመር የጀነት ነው፤ ዑሥማን የጀነት ነው፤ ዐሊይ የጀነት ነው፤ ጦላሐህ የጀነት ነው. . . » እያሉ አስር ሰዎችን ስም አከታትልለው ጠሩ። [ቲርሚዚይ፤ አልባኒ “ሶሒሕ”]
ኢብን ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዳስተልላፉት የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ከሶሓቦቻቸው ቁጭ ብለው ሳለ . .
«” ከዚህ መንገድ አንድ ሰው ብቅ ይላል። ይህ ሰው የጀነት ነው።” አሉ። ከመንገዱ ዑሥማን ቢን ዐፋን ብቅ አለ።» [አሕመድ]
አቢ ዐምር አልቁረሺይ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ሲሉ አስተላለፉት. .
የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) “ሩመህ የተሰኘችዋን ምንጭ ጉድጓድ ያስቆፈረ ጀነት አለው!» አሉ። ዑሥማንም አስቆፈራት። የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) “የዑስራህን ወታደር ያስታጠቀ ጀነት አለው!» አሉ። ዑስማንም አስታጠቀ። [ቡኻሪ]
ሑዘይፋህ ረዲየላሁ ዐንሁ የአላህ መልእክተኛን (ﷺ) . .
« ዑሥማን የት ነው?» ብዬ ስጠይቃቸው . . እሳቸውም. .
«በጀነት ውስጥ!» አሉኝ። [አሕመድ]
“ዑሥማን ከዚህ ወዲህ የሰራውን ቢሰራ አይጎዳውም!”
ዑሥማን ለኢስላም ሲል ሃብት ንብረቱን በአላህ መንገድ ላይ አውሏል። ለኢስላም ሲል ያለውን ንዋይ ሁሉ ምጽዋት ሰጥቶ ከድሎት ኑሮው ወጥቶ፥ ዱኒያን ቸል ብሎ፥ በችግር፥ በረሃብና በእርዛት ኖሯል። በመሆኑም እርሱ ለዲነል ኢስላም ሲል ሁለመናውን ሰውቷልና በነብይ አንደበት ያሻውን ቢሰራ ምንም እንደማይጎዳ ተመስክሮለታል።
ዐብዱ’ረሕማን ቢን ሰሙረህ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፦
«ዑሥማን ወደ ነቢዩ (ﷺ) መጣና የዑስራህ ዘመቻ ለሚሳተፉ ወታደሮች አንድ ሺህ ዲናር (ወርቅ) በጨርቅ ጠቅልሎ አምጣና በነቢዩ ታፋ ላይ አስቀመጠው። ይሄኔ ረሱል (ﷺ) ሁለት ግዜ እንዲህ ሲሉ አየኋቸው . . «ከዛሬ ወዲያ ዑሥማን የሰራውን ቢሰራ አይጎዳውም!»”
[ቲርሚዚይ፤ አልባኒ “ሐሰን”]
ዑሥማን ሰማእት ነው!
ሰማእትነት ማለት እንዲሁ ሰዎች በስምምነት በግለሰብ ደረጃ የሚሸልሙት የክብር ኒሻን አይደለም!
ሰማእትነት በመለኮታዊ ማረጋገጫ ካልተሰጠው በቀር በልብ የሚቀር፥ እውነተኝነቱ ሁሌም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ከአንድ አላህ በቀር ማንም የማያውቀው ጥልቅ ምስክርነት ነው።
አልኢማም ቡኻሪ ረሒመሁላህ የመልእክተኛው (ﷺ) ንግግሮች በሰበሰቡበት ታላቅ ጥራዝ (ሶሒሑል ቡኻሪ] ውስጥ ይህንን ጉዳይ አንድ ርእስ ሰጥተው እንዲህ ሲሉ ሰይመውታል. .
( بَابُ لَا يُقَالُ فُلَانُ شَهِيدٌ )
«ምእራፍ፡ እከሌ ሰማእት ነው አይባልም!»
ቀጥሎም በርካታ ይህንን ጉዳይ የሚያብራሩ ሐዲሦችን ጠቅሰዋል። የቡኻሪን ማብራሪያ የከተቡት ታላቁ ዐሊም ኢማም ኢብን ሐጀር (ረሒመሁላህ) በበኩላቸው ይህንን ምእራፍ ሲተነትኑ እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ. .
أَيْ عَلَى سَبِيلِ الْقَطْعِ بِذَلِكَ إِلَّا إِنْ كَانَ بِالْوَحْي
« ይህም “እከሌ ሸሂድ ነው አይባልም” ማለት ቁርጥ ባለ ሁኔታ (አንድን ግለሰብ “ሸሂድ ነው” ማለት አይቻልም) በወሕይ (በመለኮታዊ ማረጋገጫ) ካልሆነ በቀር. . .» ካሉ በኋላ . .
የዑመር ቢን አልኸጧብ ረዲየላሁ ዐንሁን ንግግርን ሲያስከትሉ. .
ዑመር እንዲህ አለ. .
تَقُولُونَ فِي مَغَازِيكُمْ فُلَانٌ شَهِيدٌ وَمَاتَ فَلَانٌ شَهِيدًا وَلَعَلَّهُ قَدْ يَكُونُ قَدْ أَوْقَرَ رَاحِلَتَهُ أَلَا لَا تَقُولُوا ذَلِكُمْ وَلَكِنْ قُولُوا كَمَا قَالَ رَسُول اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : " مَنْ مَاتَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ أَوْ قُتِلَ فَهُوَ شَهِيدٌ "
«በዘመቻዎቻችሁ ላይ “እከሌ ሰማእት ነው!” “እከሌ ሰማእት ሆኖ ሞቷል!” ትላላችሁ። በርግጥም ግለሰቡ የጦርነት ግመሉ ይዛው ወደ ሞት ወስዳው ይሆናል። አዋጅ! ይህንን (“እከሌ ሸሂድ ነው!” የሚለውን ዓረፍተ ነገር) አትበሉ! ነገር ግን የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) እንዳሉት በሉ። (“እከሌ’’ ሳትሉ. .በጥቅሉ. . ) “በአላህ መንገድ ላይ የተሰዋ ሰማእት ነው!” በሉ!» [አሕመድ]
ቀጥለውም የታላቁን ነቢይ (ﷺ) ይህንን ሐዲሥ አስቀምጠው ርእሱ ድርድር እንደሌለው አሳውቀዋል. .
قَالَ رَسُول اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ " مَنْ تَعُدُّونَ الشَّهِيدَ ؟ قَالُوا : مَنْ أَصَابَهُ السِّلَاحُ قَالَ : كَمْ مَنْ أَصَابَهُ السِّلَاحُ وَلَيْسَ بِشَهِيدٍ وَلَا حَمِيدَ وَكَمْ مَنْ مَاتَ عَلَى فِرَاشِهِ حَتْف أَنِفَهُ عِنْدَ اللَّهِ صَدِّيقٌ وَشَهِيدٌ
የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) እንዲህ ሲሉ አስሓቦቻቸውን ጠየቁ. .
«ማንን ነው “ሸሂድ (ሰማእት) ነው!” ብላችሁ የምትቆጥሩት?»
ሶሓቦችም . . «(የጠላት) መሳሪያ የገደለውን” ሲሉ መለሱ. .
ረሱልም (ﷺ) ፦ «ስንትና ስንት ነው (የጠላት) መሳሪያ ገድሎት ሰማእት ያልሆነው! ግና ስንትና ስንቱ ነው ፍራሹ ላይ ሞቶ አላህ ዘንድ ሲዲቅ እና ሰማእት የሆነ!” ብለው ነገሯቸው። [ፈትሑል ባሪ]
አቡ ሁረይራህ ረዲየላሁ ዐንሁ የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) እንዲህ አሉ፦
اللَّهُ أَعْلَمُ بِمَنْ يُجَاهِدُ فِي سَبِيلِهِ وَاللَّهُ أَعْلَمُ بِمَنْ يُكْلَمُ فِي سَبِيلِهِ
«አላህ (ብቻ) በርሱ መንገድ ላይ የሚታገለውን አዋቂ ነው። አላህ በርሱ መንገድ ላይ የሚቆስለውን አዋቂ ነው።» [ፈትሑል ባሪ]
በዚህ አማኻኝነት “እከሌ ሸሂድ ነው” የሚሉትን ሰዎች እግረ መንገዳችንን ሊታረሙ እንደሚገባቸው እያሳሰብን ይህ ድርጊታቸው “የሩቅን አዋቂ ነኝ!” ከሚል አጸያፊና አሰቃቂ ቃል እንደማይተናነስ ማስታወስ እንወዳለን። “እከሌ ሸሂድ ነው!’ ማለት ‘’እከሌ የጀነት ነው” ማለት እንደሆነና በነቢያዊ ትንቢት ሸሂድ መሆኑን ወይንም የጀነት መሆኑን ያልተረጋገጠውን ግለሰብ ስለወደዱት አሊያም “በጠላት እጅ ሞቷል” በማለት በስም ጠርተው “ሸሂድ ነው” ማለታቸው በፍጹም አግባብ አይደለም።
ሸሂድ ይሁን አይሁን እውቀቱ ያለው ከአላህ ዘንድ ብቻ ነው! አላህ ዘንድ ያለ እውቀትን “አውቃለሁ” ማለት አደጋን ያዘለ፤ በአላህ ላይ የታበለ ታላቅ ቅጥፈት ነው!
አላህ እንዲህ ይላል. .
{وَلَا تَقْفُ مَا لَيْسَ لَكَ بِهِ عِلْمٌ إِنَّ السَّمْعَ وَالْبَصَرَ وَالْفُؤَادَ كُلُّ أُوْلَئِكَ كَانَ عَنْهُ مَسْئُولًا}
እውቀት በሌለህ ጉዳይ ላይ አትናገር! መስሚያም፣ መመልከቻም፥ ልቦናም እነዚህ ሁላቸውም ተጠያቂዎች ናቸው። [አልኢስራእ 36]
አስተዋይ ልቦና ያለው ያስተውል!
ታላቁ ኢማም አጥጦሓዊ (ረሒመሁላህ) የአህሉልሱንናዎችን የእምነት አቋም በሚተነትኑበት «አልቂደቱል ጦሓዊይያህ» በተሰኘው ኪታባቸው ላይ እንዲህ ይላሉ. .
"وَلَا نُنَزِّلُ أَحَدًا مِنْهُمْ جَنَّةً وَلَا نَارًا،
« ማንንም ቢሆን (ነቢያዊ ትንቢት ማስረጃ እስካልመጣበት ድረስ) የጀነት ወይንም የጀሃነም ነው ብለን አናውጀም። » [አልቂደቱል አጥጦሓዊ]
በመሆኑም እኛ “ዑሥማን ሸሂድ ነው” ስንመሰክር እንደነ እንቶኔ ከመሬት ተነስተን፤ በስሜት ተነድተን፤ በውዴታ ብቻ ከንፈን አይደለም። የታላቁ ነቢይን (ﷺ) አሓዲሦች ከፊታችን እያስቀደምን ቢሆን እንጂ. .
ኢብን ዑመር ባስተላለፉት መልእክት የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ስለአንዳች ፈተና እያወሱ ሳለ እንዲህ አሉ፦
«ይህ (ዑሥማን) በዚህች ፈተና ተበድሎ ይገደላል!» አሉ። [ቲርሚዚይ አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል]
አነስ ኢብን ማሊክ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዳስተላለፉት. .
« የአላህ መልእክተኛ (ﷺ)፥ አቡ በክር፥ ዑመር እና ዑሥማን በኡሑድ ተራራ ላይ ወጡ። ያንኔ ተራራው ተንቀጠቀጠ። የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) “ኡሑድ ሆይ! ተረጋጋ! በአንተ ላይ ያለው ነቢይ፥ ሲዲቅ (አቡ በክር) እና ሁለት ሰማእታት (ዑመርና ዑሥማን) ናቸው!” አሉ። [ቡኻሪ]
ዑሥማን ሰውም መላኢካውም ያፍረዋል!
አይናፋርነት በኢስላም ተወዳጅ ባህሪ ነው። እንዲያውም አይናፋርነት የኢማን አንድ መገለጫ ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሁ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦
«አይናፋርነት የኢማን ቅርንጫፍ ነው።»
የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ስነ ምግባራቸው ሲወሳ ጫጉላ ቤት ውስጥ ካለች ሙሽሪት በላይ እጅጉን አይናፋር ነበሩ። ይህን የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ጸባይ ደግሞ ከዑሥማን በላይ የሚጋራቸው የለም። በአንድ ሐዲሥ ላይ የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ዑሥማን በስነ ምግባር (በጸባይ) ከአስሓቦቻቸው በጠቅላላ የበለጠ እርሳቸውን እንደሚመሳሰል ተናግረዋል።
ዑሥማን በዚህ ጸባዩ አማኻኝነትም አብረውት ይኗኗሩት የነበሩ ሰዎች እርሱ እንደሚያፍረው ሁሉ እነርሱም ያፍሩት ነበር. .
ኢብን አቢ አውፋ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላል፦
« ነቢዩ (ﷺ) ዘንድ አንዲት ሴት ባሪያ ዱፍ እየመታች ሳለ አቡ በክር ወደ ውስጥ ለመግባት አስፈቀደ። ተፈቀደለትም።
ከዚያም ዑመር መጣና አስፈቀደ። ተፈቀደለትም።
ከዚያም ዑሥማን መጣና አስፈቀደ። ተፈቀደለትም። ያኔ ሴቷ ዱፉን መምታት አቆመች።
እናም ረሱል (ﷺ) እንዲህ አሉ፦ “ዑሥማን እኮ አይናፋር የሆነ ሰው ነው።” [አሕመድ]
መላኢካውስ መቼ ይደፍረውና!?
እናታችን ዓኢሸት ረዲየላሁ ዐንሃ እንሳተላልፈችው . .
«የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) በቤቴ ውስጥ ደገፍ ብለው ቁጭ ብለው ነበር። ታፋቸው ተገልጦ ነበር። አቡ በክር መጣና ወደ ቤት ውስጥ ለመግባት አስፈቀደ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ (ታፋቸውን ሳይሸፍኑት) ተፈቀደለትም። ማውራት ጀመሩ።
ዑመር መጣና ወደ ቤት ውስጥ ለመግባት አስፈቀደ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ (ታፋቸውን ሳይሸፍኑት) ተፈቀደለትም። ማውራት ጀመሩ።
ዑሥማን መጣና ወደ ቤት ውስጥ ለመግባት አስፈቀደ። ረሱል (ﷺ) ተስተካክለው ቁጭ አሉ። ልብሳቸውን (ታፋቸውን በመሸፈን) አስተካከሉ።»
ይህንን ትከታተል የነበረችው እናታችን ዓኢሻ እንግዶቹ በወጡ ግዜ እንዲህ ስትል ረሱልን (ﷺ) ጠየቀቻቸው. .
“አቡ በክር ሲገባ አልደነገጡም። ቦታም አልሰጡትም። ከዚያም ዑመርም ሲገባ አልደነገጡም። ቦታም አልሰጡትም። ነገር ግን ዑሥማን ሲገባ ተስተካክለው ቁጭ አሉ። ልብሶትንም አስተካከሉ። (ለምንድን ነው?)"
የአላህ መልእክተኛም እንዲህ ሲሉ መለሱላት. .
«መላኢካዎች የሚያፍሩት የሆነውን ሰው (ዑሥማንን) እንዴትስ አላፍረውም?» [ሙስሊም]
አላሁ አክበር!
አባቴ፥ እናቴ፥ ነፍሴ ትሰዋልህ ዑሥማን ሆይ!
ለሚያስተነትን. . !
ጂብራኢል ስንት ክንፍ አለው? ስድስት መቶ ክንፍ ብላችሁ እንደምትመልሱ አልጠራጠርም። እንዲያውም ረሱል (ﷺ) እንደተናገሩት ጂብሪል አንዱን ክንፉን ብቻ ቢዘረጋው ሰማይን ከአጽናፍ እንስከ አጥናፍ ይሸፍናል። በሌላ ሐዲሥ የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) እንዲህ ይላሉ፦
« ዐርሽን ከሚሸከሙት መላኢካዎች ውስጥ ስለ አንዱ መላኢካ እንድናገር ተፈቀደልኝ። ከጆሮው ታችኛዋ ጫፍ አንስቶ እስከ ትከሻው ድረስ ሰባት መቶ ዓመታት ያህል ያስኬዳል።» [አልባኒ “ሶሒሕ”]
ታዲያ እነኚህ እጅጉን ግዙፍ የሆኑ፤ አላህን አንድም ቀን አምጸውት የማያውቁ የጌታችን ፍጥረታት ይህንን ታላቅ ሰማእት የሚያፍሩት ከሆነ እኛ በምንስ አንደበታችን ዑሥማንን በክፉ ልናነሳው ድፍረቱ ይኖረናልን? እነዚያ ደም የተጠሙት አማጽያን ይህንን ታላቅ ሰው በጩቤ ወጋግተው ለመግደል እንዴትስ አስቻላቸው?
የዑሥማን ገድል በዚህ አያበቃም!
በቀጣይ ዑሥማን በኺላፋው ዘመናት ለዚህ ዑማ ያበረከተውን ታላቅ ስራ እያስታወስን እናወሳዋለን። ከአውሮፓ እስከ አፍሪካ ተውሒድን ያስፋፋበትን ታላቅ ገድል አንስተን እንዘክራለን።
ኢን ሻ አላህ
Abu Aisha